ሰሞኑን በፕሮፌሠር ፍቅሬ ስራዎች ለማሾፍ እና የእርሳቸውን ክብር ለማውረድ በጅምላ እየተካሄደ የሚገኝ የስም ማጥፋት ስራ እየተመለከትኩኝ ነው አንዳንዶቹ ባለማወቅ እና ከብስለት ማነስ የሚያደርጉት መሆኑን ባውቅም የተወሰኑት ግን ሆን ብለው የሚፈፅሙት ተግባር መሆኑን ለማወቅ ችያለው፡፡ በፕሮፌሰሩ ላይ እየተካሄደ የሚገኘው የማንቋሸሽ ተግባር ከየት እንደመነጨ ለምን እንደሚካሄድና እነማን እንደሚፈፅሙት መመልከቱ መልካም ይመስለኛል፡፡

ፕሮፌሠር ፍቅሬ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ትክክለኛ የዘር ምንጭ የተሰኘው መፅሐፍ ለገበያ ከዋለ በኋላ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ ተፈላጊ መፅሐፍ በመሆን መነበብ የቻለ ትልቅ መፅሐፍ ነው በዚህም በኢትዮጵያ የመፅሀፍ ታሪክ ውስጥ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በተደጋጋሚ በመታተም ታሪክ የሰራ መፅሀፍ ነው፡፡ ይህ መፅሀፍ የኦሮሞውና የአማራው ህዝብ ሌሎች ፀሐፊያን እንደሚሉት የተለያየ ዘር ያላቸው ከተለያዩ ሀገራት ፈልሰው ወደኢትዮጵያ መጡ የሚለውን የታሪክ ፀሀፊዎቹን የዘመናት አስተሳሰብ የሠበረ ለዚህም ማስረጃ ያቀረበ መፅሐፍ በመሆኑ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ የሚሉ የታሪክ ፀሀፊያንን ስራዎች አፈር በመክተቱ ምክንያት የታሪክ ፀሀፊዎች ስህተታቸውን ከመቀበል ይልቅ ፕሮፌሠር ፍቅሬን በተለያዩ መንገዶች ማጥቃት እንዲጀምሩ ምክነያት ሆኗል፡፡

በአንድ ወቅት ይህ መፅሀፍ ከመታተሙ በፊት ፕሮፌሰር መስፍን ስለፕሮፌሠር ፍቅሬ ሲገልፁ የኢትዮጵያን ታሪክ መፃፍ ያለበት ፍቅሬ ቶሎሳ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ፕሮፌሠር መስፍን ትክክል ነበሩ ምክንያቱም ፕሮፌሠር ፍቅሬ ከጎሳ አስተሳሰብ ነፃ የወጣ ሙሉ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ካለምንም ወገንተኝነት እንደሚፅፈው እሙን ነበር፡፡ ይህ ግን እራሳቸውን ከጎሳ አስተሳሰብ ነፃ ማውጣት ላልቻሉ የሀገራችን ምሁራን ተቀባይነት አልነበረውም ምክንያቱም ለበርካታ አመታት ህዝቡን ለመነጣጠል የፃፉት ፀረ አንድነት የታሪክ ፅሁፎች አፈር እንደሚገቡ ያውቁታልና በዚህም የተነሳ እነዚህ ከፕሮፌሰር ፍቅሬ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ጋር በተቃራኒ የቆሙ ወገኖች አንድ ንብረትነቱ የኤፈርት የሆነ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሚገኝ የቴሌቪዥን መድረክ መሪ በመጠቀም ፕሮፌሠሩን ለማሸማቀቅ ሞከሩ ለተወሰነ ጊዜ የተሳካ ቢመስልም ፕሮፌሠር ፍቅሬ ከቆይታ በኋላ በለቀቋቸው ፅሁፎች ማንበብና ማገናዘብ የሚችለውን በመረጃ ማሳመን ሲጀምሩ የተወሰኑ ምሁራን አሁንም የጥላቻ የመሰለ ትችታቸውን መፃፋቸውን ቀጠሉ፡፡ ሆኖም ፕሮፌሠር ፍቅሬ በቀና ልቦና የመጨረሻ መልሴ ያሉትን ምሁራዊ መልስ ሠጡበት፡፡ ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ ያልቻሉት የፕሮፌሰር ፍቅሬ ሀሳብ ያሸማቀቃቸው ፀሀፊያን ከመፅሀፉ ትችት ወደፕሮፌሠር ፍቅሬ ግጥሞች ዞሩ፡፡

Related stories   Is TPLF prison empire in Ethiopia silently approach towards half a century?

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የፕሮፌሠር ፍቅሬ መፅሀፍ ያልናደው የታሪክ ውሸት ያልሰባበረው የታሪክ ስንክሳር የለም፡፡ ይህ ደግሞ በባዶ ሜዳ ላስቀራቸው የታሪክ አዋቂ ነን ባዮች ትልቅ ኪሳራ ነበረ፤ ይህንን የእውቀት ኪሳራ መቀበል ያቃታቸው ፀሀፊያን ሌሎች መረጃዎችን በማሰባሰብ ሌላ ተጨማሪ ነገር ይዞ ከመቅረብ ይልቅ በቀጥታ የፕሮፌሰሩን መፅሐፍ በዛ የቴሌቪዥን መድረክ መሪ አማካኝነት ተረት ተረት ነው ለማለት ደፈሩ፡፡ በዚህ የፕሮፌሰር ፍቅሬ መፅሐፍ ተቃዋሚ ጎራ ውስጥ ከእድሜ ጠገብ ምሁራን እና ፀሀፊያን ጀምሮ እስከተራ የፌስቡክ ፀሀፊያን ድረስ የሚገኙበት ነው፡፡ በመሠረቱ የፕሮፌሠር ፍቅሬ መፅሀፍ መተቸት የለበትም የምል አይነት ግለሰብ አይደለሁም፡፡ በጣም የወደድኳቸው ትችቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ወዳጄ እያስፔድ ተስፋዬ የግሪክ ፀሐፊያንን ፅሁፎች በመጥቀስ ጥሩ ሊባል የሚችል የበሠለ ትችት አቅርቦ ነበረ በዚህም ከፕሮፌሠር ፍቅሬ ጋር ተገናኝተው ለሰዓታት የቆየ ውይይት አድርገው መስማማት ችለዋል፡፡ የሌሎቹ ግን ከጥራዝ ነጠቅነትና ከጥላቻ እንዲሁም ከአልሸነፍም ባይነት የመነጨ ነበረ ነውም፡፡

ታሪክ የተሻለ ማስረጃ በተገኘ ቁጥር የሚሻሻል ምሁራዊ እርምት የሚሠጥበት የማህበራዊ ሳይንስ ጥናት አንድ አካል በመሆኑ ሌሎች የተሻለ ማስረጃ ይዘው በሚቀርቡ ጊዜ የፕሮፌሰር ፍቅሬ መፅሐፍ ሊሻሻል የሚችል ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ አሁን ባለን የታሪክ ፅሁፍ ደረጃ የፕሮፌሰር ፍቅሬን መፅሐፍ ከመቀበል ውጭ ሌሎች አማራጮች አልቀረቡልንም፡፡ ከዚህ ቀደም ግሩም ዘለቀ እንዳለው የፕሮፌሠር ፍቅሬ መፅሐፍ ትልቅ ስህተት በኢትዮጵያዊ ምሁር መፃፉ ነው፡፡ ለዘመናት ፈረንጆች የፃፉልንን የተንሸዋረረ የታሪክ መፅሀፍ ስናነብ ለኖርን እና ፈረንጅን እንደመለአክ ለምንመለከት ሰዎች የፕሮፌሰር ፍቅሬን መፅሐፍ አዕምሯችን ሊቀበልልን አልቻለም፡፡

ይህ በጊዜ ሁኔታ ሊቀየር እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ጋሽ ፍቅሬ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ማዕዘን አሰባስቦ ሊያኖር የሚችል ትልቅ መሰረት በአንድ መፅሐፍ አሰቅምጦልን ታሪክ ሰርቷል ይህንንም በአካል ተገናኝተን አጫውቼዋለሁ ሌሎቻችንም ክብር ልንሠጠው ይገባል፡፡ ይህንን የአንድነት ማዕዘን የሆነ መፅሀፍ የመጠበቅ የሁላችንም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የምንል ወገኖች ሃላፊነት ነው በተረፈ የፕሮፌሰርን ግጥሞች ስለተቸን ገጣሚ ነን ብለን የምናስብ የታሪክ መፅሀፉን ተረት ተረት ነው ስላልን ታሪክ ፀሀፊ ነን የምንል ካለን አእምሯችንን መፃፍ ብቻ ሳይሆን ማንበብም ልናስተምረው ይገባል፡፡

Related stories   «ያ» ትውልድ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ጸረ ኢትዮጵያ ሴራ ሲጋለጥ - ክፍል ፩

እንደዚህ አይነቱን ለኢትዮጵያ መልካም አስተሳሰብ ያለውን ቅን ምሁር ለማዋረድ መሞከሩ መልካም አይመስለኝም፤ ልብ ወለድ ፀሀፊዎቹም ፕሮፌሰሩን ለቀቅ በማድረግ የቧልት ፅሁፋችሁን ጠበቅ ብታደርጉት አእምሯችሁ በማታውቁት ነገር ከመወጠር የሚያርፍ ይመሰልኛል፡፡

(ኤርሚያስ ቶኩማ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *