ዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ፤ በ‹‹ የሠዓሊገብረ ክርስቶስ ደስታ የመጀመሪያ የሥዕል ትርኢት ካታሎግ ፲፱፻፶፮ ዓ.ም ›› ላይ ያቀረቡት የመግቢያ ጽሑፍ። የካቲት ፳ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም

ይህ ደራሲ እንደሚለው ሰው ከሌሎቹ ሕያዋንየሚለይበት ዋናው ምልክት ጥበብ የምንለው ነው። የተሳሳተ አይመስለኝም። ፈረንጆችን የጥበብን ባሕርይ በሚገባ ስለሚረዱ ሌላ መግለጫ ዘዴ ቢያጡ የጥበበኛውን የሥራ
ጠባይ ከፈጣሪነት ጋር አስተካክለው ይናገራሉ።
በሀገራችን የሐሳብ ዘዴ ፈጣሪነት ከመለኮት ጋር ብቻ የተያያዘ ነው። በዕውነቱ የታላላቆቹን ጥበበኞች ረቂቅ ሥራ ሲመለከቱት ሰው ምን አይነት ጉልበት በውስጡ የደበቀ መሆኑን መረዳት ይቻላል። አንድ ትልቅ የጥበብ ሥራ ተቀዳሚ
ምሳሌ የሌለው እምኀበ አልቦ እንደተገኘ የሚቆጠር ነገር ነው። የማይመለስ ፤ የማይደገም ለሁል ጊዜ ብቻውን የሚዘልቅ ካስገኘው ጠቢብ ጋር ውስጣዊ ነፍሳዊ ግንኙነት ያለው ረቂቅ ፍጥረት ማለት ነው።

የጊዜና የቦታ ድንበር ወይም ውሳኔ የማያግደው፤ ዓላማው ዘለዓለማዊ UNIVERSAL ETERNAL ዋጋ ያለው ነው።

ጥበብ ስንልበአማርኛችን ከሌላ ዘይቤዎች ጋር የማይደባለቅ
ስለሆነ ፤ ለይተን መረዳት አለብን። ጥበብ ወይም የውበት ጥበባት FINE ARTS የሚባሉት ከቃላት ፤ከድምፅ፤ ከቅርፅ እና ከቀለም ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። እነዚህም ሥነ ጽሑፍ ፣ዝማሬ ወይም ሙዚቃ ፣ ሥነ ሕንፃ እና ሥዕል
ናቸው። እሊህን ጥበባት የሰውነት HUMANITY መታወቂያ መለዮ ብሎ ሺለር የተባለው ዝነኛ ደራሲ ጠርቶአቸው እንዲህ ያለ ጥበብ የማይገኝበት ዘመንና ቦታ የለም። በዝቅተኛ
መልክ የሚታዩበት የታሪክ ዘመን ትልቅ የመንፈስ ድኅነትን ይመሰክራል። ዳብረው ጎልተው የሚታዩበት ዘመን ግን ብርሃን የበዛበት የሰው ልጅ በረቂቅ ክንፉ ከከፍተኛ ምጥቀት የደረሰበት ወርቃዊ ብርሃናዊ ዘመን ነው። በሀገራችን በሥነ
ጥበባት ረገድ ወደ እንዲህ ያለ ዘመን በመድረስ አምርተናል። ተቃርበናል ለማለትም ያስደፍራል ብርሃን የሆኑ ብዙዎች ከዋክብት መታየት ጀምረዋል።

ከነዚህ አንዱ በዚህች አነስተኛ ጽሑፍ ለማስተዋወቅ የምንፈልገው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ነው። ትሁትነቱን በማክበር ስለርሱ ብዙ መናገር አልፈልግም። ከዚያም በላይ ችሎታዬም አይፈቅድልኝም። አንድ ሊቅ እንደሚለው ፤
‹‹ጥበብ የራስዋ ካህንና ምእመን አሉዋት›› ቁጥሬ ከጥበብ ምእመናን ነው። ግን ተቀዳሚ ፍርድ PREJUDICE በሌለው ምዕመናዊ ዓይኔ ይህንን ለመመልከት ችዬአለሁ። በተረዳሁት መጠን ያልተጠነቀቀ ሰው በመጀመሪያ ስሜት
‹‹እሊህ ሥዕሎች የዘመናዊ ረቂቅ ጥበብ ቁጥሮች ናቸው›› በማለት ጠቅላላ ፍርድ ሊሰጥ ይችላል። የሚሳሳት አይመስለንም። እውነት ነው።

ገብረ ክርስቶስ የዘመናዊ ጥበብ ተከታይ ነው። በጥበብ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የሰው መንፈስ ራሱን በመግለጽ በሚጥርበት ስልቶች ረገድ ሰው የዘመኑ ልጅ ነው። በዚህ ረገድ ሰው ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይመለከትም። መንፈሱ እስካሁንበተከማቹት የጥበብ ሀብታት ውስጥ አልፎ አልፎ
አዲስ ለማስገኘት ይጥራል። ገብረ ክርስቶስ ከሌሎቹ ዋናዎቹ ሰዓሊዎች ጋር የሚካፈለው አንድ ጠባይ አለው። ይህም ባሕታዊ፤ ብቸኛ የገዛ ራሱ ብቻ የሆነ የሥዕል ጠባይ ያለው መሆኑ ነው። የነገሮችን ጠባይ ብቻውን ቆሞ
የሚመለከትበት አንድ የራሱ ዳርቻ አለው። የስእልን ጣእም የለመደ ሰው በመልኮቹ ቅርጽ ፤ በቀለሞቹ ኅብራዊነትና ተቃራኒነት፤ በጠቅላላው በሥዕሎቹ ቁመትና ጥላ የሰዓሊውን ልዩ ጠባይ ወይም ስታይል ለመረዳት ይችላል። ለዚህ
ማስረጃ ከታላላቆቹ ሥእሎች አንዱን እንመልከት። ሠዓሊ ተብሎ የጎልጎታን ተራራ ያልወጣና ትልቁን ትራጀዲ ያላየ የለም። ግን የገብረ ክርስቶስ ሥነ ስቅለት ለብቻው ነው። ቀለም ተናጋሪ ሆኖአል። የሚታየው ንጹሑ ብቻ ነው። ግራና ቀን የነበሩት ፈያት ቦታ የላቸውም ። ተዘንግተዋል። ወይም ሠዓሊው ሊያያቸው አልፈለገም። ይገርማል። ጥበብ ከንጹሕነት፤ ከጽርየት፤ ከርቀት ጋር ብቻ እንጂ ከሌላ ጋር
ግንኙነት የሌላት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል። ስለሌሎቹ ሥዕሎች ሁሉ ያለኝን ስሜት በዚች ጽሑፍ፤ ለማስፈር እፈልግ ነበር። ለምሳሌ ከእስትራቪንስኪ ሙዚቃ ጋር ግንኙነት ያለውን
ሥዕል እንዲሁ ለማለፍ አይቻልም።
ግን ቦታው አይፈቅድልኝም። ከዚያም በላይ የተመልካችን
አስተያየት መምራት ይሆናል። ሥዕሎች በመላ ለያንዳንዱ ሰው በተለይ የሚገልጹት ልዩ ምሥጢር አላቸው። የገብረ ክርስቶስም እንዲህያለ ጠባይ ያላቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ
ግን የሥዕልን ውበት በመመልከት የራሱ ጣእም ያበጀ ሰው ያስፈልጋል። እንዲህ ያለ ሰው በዘመናችን ብዙ አይገኝም። የገዛ ራሱን ፎቶ ግራፍ በአራቱም ግድግዳዎች ሰቅሎ ራሱን
በማድነቅ ጊዜውን የሚያሳልፍ ይበዛል። አብዛኛው ሰው በገዛ ራሱ እንቅልፍ ውስት ተዘግቶ የሚኖር ነው። ገና ወደ ውጭ
አልወጣም። የአትክልት የጽጌያትን ውበት ፤ የተራሮች የጫካዎችን ግርማ፤ የፀሐይ መውጣትና መጥለቅ ልዩ ኅብር፤ የከዋክብትን ማንጸባረቅ በማድነቅ ጀምሮ የለሰለሰችው፤ የረቀቀችው የጥበበኛው ነፍስ በሥዕል መልክ
ያስገኘችውን ውበት እስከመረዳትና ማድነቅ ለመድረስ ጊዜና ትምህርት ያስፈልጋል። ይህንን ነገር ከሌላው ሰው ይልቅ ሠዓሊው አስቀድሞ የሚያውቀው መሆኑን አልዘነጋም። በተለይም ገብረ ክርስቶስ ሌሎች ስጦታዎችም ያሉት
ስለሆነ፤ ስለዘመናችን ሁናቴ የበለጠ እውቀት ሊኖረው ይችላል። እዚህ ላይ ከታሪክ ዕውቀቴ አንድ ትልቅ ሰው ትዝ ይለኛል። ሌኦናርዶ ዳቪንቼ ነው።

ይህ ሰው ሠዐሊ፤ደራሲ ሰካልፕተር ጸራቢ፤ ሳይንቲስት
ሙዚቀኛ፤ፈላስፋ ነበር ይባላል። ገብረ ክርስቶስ ሠዓሊ ብቻ አይደለም ። የመጀመሪያ ትምህርቱ ሳይንስ ነበር ።ጀርመን አገር በሥዕል ትምህርት ቤት ሳለ ከመተዋወቃችን በፊት
በየጊዜው በጋዜጣና በመጽሔት ያሳተማቸውን ጥልቅ አስተያየት የመላባቸውን ግጥሞች በማንበብ ደራሲነቱን ማድነቅ ጀምሬ ነበር።
ለሙዚቃ ልዩ ዝንባሌ ያለው ነው። ደግሞም በየጊዜው በተገናኘን ጊዜ በምናደርገው ጭውውት ከጥበብ ፍልስፍና አንሥቶ እስከ ሜታፊዝክ ድረስ በሚገኙት አርእስቶች
ስለምንከራከር በተለያየ ጊዜ ስለብዙ ነገሮች በመጠራጠርና በሌላ በኩል ማየት እጀምራለሁ። ብዙ ስጦታ ያለው ነው። በነዚህ የመንፈስ ስልቶች ሁሉ ብዙ ነገር ሊያስገኝ ይችላል።
እስካሁን ባስገኘው ንጹህ ደስታዬን ፤ ለወደፊቱ
ተስፋ ትልቅ ተስፋ እየገለጽኩ ፤ የስእሎቹ ትዕይንት ኤክስፖሲዮን ከዚህ ቀደም በውጭ አገር እንዳደረገው ፤ በአዲስ አበባም ብዙ አድናቂዎች እንዲማርክ ልባዊ ምኞቴን
እገልጻሉሁ።

Senedu Abebe face book

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *