ከዝግጅት ክፍሉ:- “አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ስለምን ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር ተሳነን?” በሚል ርዕስ ተከታታ ጽሁፎች ስናትም ሰንብተናል፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ሙሉ ጽሁፍ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡ እርግማን ሁለት “ሚኒልክ ኤርትራን ሸጠ፤ ትግራይን በደለ” የሚለው ሁለተኛው ክፍል ደግሞ እዚህ ላይ ይhttps://zaggolenews.com/2017/03/06/1370/ገኛል፡፡ በዚህ በሦስተኛው ክፍል የመጨረሻውንና ማጠቃለያውን ይዘን ቀርበናል፡፡

አፄ ምኒልክ ባልዋለበት ማዋል የዘመናችን “ፖለቲከኞች” ከታሪክ የሚያገኙት ግብር – አልባ ትርፍ ሆኗል፡፡ የአፄውን አገር የማቅናትና የግዛት አንድነትን  የማስከበር ዘመቻ በ“ቅኝ ግዛት” የሚተረጉሙት እንዳሉ ሁሉ የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ ከትግራይ ወደ ሸዋ በመዞሩ ምኒልክን “ባንዳ” እና “አገር ሻጭ” እያሉ የአባቶቻቸውን ዝንፈት በአደባባይ ምኒልክ ላይ የሚለጥፉ ብልጣብልጥ “ፖለቲከኞች” ተበራክተዋል፡፡ በዚህ መሀል የእልህ – እልህ ፖለቲከኞች መገለጫ የሆነ አሳዛኝ ክስተት እየታየ ነው፡፡ እሱም “ምኒልክ የእኛ ነው” የሚሉ ደረቅ “ፖለቲከኞች” አደባባዩን ተቀላቅለዋል፡፡

በምኒልክ ላይ የሚወርደውን ፖለቲካዊ እርግማን “እንከላከላለን” የሚሉ ወገኖች “ምኒልክ የኛ ነው”  ሲሉ እየተስተዋለ ነው፡፡ የአድዋ ድል በዘውግ ደረጃ ተቧድኖ ማክበር፤ ምኒልክንም ሆነ በርሱ ዘመን የተከወኑ ዘመን ተሻጋሪ ድሎች በተቧዳኙ ዘውጋዊ ማንነት ብቻ ለመቀንበብ በሚደረግ ጥረት ሊተረጎም ይችላል፡፡

ይበልጥ ግልጽ ለመሆን ያህል … “ምኒልክን” መርገም ዘውግ ተኮር የፖለቲካ ጥቅም አለው ብለው የሚያምኑ የኦሮሞና የትግራይ ጠርዘኛ ዘውጌ ብሄርተኞች አሉ፡፡ በአንፃሩ ምኒልክን እንደፍፁም መሲህ አድርጎ የሚያየው አዲሱ የአማራ ዘውግ ተኮር ስብስብ አለ፡፡ እነዚህ ጠርዝ የታከኩ  አመለካከቶች የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት የሚኳትኑ ቡድኖች ናቸው፡፡ አፄውን አብዝቶ በመርገም እና መሲህነቱን በማጎን ታሪክን የተንተራሰ ዘውጋዊ ንቃት መፍጠር የእንቅስቃሴዎቻቸው መገለጫዎች ናቸው፡፡

የአማራ ዘውጌ ብሄርተኝነት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፍጹም አዲስ ክስተት ነው፡፡ መአህድ በህወሕት ጫና፣ ከኘ/ር አስራት በኋላ በነበሩ አመራሮች ድክመት፣ በዘውግ ማንነትና በአገራዊ ማንነት ግጭቶች የተነሳና በሌሎችም ምክንያቶች በፖለቲካው ሜዳ ላይ ከከሰመ በኋላ የአማራ ልሂቃን በህብረት ብሄራዊ ፓርቲዎች ዙሪያ በመስብሰብ ከእስር እስከ ህይወት ዋጋ የተፈራረቀ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ታሪክን የታከለ የዘውግ ውርክቦች ቢፈጠሩም “ምኒልክ የኛ ነው” በሚል በዘውግ ደረጃ በመቧደን የአድዋን ድል ያከበረ የፖለቲካ ኃይል ሲቪክ ማህበር፣ የኮሚኒቲ (ዘውጋዊ) ማህበር፣ … ጨርሶ አልነበረም፡፡

