የዛጎል ዜና – በአንድ ወቅት ቆሼ ሰፈር ለረጅም ሰዓት የሚያስቆይ አጋጣሚ ነበርና አይኔ የቻለውን ሁሉ አይሁ። ቆሼ ሰፈር ቆሻሻ ተከምሮ ራሱ እንደ ክረምት ማገዶ ይጨሳል፣ ይግፈጠፈጣል። አውቀው ያቃጥሉት፣ ራሱ ይጭስ በወቅቱ መረዳት አልቻልኩም ነበር። አይኔን ማመን አቅቶኝ የምመለከተው ትዕይንት ልቤና ቀለቤን ስለሰረቀው በወቅቱ በውሉ ስለማሰቤ አሁን ድረስ እርገጠኛ አይደለሁም። በቃ ህዝበ አዳም ቆሻሻ ላይ የተራመሳል። ጆንያ ይጠቀጥቃል።

ከቆሼ ሰፈር ልጆች የተፃፈ መልዕክት
«ክፉ ነው ደሃ መሆን»
(ለቆሼ ሠፈር ልጆች) የችግሩ ጥግ ቆሻሻ ላይ የላስቲክ ቤት ያሰራሃል፡፡ መሠረት ስለሌለህ የሚያውቅህ የሚያስብልህ መንግስት አይኖርህም፡፡ ጥሩ መልበስ ንፁህ መብላት ያንተ የልብ መሻቶች አይሆኑም፡፡ አንገትህን ደፍተህ ነገን ትናፍቃለህ፡፡ ተፈጥሮ ፊቷን አዙራብህ ስትፍጨረጨር ሠዎች በፈጠሯቸው ተልካሻ ምክንያቶች ሕይወትህ ያልፉል፡፡ ቤትህ ተንዶ ማቅ ላይ ብትሆን እንኳን ጩኸትህን የሚሰማ አምቡላንስ እንጂ የሚያድን ወገን የለህም፡፡ ምክንያቱም አንተ ደሃ ነህ!
‹‹ኢስከን›› ( ትርፍራፊ) እየበላህ ያደክ ፤ የተማርክ ደሃ! ይሄ ነው የኔና የሠፈሬ ልጆች ኑሮ፡፡ ይሄም ኑሮ ሆኖ ይሄ ሁሉ ሃዘን ታዲያ ስለምን? … ዳሩ አንድ ቀን እንደ ሠው የምንታይበትና የምንኖርበት ቀን ይመጣል፡፡ ለሞቱት ነፍስ ይማርልን! … በጣር ላይ ላሉትሞ እግዚሔአብሔር ይሁናቸው፡፡ … ወይ ቆሼ ምግባችንም፤ ሞታችንም አንተው ትሆን! …››

በአሽናፊ እንዳለ  – ከፌስ ቡክ የተወሰደ 
 
ወገባቸውን በነተበ ነጠላ ያሰሩ እናቶች፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶች፣ ጎረምሶች፣ ታዳጊዎች፣ … ዘርዝሬ የማልጨረሳቸው ሰዎች ቆሻሻው ላይ ልክ  እንደ አሳማና ግልገሎቹ ይርመሰመሳሉ። ቆሻሻ የሚዘረግፉ መኪኖች ሲመጡ ይረባረቡበታል። ከቆሻሻ ውስጥ ለቀሞ ህይወት ለማኖር ትግል !! ከተጣለና ከሸተተ ብስባሽ ውስጥ ህይወትን የሚያለመልም ” መና ” ፍለጋ!! … እዛው እያለሁ ጭድ ተራ ሄድኩ። ጭድ ተራ ታወሰኝ። ከዛም ከበደ ደበሌ ሮቤ ” የአር ባህር ” ብሎ የጻፈው ጉድ እንደ ቅርቃር ጉሮሮዬን አነቀው። እንባ ተናነቀኝ።
አዲስ አበባን በባለ አደራነት ያስተዳደሩትን አቶ ብረሃነ ደሬሳን ቃለ ምልልስ ሳደርግላቸው ይህንኑ ችግር አንስቼባቸው የመለሱልኝ መልስ ዛሬ ትዝ አለኝ። እንዲህ ነበር ያሉት። ” ከደሃ ህዝብ ላይ መስረቅ ከአጥንት ስጋ የመጋጥ ያህል ነው። ሌብነቱ ልክ አልፏል፤ ከደሃ ህዝብ ላይ ዝርፊያ… ” አሉና አቀረቀሩ። የሁሉም ችግር መቋጫው እሳቸው ያሉት ጉዳይ ነውና ወደ ሃሳቤ ልመለስ።
ከበደ ደበሌ እንዲህ ጽፎ ነበር። ቦታው መርካቶ ዶሮ ተራ ያለው ወንዝ ቢጤ መሆኑ ነው። ዶሮ ተራ ዶሮ ሲገበያዩ የሚቆሙበት ድልድይ። ዛሬ አቋሙን ባላውቀውም ከቤ እያዋዛ ባስቃኘን መሰረት በጊዜው እቦታው ላይ ሄጄ ያላስተዋልኩትን አስተወያለሁ። አዎ እውነቱን ነው የአር ኩሬ ነው። አካባቢው ያሉ ሰዎች አራቸውን በፌስታል እየተጸዳዱ ይጥሉበታል። መጸዳጃ ቤታቸውን ደፍነው / ያላቸው ለማለት ነው/ መንገድ ላይ ለሚቸረችሩ ቸርቻሪዎች በመጋዘንነት እያከራዩ ፌስታል ላይ ካካ ይላሉ። ወንዙ ይቀበላል። ከተቀበለው ካካ ብዛት ወሃው አይታይም። ካካ ሸፍኖታል። ፌስታሉ እየተንሳፈፈ …. አይ አዲስ አበባ። ብዙ አስገራሚ ጉራንጉሮች አሉ። እስጢፋኖስ ጀርባ፣ ግንፍሌ ወንዝ ውስጥ ውስጡን፣ ቀበና፣ ፒያስ አሰራተና ሰፈር፣ አምስተኛ ….. ጣሊያን ሰፈር…..አዲስ አበባ ጉድ የተሸከመች ከተማ…
ከቤ እንዳለው ካካው በበጋ ይደርቃል። ፌስታሉን የሚለቅሙና አጥበው ለሽሮ፣ ለበርበሬ፣ ለቅመማ ቅመም መቋጠሪያ ይሆን ዘንድ ለባለ መደቦች ይቀርባል። ወንዙ የአር ባህር የተባለው ለዚህ ነው። በበጋ ውሃው ሲደርቅ ካካውን በሜትር እየከፋፈሉ የሚሸጡ ራሳቸውን የካካው ባለንብረት ያደረጉ አሉ። በሜትር የተከፋፈለውን ደረቅ ካካ ገዝተው በአካፋ ማዳበሪያ እየሞሉ የሚያገዙ እናቶች አሉ። በቆሎ ይቀቀልበታል። ስኳር ድንች፣ ድንች፣ የበግ አንጎል…. ይንተከተክበታል። አሁንም ለከቤ የነግሩት እንዳሉት የደረቀ ካካ ትንሽ ላምባ ጠብ ካለበት ውዲያው ትርክክ ያለ ፍም ይሆናል። በካካ የተቀቀለ በቆሎ ለነጫቹህ፣ አንጎል ለበላቹህ፣ …..
ጭድ ተራ የተቀደድ የውስጥ ሱሪ፣ አንድ እግር ካልሲ፣ የተቦጨቀ መሃረብ፣ የተነደለ ጀበና፣ የተነደለ ድስት፣ በጥቅሉ የማይጥቅም ነገር ገበያ ይወጣል። ምን አልባት አሁን የድርብ ኢኮኖሚ እድገቱ የጭድ ተራን ገበያ “ተረት” አድርጎት ከሆነ እንጃ። የምታውቁ ምስክርነታችሁን ስጡበት።
ወደ ቆሼ ተራ እንመለስ። ቆሼ ተራ የሰው ልጆች ለመኖር ሲሉ ቆሻሻ ለመልቀም በየቀኑ ይማስናሉ። በሚሰነፍጠው ቆሻሻ ውስጥ ውለው ቆሻሻ ለቀመው፣ ለቆሻሻ ተጠቃሚ ሰው መሳዮች ለማስረከብ ወደ ገበያ ይሮጣሉ። የአገራችን የቆሻሻ ሪሳይክሊንግ- መልሶ የመጠቀም ደረጃ ይህ መሆኑ ያሳዝናል። ይህንን ያነሳሁት እዚህ ባህር ማዶ ” አበሻ ኩሩ፣ አበሻ ነኝ ኩሩ ኢትዮጵያዊ…” የሚል ካኔቴራ ተሸክመው ይቅርታ ለብሰው የሚዞሩ ሙልጭ ያሉ ድሆች ጉዳይ የሚነሳበት መልካም አጋጣሚ ሆኖ ስላገኘሁት ነው።

Related stories   ዶክተር አብራሃም በላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ!

አዲስ አበባ መልከ ብዙ የሁለት ዓለም ሰዎች መኖሪያ፤ እዚህ ሰፈር ንጹህ አየር ፍለጋ የኖራል። የአዲስ አበባ እብቅ አየር ያስፈራቸው የሚኖሩበት መንደር። ሲሲዲ 

Image result for ccd ethiopia
እዚህ አውሮፓ ሆነው ወይም አሜሪካ በባዶ ጉራ ስለ ኩራት ለሚያወሩ አንድ እፍረት ልጋብዝ። ቆሼ ሰፈር ቆሻሻ ተደርምሶ ያለቁትን ሰዎች ዜና ለአንድ ወዳጄ አሳየኋት። ለጠየቀችኝ ሁሉ መለስኩላት። በደንብ እያየችና እያደመጠች ቆይታ ” አዲስ አበባ ዋና ከተማ ነው፤ እንዴት ሰዎች ቆሻሻ ውስጥ ይኖራሉ? ይገርማል” ስትል ጥያቄም አስተያየትም ሰነዘረች። እውነት መስሎ የተሰማኝን አጫወትኳት። ሁሉን ትተነው ሌላ ጉዳያችንን ስናከናውን ቆይተን፣ ድንገት ሌላ ጥያቄ አከለችልኝ።
” በጣም ከአፍሪካ የተለያችሁ፣ ሃብታሞች እና ኩሩ እንደሆናችሁ የምትነግረኝ የአገርህ ልጅ ነበረች” ብላ ስሟን ጠቅሳ ትጠይቀኝ ጀመር። ብዙ መከራከሪያ ስላላስፈለገኝ ” ውሸቷን ነው። ሙልጭ ያልን ድሆች ነን። ብዙ ገብና አለን። ድህነታችንን ማመን የተሳነንና በባዶ ተረት የምንኖር ህዝብ ነን” ብዬ ያለሃፍረት ነገርኳት።
ቆሻሻ ለመብላት ከመጋፋት፣ በአር አብስሎ ከመብላት፣ የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ከመተራመስ፣ በፈረቃ ከመተኛት በላይ ምን ድህነት አለ? የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ህይወት አጠፋ ብሎ የሃዘን መግለጫ ጋታና ሻማ ለኩሶ ” የሰላም እንቅልፍ” ማለት ደግ ቢሆንም፣ እኒህ ሰዎች መጀመሪያስ እየኖሩ ነበር? የከተማችን ነዋሪዎች ነበሩ? ግብር ከፋዮች ናቸው? ለመሆኑ ቤታቸው እንዴት ነው የተገነባው? ሳሎኑ፣ መኝታ ቤቱ… ይህ ዜና የሚነግረን ከድህነት ወለል በታች መሆናችንን እንጂ ሌላ አይደለምና ማልቀስ ለአገሪቱ ነው።
እንደ እውነት ከሆነ አገሪቱ ሊታወጅላት የሚገባው ” ድህነትን የመዋጋት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” በሆነ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ስልጣን ላይ ያሉትም፣ ተቃዋሚ የሚባሉትም፣ ስልጣን ተለክቶና ተሸንሽኖ የተሰጣቸውም፣ የተማሩ የሚባሉትም፣ የሚያስተምሩትም ….. ቪላ የገነቡትም፣ በሚሊዮን የሚቆጥሩትም … ነፍጥ የያዙትም ሁሉም የቆሼ ሰፈር ሟቾች አይነት አንድ ድንገት እንደ አምፑል የምትቃጠል ህይወት ባለቤት መሆናቸውን መዘንጋታቸው ነው።
ያደለው ትውልድ በአያቶቹ አጥንትና ደም የታነጸ አገር ይረከባል። እኛ ኑሯችንና ሞታችን ተመሳስለው እንደሞትን ኖረን አፈር እንገባለን። ቆሼ ውስጥ ለቅመን፣ ቆሼ ውስጥ ኖረን፣ ሲያልቅ ቆሼ እንሆናለን። ይህም ኑሮ ሆኖ መናገርና መተንፈስ እንከለከላለን። የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ ኢህአዴግ ቆሼ ሰፈርን እስከ ዛሬ አናውቀውም ካላሉ በቀር አሁን የሃዘን መግለጫ ማውረዳቸው ሃፍረታቸውን አይሸፍነውም። አደግን፣ ተመንደግን፣ የሚሌኒየም የልማት ግብ አሳካን፣ በ2020 አገሪቱ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃዋ ያድጋል፣ የእናቶች ሞት ይቆማል፤ እህል ኤክስፖርት እናደርጋለን፣ ……. ከሚለው ከቆሼ ሰፈር በሚብስ ሁኔታ የሚሽተውን ጉራና ባዶ ቅስቀሳ በማቆም ዛሬ ሃፍረታቸውን ሊያውጁ በተገባ ነበር።
አንድ አገር ዜጎቿን ቆሻሻ ውስጥ አኑራ ከቀበረች በሁዋላ ሌላ ማስረጃና መፈክር ረብ የለውም። ከዚህ በላይ አሳፋሪና ህሊናን የሚያሰብር መርዶ አይኖርም። ባንዲራ ዝቅ አለ፣ ሃዘን ታወጀ፣ የሚፈይደው ነገር የለም። ሊቢያ ወገኖቻችን ሲታረዱ አልቀሰንና ባንዲራ ዝቅ አድርገን ስደቱን ማስቆም አልቻልንም። ሊቢያ የታረዱ ወግኖች ሃዘን ሲሰማ ወደ ሊቢያ ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሌ፣ ደ/ አፍሪካ ለመሰደደ ጉዞእ የጀመሩ ነበሩ። አሁንም ስደቱ ብሷል። ቆሻሻ ውስጥ ከምኖርና ከመሞት በሚል። ይህ ኩራት ከሆነ ኩሩ!! በባህር፣ በየብስ፣ በበረሃ…. መሞት ….. ይህ ሁሉ ድህነት ደህነት ድህነት ደህነት…… እንጂ ሌላ አይደለምና መሪዎቻችን ሃፈረታችሁን ተቀበሉ። በባዶ ቂጥ ” ኩሩ አበሻ” የምትሉም አስቡ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *