“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሁለት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች በሌብነት ተከሰሱ

ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የተጠረጠረን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ የተሰማሩ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሁለት ሠራተኞች ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የደኅንነት ሠራተኞቹ አቶ ባህሩ አዱኛና አቶ ደራ ደስታ የሚባሉ ሲሆኑ፣ ክስ የመሠረተባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡አቶ ባህሩ አዱኛ በተቋሙ በደኅንነት ጥበቃ ዋና መምርያ ጀማሪ ኦፊሰር ሲሆን፣ አቶ ደራ ደስታ ደግሞ የመምርያው ሾፌር መሆናቸውን የገለጸው ዓቃቤ ሕግ ድርጊቱን የፈጸሙት በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ውስጥ መሆኑን በክሱ አስረድቷል፡፡ ተከሳሾቹ አቶ ዑመር አብዶ ዌቦ የተባሉት ግለሰብ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በመጠርጠራቸው፣ ታኅሳስ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በተጠርጣሪው ሱቅ ውስጥ ገብተው ፍተሻ እንዲያደርጉ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ትዕዛዙን ፈጽመዋል፡፡

ድርጊቱን (ብርበራውን) ሲያከናውኑ እማኝ የሚሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎችና ፖሊሶችን በማሳተፍ የሚያገኙትን ንብረት በቬርቫል ላይ (የብርበራ ቃለ ጉባዔ ማስፈሪያ) በመመዝገብ ተጠርጣሪውን በሰነዱ ላይ ማሥፈር የነበረባቸው ቢሆንም፣ ያንን ሳያደርጉ ንብረቶቹን ወደ አዲስ አበባ ይዘው መምጣታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በብርበራ ወቅት 418,500 ብር ያገኙ ቢሆንም፣ 30,000 ብር ብቻ በኤግዚቢትነት አስይዘው (አስመዝግበው) ቀሪውን 388,500 ብር ሳያስመዘግቡ በመቅረታቸው ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ወንጀልና በሥራ ተግባር ላይ የሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር ወንጀል ክስ ተመሥርቷል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱ ከተሰጣቸው በኋላ ጠበቃ ለማቆም አቅም እንደሌላቸው ለፍርድ ቤት በመናገራቸው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ፣ ክስ ለመስማት ለሚያዝያ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር አማርኛ

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0