” … ተድብድቤ በቃሬዛም ቢሆን ያምጡኝ እንጂ ካሁን በሁዋላ በራሴ ፈቃድ አልመጣም” ሲሉ በፍርድ ሂደቱ መሰላቸታቸውን አቶ በቀለ ገርባ ተናገሩ። አቶ በቀለ ይህንን የተናገሩት ሃሙስ ባስቻለው ችሎት የመናገር እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው ነው።
ከሁለት ቀን በፊት አቃቤ ህግ በማስረጃነት አቀርበዋለሁ ሲለው የነበረውን የድምጽ ከምስል ማስረጃ አስተርጉሞ እንዲያቀርብና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ሃላፊ ችሎት እንዲገኙ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ በቀጠሮውና በትዕዛዙ መሰረት ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ በቀለ ገርባ ላይ ያቀረበውን የድምፅ ከምስል ማስረጃ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዛሬም እንዳላስተረጎመው አሳውቋል።
የኤጀንሲው ሃላፊ ችሎት አልተገኙም። የክልሎች ቋንቋ ሃላፊ ጸጋ ልዑል ወልደኪዳን ” ብቁ ጋዜጠኞች ስለሌሉ አልተተረጎመም” በማለት የሰጡትን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ሳያንገራግር ውድቅ አድርጎታል። ቀደም ሲል ከሳሻቸው ትርጉሙ ሳይገባው እንዴት ሊከሳቸው እንደቻለ ሊገባቸው እንዳልቻለ፣ ይልቁኑም ” ታስሮ ይቀመጥ” ከሚል እሳቤ በመነሳት የሚፈጸም እንደሆነ ያስታወቁት አቶ በቀለ ገርባ በዛሬው ችሎት የመናገር እድል ጠይቀው ምሬት የተሞላበት “ህሊናን” የሚፈታተን መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ተደብድቤ በቃሬዛም ቢሆን ያምጡኝ እንጂ ” አሉ አቶ በቀለ ገርባ ” በራሴ ፈቃድ ካሁን በሁዋላ አልመጣም” ችሎቱ ላይ የነበረ ለዛጎል እንደገለጸው እሳቸው ይህንን ሲናገሩ በዳኞቹ ላይ የጭንቀት ስሜት ይታይ ነበር ብሏል።
ቀደም ሲል የድምጽ ከምስል ማስረጃው ቢተረጎም እሳቸውን እንደሚጠቅማቸው ያመለከቱት አቶ በቀለ ኤጀንሲው ሶስተኛ ወገን ሆኖ ጉዳዩን እያጓተተው መሆኑንንም አመልክተዋል። ምን ያህል በቀጠሮ እየተንገላቱ እንደሆነ ሲገልጹ ” ለናንተ እተወዋለሁ” ብቻ ነው ያሉት።
ጠበቆቻቸውም ” ጉዳያቸን ከኤጀንሲው ጋር አይደለም” ሲሉ ሶስተኛ ወገን ሆኖ ኤጀንሲው የሚያደርገውን የቀጠሮ ማንዛዛት እንዲቆም ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ በአቃቤ ህግ የቀረበውን ምክንያት ውድቅ በማድረግ ለመጨረሻ ብይን ለግንቦት 7 ቀጠሮ ሰጥቷል።
የቪኦኤ የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