“ … ወታደር ባለመሆኔ የጦርነቱን ውሎ ማተት አያምርብኝም፡፡ ያም ሆኖ የአድዋ ድል ዛሬ ብርቅ በሆኑብን ሁለት እሴቶች ረድኤት የተገኘ ይመስለኛል፡፡ እኒህ ሁለት እሴቶች መተባበርና መደማመጥ ናቸው፡፡ ጣልያኖቹ በጊዜው ወደ ጦርነት ሲገቡ ተስፋቸውን የጣሉት በመድፍና በጠመንጃቸው ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዝነኛ በነበሩበት የውስጥ መቆራቆስ ላይ ነው፡፡ የትግራይ ቅልጥም ሲመታ ሸዋ ያነክሳል ብለው አላሰቡም፡፡ በርግጥም በክፍለ ሀገሮች ውስጥ የተለያዩ ሽኩቻዎች ነበሩ፡፡ እኒህን ሽኩቻዎች አስረስቶ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለአንድ አላማ ማሠለፍ ምኒልክነትን ይጠይቃል፡፡

“መደማመጥ ያልሁትን ላሳይ፡፡ አባ ዳኘው ከዛሬው የይስሙላ ፓርላማችን በተሻለ ሁኔታ ለልዩነቶች ቦታ የሚሰጥ ተንቀሳቃሽ ምክር ቤት በጦርነቱ ወቅት መፍጠር ችለዋል፡፡ ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በውጊያው ዋዜማ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል

‘… አፄ ሚኒልክም በበነጋው ሰራዊቱን የቀኙን በቀኝ፣ የግራውን በግራ አሰልፈው ነጋሪትዋን እያስመቱ ወደሱ ተጓዙ፡፡ ኢጣሊያኖችም ዘበኛው ሲመጣ ባዩ ጊዜ ተመልሰው ወደ እርዳቸው ገብተው ተኙ፡፡

ከዚህ በኋላ ሰራዊቱም እንደ ኤሊ ስንመጣበት ከድንጋይ ይገባል፤ ስንመለስ ይወጣል፤ እንዲህ አርጐ ሊጫወትብን ነውን? ብሎ እጅግ አጥብቆ ተናደደ፡፡ መኳንንቶቹም ተሰብስበው ከዚህ ሰፍረን አድረን በማለዳ እዚያው ካሉበት ከርዱ ድረስ ሄደን እንዋጋለን ብለው መከሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እሺ ብለው ድንኳኑን ለማስመጣት አዘዙ፡፡

ይህ ምክር ካለቀ በኋላ የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ተሰልፎ በፈረስ ሆኖ መጣ፡፡ እሱም ይህ ምክር እንዳለቀ ባዬ ጊዜ አንድ ነገር ልናገር ይፍቀዱልኝ ብሎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ እንዲህ አለ፡፡ እንደ ተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ልናስፈጀው ነውን? አለ፡፡ ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክም ተመልሰው ከድንኳንዋ ከገቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡፡ እንግዲህ ከሰፈሬ ወጥቶ ተኩስ አልጀመረ ባይኔ ካላየሁት ተሰልፌ አልወጣም፡፡’

Related stories   ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደምታነሳ አስጠነቀቀች፤ "ብሄራዊ የጀግንነት ጥሪ ያፈልጋል"

“ፀሐፌ ትእዛዝ ያቀረቡትን ዘገባ ወደ ዘመናዊ አማርኛ አሳጥሬ ሳዛውረው የሚከተለውን ይመስላል፡፡

“ርዕሰ-ብሔር ምኒልክ ሰራዊታቸውን እየመሩ ወደፊት ሲገሰግሱ የጣልያን ሰራዊት ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ ወደ ምሽጉ ገባ፡፡ ምኒልክ በቀጣዩ ስትራቴጂ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ በስብሰባው ላይ ወደ ጠላት ምሽግ ሄደን እንዋጋ የሚል ሐሳብ ቀርቦ ባብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡ ምኒልክም በብዙሃኑ ተሰብሳቢ የቀረበውን ሐሳብ ለማስፈፀም ተዘጋጁ፡፡ ይሁን እንጂ ጄኔራል መንገሻ ዮሐንስ ዘግይቶ ስብሰባውን ከተቀላቀለ በኋላ “ምሽግ ድረስ ሄዶ መዋጋት በወገን ጦር ላይ ጉዳት ያስከትላል” ብሎ መከራከር ጀመረ፡፡ ምኒልክም “እኔ አንዴ ወስኛለሁ፤ ውሳኔዬ ካልጣመህ በሊማሊሞ በኩል ማቋረጥ ትችላለህ” ብለው ሳያሸማቅቁት ሐሳቡ እንዲጤን አደረጉለት፡፡ ሐሳቡ በድምፅ ብልጫ ፀደቀ፡፡ በድምፅ ብልጫ ያልሁት “ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ” የሚለውን የፅሐፌ ትዕዛዙን አማርኛ ተርጉሜ ነው፡፡”

“እንደተመለከተው አጤ ምኒልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማዳመጥና አወዳድረው የነጠረውን ሐሳብ ለማስፈፀም ዝግጁ ነበሩ፡፡ በአራት ነጥብ የታጠረ ግትርነት አልነበረባቸውም፡፡

“ሾፐናወር የተባለ የጀርመን አገር ፈላስፋ ከአድዋ ሠላሳ አምስት አመት አስቀድሞ “ከጥንት ግብፃውያንና ከህንዶች ውጭ ያለው ታላቅ የስልጣኔ ፍሬ ሁሉ በነጮች ጥረት ውጤት ነው፡፡ ከጥቁር ህዝቦች መካከል እንኳ የገዢነትን ስልጣን የሚይዙት በቀለም ፈካ ያሉት ናቸው” ብሎ ነበር፡፡ ያጤ ምኒልክ ፊት ይህንን ንድፈ ሐሳብ በይፋ ለማስተባበል የተፈጠረ አይመስልም?”

በዕውቀቱ ስዩም፤

ምንጭ፡ ፍትህ፤ ቅጽ 5፣ ቁጥር 177፤ የካቲት 23፤2004ዓም

ጊዜ በማያደበዘዝው የአድዋ ድል ማግስት…

የዓለም ህዝብ ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን ድል ያደረገውን የጥቁር ጦር መሪ አጤ ምኒልክን ለማወቅ እጅግ ጓጓ፡፡ ምስላቸውን ለማየት ተቁነጠነጠ፡፡ ሙሉ ታሪካቸውን ለመስማት ተንሰፈሰፈ፡፡ ይህንኑ ተከትሎም፤ “እንኳንም ደስ አለዎት” ለማለት ከቁጥር የበዙ ደብዳቤዎች ይጎርፉላቸው ነበር፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በፖስታ ቤት በኩል የኢትዮጵያ ቴምብር የተለጠፈበት መልስ እንዲላክላቸው ይጠይቁ ነበር፡፡ ለምን… ?

ቴምብሩ ላይ ያለውን የምኒልክን መልክ ለማየት፡፡ ባለ ብዙ ዝናና ክብር ባለቤት የሆኑትን የምኒልክን ጥቁር ፊት ለማየት፡፡ የሰው ሀገር ሰው ሁሉ፤ “ዝናውን እንደሰማሁ መቼ ሄጄ ባየሁት”፣ “በጀግንነቱ እንደ ተማረኩ መች ተጉዤ ባገኘሁት”፣ “ካሁን ካሁን ፈቅዶልኝ ወታደር ሆኜ ባገለገልኩት” ያለላቸው አጤ ምኒልክ የኛ ናቸው፡፡ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭን ያንበረከከ የጥቁር ጦርን የመሩት ንጉስ የኛ ናቸው፡፡መወድስ የማይበዛበት የአድዋ ድልም የኛ ነውና፣  እንኳን ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ለምንኮራበት በዓላችን በጤንነት አደረሰን! (ምንጭ: ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር – Hiwot Emishaw)

Related stories   እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እቅዷን ይፋ አደረገች፤ ዶክተር ዳንኤል የማይካድራን ጂኖሳይድ ዝም ማለቱ ክህደት ነው

ዝክረ አድዋ!!

(የጥቁር ሕዝብ ኩራት!!)

ልክ የዛሬ 121 ዓመት እብሪተኛውን ጣልያን አድዋ ላይ ገጥሞ አይቀጡ ቅጣት የቀጣው የኢትዮጵያ ጦር በእምዬ ምኒሊክ ፊታውራሪነት በድል ተመልሶ አዲስ አበባ ሲገባ ህዝቡ በታላቅ እልልታና ጭፈራ ተቀበላቸው፤ ወዲያውም ግዳይ ሲጣልና ሲፎከር ለጀግኖቹ ክብር የሚከተለው ተገጠመለታቸው፡-

ተፈጠመ ጣልያን አበሻ እንዳይደርስ፡፡
***************
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ፡፡
በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈጠመ ጣልያን አበሻ እንዳይደርስ፡፡
ምኒሊክ ተጉዞ የምትጠይቁኝ
ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ፡፡
አባተ በመድፉ አምሳውን ሲገድል
ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል
የጎጃሙ ንጉስ ግፋ በለው ሲል
እቴጌ ጣይቱ እቴጌ ብርሀን
ዳዊቱዋን ዘርግታ ስምዓኒ ስትል፡፡
ተማራኪው ባዙቅ ውሃ ውሃ ሲል
ዳኛው ስጠው አለ ሠላሳ በርሜል፡፡
እንደ በላኤ ሰብዕ እንደመቤታችን
ሲቻለው ይምራል የኛማ ጌታችን
መድፉን መትረየሱን ባድዋ መሬት ዘርቶ
እንክርዳዱን ነቅሎ ስንዴውን ለይቶ
የተዘራውን ውል አጭዶና ወቅቶ
ላንቶኔሊ አሳየው ፍሬውን አምርቶ
እንፋቀር ብሎ ለምኖ መሬት
ንግድ ሊያሰፋበት ሊዘራ አታክልት
እያመጣ ሊሰጥ ግብሩን ለመንግስት
ለጉዋዙ ማረፊያ አገር ቢሰጡት
ተጠማኝ ሰንብቶ ሆኖ ባለ ርስት
ወሰን እየገፋ ጥቂት በጥቂት
እውነት ርስት ሆነው ተቀበረበት
ባሕር ዘሎ መምጣት ለማንም አትበጅ
እንደተልባ ስፍር ትከዳለች እንጅ
አትረጋምና ያለ ተወላጅ፡፡
የዳኛው አሽከሮች እየተባባሉ
ብልት መቆራረጥ አድነት ያውቃሉ
አድዋ ከከተማው ሥጋ ቆርጠው ጣሉ፡፡
የእስክንድር ፈረስ መቸ ተወለደ
የሚኒሊክ ፈረስ በክንፎቹ ሄደ
ደንገላባ ሲዘል እየተጓደደ የሮማውን ኩራት በእግሩ አሰገደ
አገርህን ሚኒሊክ እንዳሁን ፈትሻት ባያይህ ነውና ጠላትህ የሚሻት
እጁን ቀምሼ አላውቅ እያለ ሲያማህ
ቀመሰና እጅህን መጥቶ ጠላትህ
ሮም ላይ ተሰማ ለጋስ መሆንህ፡፡

Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

(ምንጭ: This day in Ethiopian History facebook page)

አድዋ! 121 ዓመት!

“… የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ ኤሮጳን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል፡፡ የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፤ ጠመንጃና ጦር ይዘው፤ ጎራዴ ታጥቀው፤ የነብር ያንበሳ ቆዳ ለብሰው፤ አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ፤ ቄሶች፤ ልጆች፤ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የኢጣሊያን ክፍል አሸበሩት” የበርክለይ ምስክርነት፤ አጤ ምኒልክ በጳውሎስ ኞኞ፤ ገጽ 195

 

eth at adwa

source- ጽሁፎቹ ከዚህ በፊት ካተምናቸው የተቀናበሩ ናቸው፡፡

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *