• የግል ቤት የሌላቸው የክልሉ ተወላጆችና የኦሮሚያ ዳያስፖራዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ
• የመጠጥ አምራች ኩባንያና የሲሚንቶ ፋብሪካ አክሲዮኖች ለክልሉ ተወላጆች ይቀርባሉ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ ተወላጆቹ በሙሉ በክልሉ ከተሞች የመኖሪያ ቤት መስሪያ የከተማ ቦታ በነፃ እንዲያገኙ ወሰነ፡፡
በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ የግል መኖሪያ ቤት የሌላቸው የከተማ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ መምህራንና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ የኦሮሚያ ዳያስፖራዎች በሙሉ የመኖሪያ ቤት መስሪያ የከተማ ቦታ በነፃ እንዲያገኙ መወሰኑን የኦሮሚያ የከተማ ቤቶች ልማት ም/ሃላፊ አቶ ሽመልስ አብዲሣ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ከዚህ ውሣኔ ላይ የደረሰው የክልሉ ከተሞች የተወላጆችን ጥቅም ባማከለ መልኩ እንዲያድጉና ተወላጆች በከተሞች ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑም ተገልጿል፡፡ የክልሉ መንግስት ባደረገው ግምገማ፤ የቤት ኪራይ ዋጋ ውድነት ነዋሪዎችን ላልተፈለገ ወጪ መዳረጉንና እንዳይረጋጉ ማድረጉን፣ ቀደም ሲል በነበረው አካሄድ የክልሉ ከተሞች እድገትም በሚፈለገው መጠን አለመሆኑን እንዲሁም የክልሉን መሬት ለህገ ወጥ ደላሎች ያጋለጠ አሰራር እንደነበረ ደርሶበታል፡፡ እነዚህን ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባትም ዜጎች የቤት መስሪያ የከተማ ቦታ እንዲያገኙ የሚያስችለው ደንብና መመሪያ ሊወጣ መቻሉን ም/ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡
‹‹ህብረተሰቡ የከተማ ህይወት እንዲኖር ይፈለጋል›› ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ይህ የክልሉ መንግስት እቅድ ይሄን ለማሳካት ያለመ በመሆኑ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በዚህ ማዕቀፍ እንዲካተቱ መደረጉን አብራርተዋል፡፡ ከመከላከያ ሰራዊት ጡረታ የወጡ ግለሰቦችና ሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
በአካባቢው ለሁለትና ከዚያ በላይ ዓመት የኖሩ፣ የቤት መስሪያ ገንዘብ መቆጠብ የሚችሉና ቀሪ ገንዘብ መንግስት በሚያመቻቸው ብድር ለማግኘት ፍቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች የቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት መደራጀት እንደሚችሉ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡
ቦታ ፈላጊዎች የሚደራጁት በ4 አይነት አማራጮች ነው ተብሏል፡፡ በጋራ አፓርትመንት ለመገንባት የሚፈልጉ፣ G+1 እና ከዚያ በላይ መገንባት የሚፈልጉ እንዲሁም ቪላ ቤት መስራት የሚችሉ በሚል ሲሆን ይሄን ለማድረግ አቅም የሌላቸው መለስተኛ ቤቶችን ለመስራት የሚችሉባቸው አማራጮች መቀመጣቸውን አቶ ሽመልስ አብራርተዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በዝቅተኛ ወጪ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የሚገነቡ የቤት አማራጮችን እያጠና መሆኑም ተገልጿል፡፡ አንድ ግለሰብ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ የተሰጠውን ቦታ መሸጥ መለወጥና ከህጋዊ ወራሾች በስተቀር ለ3ኛ ወገን ማስተላለፍ እንዲሁም በውክልና ማሰራት አይችልም ብለዋል፤ ሃላፊው፡፡ እስከ 10 ዓመት ድረስም ካርታ እንደማይሰጥ አክለው ገልፀዋል፡፡ በነዚህ ጥብቅ መመሪያዎች እንዲታጠር የተደረገው የመሬት ብክነትንና ያለአግባብ መገልገልን ለማስቀረት በማሰብ ነው ተብሏል፡፡
በክልሉ ከ9 ዓመት በላይ መሬት በዚህ መልክ ተሰጥቶ እንደማያውቅ የጠቆሙት አቶ ሽመልስ፤ የክልሉ መንግስት ይሄን ሰፊ እቅድ ሲተገብር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም በዝርዝር መለየቱን አስታውቀዋል፡፡ ከተለዩ ተግዳሮቶች መካከል የመሬት አቅርቦት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በተለይ ለአርሶ አደሮች የሚከፈል የመሬት ካሳና መንግስት መሬቱን ያለምንም የሊዝ ክፍያ ገቢ ሳያገኝበት በነፃ ለፈላጊዎች ማስተላለፉ ጫና ሊፈጥርበት እንደሚችል ጠቁመው፣ ለዚህም የተለያዩ አማራጮች እየተፈተሹ መሆኑን አስረድተዋል። ሌላው ተግዳሮት ለብድር አቅርቦት የሚሆን የፋይናንስ አቅም ሲሆን ይህንንም የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ለዚህ ፕሮጀክት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ዝግጅት ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን በአሁን ወቅትም ቤት የሌላቸውን ሰዎች ለይቶ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ የመሬት አቅርቦቱም ሰዎች በፈለጉት የቤት አይነት ተደራጅተው ሲቀርቡ ወዲያው የሚፈፀም መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ይፋ ባደረገው ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት››፣ ከኦዳ ትራንስፖርት አክሲዮን በተጨማሪ በቅርቡ የተለያዩ መጠጥ አምራች ኩባንያና የሲሚንቶ ፋብሪካ አክሲዮኖችን ለክልሉ ተወላጆች በሽያጭ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የመንገድ ትራንስፖርት ሃላፊ አቶ ታከለ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

Related stories   ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ዜናና ፎቶ አዲስ አድማስ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *