ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

” ድፍን ኦህዴድን አታውግዙ፣ ተጠቃሚው ሌላ አካል ነውና”

“ዳኞቹ  ምን ተሰምቷቸው ይሁን?” ይላል ሶስት እነድሆኑ ጠቅሰው መልዕክት የላኩት ክፍሎች። ” አጭር እና የልብ ውሳኔ የሚፈልግ” ሲል ይጠይቃል። ለዝግጅት ክፍላችን መልዕክቱን የላኩት ክፍሎች የተጠቀሙት ስም የጋራ ምህጻረ ቃል ነው። የሚኖሩት አዲስ አበባ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል መዋቅር ውስጥ ታቅፈው እንደሚሰሩ አመልክተዋል። ከመዋቅራቸው ዙሪያ ቅሬታ እንዳለና ቅሬታውም አንድ ቀን ባልታሰበ መንገድ ሊፈነዳ እንደሚችል  ያስገነዝባሉ።

በዝግጀቱ አድራሻ በዋትስ አፕ የተላከው መልዕክት አንድ ትልቅ ማስጠንቀቂያ አለው። ማስጠንቀቂያውም ” ድፍን ኦህዴድን አታውግዙ፣ ተጠቃሚው ሌላ አካል ነውና ፤ መታገስ ደግ ነው” ይላል። ኦህዴድ ውስጥ አሁን ነገሮች ተቀይረዋል። ከ20 ሺህ በላይ የመዋቅር ሰዎች ቢባረሩም አዳዲስ የሚተኩትም ቢሆኑ ደማቸው የመረረ ነውና እንደ ቀድሞው ነገሮች ይቀጥላሉ ብለው የሚያስቡ ካሉ አሁን አገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካ የማይገባቸው ብቻ ናቸው።

በተቀጣጠለው የህዝብ ተቃውሞ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊው  ለማንም ግልጽ እንደሆነ የሚጠቁሙት የመዋቅር ሰዎች፣ “አገሪቱ በወታደራዊ እዝ ስር የወደቀችው  ህዝብ ስላመጸ ብቻ ሳይሆን መዋቅር ስለፈረሰ ነው” ሲሉ ኦህዴድ መክዳቱን ይጠቁማሉ። አያይዘውም ” አሁን እየተሰራ ያለው ኦህዴድ እንደ ቀድሞው ኦህዴድ በቀላሉ ተቦክቶ የሚጋገር አይደለም። ስለዚህ ወታደራዊ እዙ ይቀጣላል” የሚል መላምት ያሰቀምጣሉ። ያልዳነው ኦህዴድ ቀድሞም ሆነ አሁን ህሊናና ነብስ ያላቸው፣ በወገኖቻቸው ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ግፍ የሚያቃጥላቸው ጭምር ያሉበት በመሆኑ በጅምላ መራገም አግባብ አይደለም” ሲሉ ያስጠነቀቃሉ።

ድርጅታችን ውስጥ ” የንጹሃን ነብስ የሚጨፍርባቸውና ህይወታቸው በስጋት የተሞላ አሉ። እነሱም ቢሆኑ ዛሬ ላይ ሙሉ እምነት አይጣልባቸውም” የሚል ሃሳብ የተካተተበት መልዕክት፣ ” እነዚህ ክፍሎች በተግባራቸው የወለዳቸውን ህብረተስብ ስለካዱ ሌላ አማራጭ የለንም በለው ራሳቸውን በሰሩት ጥፋትና ክህደት መጠን ስለሚመዘኑ ማስፈራሪያና ዘለፋው ለጊዜው ቢቆይላቸው መልካም ነው? ምክንያቱም እንዚህን አካላት ባስፈራራን መጠን የከዳውን ኦህዴድን መልሶ ከማደራጀት የዘለለ ፋይዳ የለውም”ሲል ይመክራል።

” አሁን ያለው የፖለቲካ ወበቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው፣ ከተራ ብሽሽቅና ንትርክ በመውጣት ‘ ተኩላ’ ሆነን የምንጓዝበት፣ ተኩላ ካልሆን ተኩላዎች እንዲያጠፉን የምንመቻችበት፣ ከሁሉም በላይ የስድብ ፖለቲካን በማቆም፣ ህዝብ የሰለቸውን የጥላቻ ፖለቲካ ወደጎን በመተው የእድሜ ማራዘሚያ ፕሮፓጋንዳውን ማምከን አለብን” ሲል ወደ ማጠቃለያው የሚሄደው መልዕክት ” ኢህአዴግ ውስጡ ሟምቶ ሳለ ጥንካሬ የሚላበሰው በተቃራኒ ጎራ ያሉ ሃይሎች በውስጥም በውጭም የሚያራምዱት ፖለቲካ ህዝብን ለማስፈራራት በሚጠቅም መልኩ ስለሚካሄድ ነው” ይላል” ሲያጠቃልልም ” አንዳንዴ የሚሰማው የተቃራኒ ፖለቲካው ጉዞ ከኢህአዴግ ጋር በምንሰራውና ሁሌም የስድብ ውርጅብኝ ከሚወርድብን በላይ የሚያሳፍርና የሚያሸማቅቅ ነው። አማራጭ የሚፈልገውም ህዝብ እምነት የሚያጣው ለዚሁ ነውና ሚዲያው እኛን የሚቀጠቅጠውን ያህል እነሱንም ሊያርቃቸው ይገባል ሲል ይጠይቃል።

በመነሻው ” ዳኞቹ ምን ተሰማቷቸው ይሆን” በማለትና ” የልብ ውሳኔ ይጠያቃል” በማለት የገለጹት  ” ጥልቅ የኦሮሞ ልጆችና የመላው ኢትዮጵያዊያን ክብር” ያላቸው ዶክተር መረራ ላይ እየተወሰደ ያለውን ርምጃና የፍርድ ቤት ሂደት አስመልክቶ ሲገልጹ ነው። የዶክተር መረራን የፍርድ ቤት ውሎ ከቭኦኤ አንድ ላይ ሆነው እንደሰሙት የገለጹት ። “በወቅቱም እንንቀጠቀጥ ነበር። ይህ የሁሉም ኦሮሞ ስሜት ነው። ኦህዴድንም ጭምር”

merera-2

ችሎቱ ሲጠናቀቅ ዶክተር መረራ ለመናገር ጠይቀው ተፈቀደላቸው። እናም እንዲህ አሉ  ” ከጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና ከጄኔራል ታደሰ ብሩ ዘመን ጀምሮ ከአንድ ትውልድ በላይ ገዳዮችና ሟቾች፣ አሳሪዎችና ታሳሪዎች በበዙበት የአገራችን ድራማ ውስጥ በመቆየት አንድ ከሆዱ በላይ ለአገሪቱ የሚያስብ ምሁር ማድረግ እንዳለበት ሁሉ፣ ከ45 ዓመታት በላይ ለአገሬ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ በታማኝነት መታገሌ እየታወቀ ወደ ጎን ተገፍቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ቀጥለውም፣  ‹‹ለሁላችንም የምትሆንና በእኩልነት የምታስተናግደን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠርና ነፃ የፍትሕ ሥርዓት በአገራችን እንዲሰፍን ላለፉት 25 ዓመታት በመታገሌ መከሰሴና የአገሪቱ የፓርላማ አባል ጭምር የነበርኩ ሰው ለተራ ወንጀለኛ የሚፈቀድ የዋስ መብት በመከልከሌ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን ለራሴ ብቻ ሳይሆን፣ እኛም ሆንን ልጆቻችን በሰላም ይኖሩባታል ለምንላት መከረኛ አገራችንና አላልፍለት ብሎ ሲታመስ ለሚኖረው መከረኛ ሕዝባችን ጭምር መሆኑን እንዲታወቅልኝ ነው” ይህን ከላይ የተጠቀሰውን የዶክተር መረራን ማሳሰቢያ አዘል ንግግር የመርዶ ያህል ውስጥን ዘልቆ የገባ፣ እሳቸውን ለሚያውቋቸው ሁሉ ህመም የሆነባቸው ነው።