እውነቴን እኮ ነው፡፡ እሰቲ ወደ ከተማ ውጡ፡ እስቲ ቴሌቪዥኑን እዩት፡ እስቲ ራዲዮውን ስሙት… የሆነ የሚጨንቅ ነገር የለውም? የእኔውማ Phobia ሁሉ ይመስለኛል… በዓል ሲደርስ…ይደብረኛል …ይከፋኛል … ብርድ ብርድ ይለኛል … ሽፍፍ ይልብኛል…ያሳክከኛል…ብን ብሎ በዓል የሌለበት ሀገር መሄድ ሁሉ ያምረኛል፡፡ ብዙ ነገር -ኛል ፡ሚዲያዎቹ “የደስታ እና የፌሽታ…” ሲሉ ይገርመኛል፡፡ አዎ ሊሆን የሚገባው እንደዛ ነው… ሃይማኖታዊ ፋይዳውን…የክብረ በዓሉን ትሩፋት እያሰቡ በፀሎት…በዝማሬ በአምልኮ…በምስጋና ከአምላክ መገናኘት ነው… መሆን የሚገባው…እኛ ግን… ወደድንም ጠላንም በዓላችን እና ሆዳችን ላይለያዩ ተዛምደዋል፡ ተዋደዋል ፡ተጋምደዋል፡፡
ደስታ በመብል ሰሃን … ፌሽታ በመጠጥ ዋንጫ …ፍሰሃ በብርሌ …ካልሰፈርን እንላለን …ውሃን በኪሎ … ድንችን በሊትር እንደመለካት ይመስለኛል፡፡ ቀድሞ ነገር መለኪያ ሚዛኑ ራሱ ተሳስቶ መጠኑ በምን ይታወቅ?
.
ይሄ ዝምድና አይመቸኝም…ለዝምድናው ጥንካሬ የሚደረገው ነገር… ትጋቱ ደግሞ የበለጠ ያናድደኛል… በየበዓላቱ ድግግሞሹ ስላልተቀየረ እኔም ከዚህ የተለየ አዲስ ነገር ስለማልፅፍ ይህንኑ ከጥቂት ማሻሻያ ጋር ድጋሚ ላስነብባችሁ ነው …የማጀቱ ስራ…የጓዳ እና የአደባባይ … ግር ግሩ… ከገበያ ጀምሮ…ኤግዚብሽን…ባዛሩ… ኤክስፖ… ጩኸት ጩኸት… ከሞል እስከ ጉልት…በግ ተራ… ዶሮ ተራ…ሱፐርማርኬት…ሱቅ…መከራከር… መደራደር ….መጨቃጨቅ… (መግዛት ላይቀር) እህል …ማስፈጨት…ማቡካት…መጋገር…መላጥ…መክተፍ…ማብሰል…ማቁላላት…መከለስ …መጥበስ… መቀቀል… ማማሰል…መቅመስ…(ጨው …እርድ… ቃሪያ…በሶብላ ) እንሰሳ…በግ … ዶሮ … በሬ.…ቅርጫ…ማረድ…መግፈፍ…መገንጠል… መበለት…ደም…ውሃ…መጥረግ…መድፋት…መዘፍዘፍ …ማጠብ….መወልወል…እሳት…ጭስ… እንፋሎት … ዶሮ ወጥ… ቀይ ወጥ… ዱለት… ቅቅል …ጥሬ… ለብ ለብ.. ጥብስ…ክትፎ … እንጀራ… ዳቦ… ጎንበስ… ቀና …ወዲህ… ወዲያ …ኤዲያ!
.
ከዛም … ሳሎን ሶፋ ጥግ ላይ በቁምጣ እና በቲሸርት ጋደም ብሎ ሪሞትኮንትሮል የታቀፈ… “የበአል ልዩ የቴሌቭዥን መሰናዶ” ቻናል እየቀያየረ የሚያይ “ስራ-ፈት” አባወራ… ወይም Gemechu ን የሚመስል ወንድም “አልደረሰም?” የሚል ጎርናና ድምፅ … (ብራዘር ወጣ ብለህ የበግ ቆዳ ስንት እንደሚሸጥ ጠይቅ እንጂ) ይህን ፍራቻና ጥላቻ የበዓል ሰሞን የሆነ የምገባበት…. ግርግሩ አልፎ በማግስቱ “ብቅ” የምልበት ጉድጓድ ወይም ዋሻ ነገር ባገኝ ራሴው ለመቆፈር ፈቃደኛ ነበርኩ… በመሃል ደግሞ ወሽመጥ ቁርጥ የሚያደርጉ ገጠመኞች አይጠፉም ….ቲማቲም እና ሽንኩርት የተገዛበት ፌስታል አስፋልት መሃል እንደ መበጠስ ያለ …. ቲማቲሙ በየጎማው በየመንገደኛው እግር ስር ሲንከባለል…ሲታጠብ ተውሎ የተሰጣ ልብስ ሳይደርቅ ማስጫው እንደመበጠስ ያለ (ጋቢ ሁሉ አለው)…ከገበያ የመጣው እንግዳ ዶሮ ማሰሪያውን በጥሶ ጊቢ ለጊቢ እንደመሯሯጥ ያለ….አብሲት ተጥሎ ኩፍ እንዳለ…ወይም ፀጉር ቤት ታጥቦ ተጠቅልሎ ቁጭ እንዳሉ …መብራት እንደመጥፋት ያለ….ዶሮው ታጥቦ ሳይጠራ ውሃ እንደመጥፋት ያለ…የመንደር ባለጌ ድመት የዶሮውን ፈረሰኛ ይዞ እንደመሮጥ ያለ…ኧረ ስንት ነገር አለ…
ዶሮ ወጥ መስራት እና መብላት ሐገራዊ ጉዳይ መሆኑን ይበልጥ የምትረዱት፡ ፈረሰኛውን ከተቀረው አካል ለመገንጠል፡ የሚደረገው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ያክል ከባድ መሆኑን ስታዩ ነው፡፡ ያጋነንኩ የመሰለው ይሞክረው …
.
“እሰይ ደስ ይበለን
ዓውደ-አመት መጣልን”
በሚለው ክሊፕ ላይ የሚቆረሰው ዳቦ የተጋገረበት ስንዴ ሲለቀም አናይም… የሚጨለፈው ዶሮ ወጥ አገነጣጠል እና አስተጣጠብ ታሪካዊ አመጣጥም አይነገረንም (ቢነገረንም በእነ እትዬ ጆርዳና በቅንጡ ወጥ ቤታቸውና በ “ready made” ዶሮአቸው ስለሚሆን የአብዛኞቻችን አኗኗር አይገልፅም-ኧረ የሩባችንንም አይገልፅም… ይታያችሁ ጆርዳና ታርዶ ላባው በፍል ውሃ የተገፈፈ ዶሮ በቀሰም ነፍታ በእሳት ስትለበልብ…የማይመስል ነገር!) ክሊፑ ላይ የበርበሬው አፈጫጭ…የአስፈጪው ንጥሻ… የቂቤው አነጣጠር …የኮሰረቱ አጣጣል አይታየንም…የሚንቆረቆረው ጠላ ሲጠነሰስ፤ሲጠመቅም አናውቅም… ጠጁስ ሲጣል ማሩ ሲበጠበጥ የታል?
ብቻ ጥበብ ቀሚስ የለበሰች በወርቅ የተንቆጠቆጠች ሴት ወይዘሮ ሰፌድ ሙሉ የበረዶ ቁልል የመሰለ ፈንዲሻ ስታዘግን…እዛጋ ጨረቃማ ሲኒዎች ደርድሮ የተዘረጋ ረከቦት ከነጀበናው …የቄጠማው ጉዝጓዝ….በሙካሽ ዝምዝማት ያጌጠ ካባ የደረበ አባት… የወተት አረፋ የመሰለ ጭራውን እየነሰነሰ…. ዳቦ ለመቁረስ ሲባርክ…ለመብል ያላነሱ ለስራ ያልደረሱ ልጆች በነጫጭ ልብሶቻቸው ውስጥ ሆነው ወዲያ ወዲህ ሲሯሯጡ….
ኧረ ክሊፑ ያምራል፡፡እውነት ያምራል፡፡ያስቀኑኛል፡፡ ሁሌም ዝንጥ እንዳልኩ… አይኔ በሽንኩርት ሳያለቅስ… ጥፍር ቀለሜ ሳይለቅ…ከተረከዛማ ጫማዬ ሳልወርድ…ወጥ ሳይፈናጠቅብኝ…እንፋሎት ሳይጨስብኝ…ሽቶዬን አርከፍክፌ…ነጠላዬን ነስንሼ …መሃላቸው ተገኝቼ በአሉን አብሬአቸው ባሳልፍ እመኛለሁ፡፡ ሊፒስቲክን አደማምቆ … ጠጋ … ሳቅ እያሉ ፎቶ መነሳት… ነበር!
“አሁን እኮ ዘመኑ ሰልጥኗል ያ ሁሉ ልፋት ቀርቷል እንደ ‘Middle Age’ ነው ወይ የታስቢው? ከሱፐርማርኬት የተገነጠለ ዶሮ… ከነቁሌቱ “Pick” አድርጎ አንድ ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አብስሎ ‘የዶሮ ወጥ’ ማግኘት ይቻላል… ወንዶቹም ቢሆኑ እቃ ማጠብ እና ቀለል ቀለል ያለ የፅዳት ስራ ያከናውናሉኮ… አበዛሽው… አጋነንሽው…” ካላችሁ….“መቼ እንደታረደ.. መቼ እንደ ተሰራ የማይታወቅ ዶሮ አልበላም!” የምትል እናት የለቻችሁም ማለት ነው፡፡ እንግዲያውስ ይግረማችሁ እኛ ቤት ዛሬም ድረስ ሽሮ ይከካል…በርበሬ ይደለዛል…ገብስ ይፈተጋል… ታዲያ ይሄ ሁሉ ሲሆን ገጠሬዋ እኔ ወገቤን ታጥቄ እገባበታለሁ እንጂ “ኧረ ይሄ ነገር ከሰላም ባልትና ይገዛ” ማለት እንዴት ይቻለኛል?
.
በመጨረሻም…
እሰይ! ጌታ ተነሳ፡፡ በሰው እና በአምላክ መካከል የነበረ የጥል ግድግዳ ፈረሰ…. ደስ ይላል! በጣም… ይሄን የመሰለ ክብረ- በዓል ግን … በረት ሙሉ በሬ ካልተቃረጥንበት … ጣባ ሙሉ ክትፎ ካልጨረስንበት… እንስራ ሙሉ ጠላ ካላንቆረቆርንበት …ሳጥን ሙሉ ቢራ ካልጨለጥንበት… ሰፌድ ሙሉ ዳቦ ካልገመጥንበት… ምኑን በአል ሆነው? የሚባለው ነገር አይገባኝም…አይዋጥልኝም… እስቲ አሁን “ቃልም ስጋ ሆነ” በሚል ሰበብ… ስጋ ሲቆርጡ ከመዋል በላይ “ስጋዊነት” ምን አለ?
መልካም በዓል!!!

Related stories   ሲሲሊ፥ ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን
Teym Tsigereda Gonfa

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *