“የዜን መምህሩ ቴትሱገን በቻይንኛ ቋንቋ የነበረውን የቡድሃን አስተምህሮ የያዘውን መፅሐፍ ጃፓን ውስጥ ለማሳተም ተነሳ፡፡ ሕትመቱ በእንጨት ላይ ነበር እናም ደግሞ 7000 መፅሐፍት ነው ለማሳተም ያሰበው፡፡ ሥራው የዋዛ አልነበረም፡፡ ብ ልፋትና ገንዘብም ይፈልጋል፡፡ ስለዚህም ቴትሱገን ይህን የቡድሃን አስተምህሮዎች የያዘ መንፈሳዊ መፅሐፍ ለማሳተም ገንዘብ ማሰባሰብ፣ መለመን ጀመረ፡፡ ጥቂቶች የወርቅ ሳንቲሞች ሰጥተውታል … ሌሎችም ያላቸውን መፅውተዋል – ቴትሱገን ሁሉንም እኩል አመስግኗል !!
ከ10 ዓመታት በኋላ ቴትሱገን መፅሐፍቶቹን ለማሳተም የሚበቃ ገንዘብ አሰባስቦ ልክ ወደ ሕትመቱ ሊገባ ሲል ግን ያልታሰበ አደጋ ደረሰ፡፡ የኡጂ ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ የሐገሬውን ሰብል እንዳይሆን አደረገው፡፡ ሕዝቡ የሚላስ የሚቀመስ አጣ፡፡ ይሄኔ ቴትሱገን ለመፅሐፍቶቹ ማሳተሚያ ያሰባሰበውን ገንዘብ አንድም ሳንቲም ሳያስቀር ለሕዝቡ ምግብ መግዢያ አዋለው፡፡

ጥቂት ወራት ቆይቶ ቴትሱገን መፅሐፉን ለማሳተም ዳግም ገንዘብ ማሰባሰቡን ተያያዘው፡፡ በዓመታት ጥረት አሁንም በርካታ ገንዘብ ለማሰባሰብ ቻለ፡፡ ቢሆንም ግን አሁንም ዳግም በሐገር ላይ መከራ መጣ፡፡ የሐገሬውን ሕዝብ ሰብል የአንበጣ መንጋ መጥቶ እምሽክ አደረገው፡፡ ተራበ ሕዝቡ… ቴትሱገን አሁንም ያሰባሰበውን ገንዘብ ለሕዝቡ መልሶ እንካችሁ አለ፡፡ ሕዝቡ በዚህ ገንዘብ በተገዛ እህል ክፉውን ቀን አሳለፈ፡፡

ቴትሱገን ለ3ኛ ጊዜ ለመፅሐፉ ማሳተሚያ ገንዘብ ማሰባሰቡን ጀመረ፡፡ አሁን በ3ኛው ተሳካለት፡፡ መፅሐፉን ለማሳተም ከተነሳ ከ20 ዓመታት በኋላ እነሆ ቴትሱገን የቡድሃን አስተምህሮዎች የያዘውን መፅሐፉን ለማሳተም በቃ… ቴትሱገን መፅሐፍቱን ያተመባቸው የእንጨት ቅርፆች ጃፓን፣ ክዮቶ ውስጥ ባለው የኦባኩ ገዳም ውስጥ አሁን ድረስ ይገኛሉ…
እናም አሁን ድረስ ጃፓናውያን የቴትሱገንን መፅሐፍት አስመልከተው ለልጆቻቸው እንዲህ ሲሉ ይናገራሉ… “የቡድሃን አስተምህሮ በተመለከተ ቴትሱገን 3 ጊዜ መፅሐፍት አሳትሟል … እናም ደግሞ የመጀመሪያዎቹ በዓይን የማይታዩት ሁለቱ ከሦሰተኛው እጅጉን የላቁ ናቸው”

Paul Reps ያሰባሰባቸውን ጣፋጭ የዜን ታሪኮችን ለዓለም ባስኮመኮበት ምርጥ መፅሐፉ “ZEN FLESH, ZENBONES” ውስጥ ያገኘኋት ታሪክ ነች፡፡ እናም ደግም እውነቴን ነው የምላችሁ  ይሄን መፅሐፍ ካገኛችሁ አትማሩት…

ይህቺን ታሪክ በጣም ነው የምወዳት… በጣም…  Senedu Abebe

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *