ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ለድርድሩ መመሪያ ሰነድ ለማዘጋጀት ተስማሙ

– “ሁሉም ፓርቲ በእጣ፣ በዙር ያደራድር” – ገዥው ፓርቲ
– “ገለልተኛ አካል ያደራድረን” – ተቃዋሚዎች
– ሚዲያዎች በመግለጫ ብቻ እንዲስተናገዱ ሃሳብ ቀርቧል

ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በሁለተኛው ቀጠሮአቸው ድርድሩ የሚመራበት የጋራ መመሪያ ሰነድ እንዲዘጋጅ ተስማምተው፤ ያቀረቡት ሀሳብ በንባብ ተሰምቷል፡፡
ፓርቲዎቹ ቀደም ሲል በነበረው ስብሰባቸው ድርድሩ በማን ይመራ፣ ማን ይታዘበው፣ በምን ዓይነት ስነ ምግባርና ስርአት ይመራ እና ሚዲያዎች እንዴት ባለ መንገድ ይዘግቡት በሚሉ 4 ፍሬ ነገሮች ላይ ያላቸውን ሀሳብ እንዲያቀርቡ በተጠየቁት መሰረት፤ በቡድንና በተናጥል ተከፋፍለው፣ ለፓርላማው ፅ/ቤት ያቀረቡት ሀሳብ ባለፈው ረቡዕ በንባብ ከተሰማ በኋላ፣ ሰፊ በመሆኑ ተቀናጅቶ በአንድ ሰነድ እንዲቀርብ ተስማምተዋል፡፡
ኢህአዴግ የድርድሩ አላማ “በክርክርና በድርድሩ የሚነሱ ሀሳቦችን በግብአትነት በመውሰድ የሚሻሻሉ ህጎች ማሻሻል፤ እንዲሁም የአፈፃፀም ጉድለቶችን ማስተካከል” ነው ሲል መድረክ በበኩሉ “የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ችግር ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ እንዲሰጥ ማስቻል”
የድርድሩ አላማ ይሁን በማለት ሀሳቡን አቅርቧል፡፡ መኢአድን ጨምሮ 6 ፓርቲዎች፤ በድርድሩ ህዝብ የሚጠብቀው ነፃና ፍትሃዊ በሆነ የምርጫ አካሄድ፣ በራሱ ፍላጎት መንግስት ማውረድና ወደ ስልጣን ማምጣት ነው” የሚል ሀሳብ አቅርቦ እንደነበርና በንባብ ሳይሰማለት መቅረቱን የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በንባብ ከተሰማው የየፓርቲዎቹ ፕሮፖዛል መረዳት እንደተቻለው፣ ገዥው ፓርቲ ድርድሩ በማን ይመራ ለሚለው “ሁሉም ፓርቲ በእጣ ተከፋፍሎ፣ በየተራ እንምራ” የሚል ሀሳብ አቅርቧል።
መኢአድ፣ ኢዴፓና ሰማያዊ የተካተቱበት የ6 ፓርቲዎች ቡድን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው 11 ገለልተኛ ሰዎች ድርድሩ እንዲመራ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን መድረክ በበኩሉ፤ 4 ገለልተኛ ግለሰቦች ድርድሩን ይምሩት የሚል ሀሳብ አቅርቧል። ሌሎች ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ድርድሩ በገለልተኛ ወገኖች እንዲመራ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
ድርድሩን ማን ይታዘበው በሚለው ላይ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ አብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ገለልተኛ ወገኖች ድርድሩን እንዲታዘቡት ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን ገዥው ፓርቲ ታዋቂ ሰዎች ይታዘቡት ሲል፤ የእነመኢአድ ቡድን፤ ታዛቢዎቹ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ አምባሳደሮች የመሳሰሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ የውጭ ዜጎችና የሲቪክ ማህበራት እንዲሆኑ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
ፓርቲዎቹ ድርድሩ ይመራበት ያሉትን የስነ ምግባርና ስነ ስርአት ሀሳብም አቅርበዋል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች፣ የፓርቲዎችን ኃላፊነትነና ልዕለ ስብዕና የሚነኩ ንግግሮችና ተግባራት የተከለከሉ እንዲሆኑ ሀሳብ አቀርዋል፡፡
በድርድሩ አንድ ፓርቲ በ4 ግለሰቦች ይወከል የሚል ሀሳብ ኢህአዴግ ያቀረበ ሲሆን የእነ መኢአድ ቡድን በ3 ግለሰቦች እንዲወከል ሀሳብ ማቅረቡን መረዳት ተችሏል፡፡
ኢህአዴግ የድርድር መድረኩ ስያሜ “የገዥው ፓርቲ እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም” እንዲባል ሀሳብ ሲያቀርብ፤ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ መድረኩ ከወዲሁ “ፎረም” ከተባለ በህዝብ ዘንድ ሊኖር የሚችለውን አመኔታ ስለሚያሳጣ ጠቃሚ አይሆንም በሚል ለጊዜው “የገዥው ፓርቲ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድርድር” በሚል ይጠራ ማለታቸውን የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ አስረድተዋል፡፡
የሚዲያ አዘገጋገብን በተመለከተ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ተቀራራቢ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ሚዲያዎች ሁሉንም የድርድር ሂደት በቀጥታ እየተከታተሉ ከሚዘግቡ ይልቅ በመግለጫዎች እንዲስተናገዱ ሃሳብ ቀርቧል፡፡
የድርድሮቹን መግለጫዎችም በቀጥታ ከፓርቲዎች ሳይሆን በገለልተኛ አደራዳሪው አካል በኩል ሚዲያዎች እንዲያገኙ የነመኢአድ ቡድን ሃሳብ አቅርቧል፡፡ ማንኛውም ሚዲያ ሂደቱን አዛብቶ የሚዘግብ ከሆነ፣ በሃገሪቱ ህግ መሰረት እንዲቀጣ፣ ሂደቱን ከመዘገብ እስከ መታገድ የሚደርስ ቅጣት እንዲወሰንበትም ይሄው ቡድን ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በረቡዕ ውይይት ኢህአዴግ ፓርቲዎች ሊወያዩ ወይም ሊደራደሩ የሚፈልጉባቸውን አጀንዳዎች ከወዲሁ ለፓርላማው ፅ/ቤት እንዲያስገቡ የጠየቀ ሲሆን የሂደቱ ተሳታፊ የሆኑት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ የመደራደሪያ አጀንዳችንንና ሃሳባችንን ፈቅደን ልንሠጥ የምንችለው ለሚመለከተው ገለልተኛ አደራዳሪ ወገን ብቻ ነው›› የሚል አቋም መያዙን አስረድተዋል፡፡
የመጀመሪያውን የድርድርና ውይይት መድረክ ኢህአዴግን ወክለው የመሩት የኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ሙሉጌታ በወቅቱ ፓርቲያቸውን ጨምሮ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ “መድረኩ ወሣኝ ሆኖ ሣለ እንዴት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይሠበስቡንም? የሚል ሃሳብ ተሰንዝሮ እንደነበር ጠቁመው፤ “ማስተካከያ የተደረገበት በሚመስል መልኩ የረቡዕ መድረክ በም/ጠ/ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተመርቷል፤ ይህንንም በበጎ ተመልክተነዋል” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚሁ የረቡዕ እለት የድርድር መድረክ ላይ የሶስት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ለየት ያለ ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን ድርድሩም በኢህአዴግና በመድረክ መካከል እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡ ፓርቲዎቹ በመረጧቸው ኮሚቴዎች የሚሰናዳላቸውን ሰነድ ተመልክተው ቀጣዩን ሂደት  ለማስቀጠል በፓርላማው ፅ/ቤት በድጋሚ ለመገናኘት ለየካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም ተቀጣጥረዋል፡፡

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

Written by  አለማየሁ አንበሴ addisadmass

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *