አንድ እሁድ ቀን ፣ ባለቤቴ የሰባት ወር ቅሪት ስለነበረች፣ ሐኪሟ ብዙ በእግርሽ መጓዝ አለብሽ ስላላት በዛውም ለመናፈስ ቡዳፔስት ውስጥ ወደ ታወቀው ቪዳም ፓርክ (መናፈሻ) ለመንሸራሸርና ወሬም ለማየት ሄድን፡፡ እዛም ስንዟዟር ሌሎች አምስት ኢትዮጵያውያን አገኘን፡፡ ከነሱ ጋር እየተወያየን ስንዟዟር አንድ ካፖርት የለበሱና በእጃቸው ቦርሳ የያዙ ሁንጋር ሰውዮ ቀረብ ብለው፣ “አማርኛ ስትናገሩ የሰማሁ መሰለኝ፣ ከኢትዮጵያ ናችሁ?” አሉን፡፡ እኛም በመገረም አዎንታችንን ገለጽንላቸውና፣ “እንደዚህ የተቀላጠፈ አማርኛ የት ተማሩ?’ አልናቸው፡፡ “አገራችሁ ኢትዮጵያን በቆየና በሚያኮራ ታሪኳ ስለማደንቃት፣ ስለ ሀገሪቱም የበለጠ ለማወቅ ስለምፈልግ በሞስኮ ዩኒቨርስቲ የቋንቋ ኢንስቲቱዩት በግል ጥረቴ አማርኛ ለመማር ቻልኩ” ብለው መለሱልን፡፡ ከብዙ ውይይትና ቆይታ በኋላ ጊዜው እየመሸ ስለሄደ ፣ “በሉ እንግዲህ በመገናኘታችን በጣም ደስ ብሎናል፣ ከርስዎም ጋር ብዙ ብንቆይ የበለጠ ደስ ይለን ነበር፣ ነገር ግን ባለቤቴ እርጉዝ ስለሆነች እንዳይደክማት ቶሎ ወደ ቤታችን መመለስ አለብን” አልኳቸውና ተሰነባብተን ጉዞ ጀመርን፡፡ ጥቂት እንደተራመድን ዞር ብለው፣ “የኔ ወንድም! ይሰሙኛል?” ዘሉኝ፡፡ “አቤት!” አልኳቸው፡፡ “እኔ እንኳን ከርስዎ የበለጠ ቋንቋውን አውቃለሁ ለማለት ሳይሆን፣ ደግመው እንዳይሳሳቱ ለማስታወስ ያህል ‘ባለቤቴ እርጉዝ ነች’ አይባልም፣ እርጉዝ የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት ለእንስሳት ነው፣ ለሰው ልጅ ግን ‘ባለቤቴ ነፍሰ-ጡር ነች’ ነው የሚባለው አመሰግናለሁ” ብለው እኔ ማመስገን ሲገባኝ እሳቸው አስተምረውና አመስግነው ፊታቸውን አዙረው ፈትለክ አሉ፡፡

በዚህን ጊዜ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የሳቁት ሳቅ ከጽሑፍ ይልቅ በዐይነ ሕሊና መሰለቱ ይቀላል፡፡ እኔም በግርምታ ለምን የራሴን ቋንቋ ፈረንጅ አረመኝ ብዩ ንዴቴን ውጨ በአለሁበት ሳልንቀሳቀስ ሰውዮው ወደሄዱበት አቅጣጫ ስመለከት ከቆየሁ በኋላ ባለቤቴን እንሂድ በማለት እጇን ሳብ አድርጌ ወደ ቤታችን አመራን፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም አንድ የአማርኛ ቋንቋ ምሁር የሆነ ሰው ጠይቄ እንደተረዳሁት በዘልማድ ‘እርጉዝ’ ይባል እንጂ በትክክል ‘እርጉዝ’ የሚባለው ለእንስሳት ሲሆን ለሰው ልጅ ግን ሁንጋሩ ሰውዮ እንዳሉት ትክከለኛው ቃል ‘ነፍሰ-ጡር’ ነው፡፡ ይህም ሲተረጎም ነፍስ የምትጦር፣ የምትመግብ፣ የምታሳድግ ማለት እንደሆነም ጨምሮ ነገረኝ፡፡

(ዶ/ር ጌታቸው ተድላ “#የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ” ገጽ፣117-8)

ምስጋና – ለ Misganaw Gishen

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *