የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) መስራችና የኦፌኮ ሊቀመንበር እንዲሁም የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና የፊታችን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ከሁለቱ የዶክተር መረራ ጉዲና ጠባቆች አንዱ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ ስለ ደንበኛቸው ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ደንበኛችን ጤንነታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የፊታችን ሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። እኛም የመጀመሪያ መቃወሚያችንን እናቀርባለን” ብለዋል።

አቶ ወንድሙ አያይዘውም “መቃወሚያ የምናቀርበው ዶክተር መረራ ጉዲና ላለፉት ከ20 ዓመታት በላይ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፖለቲካ ፓርቲ መስርተው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን አድራሻቸውም እዚሁ አገር ውስጥ ነው። ሌሎች ከእሳቸው ጋር የተከለሰሱት ሁለቱ ተከሳሾች ግን (ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አና አቶ ጀዋር መሃመድ) ከአገር ውጭ የሚኖሩ በመሆኑና ፍርድ ቤት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጥሪያ ቢያወጣም ሊቀርቡ አልቻሉም። ስለዚህ የዶክተር መረራ ክስ ለብቻ እንዲታይና ደንበኛችን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በነጻ እንዲሰናበቱ ስንል መቃወሚያችንን እያዘጋጀን ነው” በማለት ተናገረዋል።

ዶክተር መረራ ጉዲና መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቃል ክርክር ከተካሄደ በኋላ ከማዕከላዊ ማቆያ ወደ ቃሊቲ ዞን አራት ማቆያ ክፍል መዘዋወራቸውን ያስታወሱት አቶ ወንድሙ፣ “ደንበኛችን የተከሰሱበት ወንጀል ዋስትናን የሚከለክል ባለመሆኑ ይግባኝ ጠይቀን ነበር። ሆኖም ይግባኛችንን ፍርድ ቤት ሊቀበለው አልቻለም” ብለዋል።

ዶክተር መረራ ጉዲና የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ቤልጂየም ብራሰልስ በተካሄደ ጉባኤ ሲጠራቸው “በቦታው ተገኝተው ጉባኤውን የተካፈሉት ይታሰራሉ ተብለው ቢነገራቸውም ወደ አገራቸው ለመመለስ ሳይፈሩ ነጻነታቸውን አውቀው የተመለሱ ናቸው። ይህም ሰላማዊ የፖለቲካ ታጋይ መሆናቸው እየታወቀ ሊታሰሩ አይገባም” ሲሉ አቶ ወንድሙ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 ዶክተር መረራ ጉዲና ህገ መንግስቱን በሀይል በመናድና መንግስትን በሀይል ለመገልበጥ ከሽብርተኛ ድርጅት መሪዎች ጋር በመገናኘት አሲረዋል በሚል ወንጀል ነው የታሰሩት።

ሰንደቅ ጋዜጣ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *