FB_IMG_1492410557354
ዛሬ አዲስ አይደለም በለኮሰው እሳት የነካሽ ሲቃጠል……
ኢትዮጵያን የቃል ኪዳን ሀገር ናት ሲባል ይህን ተረት ተረት ተው የሚል ትውልድ በበዛበት ፤ ኢትዮጵያ የሺ ዘመን የታሪክ ድርሳን ሀገር ናት ሲባል የድሮው የገዢው መደብ ድራማ ነው እንጂ ኢትዮጵያ 100 ምናምን አመቷ ነው ብሎ ታሪክ የሚያጣርዝ ፖለቲከኛ ባፈራንበት ሀገር ኢትዮጵያን ማንቆለጳጰስ ሲያንሰን ነው።በንጉሱ ፣በደርግ እና በኢህአዴግ አሰተዳደር ኢትዮጵያ ላይ የእየራሳቸውን ሰህተት ሰርተው አልፈዋል እየሰራም ያለ ገዢ አለ።ይህ ስህተት ደሞ አንዴ ህዝቦች ሲያናቁር ፣አንዱ ጨቋኝ አንዱ ገዢ ያደረገ ፣ የሀገር ፍቅር አመጣለው ብሎ በደከመ ጨፍጫፊ ተብሎ የተፈረጀ ፣የብሄር እና ጎሳን  ፖለቲካ መርዝ ይዞ አንድነትን የሻረ መንግስት ይዘናል።
በዚህ ሁሉ አመታት ግን ሰልጣን ቢቀያየርም ፣ገዢው ቢለያየም ፣ ጨቋኙ መልኩን ቢቀያይርም የማትቀየረው ኢትየጵያ ላይ የዘሩት ፍሬ ዛሬም ሀገር ሊያፈርስ እየሞከረ ነው።አንድነት ትተን ወደ ጎሳ የመጣንበት መንገድ እርስ በእርስ እያጫረሰ ነው ፤ በድሮ ታሪክ ዛሬ ማሰባችን ስህተቱን እያበዛብን ነው ፤ የታላላቅ አባቶችን ደም እና ክብር መርሳታችን አላዋቂ ብቻ ሳይሆን በህዝብ እንድንጠላ እያደረገ ነው።በንጉሱ የተለኮስ እሳት ነበር ፤ በደርግም የተለኮሰ እሳት ነበር ፣በኢህአዴግም የተለኮስ እሳት አለ።ንጉሱን እና ደርግ በለኮሱት እሳት ተበልተዋል።ባለተረኛው በለኮሰው እሳት ዛሬም በብሄር ፖለቲካ የእርስ በእርስ ግጭት እየተበላ ነው።ለዚህም ነው ንጉሱ ቴዲሻ “ዛሬ አዲስ አይደለም በለኮሰው እሳት የነካሽ ሲቃጠል……” ያለው መሰል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብሄር ፣ዘር እና ሃይማኖት ሳይለይ ብዙ ጀግናዎች ለሀገር ወድቀዋል።ለሀገር ፍቅር የህይወት መሰዋትነት የከፈሉ ፣ለሚሊየኖች የተሰው ፣ ለሀገር መሬት እና ባንድራ ወደ ኋላ ያላሉ ጀግኖች ስም ብንጠራ አመታት ይፈጅብናል።ቀድሞ ቴዲ አፍሮ በሰም የተወሰኑትን ጠርቶ ክብር ሲሰጣቸው በሙዚቃ ሲያነሳቸው የእኛ ሰፈር ሰዎች አልተጠሩም የሚሉ አጉል የብሄር ፖለቲከኛ ድምፆች ይሰማ ጀመር።ለዚህም ምላሹ በዚህ ኢትዮጵያ ነጠላ ዜማ እንዲ በማለት መልሶታል።
ስንት የሞቱልሽ ለክብርሽ ዘብ አድረው
አልፈው ሲነኩሽ ባህረሽን ተሻግረው
የጀግኖች አገር የአዳም እግር አሻራ
ፈለገ ጊዎን ያንቺ ስም ሲጠራ … …
የሀገር ፍቅር ከባንድራ ይቀዳል።የኢትዮጵያ ባንድራ ጨርቅ እንዳልሆነ የሚናገር ስራ ነው ኢትዮጵያ ነጠላ ዜማ።ሀገር ፣ታሪክን እና ክብር የማይገባው ሁላ የራሱን ፖለቲካ ለማዋደድ ርካሽ ሀሳብ በባንድራ ላይ ያስቀምጣል።ባንድራ ጨርቅ ነው ፤ ሀገር ማለት ሰው ነው ብለውናል።ግን ባንድራችን የትኛው ቦታ ላይ እንደሚቀመጥ ፤ የክብሩ ጫፍ ምን ድረስ እንደሆነ የቴዲ ብዕር እና አንደበት እንዲብለውናል አሰምቶናል
በቀስተ ደመናሸ ሰማይ መቀነቱን ባንዲራሽን ታጥቆ
አርማሽ የታተመ እንኳን በዓለም መዳፍ በአርያም ታውቆ
በዚህ ብቻ አላበቃም።ባንድራች በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይ የሚታወቅ ቀደምት እንደሆነ ከተናገረ በኋላም የእኛን ባንድራ ያየ አይደለም ኢትዮጵያ ሲባል እንደ ገደል ማሚቱ የሚያሰተጋባ የአለም ህዝቦች አሉ ነው ያለው።
እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
ስምሽ ሲጠራ ማን ዝም ይላል ሠምቶ
እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሠምቶ
የሀገራችን ባንድራ አንድ ነፃ አውጪ ነኝ የሚል ጁንታ ታጣቂ ፣ቁምጣ ለባሽ ፣ጫካ ሰፋሪ ፣ፀጉር አጎፋሪ ተሰባሰበው ያወጡት እንዳልሆነ ይታወቃል።በሰብሰባ የወጣ የክልል ባንድራ አጠገቡ መቆም ይከብደዋል።ምን ይሻለና እየተባለ ህዝቦች ጥቁር ፣ነጭ፣ቢጫ ፣አረንጓዴ እያሉ የሰየሙት አይደለም።የእኛ ባንድራ ከሰማይ በቀሰተ ዳመና የሚመሰል ፣በምድር በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በተምሳሌትነት የወሰዱት ብዙ ዘመናት የተሻገረ የክብር መለኪያ መስፈርት ነው።ባንድራችን ሰማይ ላይ ነው!
በሠማዩ ላይ ቢታይ ቀለም
የሷ ነው እንጂ ሌላ አይደለም
የሰው ልጅ መገኛ ፤ የአዳም እና ሄዋን ቤት ኢትዮጵያዊያ መሆኗን ቴዲያችን ይናገራል “የፍጥረት በር ነሽ የክብ ዓለም ምዕራፍ ዞሮ መጀመሪያ”። ኢትዮጵያዊ ማን ነው? በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊው ማን ነው የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ፈታኝ ነው።የብሄር ፖለቲካ ከኢትዮጵያዊነት በልጧል።ኦሮሞ የሚባል ዜግነት ፣አማራ የሚባል ዜግነት ፣ትግራ የሚባል ዜግነት የሚሻ ትውልድ የሚፈጥር ፖለቲከኛ ነው የበዛው።ለዚህም ነው ዛሬ ኢትዮጵያዊ የሆነ መሃል ሰፋሪ ነው።ተቃዋሚው ፅንፈኛ ፣ መንግስቱ ብሄርተኛ ሁን ይሉሃል።አይ ብለህ ወደ ኢትዮጵያዊነት ከሄድክ መሃል ሰፋሪ ሆነ ከሁለት ቦታ ድንጋይ ይወረወርብሃል።እኔሰ በበኩሌ ኢትዮጵያዊ ነኝ።ለዚህም ደጋግሜ እንዲ እላለው።
ተውኝ ይውጣልኝ ልጥራት ደጋግሜ
ኢትዮጵያ ማለት ለኔ አይደል ወይ ስሜ
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ  ብዮ ብጮህ አይወጣልኝ።ሀገር አለኝ የተከበረ ፤ ሀገር አለኝ የገዘፈ ፣ ሀገሬ ክብሬ የህይወት ማህተቤ ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ።ሀገር አለኝ የትም ሆኜ የማስታውሰው ፣ሀገር አለኝ ማነረም የሚያውቃት ፣ሀገር አለኘ ቅዱሱ መፃፍ የሚያውቃት።
ባልፍም ኖሬ ስለ እናት ምድሬ
እሷ ናት ክብሬ ኸረ እኔስ ሀገሬ
ባለፉት መንግስታት ሆነ በአሁኑም አልፎም ወደፊት በሚመጣው የተለያዮ ችግር ሲገጥመን ከሀገር መገንጠል ሳይሆን ፤ ሀገር ማፍረስ ሳይሆን መፍትሄው በጋራ ለውጥ ማምጣት ነው።በጋራ ጠላታችን በማሸነፍ ኢትዮጵያን ማቆየት ነው ፤ ያልተመቸንን መሪ በማሰናበት የሚበጀንን ማምጣት ነው እንጂ ተበድያለው ብሎ መሸሽ አያዋጣም።ማንም ከእኛ ስለማይበልጥ ለሁላችንም የሚመች ሀገር በጋራ እንሰራለን።መሸሽ የፈሪ እንጂ የሀገር ፍቅር ፣የብሄር ፍቅር ምልክት አይደለም።
ቢጎል እንጀራ ከመሶቡ ላይ
እናት በሌላ ይቀየራል ወይ
ይዤ አላነሳም እጄን ከቀሚሷ
እናት እኮ ናት ተስፋ አልቆርጥ በሷ
ኢትዮጵያን አትንኩ አራት ነጠብ።ይህ ሰው ያለው ሳይሆን  ነብይ ነው።ቅዱስ ቃሉ የሚያውቃት የሀገር ተወካይ ናት።በአለም ላይ እንደ አሜሪካ የናጠጠ ተፈሪ ብትሆን ፣እንደ ራሺያ ብትሆን፣ እንደ አረብ ሀገራት ነዳጅ ቢኖርህ ፣እንደ አውሮፓዎች በሀብት ብትንበሻበሽ እንደ ኢትዮጵያ መፃፍ ቅዱስ ላይ መስፈር ግን ከምን ከማንም ጋር በአለም ሆነ በሰማያው መንግስት የሚበልጥህ የለም።በቅዱስ ቃሉ ያለችው ኢትዮጵያ ስሟም ፣ባንድራዋም እና ህዝቦቾ ከማንም በላይ መሆናቸው መፃፉ ይናገራል።
በቶማስ ሰብስቤ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *