ዶክተር ቄስ ገመቺስ ደስታ ይባላሉ፡፡የተወለዱት በአዲስ አበባከተማ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ ሲሆን፣ ያደጉት በወለጋ ነው፡፡የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በነቀምት ከተማከ ተማሩ በኋላ፣ የመጀመሪያዲግሪያቸውንና ሁለተኛዲግሪያቸውን ከአዲስአበባዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

ከአሜሪካም በአፍሪካ ቤተክርስቲያን ታሪክ ፣በቲኦሎጂና በሥነትምህርት በተመሳሳይ የማስትሬት፣ በሊደርሺፕ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪም አላቸው፡፡በአሁኑሰዓት ቺካጎበሚገኘው የዓለም የሉተራን ዋናመሥሪያ ቤት የአፍሪካ ሚሽን ዳይሬክተር ናቸው። 

ሪፖርተር፣ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ዋና ጉዳይ በመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተፈጠረ የመከፋፈል ችግር ነው። የችግሩን መንስኤ ቢገልጹልኝ?

ቄስገመቺስ፡በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተነሳው ግጭት ዋና ምክንያት የኦሮሚኛ ቋንቋ ጉዳይ ሲሆን፣ ሌላው የተፈጠረውን ችግር እንዴት እንያዘው ወይም እናስተናግደው በሚል የተፈጠረ የሐሳብ ግጭት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡በኦሮሚኛ ቋንቋ ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ግልጽ ቢያደርጉልኝ?

ቄስገመቺስበአዲስ አበባ ባሉ የመካነ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ወንጌል በኦሮሚኛ ቋንቋ እንዲሰበክ ተወላጅ የሆኑ ምዕመናን ያቀረቡት ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ጥያቄው መልስ ሳያገኝ ውስጥ ውስጡን ታፍኖ በመቆየቱ ፈነዳና ቤተ ክርስቲያኗ ለሁለት በመከፈሏ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ተዳረሱ፡፡ ለማስታረቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙከራ ተደረገ፡፡ እርቅ ለማውረድ ከቤተመንግሥት፣ ከአብያተ ክርስቲያናት፣ ከተባባሪ አብያተ ክርስቲያናት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ በመቅረቱ በመጨረሻ ላይ የሉትራን ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን በቀጥታ በመያዝ ሽምግልናውን፣ ጥፋተኛ እገሌ ነው በማለትና ቁልፍ የሆኑ ሰዎችን በመውሰድ፣ በማስታረቁ ላይ ሠራን፡፡ “በመሸነፍ ማሸነፍ” በሚለው ሃይማኖታዊ መርሕ መሠረት የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ችለናል፡፡ ለሁለት የተከፈለችው ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ባለስልጣናት በተገኙበት እርቅ አውርዳለች፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር በመሄድም አንድ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ወስደዋል፡፡

ሪፖርተር፡እርቁ በምን ዓይነት ስምምነት ተጠናቀቀ?

ቄስገመቺስ፡በኦሮሚኛ ቋንቋ ስብከት ተከለከልን ያሉ ስብከቱ በኦሮሚኛ እንዲደረግላቸው ተደረገ፡፡ የምዕመናኑን ጥያቄ አልመለሱም የተባሉት የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አመራሮች ጥያቄውን የማፈን ጉዳይ ሳይሆን፣ የጥያቄው አያያዝ ችግር ስለነበረበት መሆኑን ገልጸው ይቅርታ ተጠያይቀዋል፡፡ አፈ ጉባኤ ተሾመ ቶጋ ባሉበት የተከናወነው እርቅና ውህደት በሕግም የጸና ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡እርስዎ የቋንቋ ችግር አሉት እንጂ እግዚአብሔርን ከመስበክ በስተጀርባ የሚሠራ የፖለቲካ ሥራ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ቤተክርስቲያናችሁን እየጠሩ አስተያየት የሚሰጡ አሉ፤

ቄስገመቺስ፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በርዕዮተ ዓለም ብቻ ሳይሆን፣ ብሔረሰብን መሰረት የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ቤተ ክርስቲያን መግባት የለበትም፡፡ ከገባም ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው፡፡ ፖለቲካና ቤተ ክርስቲያን የየራሳቸው አሰራር አላቸው፡፡ ፖለቲከኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ሰው ነው፡፡ ከቤ ተክርስቲያን ሲወጣ ደግሞ ፖለቲከኛ ነው፡፡ በአሜሪካ ሪፐብሊካንና ዲሞክራቶች የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ሰዎች ናቸው፡፡ ሲወጡ ደግሞ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማንም ሰው የፖለቲካ አቋም አያራምድም ማለት አይቻልም፡፡ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት፣ ከአገልጋይ ጋር የፖለቲካ ጉዳይ ማንሳት ክልክል ሊሆን አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የማታደርገው ነገር ቢኖር፣ የአንድን የፖለቲካ ፓርቲ አቋም አድርጋ ማራመድ የለባትም፡፡ ፖለቲካ ይቀያየራል፡፡ የፖለቲካ መሪ ይሾማል፤ ይወርዳል፡፡ ቤተ ክርስቲያን አትቀየርም፡፡ የፖለቲካ መሪ ሲመጣ ትጸልያለች፡፡ ሲወርድ ትጸልያለች፡፡ ሲያጠፋ ትገስፀዋለች፡፡ ይህንን የማታደርግ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት አገልጋይ ትሆናለች፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን መለየት አለባት፡፡

ሪፖርተር፡በጸሎት ስም፣ በኮንፈረንስ ስም ሥራ ቆሟል ይባላል፤ ከሶስት ዓመት በፊት ሐዋሳ በተካሄደ የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተነሣም ጉዳይ ነበር፣

ቄስገመቺስ፡ የምኖረው በኢትዮጵያ ውስጥ ባለመሆኑ፣ ዝርዝር መልስ ለመመለስ እቸገራለሁ፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ስም፣ በበዓላት ስም፣ በፕሮግራሞችና በጸሎት ስም ሰዎች ሥራ እንዲፈቱ የምታደርግ ከሆነ፣ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ሰው እንዲሠራ ነው የሚፈለገው፡፡ ሰው የተፈጠረው ሠርቶ እንዲበላ ነው፡፡ “የማይሠራ አይብላ” የሚል ጥቅስ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከተለያዩ የሃይማኖት ክፍሎች የሚያከሩ ይፈጠራሉ፡፡ አክራሪነት ውስጥ ሲገባም ለራስም ሆነ ለአገር ፀር የሆነ ተግባር ውስጥ ይገባል፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ያለው ብልጽግና ከየት መጣ ቢባል የፕሮቴስታንት የሥራ ዲሲፒሊን አማካይነት ነው፤ የሚባል አነጋገር አለ፡፡ ማክስ ዌበር በጻፈው መጽሐፍ እነ ሉተር የጀመሩት የመነቃቃትና የሕዳሴ እንቅስቃሴ መሠረት ነው፡፡ በርግጥ በአገራችን እንደሚታየው ምዕመናንን በመሰብሰብ መዝሙር ማዘመር ብቻ ከሆነ ትክክል አይሆንም፡፡ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንትና ሚኒስትሮች ያበረከተች ከፍተኛ የልማት ሥራ ውስጥ የተሰማራች ነች፡፡

ሪፖርተር፡በኢትዮጵያ የሚሰበከው ወንጌል በአብዛኛው የድሃውን ልብ የመሙላት፣ ድህነትን መጠቀሚያ ያደረገ ባዶ ተስፋ የሚመግብ ነው በሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ፣

ቄስገመቺስ፡ ካርል ማርክስ፣ ስለቤተ ክርስቲያን ሲናገር “ሃይማኖት የጭቁኖች ሐሺሽ ነው” ይላል፡፡ ማርክስ እንዳለው፣ ድሆች ቤተ ክርስቲያን ሄደው “ሐሺሹን” (ስብከቱን) ያዳምጡና ድህነታቸውን ይረሱታል፡፡ ሃይማኖት የጭቁኖች “ሐሺሽ ” መሆን የለባትም፡፡ ባዶ ተስፋ የምትዘራ መሆን የለባትም፡፡ ተስፋ የቆረጡ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ሞራላቸው ቢነሳሳ መልካም ነው፡፡ ሞራሉ ታድሶ ወደ ሥራ ይሄዳል፡፡ ዝም ብሎ የዘይት እቃህ፣ የዘይት እቃሽ ይሞላል፤ በባንክ አካውንትህ ገንዘብ ይገባል፤ እየተባለ የሚሰበክ ከሆነ ክርስቲያናዊ አይደለም፡፡ ይህ የሜታፊዚክስ ዓይነት የሆነ ስብከት በአውሮፓም አለ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር የሚሆነው ተራ ታዋቂነትን ለማግኘትና ደጋፊ ለማብዛት የሚደረግ በድህነት ላይ ድህነትን የሚያመጣ፣ ድንቁርናን የሚያስፋፋ፣ የቀድሞውን የመተትና የጥንቆላ አሰራር የሚያስታውስ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡ከቤተክርስቲያን እየተገነጠሉ ቤተክርስቲያን መክፈት፣ ቤተክርስቲያንን የገቢ ምንጭማድረግና የስነምግባር ጉድለት ችግር እየተስፋፋ መሆኑ ይደመጣል፣

ቄስገመቺስ፡ ጤነኛ የሆነና ያልሆነ ፖለቲካ አለ፡፡ ጤነኛ የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንዳለች ሁሉ ጤነኛ ያልሆነችም ትኖራለች፡፡ መመርመር ያለባቸው የቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮች ናቸው፡፡ መንግሥትም እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ መመርመር አለበት፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ጤነኛ ያልሆኑ የእምነት አካሄዶች ተፈጥረው ብዙዎች ራሳቸውን የሚያጠፉበት እና የሚያብዱበት ሁኔታ አለ፡፡ በአገራችንም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ የሰው ገንዘብ ይዘው የሚጠፉ የሃይማኖት መሪዎች እንዳሉ እየሰማን ነው፡፡ የመጀመሪያው ተቆጣጣሪ የእምነቱ ተከታይ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ መንግሥት ነው፡፡ ትክክለኛ ያልሆነ የቤተ ክርስቲያን መራባት በግሌ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሃያና ሰላሳ እየሆኑ በመገንጠል እምነትን የሥራ መስክ፣ የገቢ ምንጭ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ሪፖርተር፡ከቤተክርስቲያን ዓላማዎች መካከል አንዱ በአገር ደረጃ ሰላም እንዲወርድ መሥራት ነው፡፡ከዚህ አንፃር  በፖለቲካ አስተሳሰብ የተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን ለማስታረቅ እየሠራችሁ ያላቸሁት ነገር አለ?

ቄስገመቺስ፡ በተለያዩ አገሮች የፖለቲካ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የዓለም የሉተራን ቤተ ክርስቲያን በስፋት ይሠራል፡፡ በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል ሰላም እንዲሰፍን ብዙ ልዑካን አሉ፡፡ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ባለው ሁኔታ ብዙ እየሠራን ነው፡፡ ከፍተኛ የደም መፋሰስ በነበረበት ወቅት ጣልቃ ገብተን እንረዳ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን በአገር ውስጥ ያሉና በውጪ  ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ የሠራነው ሥራ አለ፡፡ ምን ያህል ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባት እንደሚያስፈልግ ባላውቅም እየሠራን ያለነው ሥራ እንዳለ ለመግለጽ ግን እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡በተለያዩ አጋጣሚዎች እርቅን በተመለከተ ሲገለጹ የነበሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ስለዚህ ምስጢር ባያደርጉት፤

ቄስገመቺስ፡አስታራቂ የታራቂዎችን ፈቃድ ሳይጠይቅ እከሌንና እከሌን እያስታረቅኩ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ ለዚህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡እርስዎ ግልጽ ማድረግ ካልፈለጉ፣ መንደርደሪያ ሐሳብ በማንሣት እኔ ይፋ ባደርገውስ?

ቄስገመቺስ፡ምን ያህል በዝርዝር እንደምገባበት አላውቅም እንጂ ትችላለህ፡፡

ሪፖርተር፡ኦነግ ወደ ሰላማዊ የትግል መድረክ እንዲመጣ፣ መንግሥትንና ኦነግን የመሸምገል ሥራ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሕዝብ የወከላቸው አካላት ጋር አብራችሁ እየሠራችሁ እንደሆነ ይታወቃል፤ የቀድሞው የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንትም ይህንኑ  ጥያቄተጠይቀው በግልጽ ተናግረውነበር፤

ቄስገመቺስ፡በግንባር ቀደምትነት ይህንን ሥራ ሲሠሩ የነበሩ ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ ቄስ ኢተፋ፣ አምባሳደር ብርሃኑና አቶ አበራ ቶላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አነጋግረው፣ ከእኛ ዘንድ መጥተው ነበር፡፡ አሜሪካ በመጡበት ወቅት የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን፣ የአገር መሪዎችንና የምሁራን ማኅበረሰብ አካላትን አነጋግረው ነበር፡፡ ፍትሕ፣ እርቅና ሰላም የሉተራን ቤተ ክርስቲያን መርሖች ስለሆኑ ሐሳቡን መደገፍ ነበረብን፡፡ በእኛ እምነት እርቅ ስንል ዝም ብሎ እርቅ አይደለም፡፡ ፓርቲዎችን የማዋሃድ ጉዳይም አይደለም፡፡ እኛ የምንደግፈውና የምንመኘው እርቅ፣ ፍትሕን ያጠቃለለና ሰላምን ያካተተ እርቅ ማውረድ በመሆኑ፣ ሽማግሌዎቹ መጥተው ሲያናግሩን ለመደገፍ የወደድነው እንደ እግዚአብሔር አገልጋይነታችንና እንደ ሃይማኖት መሪነታችን እርቅን ማውረድ ዋናው ዓላማችን፣ የሚመለከተን ጉዳይና ስንሠራበት የቆየንበት ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡

ወደ ጥያቄው ስመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያነሣቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ኦነግም በበኩሉ የሚያነሣቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ሁለቱም የሚያነሡት አገራዊና ብሔራዊ አስተያየቶች አሏቸው፡፡ እኛ ደግሞ ሕዝባዊና አገራዊ ስሜት አለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሃይማኖታዊ መርሖዎች ስላሉን ከነዚህ መርሆች በመነሣት ለተጠየቅነው ጥያቄ ድጋፍ ሰጥተናል፡፡ እርዳታም አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡ከመንግሥት ባለስልጣናትና ከኦነግ አመራሮች ጋር የተነጋገራችሁባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ምን ይመስላሉ?

ቄስገመቺስ፡ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም፡፡ የመንግሥት መሪዎች ይህን አሉ፡፡ እኛ ይህንን አልናቸው፡፡ የኦነግ አመራሮች ይህን ተናገሩ ማለቱ ለማን ይጠቅማል፡፡ ሁለት ተደራዳሪ አካላት በልዩነታቸው ዙሪያ ሐሳብ ያነሣሉ፡፡ ይህ የሚታወቅ ነው፡፡ እርቅ ለማውረድ ሕጋዊ ደብዳቤዎችን ጽፈናል፡፡ ሁኔታዎችን አመቻችተናል፡፡ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡እርቁ ከምን ደረጃ ላይ ደረሰ?

ቄስገመቺስ፡እርቁ ብዙም ወደ ግቡ እንዳልደረሰ እየሰማን ነው፡፡ እስካሁን ድረስም በእንጥልጥል ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በእርቁ ዙርያ ኢህአዴግም ሆነ ኦነግ የሚያነሷቸው የየራሳቸው ነጥቦች አሉ፡፡ ታራቂዎች ፈቃደኛ ሆነው ልዩነታቸውን በማቻቻል እርቅ አውርደው በአገር ግንባታ ላይ በአንድነት ቢሠሩ መልካም ነበር፡፡ በእኛ በኩል ጫና ለማድረግ ሞክረናል፡፡ መጨረሻውን ደግሞ ወደፊት እናያለን፡፡

ሪፖርተር፡በእርቁ ሂደት ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ፣

ቄስገመቺስ፡በእርቅ ተስፋ አይቆረጥም፡፡

ሪፖርተር፡የእምነታችሁ ተከታይ የሆኑ የፖለቲካ መሪዎች፣ ነጋዴዎችና ባለስልጣናት በተለያዩ የአመራር ደረጃ ላይ አሉ፡፡ እነዚህ አባሎቻችሁ ከሙስና የፀዱና ቀና የሕዝብ አገልጋይ እንዲሆኑና ከስግብግብነት እንዲላቀቁ በተለይ የምትሠሩት ሥራ አለ?

ቄስገመቺስ፡ የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሁኔታ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ከምከታተለው ውጪ የጠለቀ እውቀት የለኝም፡፡ እንደ ሃይማኖት መሪነቴ ግን አስተያየት የምሰጥበት ጉዳይ ነው፡፡ ሰው ከሙስና፣ ከስልጣን ብልግና፣ ከሃብት ብልግና ነፃ መሆን እንዳለበት ፍጥረታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ስነ መለኮታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰዎች ከፍተኛ ሹመት ይሰጣቸዋል፡፡ ከፍተኛ ሀብት እንዲጠብቁ አደራ ይቀበላሉ፡፡ ይህ ሁሉ በገንዘብና በስልጣን ወደ መባለግ ሊያስኬድ ይችላል፡፡ ከምድር ጉዳይና ፍርድ ማምለጥ ይቻል ይሆናል፡፡ ባላቸው ጊዜያዊ ትስስር፣ ባላቸው ስልጣን ተደባብቀው የምድር ሕይወታቸውን ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ አንድ ቀን ግን የማያመልጡት የፍርድ ዙፋን ፊት መቆም ግድ ነው፡፡ ይህንን እንደ ሃይማኖት መሪነቴ ለመናገር እወዳለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ አንድ ባለስልጣንም ሆነ ሹመኛ፣ ነጋዴም ሆነ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ተላላኪም ሆነ የጽዳት ሠራተኛ. . . የራሳቸው ያልሆነ ነገር ሲወስዱ፣ ወይም ሲሰርቁ ኅሊናቸው መስረቃቸውን ይነግራቸዋል፡፡ አንዳንዴም ጎረቤትም ይነግራቸዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ወደ ጎን በመተው በስርቆት የሚቀጥሉ መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ሰው ኅሊናውን እንዴት ይክዳል? የሚገርመኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሰው ኅሊናውን ክዶ፣ ጎረቤቱን አልሰማም ብሎ፣ ከደሀ ሕዝብ ላይ ሲሰርቅ ፍርዱ ቀላል ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ ተሳስተዋልና ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ እመክራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡ለእንደዚህ ዓይነቶቹ በተለይ የምትሰጡት ትምህርት አለ? በተለይም ለፖለቲካ መሪዎች ?

ቄስገመቺስ፡ወንጌልን እንሰብካለን፡፡ በወንጌል ውስጥ ሁሉም ነገር አለ፡፡ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው፡፡ በአፍሪካ የበርካታ መሪዎችና የፖለቲካ መሪዎች መጨረሻ አያምርም፡፡ ከተከበሩበት ቦታ ሲነሱ ውርደትና ሃፍረት ውስጥ ነው የሚገቡት፡፡ ክቡር ተብለው የተጠሩ የአፍሪካ መሪዎች የመጨረሻ እጣ ፈንታ እስር፣ ስደት፣ ስቅላት. . . በጥቅሉ የሕይወት መዝገባቸው የሚዘጋው በውርደት ነው፡፡ ሰው የተፈቀደለት ሰርቶና ለፍቶ እንዲኖር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በሙስና መዘፈቅ፣ በስልጣን መባለግ ለሰው ልጅ አልተፈቀደም፡፡ መጨረሻቸውም ከላይ እንደጠቀስኩት መልካም አይሆንም፡፡ ሰው ከራሱ በላይ ለቤተሰቦቹ ማሰብ ይገባዋል፡፡ አንድ ሰው፣ ባለስልጣን፣ ሹመኛ. . . ሰርቆ ለራሱ ሊበላ ይችላል፡፡ የሰረቀውን ግን ለልጆቹ ሲያበላ ልጆቹን እርግማን እያጎረሰ እንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡ በእርግማን ለልጆቹ ቤት እየሠራ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል፡፡ ልጆቹ ነገ የሚወርሱት ንብረት እርግማን በመሆኑ እርግማን እያወረሰ እንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡ በስርቆትና በሙስና ወደ ቤት የሚገባ ገንዘብ ለራስም መርዝ ነው፡፡ ለልጆችና ለቤተሰብ ደግሞ እርግማን ነው፡፡ ትውልድንም ያጠፋል፡፡ በእርግማን የሚገኝ ገቢ ለሁለተኛ ትውልድ በረከት አይሆንም፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ደረጃ በኃላፊነት ላይ ያለ ሰው መጀመሪያ ለራሱ፣ ቀጥሎ ለቤተሰቦቹ፣ በሶስተኛ ደረጃ ለአገሩና ለዚህ ደሀ ሕዝብ ሲል በታማኝነት ማገልገልና እንደተከበሩ በክብር ማለፍን መርሕ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ሁሉም ነገር የቀን ጉዳይ ነው፡፡ ለሁሉም ቀኑ ይደርስበታል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ግንባታ፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የኢኮኖሚ መነቃቃት እየታየ ነው፡፡ ይህ ሁሉ አቀፍ እንቅስቃሴ እየሰፋ ሲሄድ አገር እንድትባረክ፣ ትውልዱም የተባረከ እንዲሆን የአገር መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ወታደራዊ መሪዎች ታሪኮች እንዴት ይጠናቀቃል? ለቀጣዩ ትውልድ ምን ላስተላልፍለት? በማለት ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ሊያስቡ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩ ሹመኞች ተረሽነዋል፡፡ ከሁለትና ከሶስት ሚኒስትሮች በስተቀር በአንድ ጉድጓድ ገብተዋል፡፡ የደርግ ባለስልጣናት ሕይወታቸውን በእስር እያጠናቀቁ ነው፡፡ ወደፊትስ? አንዱ ከሌላው ተምሮ ሕይወትን በክብር ጀምሮ በክብር መጨረስ ይገባዋል፡፡ ወደ ጥያቄው ስመለስ ሰው ለራሱ ሲል፣ ሰው ለቤተሰቡ ሲል፣ ሰው ለአገሩና ለወገኑ ሲል፣ ሰው ለታሪኩ ሲል ነፃ ሆኖ በቀናነት አገልግሎ የሕይወት ዘመኑን ማጠናቀቅ ይገባዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ውጪ የሆነው አስተሳሰብ የውርደት ነው በማለት በግልጽ እናስተምራለን፡፡

ሪፖርተር ፖለቲካ በሩቁ የሚሉ የሃይማኖት መሪዎች አሉ ፖለቲካና ሃይማኖት መቀላቀል የለባቸውም የሚሉ ጥቂት አይደሉም እርስዎስ?

ቄስገመቺስ፡እኛ በቤተ ክርስቲያናችን የምናስተምረው ሰዎች በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉ አባሎቻችን በሙሉ ሰባኪ እንዲሆኑ አንፈልግም፡፡ በተለያዩ ሙያዎች እንዲሳተፉ እናደፋፍራለን፡፡ ወታደር፣ ሐኪም፣ መሐንዲስ፣ ነጋዴ. . . መሆን አለባቸው፡፡ የምናሳስበው ግን በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ላሉበት ቦታ ጨውና ብርሃን እንዲሆኑ ነው፡፡ ጨውነታቸውንና ብርሃንነታቸውን ከጣሉ ልዩነት አይፈጥሩም፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ 29 የሚጠጉ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች አሉን፡፡ ጋዜጠኞች፣ የፊልም አክተሮች፣ ዶክተሮች፣ መሐንዲሶች. . . ይመረቁበታል፡፡ በእኛ እምነት ብቁ የኾነ ትውልድና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲመጣ እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ አንፃር የቤተ ክርስቲያናችን አባላት በፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ እንፈልጋለን፡፡ “በፖለቲካ ውስጥ መግባት ለሙስና ያጋልጣል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ፖለቲከኛ ሰው ይበላል፡፡ ወይም ራሱ ይሞታል” በሚል ከፖለቲካ ውስጥ የመግባት ፍርሃት ነበር፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ጸሐፊ “በኢትዮጵያ በሰላም ስልጣን ይዞ በሰላም የለቀቀ መሪ ብርቅ ነው” በማለት ጽፈዋል፡፡ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ የቤተ ክርስቲያን አባላት ፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ እያበረታታን ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ ካሉ ሴናተሮች ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ አንድ አራተኛ የሚሆኑት የሉተራን ቤተ ክርስቲያን አባላት ናቸው፡፡ ሁለት ሶስተኛው ኤፒስኮፔሊያን ሲሆኑ፣ ካቶሊኮችና ባብቲስቶችም አሉበት፡፡ አንድ ሰው እነዚህን የሴኔት አባላት ለማግኘት አይቸገርም፡፡ እኛም አገር እንዲሆን የምንፈልገው ይሄው ነው፡፡ በአገራችን ፓርላማ ውስጥ ጥሩ ሙስሊም፣ ጥሩ ክርስቲያን ቢኖር እንወዳለን፡፡ ፈጣሪ አለ ብለው የሚያምኑ፣ አምላካቸውን የማይክዱ፣ ኅሊናቸውን የሚፈሩ ሰዎች ፓርላማ ውስጥ እንዲገቡ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡ከሁለ ትሳምንት በፊት የአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች በተገኙበት ከ10 ሺሕ በላይ ለሚሆን ሕዝብ ወንጌል ሰብከዋል፡፡ በተለይ ለፖለቲካ መሪዎች ያስተላለፉት መልዕክት አለ?

ቄስገመቺስ፡የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የክልል አመራሮችና ከ10 ሺሕ በላይ ሰዎች በተገኙበት ትምህርት ሰጥቻለሁ፡፡ “ዝቅታው ከፍ ይበል፣ ከፍታው ዝቅ ይበል” የሚል አጠቃላይ መልዕክት ያለው ትምህርት ነበር የሰጠሁት፡፡ እንግዲህ ከፍተኛና ዝቅተኛ ቦታ ካለ ወጣ ገባ ነው ማለት ነው፡፡ ወጣ ገባ የሆነ ነገር አይመችም፡፡ በወቅቱ የሰበኩት ስብከት ለኦሮሞ ሕዝብ በኦሮምኛ ቋንቋ ነበር፡፡ ይህ ሕዝብ ብዙ ችግር አለብኝ የሚል ነው፡፡ ቋንቋዬ ሳይከበር ቆይቻለሁ፡፡ ስልጣን አጥቻለሁ፡፡ ክብሬና ባህሌ ተናቀብኝ እያለ፣ በርካታ ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ ሸለቆ የሆነ ቦታ በገመድ ተጎትቶ አይሞላም፡፡ የጎደለው ነገር ሲጨመርበት ይሞላል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ጎደለብኝ ያለው ነገር በሙሉ በመስጠት ሸለቆውን መሙላት ይቻላል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ቀደም ሲል ተበደልኩ ሲል እንዳልነበር ሌላውን ሕዝብ የሚበድል ከሆነ ደግሞ ትርጉም የለውም፡፡ ትዕቢት ይሆናል፡፡ ትዕቢት ደግሞ ይጥላል፡፡ ሰው ከሰው፣ ቋንቋ ከቋንቋ፣ ባህል ከባህል፣ አይበላለጡም፡፡ አንድ ዘር ከሌላው ዘር እበልጣለሁ ካለ ዘረኝነት ነው፡፡ አንድ ጾታ ከሌላ ጾታ ይበልጣል ማለትም ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ትዕቢት፣ እብሪት፣ ኩራት፣ ማን አለብኝነት መልካም አይደሉምና ሁላችሁም ከእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ራቁ ብያለሁ፡፡
ሌላው የአገራችን ከፍተኛ ችግር የአብዮት ሱሰኛ መሆናችን ነው፡፡ ሰላማዊ የመንግሥት ቅብብል የለም፡፡ በዚህም የተነሣ አገሪቱ አትሰክንም፡፡ ሁሉም ነገሯ ስሜታዊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አርቀን እናስብ፡፡ ለጋራ ልብ እንሥራ፣ ሁላችን በአንድ ላይ እንበልጽግ፣ ሁላችንም በአንድ ላይ እንደግ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሁኔታ ሰከን ያለ ይሁን በማለት አስተምሬያለሁ፡፡ በምሳሌነት ያነሳሁት ጥቅስ አለ ..ጭር ሲል አልወድም.. እንደሚባለው አገሪቱ ተረጋግታ ሁሉም ነገር ሲሰክን የማይመቻቸውና ስሜታዊ የሚሆኑ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡አገር ሲሰክን የሚረበሹ ወገኖች መነሻቸውምንድነው ብለውያስባሉ?

ቄስገመቺስ፡ በታሪካችን ይህ ሕዝብ የእኔ ብሎ የገነባው ነገር የለም፡፡ አንዱ ተነሥቶ መንግሥት ይመሰርታል፡፡ ሌላው ይመራል፡፡ ሌላው ደግሞ የነበረውን መንግሥት ይገለብጥና ሌላ መንግሥት አቋቁሞ ሌላውን ሰብስቦ ይመራል፡፡ በጋራ የገነባነው ነገር ስለሌለ የመረጋጋት ስሜት የለም፡፡ በጋራ አገራችን በእኩልነት የምንወስንበት፣ በእኩል አስተዋጽኦ የምናደርግ ዜጎች መሆን አለብን፡፡ የእምነታችን መመሪያ በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚበላለጡ ሁሉ እኩል ይሁኑ ይላል፡፡ እኩልነት የኮሚኒዝም ፍልስፍና ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ሁሉም እኩል ሲሆን፣ አገሪቷ ትባረካለች፡፡ የአማራ፣ የትግራይ፣ የወላይታ፣ የኦሮሞ. . . የሁሉም እኩልነትና በእኩል የመወሰን መብት ሲከበር ለአገር በረከት ይሆናል፡፡ አንድ እውነት መናገር እፈልጋለሁ፡፡ በአገራችን ከፍተኛ መሻሻል እየታየ ነው፡፡ የተናቁና የተገለሉ፣ በአገራቸው ጉዳይ ተሳትፎ ያልነበራቸው ታስበዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ተስፋችን ማበቡን ያሳያል፡፡ የተጀመረው ተስፋ የሚመሰገን ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ ለመሪዎቻችን ያስተላለፍኩት መልዕክት ስለተጀመረው ጅምር እናመስግናለን የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፣በአብዛኛው በኦሮሞ ብሔር ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩት ለምንድን ነው ከአንድ የሃይማኖት መሪስ ይህየሚጠበቅ ነው?

ቄስገመቺስ፡ማመስገን በሚገባን ጉዳይ ላይ በነፃነት ማመስገን አለብን፡፡ ነፃ እንሁን ስል ከዚህ ይጀምራል፡፡ በአፄ ዮሐንስ ዘመን፣ በአፄ ቴዎድሮስ፣ በአፄ ምኒልክ ዘመን፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ የስልጣን ጊዜና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አመራር ወቅት የኦሮሞ ሕዝብ 20 ሺህና ከዚያ በላይ ሆኖ መሰብሰብ ይችል ነበር? ቢሆንስ ይፈቅዱ ይሆን? በፊት ያልነበረ ነገር ዛሬ አለ፡፡ ይህንን ላደረጉት ማመስገን አግባብ ነው፡፡ ግን ተደርጎ ተጠናቀቀ፤ አበቃ ማለት አይደለም፡፡ በአገሪቱ ከዳር እስከ ዳር ነፃነት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ ሊኖር ይገባል፡፡ ከሙስና የፀዳ አሰራር በአገሪቱ ከዳር እስከዳር መዘርጋት አለበት፡፡ ህዝብ ጎደለን አነሰን የሚለው ነገር ሊሟላለት ይገባል፡፡ መሪዎችም ይህንን የማሟላት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ጉድፍ እየፈለጉ መሪዎችን ማጣጣል ብቻ ሳይሆን፣ መልካም ነገራቸውንም ማጉላት አለብን፡፡ አገር በመልካም ሰዎች ስትመራ ትባረካለችና ሁላችንም በየእምነታችን፣ መሪዎቻችን መልካም እንዲሆኑ መጸለይ ይገባናል፡፡

ሪፖርተር፡በደቡብ ሱዳን በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡የተለየ ተልዕኮ አላችሁ?

ቄስገመቺስበደቡብ ሱዳን የደም መፋሰስ እንዲቆም፣ በከፍተኛ ደረጃ ሠርተናል፡፡ የሉተራን ቤተ ክርስቲያንም ተመስርቷል በደቡብ ሱዳን መንፈሳዊ ኮሌጅ ስለሌለ ጋምቤላ ባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ውስጥ የደቡብ ሱዳን አገልጋዮች እንዲሰለጥኑ ተደርጓል፡፡ በብሔራዊ ደረጃም ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ሆነው እንዲሠሩ እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችም እንሠራለን፡፡ ከስደት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ፣ በካናዳና በካሪቢያን አገሮች ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ለሚመጡ ስደተኞች ቤተ ክርስቲያን እንከፍታለን፡፡ እናሰለጥናለን፡፡ አቅም ፈጥረንላቸው ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎችንም እያፈራን ነው፡፡

እኔው አሰግድተፈራ ሪፖርትር እያለሁ አነጋግሬያቸው ነበር። SUNDAY, 21 FEBRUARY 2010

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *