መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ለንባብ የበቃው የኢሕአዴግ ልሳን የሆነው አዲስ ራዕይ መጽሔት ከጥልቅ ተሀድሶ ጋር በተያያዘ 50 ሺ የኢሕአዴግ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ይፋ አደረገ።

በጥልቅ የፓርቲው መታደስ ንቅናቄ ከዘጠና በመቶ የሚሆኑ አባሎቹ መሳተፋቸውን ያስታወሰው ሰነዱ፣ “ከአምስት ሚሊዮን በላይ ከሆነው አባል ሃምሳ ሺ ያህሉ የፈጸሙት ጥፋት ከማስጠንቀቂያ በላይ ቅጣት የሚጠይቅ ሆኖ በመገኘቱ የድርጅቱ መተዳደሪያ በሚፈቅደው መሰረት ከኃላፊነት ዝቅ የማድረግ ወይም የማንሳት፣ ከድርጅት አባልነት የማባረር የመሳሰሉ አስተዳደራዊና ድርጅታዊ ርምጃዎች ተወስዷባቸዋል” ብሏል።

አያይዞም፣ እጅግ የሚበዙት አባላት ራሳቸውን አርመው በተሃድሶ በብቃት ለመንቀሳቀስ እንደሚችሉ እምነት የተጣለባቸው ሲሆኑ የተወሰኑት ደግሞ ራሳቸውን እንዲያስተካከሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ሲል ፓርቲው አስታውቋል።

ጥልቅ ተሃድሶው ይሳካል፣ አይሳካም የሚል ሙግት በአባለት ዘንድ እንዳለ ሰነዱ ይፋ አድርጎ፣ “ከብሔራዊ ክልል ከመጡ ግብረመልሶች ከሕዝቡም ከተሰበሰቡት የዳሰሳ ጥናቶች መረዳት እንደሚቻለው በተሃድሶው መሳካት ጥርጣሬ ይታያል። በዚህ ረገድ የሚነሱ የኢሕአዴግ መታደስ የነበረበት፣ ችግሮቹን ማስተካከል የነበረበት ጊዜ አልፏል፣ በብልሽት ረጅም ርቀት ከሄደ በኋላ የመጣ ተሃድሶ በመሆኑ አይቻልም እና የመሳሰሉ አስተያየቶች ናቸው። እነዚህ እውነት የሌላቸው ሃሳቦች ናቸው ማለት አይቻልም። በርግጥ በጥልቅ የመታደሱ ንቅናቄ ቀደም ብሎ መካሄድ ነበረበት፣ ብልሽቶቹ ሰፊ በመሆናቸው ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት ቀላል አይሆነም” ሲል ስጋቱን አስቀምጧል።

ሰነዱ በጥያቄ ያነሳው፣ “ያሉን አማራጮች ሁለት ብቻ ናቸው። አንድም ጊዜው አልፏል፣ ማስተካከሉ ከባድ ነው በሚል ችግሮቹ እንዲቀጥሉ መፍቀድና የበለጠ ጥፋት፣ በአገር ላይ አርማጌዶን ማወጅ፣ አሊያም ችግሩ ከደረሰበት በላይ እንዳይሄድ መግታትና የተበላሹትን የተቻለውን ያህል ማስተካከል፣ አዳዲስ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መቆጣጠር ናቸው። ኢሕአዴግ የመረጠው ሁለተኛውን አማራጭ ነው። ይህ አማራጭ የሚጠይቀው ብዙ መስዋእትነት እንደሚኖር ቢረዳም በተቻለ መጠን በአነስተኛ መስዋዕትነት ለውጥ ለማምጣት መረባረብ እንደሚገባው ያምናል” ብሏል። ሰንደቅ ጋዜጣ

Related stories   በጋምቤላ ኢንዘስትመንት - ለ381 ባለሃብቶች ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተደራርቦ ተሰጠ!! 200 ባለሃብቶች 4.96 ቢሊዮን ብር ወስደዋል- ብሩ ለታለመለት ዓላማ አልዋለም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *