ዛጎል ዜና- “ሰላም ሰፍኗል” በማለት በተደጋጋሚ ሲናገር የቆየው ኢህአዴግ የአስቸኳይ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወር ማራዘሙን አወጀ። ለዚሁም በምክንያት የቀረበው በአጎራባች ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ሰላም ባለመኖሩ፣ በየጊዜው ወረቀት የሚበተንና የተለያዩ ቅስቀሳዎች ስለሚካሄዱ ነው። ምክንያቱ በተዘዋዋሪ በአገሪቱ ሰሜን ክፍል ከፋኝ የሚሉ ሃይሎች ወይም አርበኞች ግንቦት ሰባት / የደፈጣ ጥቃቱ የባለቤትነት ችግር ቢኖረውም/ ስለመኖሩ ማረጋገጫ ሆኖ ተወስዷል። እነዚሁ ክፍሎች በተደጋጋሚ ጥቃት ማድረሳቸውን ቢገልጹም በይፋ ግጭት ስለምኖሩ ከምንግስት ወገን የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከደፈጣ ተዋጊዎቹ መሪዎች መካከል የተገደሉ ግን አሉ።

ቦታ ሳይለይና በስም ሳይጠራ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ችግር እንዳለ ያመለከቱት የኮማንድ ፖስቱ ሰከሬታር ሲራጅ ፈርጌሳ ናቸው። በተደጋጋሚ እንደሚሰማው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተለያየ ደረጃ ጥቃት እንደሚፈጸምና ህዝቡ ጥቃቱን የሚፈጽሙትን ወገኖች እንደሚደገፍ ነው። ልክ ህወሃት ጫካ እያለ ይደረግለት እንደነበረው አይነት ድጋፍ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ህዝቡ ” ከፋኝ” በሚል ጫካ ለገቡት ወገኖቹ ድጋፍ ማድረጉ ደርግ ወያኔን ለመደምሰስ እንደቸገረው ሁሉ አሁንም ተመሳሳይ ችግር ማስከተሉን ለአካባቢው ቀርብ የሆኑ ይናገራሉ። እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት ከሆነ በሰሜኑ ያለው ግጭት ወደ ሰሜን ሸዋ እንዳይዛመት ክፉኛ ስጋት አለ።

ኦሮሚያ ክልል ውስጥም ስጋት መኖሩን የሚገለጹ ዜናዎች በየጊዜው ቢወጡም ኢህአዴግ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተነሳበትን ተቃውሞ ከሁሉ በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራበት ቢሆንም የታሰበውን ያህል ውጤት እንዳላስመዘገ ማረጋገጫው የአዋጁ መታወጅ እንደሆነ ቀደም ሲል አስተያየት የሰጡ አመልክተዋል። ከአዋጁ መራዘም በፊት አውጁ እንደማይነሳ ፍንጭ ይሰጥ ስለነበር አራት ወር የመራዘሙ ዜና እጅግም አስገራሚ አልሆነም።

ኢህአዴግ ” ህዝብ በጠየቀኝ መሰረት አውጁን አራዘምኩት” ቢልም ፕሮፌሰር በየነና የኦፌዴን አመራሮች ” ህዝብ እሰሩኝ ሲል ፈቃድ አይሰጥም” በማለት የፕሮፓጋንዳውን ቀልድነት አስቀድመው አመላክተዋል። ኢህአዴግ ግን አሁን የተገኘው ሰላም በማይቀለበስበት ደረጅ እስኪደርስ በሚል ነው አዋጁን ለማራዘሙ ዋና አላማ ሲል የሚናገረው። ለሁሉም ፋና የሚከተለውን ዘግቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዘመ

መጋቢት 21፣ 2009 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ወስኗል። ከስድስት ወር በፊት በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ለተወሰኑ ጊዜያት በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በተለመደው የህግ ማስከበር ስርዓት መቀልበስ አልተቻለም ነበር።

ይህን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰላምና ጸጥታውን ለማስጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ሲተገበር ቆይቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጠለት የስደስት ወራት ጊዜ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ መቅረቱን ተከትሎ ኮማንድ ፖስቱ የአዋጁን አፈጻጸምና ቀጣይነት በሚመለከት ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ያስፈለገበትን ምክንያት አቅርበዋል። አቶ ሲራጅ በሀገሪቱ ተጋርጦ የነበረውን የጸጥታ ችግር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቆጣጠር መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ሆኖም ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሀይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ በሁከት እና ብጥብጡ ቀንደኛ መሪዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢያዙም ቀሪ በመኖራቸው እና በወረቀት ፅሁፎችን በመበተን አሁንም ሰላም እና መረጋጋትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ወገኖች አልፎ አልፎ በመታየታቸው አዋጁን ማራዘም ማስፈለጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአንፃራዊነት ሰላም እና መረጋጋቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉን ለአዋጁ መራዘም በምክንያትነት አስቀምጠዋል። በመላ ሀገሪቱ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ህዝቡ የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን አዋጁ ቢራዘም የሚል አስተያየት እንዳለው በመረጋገጡም ነው አዋጁ እንዲራዘም ያስፈለገው ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም በመላ ሀገሪቱ ያደረገውን ቅኝት መሰረት አድርጎ አዋጁ ቢራዘም የሚል አስተያየት ለምክር ቤቱ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም በሙሉ ድምፅ ወስኗል። ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተራዘመባቸው ወራቶች አፈፃፀሙ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በጠበቀ መልኩ እንዲሆንም አሳስቧል።

በድንበር አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰላም እና መረጋጋትን የበለጠ እንዲያሰፍንም ነው ምክር ቤቱ ያሳሰበው። ምንም እንኩዋን አዋጁ ባስገኛቸው ጥቅሞች የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገው ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝና ፍተሻ እንዲሁም በሚዲያ ላይ ተጥለው የነበሩ ክልከላዎች በከፊልና በሙሉ ቢነሱም አብዛኞቹ ክልከላዎች ግን አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ እንደተካተቱ ነው።

በዚህም የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ወጥተው በስራ ላይ ያሉ ደንቦችና መመሪያዎች ተፈጻሚነታቸው የሚቀጥል ይሆናል። በኮማንድ ፖስቱ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ የተሰጡ ውሳኔዎች፣ በፍትህ አካላት የተወሰኑ ጉዳዮችና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ውሳኔዎች በዚህ አዋጅ መሰረት ተፈጻሚነታቸው ይቀጥላል።

አባላቱ የአዋጁ አፈጻጸም በአንደኛው ዙር የመርማሪ ቦርድ ቅኝት የታዩ ችግሮች በሁለተኛው ዙር መሻሻላቸው መገለጹን በማንሳት አሁንም ከቀድሞ የተሻለ አፈጻጸም ሊኖር ይገባል ብለዋል።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *