ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

በበዓል ዋጋ ንረት ነፍራ የምታነፍረው አዲስ አበባ!

  • ተባዕት ዶሮ ከ280 – 360 ብር እየተሸጠ ነው!
  • በግ ከ2,200 – 3,800 ብር የሽያጭ ዋጋ ደርሷል!
  • ድልብ በሬ ከ25,000- 37,000 እየተሸጠ ነው!

በረዥም ጊዜ ሂደት እየተዋረሰ የመጣው ኃይማኖታዊ በዓል አከባበራችን ከምግብ እና መጠጥ ጋር በጽኑ የተቆራኘ ነው፡፡ የአጽዋማትን ፍች በተመለከተ ከተቀመጡ ኃይማኖታዊ መርሆች ይልቅ ተለምዷዊ ድርጊቶች ገዥ ሐሳብ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በዓላትን የታከከ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መገለጫ ሆኗል፡፡

መንግስታዊ ኃላፊነቱን በዘነጋ አገዛዝ ውስጥ ላለችው ኢትዮጵያ የመሠረታዊ ሸቀጦችና የቁም እንስሳት ዋጋ ንረት መታየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የህዝቡ የድህነት ቁስል ላይ ለመቆም የማይሳቀቁ ስግብግብ ነጋዴዎች የዋጋ ንረቱን በማጐን ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ቀጥሎ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ተከትሎ የተፈጠረው የሸቀጦች ዋጋ ንረት ቀደም ሲል ወደነበረበት የዋጋ ሁኔታ ሳይመለስ ከፋሲካ በዓል ጋር ተያይዞ የምግብና የቁም እንሰሳት ዋጋ ንረቱ እያሻቀበ ይገኛል፡፡

በበዓላት ሰሞን የሚታየው የዋጋ ንረት ከተሰቀለበት የዋጋ ጣሪያ ለማውረድ ወራትን የተሻገሩ ጊዜያት በሰቀቀን ውስጥ ማሳለፍ ግድ ይላል፡፡ በተለይም ተራዛሚነቱን እያሳየ ያለው የአገሪቱ ድርቅ በቁም እንሰሳትና በሰብል ምርት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ የዋጋ ንረቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

ከምግብና መጠጥ ጋር ፅኑ ቁርኝት ያለው የፋሲካ በዓል ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ንረትን አስከትሏል፡፡ ፆሙ ከመግባቱ በፊት የነበረው የዋጋ ሁኔታ በመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መጨመር ቀድሞውንም የዋጋ ንረቱ የታየ ቢሆንም በዚህ ሳምንት እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ደግሞ ከቀደመው የባሰ ሆኖ ታይቷል፡፡

በአዲስ አበባ የጎልጉል መረጃ አቀባይ የከተማዋን ዋና ዋና የገበያ ማዕከላት በመዘዋወር ባደረገው ቅኝት የመሠረታዊ ሸቀጦችና የቁም እንሰሳት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የክርስትና እምነት ተከታዮች በተለምዶ የአብይ ፆምን ለመፍታት የሚጠቀሟቸው የምግብ አይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ የእህል ዘር የሆነው ተልባ ይገኝበታል፡፡ በፆም ውስጥ የቆየውን የአማኙን ሆድ ያለሰልሳል፤ ከቅባት ነክ ምግቦች ጋር ያላምዳል፤ በሚል ለፆም መፍቻነት ይውላል፡፡ ተልባ ከፆም በፊት አንድ ኪሎ 18 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ ከፋሲካ ጋር በተያያዘ የአንድ ኪሎ ተልባ ዋጋ 34 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ ተልባ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከቀደመው ጋር ሲነፃፀር 88.8% ጭማሪ አሳይቷል፡፡

አንድ ኪሎ ቅቤ 320 ብር በሚሸጥባት አዲስ አበባ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጐች ዘይትን ለምግብ ማጣፈጫነት ይጠቀማሉ፡፡ ይሁንና የዘይት ዋጋም በተመሳሳይ መልኩ አሻቅቧል፡፡ በሊትር 60 ብር ይሸጥ የነበረው ዘይት 75 ብር መሸጥ ጀምሯል፡፡

Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ

አገዛዙ በማህበር ባደራጃቸው ሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል የሚቀርበው ዘይት የአገልግሎት ጊዜው በጉልህ ያልሰፈረበትና የሚረጋ (ፈሳሽ ያለሆነ) ዘይት በመሆኑ ከጤና ስጋት ጋር ተያይዞ ተጠቃሚዎች ሲፈልጉት አይታይም፡፡ ይህም ሆኖ በቀበሌ ደረጃ በኩፖን የሚታደለውን ዘይት ለማግኘት በረዥም ሰልፍ ውስጥ መቆየት ግድ ይላል፡፡ ዘይት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከቀደመው ጋር ሲነፃፀር 25% ሆኗል፡፡

የግዥ መጠን ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ደሃውና ሐብታሙ ለፆም መፍቻ እኩል ተጋፍተው ይገዟት የነበረችው እንቁላል እንኳ በአቅሟ በዘንድሮዉ የፋሲካ በዓል ሳምንት የዋጋ ጭማሪ አሳይታለች፡፡ የአንድ እንቁላል የሽያጭ ዋጋ 3.75 (ሶስት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም) ደርሷል፡፡

በፋሲካ በዓል ለፆም መፍቻነት ለእርድ ከሚውሉ እንስሳቶች ዶሮ ተጠቃሽ ነው፡፡ የዶሮ ገበያዉም ቢሆን እንደ አንድ ገበያተኛ አገላለጽ “እጅን በግርምት አፍላይ የሚያስጭን” የዋጋ ንረት ታይቶበታል፡፡ ለበዓሉ ይበልጥ ተመራጭ የሆነው ተባዕት ዶሮ ከ280 – 360 ብር ድረስ በመሸጥ ላይ ነው፡፡ ከአብይ ፆም በፊት በነበረው የገበያ ሁኔታ የተባዕት ዶሮ ዋጋ ከ230 ብር የሚያልፍ አልነበረም፡፡ በያዝነው የፋሲካ ሳምንት የዶሮ ዋጋ እስከ 360 ብር ደርሷል፡፡ ይህን የዋጋ ልዩነት ከፆም በፊት ከነበረው የመጨረሻው (ከፍተኛው) የዶሮ ሽያጭ ዋጋ ጋር በንፅፅር ስናየው 36% የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡

አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ ዶሮ ወጥ ለመስራት በአማካይ 600 ብር ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሲባል የዘይት፣
የሽንኩርት፣ በርበሮ፣ እንቁላል (10) እና የዶሮ የሽያጭ ዋጋቸው አማካይ ስሌት ተወስዶ መሆኑ ልብ ይባል፡፡ አንድ ሙሉ ዶሮ ወጥ ለአንድ ቤተሰብ (በአማካይ 5 ሰው) ከአንድ ማዕድ (ገበታ) በላይ የሚመግብ አይደለም፡፡ የዋጋ ንረቱ በዚህ መሰል ሁኔት እያሻቀበ የሚሄድ ከሆነ ዶሮ ማርባቱም ሆነ በዓልን ጠብቆ ዶሮ ወጥ መብላቱ የገዥው መደብ ሚና ይሆናል፡፡

በአዲስ አበባ የቁም እንስሳት (በግ፣ ፍየል፣ በሬ፣…) መገበያያ ቦታዎች የታየው የዋጋ ንረት ደግሞ ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ግራ ያጋባ  ሆኖ ታይቷል፡፡ በሾላ፣ ሸጐሌ፣ ቄራና ሳሪስ የገበያ ቦታዎች በመዘዋወር የቁም እንሰሳት ሽያጭ ገበያውን የተመለከተው ዘጋቢያችን በላከልን ሪፖርት የበግ ዋጋ ከ2,200 እስከ 3,800 ብር የሽያጭ ዋጋ ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የድልብ በሬዎች የሽያጭ ዋጋ ከ25,000 እስከ 37,000 ብር ደርሷል፡፡ እጅግ የተጋነነ የዋጋ ንረት እየታየበት ያለው የቁም እንሰሳት ገበያ በሥጋ ቤቶች ላይ ላለው የኪሎ ሥጋ ሽያጭ ዋጋ መጨመር ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡

Related stories   በምናለሽ ተራ ገበያ – ከሰኞ እስከ እሁድ

ለአዲስ አበባ ከተማ የቁም እንሰሳት ንግድ አቅርቦት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ይሁንና የኦሮሚያ ክልል በድርቁ ከፉኛ በመጠቃቱ፣ የድርቁም ተራዛሚነት አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው (ምስራቅ ሐረርጌ፣ ጉጅና ቦረና ዞኖች) የበረታ በመሆኑ፣ በድርቁ መራዘም እንሰሳቱ እያለቁ በመሆኑና በከፍተኛ ሁኔታ የተጐሳቆሉ በመሆኑ በዘንድሮው የፋሲካ በዓል ለሽያጭ የቀረቡ የድልብ በሬዎች ብዛት አነስተኛ ሆኗል፡፡

“አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የሥጋ ቤቶች ብዛትና ለፋሲካ በዓል ወደ ገበያ የቀረቡ የድልብ በሬዎች ብዛት የሚመጣጠን አይደለም በዚህም የተነሳ የበሬ ሽያጭ ዋጋ አሻቅቧል” የሚሉት ባለሥጋ ቤቶች የሥጋ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ለመካድ በማይመች መልኩ የድርቁ ተፅዕኖ የአገሪቱ ዋና ከተማ ድረስ ዘልቋል፡፡ አድላቢዎች ከአርብቶ አደሮች የቁም እንሰሳቱን በመግዛት በልዩ ሁኔታ ለወራት ያህል ተንከባክበው በመቀለብ (ልዩ የእንስሳት መኖ በማቅረብ) ለሽያጭ ያወጡ ነበር፡፡ ከድርቁ ጋር ተያይዞ የአርብቶ አደሩ እንስሳቶች የተጐሳቆሉና ከሲታ በመሆናቸው አድላቢዎች እንስሳቱን ለመግዛት አልደፈሩም፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የበሬ አድላቢዎች ድርቁ ካላጠቃቸው የኦሮሚያ ዞኖች፣ ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ከደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የገዟቸውን በሬዎች ሲያደልቡ መክረማቸውን የሚገልፀው የበሬ ነጋዴ “ድርቁ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የድልብ ሥራችን ለማቆም እንገደዳለን” ሲል ይገልፃል፡፡ “በጉጅና በቦረና አካባቢ የቁም እንሰሳት ሽያጭ ዋጋ ዝቅተኛ ቢሆንም እንሰሳቱን ለማደለብ ከ6 – 9 ወራት ድረስ ይወስዳል” የሚሉት የበሬ ነጋዴዎች “ከድካማችንና ከምናወጣው ወጪ አኳያ የበሬ ሽያጭ ዋጋው መጨመሩ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን” ይላሉ፡፡

“በሬን ለማደለብ ልዩ የእንሰሳት መኖ ማቅረብና መንከባከብ የሚጠይቅ አድካሚ ሥራ ቢሆንም አንድ በሬ እስከ 37,000 ብር ድረስ ለሽያጭ መጥራት ስግብግብነት ነው” የሚሉት የሥጋ ቤት ባለሃብቱ “ሥጋ ቤቱን ከመዝጋት የሥጋ ሽያጭ ዋጋ ጨምሮ የሚመጣውን ማየት መፍትሔ ነው” ይላሉ፡፡


የጎልጉል
መረጃ አጠናቃሪ በሰበሰበው መረጃ መሰረት የበሬ አድላቢዎች ከአንድ ትልቅ የሚባል በሬ ከ10000 – 15000 ብር የሚደርስ ትርፍ ያተርፋሉ፡፡ ሥጋ ቤቶችም በተመሳሳይ ከአንድ በሬ ከ7,000 – 9,500 ብር የሚደርስ ትርፍ ወደ ኪሳቸው ያስገባሉ፡፡ ሸማቹ ህብረተሰብ ኪሱን አራቁቶ የሚያከብረው በዓል ለጥቂቶች መክበሪያ ሲሆን እየታየ ነው በማለት ሸማቾች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

Related stories   የቻይናው ሮኬት ስብርባሪ በኢትዮጵያ ቢወድቅ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወስዱ ይገባል?

በአገዛዙ የፖሊሲ ክሽፈቶች የተነሳ ከድርቅና ችጋር አዙሪት መውጣት የተሳናት ኢትዮጵያ፤ የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል የድርቁ ተፅዕኖ እና ርህራሄ የሌላቸው ነጋዴዎች በቅብብል በፈጠሩት የዋጋ ንረት ታጅቦ እየተከበረ ነው፡፡

በበዓል ዋጋ ንረት እየታመሰች ያለችው አዲስ አበባ ከኃይማኖት እና ከባህል ያፈነገጡ ስግብግብ ነጋዴዎችን በጉያዋ ይዛለች፡፡ በርግጥ ኃላፊነት የማይሰማው፣ መንግስትነቱንም የዘነጋ የሽፍታ ስብስብ በሚመራት አገር በህግና በሞራል የማያማኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መፈጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነርሱም ሥርዓተ አገዛዙ የፈጠራቸው “ምርጥ” ጌጦቹ ናቸውና፡፡ አዲስ አበባ ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት በተለይም የሥጋ ዋጋ መጨመር፤ የበሬ አድላቢዎች ለገበያ የሚያቀርቧቸው በሬዎች የዋጋ ሽያጭ መጋነን፤ የሥጋ ቤት ባለሃብቶች ከአንድ በሬ ሥጋ ሽያጭ ማግኘት የለመዱትን ትርፍ የሚቀንስባቸው ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ የሥጋ ቤት ባለሃብቶችን ወደ ሁለት ህገወጥ ድርጊቶች ይገፋቸዋል፡፡ አንደኛው የሥጋ ሚዛን ትክክለኝነት በማዛባት ከኪሎ በታች መሸጥ ሲሆን፤ ሁለተኛውን ህገወጥ ድርጊት ብዙዎች ያደርጉታል ተብሎ ባይገመትም የአገሪቱ ዜጎች ከሚከተሏቸው ኃይማኖታዊ መሰረቶችና ባህል ጋር በሚጋጭ መልኩ ለእርድ የተከለከሉ እንሰሳትን ሥጋ ለሽያጭ እስከማቅረብ በሚደርሱ ህገ ወጥ ድርጊቶች የሚዘፈቁ የሥጋ ቤት ባለሀብቶች አይጠፉም፡፡

የህዝቡን ኃይማኖታዊና ባህላዊ ገጽታዎች ባላገናዘበ መልኩ የአህያ ቄራ በተገነባበት ኢትዮጵያ፤ የአህያ፣ የፈረስና መሰል ለእርድ የተከለከሉ እንሰሳት ሥጋ በጥቁር ገበያ መልኩ በሥጋ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ለሽያጭ ቢውል የሚገርም አይደለም፡፡ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሞራላዊ እሴቶች በጊዜ ሂደት እየተሸረሸሩ ባለበት ሁኔታ ከዚህም የከፉ ድርጊቶች ሊፈፀሙ እንደሚችሉ ከዚህ ቀደም የአገዛዙ አንደበት በሆነው ቴሌቪዥን ጣቢያ (EBC) በ“ፖሊስና ህብረተሰብ” ፕሮግራም የቀረቡ አስደንጋጭ ፕሮግራሞች ስጋታችንን ይጨምራሉ፡፡

የሆነው ሆኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቆሚያ ያጣው የዋጋ ንረት በዓላት በቀረቡ ቁጥር ሲብስበት ይታያል፡፡ በዓላትን አስታክከው ዋጋ የተጨመረባቸው መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች (ምግብ ነክ የሆኑትን ነገሮች እያሰመርንባቸው) ከበዓል በኋላ ከተሰቀሉበት ዋጋ በፍጥነት ሲወርዱ አይታይም፡፡ የዘንድሮው የፋሲካ በዓልም በዋጋ ንረት ታጅቦ፣ የብዙሃኑን ሸማቾች ኪስ አጥቦ፣ የጥቂቶችን ኪስ አድልቦ አልፏል፡፡

በክርስትና ኃይማኖት አስተምህሮት የትንሳኤ በዓል ተምሳሌት ከኃጢያት የመንፃት እንዲሁም ከእስራትና ባርነት ነፃ የመሆን ምልክት ነው፡፡ እንደ ዜጋ የእኛ ጥያቄ! ነፃነት በሌለባት፣ አፈናና ጭቆና በበረታባት አገር የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን ትንሳኤን እስከመቼ ድረስ ስናከብር እንኖራለን?!

ጐልጉል የድረ ገጽ ጋዜጣ