“Our true nationality is mankind.”H.G.

በአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ መናር ህብረተሰቡ ተማሯል

“ሸማች ማህበራት ገበያውን እንዲያረጋጉ እየጣርን ነው” ንግድ ቢሮ
“የመንግሥት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ለንረቱ ምክንያት ነው”

በአዲስ አበባ ከሁለት ሳምንት ወዲህ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ መናሩ ሸማቹን እያማረረ ሲሆን ለዋጋ ንረቱ የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ፣ የሁዳዴ ፆምና ድርቁ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ማስተዋሉን ጠቁሞ፣ ሸማች ማህበራት ገበያውን ተጠናክረው እንዲያረጋጉ እየሰራን ነው ብሏል፡፡
ሰሞኑን በአትክልት ተራ፣ በሳሪስና በአቃቂ ገበያዎች ተዘዋውረን ለመጠየቅ እንደሞከርነው፤ አንድ ኪሎ ቲማቲም ከ31-35 ብር፣ ብርቱካን በኪሎ 50 ብር፣ ሙዝ ከ17-20 ብር፣ ድንች በኪሎ 9 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 65 ብር፣ ቃሪያ ከ45-50 ብር እየተሸጡ ሲሆን ሸማቾች በዋጋ ንረቱ መማረራቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ “ከ15 ቀን በፊት በ10 ብር ሲሸጥ የነበረ ጥሩ ቲማቲም፤ በምን አግባብ 35 ብር እንደገባ ግራ ገብቶናል” ያሉት አንዲት እናት፤ “በሁዳዴ ፆምና በመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ሰበብ፣ ነጋዴው ህዝቡን መጫወቻ አድርጎታል” ሲሉ አማረዋል፡፡
ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝና ብርቱካን ባልተለመደ መልኩ ዋጋቸው መናሩን የተናገሩት ሸማቾቹ፤ “ነጋዴውን ስንጠይቅ፤ ድርቅ ገብቷል፣ ገበሬው ዋጋ ጨምሮብናል እያለ 25 ብር ይሸጥ የነበረውን ብርቱካን 50 ብር፣ 15 ብር ይሸጥ የነበረውን ሙዝ 20 ብር፣ 10 ብር ይሸጥ የነበረውን ቲማቲም 35 ብር፣ 25 ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ኪሎ ቃሪያ 45 እና 50 ብር፣ 45 ብር ይሸጥ የነበረውን ነጭ ሽንኩርት 65 ብር፣ አራትና አምስት ብር ይሸጥ የነበረውን ድንች 8 እና 9 ብር፣ ከ14 ብር በላይ ተሸጦ የማያውቀውን ካሮት፡- 26 ብር በመሸጥ በተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ህብረተሰቡን እያማረሩ ነው ብለዋል – በአትክልት ተራ ያገኘናቸው ሸማቾች። እስካሁን የዋጋ ጭማሪ ያላሳየው ቀይ ሽንኩርት ብቻ እንደሆነ የገለፁት ሸማቾች፤ ውሃ የማያነሳ ምክንያት በመደርደር ማህበረሰቡን የሚበዘብዙትን ነጋዴዎች፣ መንግስት ጣልቃ ገብቶ አንድ ሊላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ያነጋገርናቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ ገበሬው ድርቅ ገብቷል፤ ምርት የለም” በሚል በከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስረክባቸው ጠቁመው፤ እነሱም ስራውን ከማቆም በሚል ባለው ዋጋ እየሸጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ “በየዓመቱ የሁዳዴ ፆም ሰሞን አትክልቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ይታያል” ያሉት አንድ የአትክልት ተራ ነጋዴ፤ የዘንድሮው በጣም የተለየና እንኳን ሸማቹን ነጋዴውንም የሚያሳቅቅ እንደሆነ ጠቁመው፣ በጣም አስደንጋጩ ደግሞ እያደር የዋጋ ንረቱ መቀጠሉ ነው ብለዋል፡፡  የአትክልት ዋጋ ከወትሮው ለምን እንደናረ የጠየቅናቸው ነጋዴዎች፤ የምርት እጥረት በመኖሩና የፆም ወቅት በመግባቱ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ከመናገር ውጭ ትክክለኛ ምክንያቱን እነሱም እንደማያውቁት ገልፀው፤ አከፋፋዮችና አምራቾች በእያንዳንዱ የአትክልት አይነት ላይ የዋጋ ጭማሪ ገበማድረጋቸው ሊወደድ እንደቻለ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ማሻቀቡን አስመልክቶ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገበያ ክትትልና ቁጥጥር ስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳሁን በየነ፤ የዋጋ ንረቱን ንግድ ቢሮው ማጤኑን ገልፀው፤ ሸማች ማህበራት ተጠናክረው ገበያውን እንዲያረጋጉ ከአመራሮች ጋር እየመከርን ነው ብለዋል፡፡ “በተለይ በግብርና ምርቶች ላይ በተለያየ ጊዜ የአቅርቦትና ፍላጎት መጠን ሲራራቅ፣ መጠነኛ የዋጋ ልዩነቶች ይታያሉ፤ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪና የደሞዝ ማስተካከያ ጠብቆ ነጋዴው የሚያደርገውን የዋጋ ጭማሪ ግን ንግድ ቢሮ አያምንበትም” ብለዋል፡፡
ንግድ ቢሮው በግብርና ምርቶች ላይ እንዲህ አይነት የዋጋ ንረት ሲፈጠር፣ ነጋዴውን ‹‹በዚህ ዋጋ ሽጥ፤ ይህን ዋጋ ቀንስ›› የማለት መብትና ኃላፊነት የለውም ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ነጋዴው እነዚህን ምርቶች ከገበሬው ላይ የሚገዛው ያለደረሰኝ በመሆኑ ለመገደብ እንቅፋት ይሆናል፣ ብለዋል። በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት ቢፈጠር በሚገበያዩባቸው ደረሰኞች የዋጋ ማመጣጠን ስራ መስራት እንደሚቻል ያስረዱት ኃላፊው፤ የሸማቾች ማህበራት የተቋቋሙበት ዋና አላማ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ገበያ ለማረጋጋት በመሆኑ፣ ዋጋቸው የናረ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በቀጥታ ከገበሬው ተረክበው፣ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
ንግድ ቢሮ፤ በየነጋዴው መደብ እየሄደ “ይህን ቀንስ፤ ያንን ጨምር” ለማለት የተሰጠው ስልጣን የለም ያሉት ኃላፊው፤ “ይህን ማድረግ ሌላ የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈጥር ይችላል” ሲሉ ሌላ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”

addisadmass

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0