ዛሬ ላይ ፍፁም ባልተለመደ መልኩ የአማራ ዘውጌ ብሄርተኝነት አራማጆች፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዘውግ ደረጃ በመቧደን በመለስተኛ አዳራሽ (በስዊትዘርላንድ ሎዛን ከተማ)፣ በፓልቶክ፣ በፌስ ቡክ፣ መጠነኛ ስርጭት ሞገድ ባላቸው ሬዲዮ ኘሮግራሞች፣ … ሲያከብሩ ተስተውለዋል፡፡ የአድዋ ድል መታሰቢያ በአልንም ሆነ የምኒልክን ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች ማክበር የሚያስመሰግንና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ ችግሩ ያለው እንዲህ ያለ አገራዊነትን ተሻግሮ የአፍሪካ ኩራት የሆነን በዓልና የድሉን መሪ አባ ዳኘው – ምኒሊክን በዘውግ ደረጃ ወርዶ ማክበሩ ላይ ነው፡፡ ስለ አፄ ምኒልክም ሆነ ስለ አድዋ ድል እንደ አገር አንጂ እንደዘውግ ተቧድኖ ማውራት በዓሉንም ማክበር የአባቶቻችንን የህብረት ድል በማፍረስ የሚበየን እልፍ ሲልም በክህደት የታጀበ የታሪክ ድኩማንነት ነው፡፡ አባቶቻችን ወደውና ፈቅደው አገራዊ ጀግና ሆነው አልፈዋል፡፡ እኛ ግን ከአገራዊ ጀግንነታቸው ጎተተን በማውረድ ዘውጋዊ ጀግና ለማድረግ ስንጣጣር እንገኛለን፡፡ ከዚህም በላይ የታሪክ ኑፋቄ ከቶ ከወዴት አለ? በታሪካችን ውስጥ ህብረትና በጎ መንፈስ  እንዳናይ  አገራዊ ዕጣ ፈንታችን ቀይዶ የያዘን ይመስል የታሪክ ገመድ ጉተታ ውስጥ መግባታችን አሳዛኝ ነገር ነው፡፡

Related stories   "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

አፄ ምኒልክ ከነጉድለቱ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ጥሎ አልፏል፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ ቅርጽ ከሞላ ጎደል የአፄው የንግሥና ዘመን ውጤት ናት፡፡ የአድዋ ድል የአባቶቻችን የመደማመጥና የመተባበር ውጤት ነው፡፡ ምኒልክን አልባ የአድዋን ድል ማስመዝገብ ይቻል (ይሆን) ነበር ብሎ ማመን ይቻላል፡፡ ይሁንና በታሪክ የምናውቀውን የአድዋን ድል ያለ ምኒልክ ማሰብ ክርስትናን ያለ ክርስቶስ፣ እስልምናን ያለ ነብዩ መሐመድ እንደማሰብ ያለ ቅዥት ነው፡፡ ይህ የታሪክ  ሀቅ የማይዋጣላቸው ዝግና የተመረጠ የታሪክ ግንዛቤ ያላቸው ዘውጌ ብሔርተኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አሁንም ቢሆን ማንነትን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ እስካልቀረ ድረስ ይህ አይነት ምልከታ መቀጠሉ ጭራሹኑ እየሰፋ መሄዱ የት ይቀራል?

በምኒልክ የንግስና ዘመን ለተመዘገቡ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች፤ ዋልታና ማገር የነበሩ አባቶችን ውለታ መርሳት የሚቻል አይደለም፡፡ ራስ ጎበና ዳጬ፣ ደጃች ባልቻ ሳፎ፣ ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ራስ መኮንን ወ/ሚካኤል ጉዲሳ፣ ራስ ዳርጌ፣ ራስ ወልደገብርኤል፣ ራስ መንገሻ አንቲከም … እያልን ከምንዘረዝራቸው ታላላቅ የጦር አበጋዞች ውስጥ ከኦሮሞና ከደቡብ የተዉጣጡ የአገር ምስረታ የፊት መስመር ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ እንደ ራስ ጎበና ዳጬ ያለ ጀግና የጦር አበጋዝ ሰባት ግዛቶችን (የደቡብና የምዕራቡን) የኢትዮጵያ አካል ማድረግ ችሏል፡፡

ዛሬ ላይ “ምኒልክ የእኛ ነው” የሚሉትን የአማራ ዘውጌ ብሔርተኞች  የምኒልክ ብርቱ ቀኝ እጅ የነበሩት የጦር አበጋዞች ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የደከሙትን ድካም፣ የከፈሉትን ዋጋ ከዚህ አንጻር በአደባባይ እየካዱ መሆኑን ይሰመርበት፡፡

አድዋ የአባቶቻችን የመደማመጥና የመከባበር ውጤት ነው ካልን በምን አግባብ በዘውግ ደረጃ ወርደን አድዋን በችርቻሮ እናከብረዋለን?  ከእያንዳንዱ የአባ  ዳኘው ምኒልክ ስኬታማ ተግባር ጀርባ የጦር አበጋዞች አሻራ አለበት፡፡ አፄው ያለ ጦር አበጋዞች ድጋፍ ኢትዮጵያን መመስረት አይሳካለትም ነበር፡፡

ለአፄ ዮሐንስ ውድቀት አንዱ ማሳያ የብርቱ ጦር አበጋዞች ድርቀት እንደሆነ ይስተዋል? አንድ ራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) ከስንቱ ጦር አውድማ ይደርስለት? (ራስ መንገሻን ረስተን አይደለም በዮሐንስ ጊዜ እዚህ ግባ የሚባል መሪ አልነበረም፤ ኋላም ለባዕድ ስርዓት የማደግደግ ተደጋጋሚ ባህሪ የታየበት ሰዉ ነበር) የአፄ ዮሐንስ አቅመ ቢስነት የምኒልክ ጉልበታምነት ምስጢር ግልጽ ነው፡፡ ቀዳሚው አባ በዝብዝ የጦር አበጋዞች ድርቅ ነበረበት፤ ተከታዩ አባ ዳኘው ደግሞ ግራ ቀኙን ብርቱ ተፋላሚ ራሶች ነበሩት፡፡ ያዉም “ከአንተ በፊት እኛ እንወድቃለን” የሚሉት!!

በጠመዝማዛው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምኒልክ እና የጦር አበጋዞች ድካም ለአገር አንድነትና ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ የተከፈለ ዋጋ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ውህድ ህላዌ መሀንዲስ  አባ ዳኝው በንግሥና ዘመኑ ራሱን እንደ አንድ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ንጉሠ ነገሥት እንጂ እንደ  አንድ የ“አማራ” ንጉሠ ነገሥት አድርጎ አስቦ አያውቅም፡፡ የምኒልክን ኦርቶዶክስ  ክርስቲያናዊ ንጉሠ ነገሥትነት ማብራራት  አስፈላጊ አይደለም፡፡ አደባባይ ላይ የተሰጣ  እውነት ነውና፡፡ ይሁንና ንጉሠ ነገሥቱ ሌሎችንም ሀይማኖቶች ባለመጋፋት “ባለህበት እደር” የሚል አዋጅ እንዳወጣ ይታወቃል፡፡

አፄ ምኒልክን በዘውግ ደረጃ ጎትቶ ማውረድና “ምኒልክ የእኛ ነው” በሚል  ቃና፤ በተአብዮ ተሞልቶ በየፓልቶኩ መመጻደቅ የታሪክ ክህደት እንጂ አዋቂነት አይደለም፡፡ የነገሩ ምጸት እነዚህ ሰዎች በየማህበራዊ  ሚዲያ “አላማችን በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ የአማራ መንግስት መመስረት ነው” ሲሉ የከረሙ መሆናቸው ነው፡፡ አባ ዳኘው ምኒልክና “አባት አገር አማራ” ምንና ምን ናቸው? ለየቅል!!

Related stories   ዶክተር አብራሃም በላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ!

በመሰረቱ ከሆነ የምኒሊክ ቀዳሚ ማህበራዊ መሰረት ሸዋ ነው፡፡ ሸዋ ደግሞ የዘመናችን ሰዎች በዘውግ ተከል ፌዴራሊዝም ቀንብበው እንደሚነገሩን ሳይሆን፤ ሸዋ የኦርቶዶክ ክርስትና እና የቱለማ ኦሮሞ የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ውህድ ውጤት የወለደዉ የወል ማንነት ነው፡፡ ይሄ የወል ማንነት በተለየ መልኩ በላይኛው መደብ ጋብቻን (በርግጥ ጭሰኛዉ መደብም አምቻ ጋብቻ ተፈጥሯል) መሰረት በማድረግ በጊዜ ሂደት ወደ ገዥ ኃይልነት እያደገ የመጣ የገዥ መደብ መሰረት ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የሸዋ ኦሮሞ ዉስጥ በሂደት እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ ጳጳሳት፣ ቀሳዉስትና ዲያቆናት የወጡት፡፡ የዉህዱ (የቱለማ ኦሮሞና የኦርቶዶክስ ክርስትና) ዉጤት ይመስላል ይህ ዘመናትን ያካለለ የውህድ ሂደት በምኒልክ ጊዜ ይበልጥ ጠንክሯል፡፡

ከብዙ ማሳያዎች አንድ ለመንገድ… የራስ ጐበና ዳጬ ልጅ ወዳጆ ጐበና የምኒልኳን ሸዋረገድን አገባ፤ በውጤቱም ወሰንሰገድ የተባለ ልጅ ተወለደ፡፡ ይህ ልጅ በአሥራ አራት አመቱ ባይቀጭ የምኒልክ አልጋ ወራሽ ይሆን ነበር፡፡ በዚህ አግባብ ምኒልክ ለጐጃም ሰው ሳይሆን ለቱለማ ኦሮሞ ይቀርባል፡፡ ከበጌምድር ሰው ይልቅ የሸዋ ኦሮሞ የምኒልክ የመጀመሪያ የንግስና ዘመናት የኃይል ምንጭ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የመንዝም ሆነ የየጁ ገበሬ ለምኒልክ ገባር ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡

ስለ “አባት አገር አማራ” እያለሙ “ምኒሊክ የእኛ ነው” ማለት በዚያኛው ጽንፍ ምኒልክ ላይ የፖለቲካ እርግማን ከሚያዘንቡ የታሪክ ኑፋቄ ዘውጌ ብሄረተኞች ድርጊት በምን ይለያል? በምንም! ለአንድም ኃልዮታዊ ትንታኔ አልመች ብሎ ባለው የኢትዮጵያ ዘውጋዊ ክፍፍል የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ራሱን ለማቅናት የሚውተረተረው የአማራ ዘውጌ አኳያም እንደ “ወደረኞቹ” ሲፈጠፈጥ እየታዘብን ነው፡፡

ደግነቱ አማራ ክፍለሀገራዊ (አካባቢያዊ) ማንነቱን ጠብቆ ከኢትዮጵያዊነት ወርድና ቁመት የማይጠብ የማይሰፋ ክቡድ ህዝብ ነው፡፡ ፖለቲካዊ መብቃት ላይ ያልደረሱት የሳይበር አርበኞች እና ደቃቅ “ፖለቲከኞች” ግን ሳይነሱ መውደቅ የመጀመራቸውን ምስጢር ከአባዳኘውና ጓዶቹ የታሪክ ግርጌ ስር ቢፈልጉት መልሱን  ያገኙት ነበር፡፡ ሌሎች የጉርምስና ሐተታ አነብናቢ ዘውጌ ብሄርተኞችም የአባቶቻቸውን አሻራ ያረፈበትን የምኒልክ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች ዝቅ ብለው ቢፈልጉ ለመፍትሔው (ለጋራ ነፃነት) ይቀርቡ ነበር፡፡

እንደ መውጫ  

የትኛውም የታሪክ ትንተናና ፅሁፍ ዘላለማዊ እውነት የለውም፡፡ አዳዲስና አስተማማኝ መረጃዎች ሲገኙ በመረጃው መሰረት እንዲስተካከል ከቶውንም እንዲለወጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ በታሪክ ያለቀለት ፍፁም እውነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ታሪክ ሁልግዜም ቢሆን አንፃራዊ እውነት ነው፡፡ በዚህ አግባብ የኢትዮጵያ አገራዊነት ታሪክ ተፃራሪ ትርጓሜዎችን (“የብሄር ጭቆና” Vs “መደባዊ ጭቆና”) በሙያው (ታሪክ) መስፈርት ተቀባይነት ባላቸው (አፈ-ታሪክን በተሻገሩ) የታሪክ ማስረጃዎች እየተመዘኑ ወደ አደባባይ እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል፡፡

ይህን አካዳሚያዊ ፅንሰ ሐሳብ በቅጡ በተጠና ሥርዓተ-ትምህርት በመደገፍ ታሪካችን የወደፊት እርምጃችን አካል እንዲሆን ማድረግ ኃላፊነት ከሚሰማው “መንግስት” የሚጠበቅ ተግባር ነበር፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ የህወሃት አፈጣጠር እንዲህ ላለው ነፃ የአካዳሚ መስመር ተፃራሪ ኃይል ነው፡፡ በረኽኞች ጥልቅ በሆነ የትላንት ድምሰሳ የሚያምኑ በመሆኑ ታሪክን በጠባቡ በማየት ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር ማቆራኘት ምርጫቸው አድርገውታል፡፡

Related stories   የኮሚሽነር አበረ ህልፈት "በነጋዴዎች" እይታና ፤ የሃኪም ትክክለኛው መረጃ " ቸልተኛነት አይተናል"

የትላንት ድምሰሳቸውን ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ የታሪክ ትምህርትን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ኮሌጆች ዩኒቨርሲቲዎች) በመርሐ-ግብር ደረጃ እያሰናበቱት ነው፡፡ በውጤቱም ታሪክን ከእውነታው ጋር ለአገራዊ ግንባታ ማዋል ቀርቶ፤ በሰነድ የተደገፈ ምክንያታዊነቱ መንምኖ ለዘውግ ፖለቲካ መቀሰቻ የሆነ መፈክራዊ ጩኽት የበዛበት የፕሮፓጋንዳ መድረክ ሆኗል፡፡

በአካባቢያዊ ማንነት የታጠረው (የተመረጠ) የታሪክ ግንዛቤያችን ዓለምአቀፋዊ ሰዎች እየተፈጠሩ ባለባት አለም ራሳችንን ነጥለን በአካባቢያዊ ማንነት በመታጠር ዘውጋዊ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገው መሯሯጥ ኢትዮጵያንና ትውልዷን በተረገመ የታሪክ ዘመን ውስጥ እንድታልፍ አስገድዷል፡፡ አድዋን የሚያህል ታላቅ የነፃነት መንፈስ ለማንቋሸሽ የተያዘው ሩጫ የዛሬዋንም ሆነ የነገዋን ኢትዮጵያ የትውልዶች መከራ ከማባባስ ያለፈ አንዳች ፋይዳ የለውም፡፡

አድዋን የሚዘክር አንድ ብሔራዊ ሙዚየም መስራት ያቃተው አገዛዝ ቂምን ለትውልድ እነሆ እያለ በየአካባቢው ለትውልድ ዕዳ የሚሆኑ ሐውልቶችን ይሰራል፡፡ የኃይማኖት አስተምህሮት ያህል ልዕልናን ተጐናፅፎ ያለው ዘውጌ ብሄርተኝነት ታሪክን ማገዶው በማድረግ ትውልዱን በተሳሳተ የታሪክ ወንዝ ጭልጥ ወዳለ ገደል እየመራው ይገኛል፡፡

ትውልዱ በታሪክ ትርጓሜ የሚቀርብለትን መረጃ ይዞ የፈለገውን አቋም መያዝ መብቱ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ ግን ለፖለቲካ ግባቸው ሲሉ በታሪክ ፊት ጥቁር መጋረጃ ጋርደው ትውልዱን በተሳሳተ የታሪክ ወንዝ እንዲፈስ ማድረጋቸው የጋራ ቤታችንን መሰረት እንደመናድ ይቆጠራል፡፡ ፍፁም መስመሩን የሳተ የታሪክ አረዳድ፤ የጥላቻና የበቀል ስሜት ማነሳሳት ለአገሪቷና ለህዝቧ ደህንነት አደጋው የከፋነው፡፡

የታሪክ አረዳድ ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ጠመዝማዛ የታሪክ ጉዞ ባሳለፈች አገር ብሔራዊ መግባባት የለም ሲባል ዘርፎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ከዘርፎቹ ውስጥ ግን ታሪክ ቀዳሚው ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር ከዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ፤ አገር የማቀናት ዘመቻዎች ጋር ተያይዞ ከተፈጠሩ ችግሮችና ተንከባላይ የትውልድ ዕዳዎች ታጋች (hostage) ከመሆን ይልቅ መታረቅ አለብን፡፡ ምዕራባዊያን በሥልጣኔ ወደፊት መጓዛቸውን ያላቆሙበት ምስጢር ከታሪካቸው ጋር ስለ ታረቁ ነው፡፡

የታሪክ መሰረቶች ላይ የሚቆሙ ልዩነቶችን መሻገሪያው ብቸኛ መፍትሔ ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ብቻና ብቻ ነው፡፡ ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ከታሪካችን ጋር እንድንታረቅ ድልድይ ይሆነናል፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም ዘውጐች (በሰሜን በደቡብ በምስራቅና በምዕራብ ያሉትን) እንዲያካልል ማድረግ ይቻላል፡፡ ታሪካችንም የ“እኛ” እና የ“እነርሱ” በሚል ሳይሆን ዜግነታዊ መሰረት ባለው መልኩ አካቶነት ያለው የጋራ ታሪክ ማንበብ ንችላለን፡፡ ይህ መንገድ . . . በደም የተዋጀው ቆይታችን በእኩልነት ስሜት አንድነታችን በፅኑ መሰረት እንዲቆም ያደርገዋል፡፡

በኢትዮጵያችን ምድር ይህ እንዲሆን ከተፈለገ የኢትዮጵያ የታሪክ ካንሰር የሆነውን ህውሃት ከፖለቲካ መድረኩ ነቅሎ መጣል ግድ ይላል፡፡ የትግል ጠረጴዛው ላይ ያሉት ምርጫዎች ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ወይ አብሮ መውደቅ አልያም በአንድነት መነሳት፡፡ በእስካሁኑ ጉዟችን የመጀመሪያውን ምርጫ የያዝን ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ከውስጥ ችግራችን አኳያ ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር የተሳነን፡፡ ሁለተኛውን ምርጫ (በአንድነት መነሳት) የያዝን ቀን የአድዋን ድል ወደ ፖለቲካዊ ድል በመቀየር በፍትህና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መፍጠር እንችላለን፡፡ በርግጠኝነት ያኔ ታሪክ ትምህርት እንጂ ፍርድ ቤት አይሆንም!!

goolgule.no 

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *