ወይ ጉድ! ቴዎድሮስ ጸጋዬም በጽሑፍ ለመተቸት ማዕረግ በቃ? በቅቶስ አልነበረም በበቁቱ ሰዎች ላይ በመንጠላጠሉ የመንጠላጠል የብልግና ተግባሩ ለመተቸት አበቃው እንጅ፡፡ ይገርማቹሀል ለምን እንደሆነ አላውቅም እኔ ስለዚህ ልጅ ስንት ወራዳ ተግባሩን እያወኩ ጉዳየ ብየ ጽሑፍ እጽፋለሁ የሚል ግምት ኖሮኝ አያውቅም ነበረ፡፡ ይሄ ልጅ ሰሞኑን የከያኔ ቴዎድሮስ ካሳሁንን ስም ለማጠልሸት ከፍተኛ ዘመቻ ላይ እንዳለ መስማቴ ነው እጽፍበት ዘንድ የተገደድኩት፡፡ ሰዉ ስለ ልጁ ብዙ የማያውቀው ነገር ከመኖሩ የተነሣ ጆሮ እየተሰጠው በመሆኑና በያዘው ስውርና ዕኩይ ዓላማ ሳይታወቅ ሰርጎ ገብቶ ሊያበላሸው የሚችለው ነገር መኖሩ በግልጽ እየታየ በመምጣቱም ጭምር ነው፡፡

ቴዎድሮስ ጸጋዬን መጀመሪያ የማውቀው (ከዚህ በታች ባለው ጽሑፍ ቴዎድሮስ ጸጋዬን ልጁ እያልኩ እቀጥላለሁ እንጅ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ የሚለውን ስም አልጠቀምም፡፡ በፍጹም ይህ ስም ለዚህ ሰው የሚገባ አይደለም፡፡ ምን ይደረግ? ስም በነጻ የመታፈሱ አደጋ ነው እንግዲህ ይሄ!) ልጁን የማውቀው 1994ዓ.ም. ይሁን 1995ዓ.ም. እርግጠኛ አይደለሁም ሬዲዮ ፋና የዛሬው FBC “ዲሞክራሲን (መስፍነ ሕዝብን) ለማዳበር!” በሚል ሐሰተኛ ምክንያት በሁሉም ጉዳዮች ላይ እሑድ እሑድ ጠዋት አድማጮች በቀጥታ የስልክ (የመናገር) ውይይት የሚያደርጉበት መድረክ ተፈጥሮ እዚያ ላይ ያደርገው በነበረ ዕኩይና ሸፍጠኛ ወያኔያዊ ተሳትፎው ነው የማውቀው፡፡ ያኔ እሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበረ፡፡

ይሄ የፋና ዝግጅት በተጀመረበት ሰሞን በቀጥታ የስልክ ውይይቱ ደውየ ገባሁና “”አሁን እስኪ ምን የመናገር ነጻነት አለና ነው ይሄንን መድረክ የፈጠራቹህት? ትክክለኛ ዓላማው ምንድን ነው? በሀገራችን ዲሞክራሲ ያለ ለማስመሰል ነው ወይስ “ማን ይጠላናል፣ ማን ይቃወመናል?” የሚለውን ልትለዩበት አስባቹህ ነው?”” በማለት ማስረጃዎችን ጠቅሸ ላቀረብኩት ጥያቄ አወያዩ የሚሰጠውን መልስ በማሳጣቴ በማግስቱ ሰኞ የኔን ድምፅ እያካተቱ በማሰማት “መንግሥት ዲሞክራሲን ለማዳበር አስቦ፣ ዜጎች በነጻ የመናገር መብትን እንዲለማመዱ እንዲተገብሩ አስቦ ያመቻቸውን የመወያያ መድረክ በያዙት አፍራሽ ተልዕኳቸው የተነሣ ተቃዋሚ ፖርቲዎች መድረኩን አለአግባብ በመጠቀም በትላንትናው ዕለት አፍራሽ ሚናን ተጫወቱ!” ብለው ዜና ሠሩና እየመላለሱ ሲያሰሙት ዋሉ አመሹም፡፡

ያኔ እንደዛሬው በየሰው እጅ ተንቀሳቃሽ ስልክ አልነበረም፡፡ የደወልኩበት ስልክ የዘመድ የመኖሪያ ቤት ስልክ ስለነበረ ካለሁበት አድነው ሊይዙኝና ሊገሉኝ እንደሚችሉ ሠግቸ ነበረ፡፡ ሰነባብቸ ሳየው ግን በእግዚአብሔር ጥበቃ ደኅና ነበርኩ፡፡ ስለዚህ… አልኩና እንደገና ደግሞ በሌላ ቀን ደወልኩኝና ልክ ልካቸውን አጠጥቻቸው ወጣሁ፡፡ በተቻለኝ መጠንም ድምፄን እየቀያየርኩ ወያኔን ማቅመሱን ተያያዝኩት፡፡ ከዚያ በኋላማ ሱስ ሆነብኝ፡፡

የየዋህነቴ የዋህነት… በኔ ቤትኮ እንዳይደርሱብኝ ማራቄ እኮ ነው! ስደውል የምጠቀምባቸው የውሸት ስሞች በሙሉ የወንድሞቸ ስሞች ነበሩ፡፡ ወደኋላ ላይ ግን ድምፄን እየለዩት ሲመጡ በሦስት ጊዜ ታናሽ ወንድሜ ስም “በውቀት ነኝ!” በሚለው ረጋሁና በዚያ ቀጠልኩ፡፡ እነሱም በኋላ ላይ ሳቅታቸው ጊዜ እደውልበት የነበረውን የቤት ስልክ (መናግር) ሲቆርጡብን፣ በሱቅ ስልኮች ስደውል ደግሞ ባለሱቆቹ “አይ እንዲህማ የምትናገር ከሆነ በእኛ ላይ ችግር ሊፈጠርብን ስለሚችል ማስደወል አንችልም!” እያሉ ከሁለትና ሦስት ጊዜ በላይ ሊያስደውሉኝ ስላልቻሉ፣ መጨረሻ ላይም ስደውል እኔ መሆኔን ሲያውቁ እየዘጉብኝ ሲያስቸግሩኝ ጊዜ በሌላ ሰው እያስደወልኩ እየገባሁ መሥመሩ ወደ ሬዲዮው (ነጋሪተ ወጉ) ከተገናኘ በኋላ እየተቀበልኩ ማቅመስ መቀጠሌን ሲረዱ መጨረሻ ቀን ላይ ስልኩን ያነሣው ሰው “ብታርፍ አይሻልም!” የሚል ማስፈራሪያ ተሰንዝሮብኝ መደወሉን ክቲ ብየ እስካቆምኩበት ጊዜ ድረስ አወያዮቹ “ጤና ይስጥልኝ! አቶ በውቀት ዛሬስ ምን የሚሉት ነገር አለ?” እያሉ እየጠየቁኝና ከአወያዮችም ከሚያቀርቧቸው የመንግሥት ሹመኞችም ጋር እየተከራከርን፤ ይሄንንም ሁኔታ በየሳምንቱ ሕዝብ በታላቅ ጉጉትና ናፍቆት ተጠባብቆ እየተከታተለው በሁሉም የውይይት ርእሰ ጉዳዮች ላይ እየገባሁ የመከራከሪያ ነጥቦቸን እያስቀመጥኩ ለአንድም ቀን ሳልሸነፍ ነበር እሳተፍ የነበረው፡፡

ማስፈራሪያው ከተሰነዘረብኝ በኋላም ዝም አላልኩም ነበረ፡፡ በማግስቱ ለአወያዩ ለአቶ ሳሙኤል በቢሮው ስልክ (በመሥሪያ ክፍሉ መናግር) ደውየ “አየህ ይሄንን ነበር ያልኩት፤ ነጻ ውይይት፣ ዲሞክራሲ ምናምን ብላቹሀል ሌላው ቀርቶ ግን ልታናግሩኝ እንኳ አልቻላቹህም! በጣም አዝናለሁ! እኔም ለማስጨረስ ብየ ነው እስከዛሬ ድረስ የዘለኩት የነበረው፤ ከዚህ በኋላ ግን እስከ ማስፈራራት ከደረሳቹህ መኖር እፈልጋለሁና ማቆሜን እንድታውቁት!” ብየው ልዘጋ ስል “አይደለም እኮ አቶ አምሳሉ እንዴት መሰለዎት ቆይ እንዲያውም አለቃየን ላገናኝዎት” አለና ስልኩን አሁን ላይ የጣቢያው ኃላፊ ለሆነው ለአቶ ቡሩክ ሰጠው፡፡ ከአቶ ቡሩክ ጋርም አውርተን መግባባት ባለመቻላችን አቶ ቡሩክ ደግሞ እንደገና “ቆይ ቆይ አትዝጋው! ከአለቃየ ጋራ ላገናኝህ!” አለና አሁን ስሙን የማላስታውሰው አማርኛ ቃላትን አስተካክሎ መጥራት የማይችል የሬድዮ ጣቢያው ዋና ኃላፊ ከሆነ ትግሬ ሰውየ ጋር አገናኘኝ፡፡ እዚያው አንድ ላይ ሆነው ነበር ያነጋግሩኝ የነበረው መሰለኝ ስልኩን ወዲያው ወዲያው ነበረ ከአንደኛው እጅ ወደሌላኛው እጅ እየተቀባበሉ ያናግሩኝ የነበረው፡፡ ይሄኛው ትግሬው ኃላፊም “ምን መሰለዎት አቶ አምሳሉ እ…. አብሮ መሥራትም እኮ ይቻላል!” ብሎ ሲል “ይህቺ ናት ጨዋታ!” አልኩና ከዚህ በኋላ እንደማልደውል ገልጨ ተሰናበትኳቸው፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ ለሬዲዮ ፋና እንኳን ልደውል ጣቢያውንም አዳምጨው አላውቅ፡፡ ምክንያቱም ካዳመጥኩ አያስችለኝማ! ያ ዝግጅትም አሁን ይኑር አይኑር እራሱ አላውቅም፡፡

ታዲያ እላቹህ ያኔ ያ ዝግጅት ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይሄ ቴዎድሮስ ጸጋዬ የተባለ ሰው እንደኔው ሁሉ እየደወለ እየገባ ቅጥረኛነቱ ሊታወቅበት በማይችል ሁኔታ እኔ ያበላሸሁባቸውን ነገሮች የቻለውን ያህል ለማስተካከል ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ሁሌም የሚገባው እኔ ከወጣሁ በኋላ ነው፡፡ አንድ ቀን ከወጣሁ በኋላ ሲገባ ተመልሸ ገባሁና ለአወያዩ ቴዎድሮስን እንዳይሸኝብኝ እንዲያቆይልኝ ለራሱም ለቴዎድሮስ እንዳይወጣ ተናገርኩና አወያዩ ዕድሉን እስኪሰጠኝ ስጠባበቅ ቴዎድሮስ የራሱን ተናገረና “ጨርሻለሁ አመሰግናለሁ!” ብሎ ወጣ፡፡ “ቆይ እንጅ!” ብለውም ሥራውን ያውቃልና ሊቆይ አልፈለገም ተፈትልኮ ወጣ፡፡ እኔ እስካቆምኩበት ጊዜ ድረስም እንዲሁ ሲያደርግ ቆየ፡፡

ከዚያ በኋላ ከልጁ ጋር የተገናኘነው መቸ መሰላቹህ? ከዓመታት በኋላ በሸገር ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) ከሙዚቃ (ከዘፈን) ባለሙያው ከሠርፀ ፍሬስብሐት ጋራ ሆኖ በኪነት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ዝግጅት ያቀርቡ በነበረበት ወቅት ነበር የተገናኘነው፡፡ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ በስልክ ነበር የምንገናኘው፡፡ ልጁ “እኔ በውቀት ነኝ!” እያልኩ ፋናን ሳስጨንቅ የነበርኩት ሰው እንደሆንኩ ያወቀኝ አልመሰለኝም፡፡ በዚሁ በሸገሩ ዝግጅታቸው ሁሌም አየር ላይ ከወረዱ በኋላ ወይም እዛው እያሉ ስልክ እየደወልኩ ምን እንደተሳሳቱ ምን ደግሞ ጥሩና ሊበረቱበት እንደሚገባ የማውቀውን ያህል እነግራቸው ነበር፡፡ ያኔ ልጁ እያደረኩላቸው ያለሁትን አስተዋጽኦ አመስግኖ ሊገልጸው ከሚችለው በላይ እንደሆነ ደጋግሞ ይነግረኝ ነበረ፡፡

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

ልጁ ውሉን አይረሳም፡፡ በተቻለው መጠን የወያኔን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችልበት ክፍተት ሲያገኝ ያንን ለማድረግ ጥረት ያደርጋል፡፡ እኔም ይሄንን ሊያደርግ እንደሚችል ስለገመትኩ ነበር በቅርብ ልከታተለው የፈለኩት፡፡ ለምሳሌ እዚሁ ሸገር ላይ እያለ አንዴ ምን አለ መሰላቹህ? ወቅቱ ቴዎድሮስ ካሳሁን በያስተሠርያል አልበሙ (የዘፈን ጥራዙ) ገኖ ከወጣበት ብዙ የራቀ አልነበረም፡፡ ወያኔ ቴዎድሮስ ካሳሁን ለወጣቱ አርአያ ሆኖ እንዳይወጣና እንዳይከተለው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ይህ የወያኔ የዘመቻ ትዕዛዝ የደረሰው ሥውሩ ተኩላ ማንትስ ጸጋዬ አንዳች ነገር ብሎ ቴዲን ማስጠላት የሚችልበትን ነገር ቢያጣ በዚሁ በሸገር ዝግጅታቸው ምን ብሎ ቴዲን ከሰሰ መሰላቹህ “ቴዎድሮስ ካሳሁንና አንዳንድ ሌሎችም እንዲሁ የሕዝብን ቁስል እየነካኩ በማድማት የሕዝብን ደም በመቸርቸር የራሳቸውን ትርፍ የሚያግበሰብሱ ጨካኝ ናቸው….” እያለ እነቴዲን ሊያስመሰግን እንጅ ፈጽሞ ሊያስተች የማይችል ነገር እያነሣ በቅጥረኝነቱ ታውሮ ምንም “ሰው ምን ይለኛል!” የሚል የስሜት ሙግት ሳይታይበት ቴዲን ለማዋረድ ጥረት እንዳደረገ ዝግጅቱን ጨርሶ ወጣ፡፡

ወዲያውኑ ደወልኩና “እንዴት እንዲህ ትላለህ? ሕዝብን ያቆሰለውን አካል ነው መኮንን ማውገዝ የነበረብህ ወይስ ይሄ የሕዝብ ቁስል ይጠግግ ዘንድ፣ ይሽር ዘንድ፣ ትኩረት መፍትሔ ያገኝ ዘንድ እንደ ሕዝብ ልጅነታቸው እየጮሁ ያሉ የሕዝብ ልጆች ናቸው መወገዝ መኮነን ያለባቸው? የገዥዎቻችን ግፍ እንዳይታወቅ፣ እንዳይገለጥና እንደፈለጉ ግፍ እየፈጸሙ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጠው ማንም ሳይወቅሳቸው፣ ሳይከሳቸው፣ ሳይተቻቸው፣ ሳያወግዛቸው፣ ሳይነኩ እንዲኖሩ ነው ወይ የምትፈልገው? ለምን? ዋነኛው የኪነት አገልግሎቷ ምን ሆነና? የሁሉም የኪነት ወይም የጥበብ ሥራዎች ተፈጥሯዊ ኃላፊነትና ግዴታ እኮ ከሕዝብና ከእውነት ጎን ቆሞ የሕዝብን በለው የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ፣ ሕዝብን ማገልገል እንጅ ከግፈኞችና ከሐሰት ጎን ቆሞ የግፈኞችን ጥቅም ማስጠበቅ እኮ አይደለም የኪነት ተልዕኮ፡፡ ኪነት እኮ ብሶት የመተንፈሻ፣ መልእክት የማድረሻ፣ የማስተማሪያ፣ የመቀስቀሻ፣ የማንቂያ … ሁነኛ መንገድ ናት እንጅ ዋነኛ ዓላማና ተልእኮዋ እኮ ሰዉን እያስጨፈሩ በማዳራት ሰውን ወደ እንስሳነት ማውረድ እኮ አይደለም ተልእኮዋና ተፈጥሯዊ ኃላፊነቷ…” እያልኩ ስወርድበት የሚለው ቢያጣ ምን ይለኛል “ምን መሰለህ አምሳሉ የግጥም ጉባኤ ምናምን እያሉ በየቦታው የሚቀርቡ ግጥም ተብየ ጽሑፎችን ብታይ እኮ በጣም ነው የምታዝነው! የሆነች ፖለቲካዊ ሽሙጥ ገና ከመናገራቸው ይጨበጨብላቸዋል፣ ይሳቅላቸዋል ምናምን፡፡ እና ለዚህ ነበር እንደዛ ያልኩት!” አለና የማይገናኝ መልስ ሰጠኝ፡፡ እኔም ግድ የለም የሚበቃውን ያህል ነግሬዋለሁ እንዲህ ከጨነቀው ማምለጫ የማርያም መንገድ ልስጠው አልኩና “እንዲህ ከሆነ ሐሳብህ ሌላ ጊዜ ልትለው የምትፈልገውን ነገር በደንብ ለይተህና አጥርተህ አድማጭ ማለት ያልፈለከውን ነገር እንዲገነዘብ ዕድል ሊሰጥ በማይችልበት አኳኋን ጥንቃቄ እያደረክ ተናገር!” ብየ ብቻ በደፈናው ሸኘሁት፡፡

እንግዲህ ይሄ ልጅ አሁንም ድረስ ቴዲን ጠምዶ ይዞ የሚያጠቃበት ምክንያት ከላይ እንደጠቆምኳቹህ ልጁ ከበፊት ጀምሮ በቅጥረኛነቱ ከወያኔ በተሰጠው ተልእኮ ነው እንጅ ቴዲ ማንም ድምፃዊ አድርጎት በማያውቀው ብቃት፣ ሙሉነትና ዝግጅት የሠራውና እየሠራው ያለው መልካም የኪነት ሥራና አርአያነት ቴዲ የሠራው ክፉ ነገር ኖሮ ይሄው ክፉ ሥራው ከመልካሙ ሥራው አመዝኖ ለትውልዱ አርአያነት ሊኖረው ስለማይገባ እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በእርግጠኝነት እንናገር ከተባለ ለሀገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሆነ ሰው ከፍተኛ በሆነ የኃላፊነት ስሜት ስለፍቅር ስለመቻቻል ስለማንነት በሥራዎቹ ተግቶ እየሰበከ ያለውን ብርቅዬ ከያኔን ያበረታታል፣ ያደንቃል፣ ያመሰግናል፣ ይደግፋል እንጅ በምንም ተአምር ቢሆን እንኳንና በቴዲ ላይ ሊጠቅሰው የሚችለው ይሄነው የሚባል ችግር ሳይኖር ቀርቶ ቢኖርም እንኳ ከመልካም ተግባሩ እንዳይደናቀፍበት በመሥጋት ይደብቅለታል እንጅ በፍጹም በፍጹም ጭራሽ የቴዲን ዋጋ ሊያወርድ፣ ከአርአያነቱ ሊያናጥብ፣ ከተቀደሰ ተግባሩ ገሸሽ እንዲል ሊያደርግ የሚችል ምንም ሊጠቅሰው የሚችለው እዚህ ግባ የሚባል ነገር ሳይኖር በባዶ ጩኸት በአሳፋሪ ድርቅና “ቴዲን ዋጋቢስ ነው ስንላቹህ፣ ጥሉልን ስንላቹህ ዝም ብላቹህ ተቀበሉንና ጥሉልን ጣሉልን!” አይልም፡፡ ይህ የልጁና የመሰሎቹ ሁኔታ በግልጽ የሚያመለክተው እውነት ቢኖር ከጀርባቸው የተለየ ዓላማ ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ እሱም ከላይ በጨረፍታ ከገለጽኩላቹህ የልጁ የኋላ ማንነት ተነሥታቹህ በቀላሉ ልትረዱት እንደምትችሉት ወያኔ በመሆኑ ነው እንጅ ልጁ ካለበት ስር የሰደደ የምቀኛነትና የእርጉምነት ችግሩ ብቻ አይደለም፡፡

ልጁ አንዴ እንዳጫወተኝ ቴዲንና ይስማዕከን አንድላይ አግኝቷቸው ለቃለምልልስ ጠይቋቸው ነበር፡፡ ይሄን ከማድረጉ በፊት አስቀድሞ ለማባበያነት እንዲረዳው ብሎ ሸገር ላይ እያለ ሞናሊዛ የሚለውን የቴዲን ዘፈን እያንዳንዷን ሐረግ እንደራሱ አተያይ እየተነተነ ዘፈኑን የዓለም አንደኛ ዘፈን፣ ቴዲን ደግሞ እጹብ ድንቅ የተዋጣለት ደራሲና ድምፃዊ እንደሆነ የሚመሰክር ዝግጅት ሠርቶ አቅርቦ ነበር፡፡ የልጁን ማንነት ጠንቅቆ የተረዳው እንቆቆው ቴዲሻ ይቺ ነገር ለማጥመጃነት እንደተሠራች ገብቶት ኖሮ ቴዲም ደራሲ ይስማዕከም ሲመቻቸው ቃለመጠይቁን እንደሚሰጡት ይመልሱለታል፡፡ ልጁ ይሄ ማለት “አንፈልግም!” ማለት እንደሆነ ገብቶት የሚመቻቸውን ጊዜ ቁርጥ አድርገው እንዲነግሩት ሲጠይቃቸው የሥራቸው ጸባይ እንዲህ ብሎ ለመንገር እንደማያመቻቸው ይነግሩታል፡፡ ልጁ ሁለቱንም ለየራሳቸው በቃለመጠይቅ አግኝቶ ያለና የሌለ እያወራና ምላሾቻቸውን ኤዲት አድርጎ (ረትዕቶ) ቆራርጦ ለራሱ ዕኩይ ወያኔያዊ ዓላማ በሚመች መልኩ አቅርቦ ጉድ በመሥራት ከአርአያነታቸው ለማንጠብ ለመጣል ያቀደው አቅድ እንደከሸፈበት ሲገባው ከዚያ በኋላ በሁለቱም ላይ አውሬ ሆኖ ተነሣባቸውና እሱን እራሱን ከፍተኛ ትዝብት ላይ የሚጥሉ የማይረቡ ትችቶችን እያነሣ የማጣጣል ጥረቱን በከፍተኛ ደረጃ ተያያዘው፡፡

ስለዚህ ልጅ አስቀድሞ ለሱ ከነበረኝ ግምት በላይ በወያኔነቱ ብቻ ሳይሆን ካለበት ስር የሰደደ የሥነልቡና ችግር የተነሣ ያለምንም ተገቢ የሆነ ምክንያት ሰዎችን የሚያጠቃ እባብ መሆኑን የተረዳሁት ከታች የምገልጽላቹህን ሁለት ክፋቶችን የሸገሩን የአየር ሰዓት ስለተቀሙ ከሠርፀ ፍሬስብሐት ተነጥሎ ኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 ላይ ሲገባና ርዕዮት የሚባል እሑድ እሑድ የሚተላለፍ ዝግጅት ከሌሎቹ አጋሮቹ ጋር ሆኖ አቋቁሞ በሚሠራበት ወቅት በግል እኔ ላይ ከፈጸመብኝ በኋላ ነበር፡፡

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

እሱ ምን መሰላቹህ በግምት የዛሬ ሰባት ዓመታት አካባቢ ነው ልጁ ደወለና “እስኪ ባክህ አምሳሉ በቀደም ለታ ስድስት ኪሎ የአማርኛ ፊደላት እንዲቀነሱና በፊደላቱ አጠቃቀም ላይ ሌሎች ለውጦችም እንዲደረጉ የሚያትት በዶ/ር ፍቅሬ ዮሴፍ የተጻፈ መጽሐፍ ተመርቋል፡፡ መጽሐፉን ከዶ/ር… እጅ ታገኘዋለህ፡፡ በዚህ ስልክ ደውለህ አግኘው፡፡ ከዶ/ር ፍቅሬ ዮሴፍ ጋር ክርክር እንድታደርጉ ስለፈለኩ ነው ላስቸግርህ?” ሲለኝ እሽ አልኩና መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ “ዝግጁ ነኝ!” አልኩት፡፡ እሱም “እሳቸውን ከምናንገላታ ቤታቸው ደብረዘይት ነው ጡረተኛ ስለሆኑ የእኛን ሰዓት አመቻችተን ብንሔድስ?” አለኝ፡፡ አኔ እንደሳቸው ዓይነት አቋም ካለው ሰው ጋር መከራከሩን በጣም እፈልገው ስለነበረ ይሄንንም እሽ አልኩትና ቀጠሮ አስይዘናቸው ሔድን፡፡ ይገርማቹሀል ጉዳዩ የሱ ሆኖ ሳለ ልጁን ለመደገፍ ከነበረኝ ፍላጎት የተነሣ የሦስታችንንም የመጓጓዣውን ሒሳብ የከፈልኩት እኔ ነበርኩኝ፡፡ ሒሳቡ ብዙ ሆኖ ሳይሆን እንዲያው ሁኔታውን እንድትገነዘቡ ያክል ነው፡፡

ከዚያም ዶ/ር ፍቅሬ ተቀበሉን፡፡ መቅረጸ ድምፆቻችንን አዘጋጀንና ጥያቄዎችን እያነሣሁ መከራከር ጀመርን፡፡ ክርክሩ ሞቅ ጋል ከበድ እያለ መጣ፡፡ ቆየት ቆየት እያለ ልጁ “ይህ ርዕዮት ነው… በዚህ በዚህ ስልክ ቁጥር ደውሉ፣ ጥያቄ አስተያየታቹህን ለግሱን…” ይላል፡፡ አሁን ከበድ የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሣሁ ወደመከራከሩ ገብቻለሁ፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ የቻሉትን ያህል እየመከቱ ነው፡፡ ይበልጥ ወደሚከብዱት ጥያቄዎችና ክርክራችን ስንገባ ዶ/ር ፍቅሬ ተጨናነቁ፡፡ ድንገት አቋርጠው ተነሡና ወደ መታጠቢያ ቤት ገቡ፡፡ እኔ ይሄ ሊፈጠር እንደሚችል ገና ከቤት ስነሣ ሥጋቱ ነበረኝ፡፡ መቅረጸ ድምፆቻችንን ፖዝ (ጠብቅ) አድርገን መጠበቅ ቀጠልን፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ፊታቸውንና ጭንቅላታቸውን በውኃ አረጣጥበው ተመለሱ፡፡ “ይቅርታ ልጆች! ትንሽ እኮ አከበድክብኝና… የቤተክህነት ትምህርት እንዳለህ ታስታውቃለህ! ዶ/ር … ታውቀዋለህ? እሱም እንደዛ ነው…” ለጥያቄዎቻቸው መልስ ሰጠሁና “ወደ ውይይታችን እንመለስ!” ብየ መቅረጸ ድምፆቻችንን መቅረጽ ስናስጀምር “የለ የለ ተውት! ይሄማ ይቅር! ይሄንን ለሕዝብ ማቅረብ ጥሩ አይደለም፡፡ ሌላ ሌላ ጨዋታ እንጫወትና ሒዱ!” አሉ፡፡ ከዛ ልጁ “አይ እኛ እኮ እንዲህ ባለበት ሁኔታ አናቀርበውም፡፡ እነዚህ የማይመቹ ነገሮቹን ሁሉ ኤዲት አድርገን እናወጣቸዋለንና ችግር የለም አይሥጉ!” አላቸው፡፡ እሳቸው ግን “አይ በደምብ ሳልዘጋጅ ነው የመጣቹህት፡፡ እንዲህ የተበለሻሸሁበትን እማ እንዳታቀርቡት አደራ!” ብለው እንኳን ልንቀጥል የተቀረጸውም እንዳይቀርብ ተማጸኑን፡፡ በዚሁም የጥያቄ ክርክሩ ነገር አከተመለት፡፡ ልጁ በሕይዎታቸውና በሰፊ የሥራ ልምዳቸው ዙሪያ ቃለመጠይቅ ሊያደርግላቸው እንደሚፈልግ ነግሯቸው ፈቃዳቸውን ጠየቀ፡፡ እሽታቸውን መለሱለት፡፡ ከዚያ ልጁ ምን ይለኛል መሰላቹህ “እዚህ አድሬ ነገ ቃለመጠይቃቸውን መሥራት ስለምፈልግ አንተ ሒድ በቃ!” ብሎ ሸኘኝ፡፡ እኔም ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡

ልጁ ያለውን ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው በሳምንቱ ጀመረና በተከታታይ አቀረበው፡፡ ስለክርክራችን ምን እንዳሰበ ስጠይቀው እንደሚያቀርበው ነገረኝ፡፡ ብጠብቅ አያቀርበውም አሁንም ብጠብቅ አያቀርበውም ወራት አለፉ፡፡ ምነው ብየ ጠየኩት “አይ እንደምታየው የበዓላት የምናምን ወቅት ስለነበረና ይሄንን ክርክር ሕዝቡ በጽሞና እንዲከታተለው ስለምፈልግ ምቹ ሰዓት እየጠበኩ ስለሆነ ነው አቀርበዋለሁ!” አለኝ፡፡ ያኔ በምንም ተአምር ሊያቀርበው እንደማይችል ገባኝ፡፡ ነገር ግን ላስጨርሰው ብየ ረጅም ጊዜ ሰጥቸ ሳላነሣበት እየጠበኩት እያለ ወደኋላ ምን ብሎ ያስተዋውቃል “ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የአማርኛ ፊደላት ይቀነሱ! ሞክሸና ፍንጽቅ ፊደላት አይጠቅሙም! የሚል አቋም እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይሄንን አቋም የሚቃወምና መከራከር የሚፈልግ ሰው ካለ እስኪ እባካቹህ ደውሉልን!” ብሎ ጥሪ አቀረበ፡፡ ደወልኩለትና “እንዴ የሠራነው አለልህ አይደለም ወይ?” ብየ ጠየኩት እሱም “ምን መሰለህ አምሳሉ ከዶ/ር ፍቅሬ ጋር በፍጹም አልተመጣጠናቹህም! አልቻሉህም፡፡ ይሄ ጎልቶ ይታያልና ቅር ያሰኛል፡፡ ጠንከር ያለ ሰው ከጠንከር ያለ ሰው ጋር የተደረገ ሌላ ተጨማሪ ክርክር ያስፈልገኛል፡፡ ከዛ ከሁለቱም እያደረኩ አቀናብሬ አቀርበዋለሁ!” አለ፡፡ የተባለውን ሰው ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ የባለጌነቱ ባለጌነት የጭንጋፍነቱ ጭንጋፍነት ከዚያ ምን አደረገ መሰላቹህ ላይችልበት ነገር እኔ ከዶ/ር ፍቅሬ ጋር ስከራከር ያነሣኋቸውን የመከራከሪያ ነጥቦቸን እያነሣ እራሱ ከዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ጋር ሆኖ ሠራና የማይረባ ዝግጅት አቀረበ፡፡ ማመን አልቻልኩም! ቆሻሻነቱ እጅግ በጣም አስደነቀኝ አስደነገጠኝም፡፡ ያኔ የኛን ክርክር እንደማያቀርበው እርግጡን አወኩ፡፡ እስከ መጨረሻውም ሳያቀርበው ቀረ፡፡

እንዲህ ዓይነት አስቀያሚ በደል ፈጽሞብኝም ግን አሁንም በየዝግጅቶቹ የምሰጠውን እርማትና አስተያየት አልነፈኩትም ነበር፡፡ ከዛላቹህ አንድ በትውልዱ እንከን ላይ ያተኮረ ነጠላ ዜማ ግጥምና ዜማ አዘጋጅቸ እኔው እራሴ ተጫወትኩትና አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ የሬድዮ ጣቢያዎችና የመዝናኛ ዝግጅቶች ላሏቸው አዘጋጆች ለብዙዎቹ አደልኩት፡፡ ለዚሁ ጉደኛ ልጅም ሰጠሁት፡፡ እንደወደደውና ከዚህ ቀደም ለአንዳንድ ዜማዎች እንዳደረገው ተረክ ሠርቶለት እንደሚያቀርበው ነገረኝ፡፡ እንኳንና ተረክ ዜማውን ብቻውን እንኳ ቢያቀርበው በጣም እንደሚገርመኝ ለራሴ እየነገርኩ “በጣም አመሰግናለሁ!” አልኩት፡፡ ይሁንና እንኳንና ይሄው ችግር ያለበት ልጅ ሌሎቹም አንዳቸውም ሳያስደምጡት ቀሩ፡፡ አንድ ፋና ላይ የመዝናኛ ዝግጅት የነበረው ሰው ሲያጫውተውም ገና ግማሽ ላይ ሳይደርስ ተቆጣጣሪው ከቢሮው (ከመሥሪያ ክፍሉ) ተንደርድሮ ሔዶ እንዲቋረጥ አደረገው፡፡ ይሄም ልጅ አላጫውተው ሲል ለማጫወት ይከፈል እንደሆነ ስንት እንደሆነ እንዲነግረኝና እንድከፍለው ስጠይቀው እንደጨዋ ሰው ተቆጣ “እንዴት ብትገምተኝ ነው ስንት ነገር እያደረክልኝ ካንተ ገንዘብ የምቀበለው?” ብሎ አኮረፈ፡፡ ስደውል አያነሣም ስደውል አያነሣም፡፡ ሰነባበትኩና በሌላ ስልክ ደወልኩለት አነሣው፡፡ ምን እንደሆነ ጠየኩት “ሰደብከኝ እኮ!” አለ፡፡ ምን ብየ እንደሰደብኩት ጠየኩት “እሱን አንተ ታውቀዋለህ… ግን ቆይ ክፍያ ብጠይቅስ ግን ምንድን ነው ችግሩ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ እኔም “ችግር አለበት ብለህ ያኮረፍከው እኮ አንተ ነህ፡፡ እኔማ ልክፈል ብየ እኮ ጠየኩህ!” ስለው የሚለው አጥቶ “በቃ ቻው! ቻው ቻው!” ብሎ ጆሮየ ላይ ዘጋብኝ፡፡ የዘፈኑም ነገር በዚያው ቀረ፡፡ ይሄንን ዜማ Fashion Amsalu Gebrekidan ብላቹህ ዩ ቲዩብ (ፈለገ እናንት) ላይ ብትፈልጉት ታገኙታላቹህ አዳምጡት፡፡

Related stories   የምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ አቅል ያጣ ፍላጎት ግን ምንድን ነው!?

እውነቴን ነው የምላቹህ የዚህን ልጅ ማንነት ሊገልጽ የሚችል ስድብ ንገረን ብትሉኝና የስድብ መዓት ስደረድርላቹህ ብውል ይሄንን ልጅ ኢምንቱን እንኳ ሊገልጸው አይችልም፡፡ ምን እንደሆነ አላውቅም! ውስጡ ችግር ያለበት ሰው ነው፡፡ አስተዳደጉን ባውቅ ኖሮ “በዚህ በዚህ ምክንያት ነው ዕኩይነትና ቀና ያለማሰብ ችግር የተጣባው?” ለማለት ምንኛ በተመቸኝ ነበር፡፡ እሾክ ከመሆኑ የተነሣ “ይሄ ሰው ባለማየት የጤና እክሉ ላይ ይሄ ክፉ ጠባይ ታክሎበት ከማን ጋር መኖር ሊችል ነው?” እያልኩ የምር አዝንለት ነበረ፡፡ ይገርማቹሀል ይሄ ጠባዩ ደግሞ ከማንም በፊት የጎዳው እራሱኑ ነው፡፡ ያው መርዝ መጀመሪያ የሚጎዳው ብልቃጡን አይደለ? ልጁ በጣም ከባድ የሆነ የጨጓራ በሽታ ተጠቂ ነው፡፡ ነውረኛ ነው፣ ባልጠበቃቹህት ሰዓት ባለጌ ይሆንባቹህና ያስደነግጣቹሀል፣ ምቀኛ በእሱ ልክ ስትፈልጉ ብትኖሩ አታገኙም፡፡ እነኝህ ችግሮች ከመጠን በላይ የሠፈሩበት ሰው ነው ይሄ ልጅ ማለት፡፡ እነዚህን ችግሮቹን ሕዝብ ፊት በቀረበበትና ለሕዝብ ወይም ለአድማጮች ክብር ሰጥተው በቀረቡለት የተከበሩ እንግዶች ፊት ቀርቦም እንኳ ሊደብቃቸው ሳይችል ሲቀሩና አፈትልከው ሲወጡበት ሳታስተውሉ የቀራቹህ አይመስለኝም፡፡

ይሄ ልጅ ይሄን ሁሉ ነገር በጋዜጠኛ (በዘጋቢ) ስም ሲሠራ ጋዜጠኛ (ዘጋቢ) ሆኖ አልነበረም፡፡ ያጠናው ሕግን ነው፡፡ እንደምታዩት ግን እንኳን ሕግን ያጠና አንዲት የሕግ አንቀጽ በቅጡ አንብቦ የሚያውቅና የተረዳም አይመስል፡፡ ዝንባሌው አለኝ ብሎ ነው ዘው ብሎ የገባው፡፡ አቅምና ሞያው የሚጠይቀው ሰብእና ኖሮት ቢሆን ኖሮ ምንም ባልነበረ፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጋዜጠኝነት ትምህርት ስላልነበረና ሥራው ይሠራ የነበረው በዝንባሌ በመሆኑ፡፡

ለዚህም ነው ልጁ የጋዜጠኝነትን ሀ ሁ ስለማያውቅና ስር የሰደደ የቀናነት ማጣትና ሥነ ሥርዓትን ያለማወቅ ችግሩ ምክንያት አየር ላይ እየወጣ ሚዛናዊነት የሚባልን የሞያውን መስፈርት ፈጽሞ ግምት ውስጥ ባላስገባና በየዝግጅቱ የሚኮንናቸው ተወጋዡ ተዘላፊው ሰው እራሱን የመከላከል ዕድል ባላገኘበት ሁኔታ ሰዎችን እያነሣ እንደፈለገ የማብጠልጠል፣ የማበሻቀጥ፣ ገጽታ የማበላሸች የዕኩይ የባለጌ የስድና የነውረኛ ሥራውን ሲሠራ የጋዜጠኝነትን ሥራ የሠራ የሚመስለውና በዚህ ነውረኛ ሥራውም ሲኩራራ የምታዩት፡፡

መጨረሻ ላይ የኔና የልጁ መጨረሻ እንዴት ተቋጨ መሰላቹህ ልጁ መቸም ቢሆን የማይጸጸት የማይታረምም መሆኑ ሲገባኝ አንድ እሑድ ቀን አየር ላይ እንዳሉ ዘፈን ጋብዘው ለረፍት በተቀመጡበት ደወልኩለትና አብረውት የሚሠሩት በፊት የፋና ጋዜጠኛ የነበረችው ክብረ ተስፋዬ እና በኋላ ላይ ያገባት ሜላት እዚያው ስቱዲዮ (መከወኛ ክፍል) ከጎኑ አሉ “የዕለቱን አስተያየት ከሰጠሁት በኋላ ቴዎድሮስ ግን ለእኔ እንዲህ የሆንከው ለምንድን ነው? በተደጋጋሚ አስቀየምከኝ! ምን ባደረኩህ ነው?” ብየ እሱን ለማነጽ ምን ያህል እንደደከምኩ ላስታውሰው ሞከርኩ፡፡ አስከትየም ስር የሰደደ የሥነ ልቡና ችግር እንዳለበትና ከዚህ ችግሩ ጋር ከሰው ጋር ሊኖር እንደማይችል ስነግረው ሁለት ሦስት ስድቦችን ሰነዘረና ስልኩን ሳይዘጋው ለቅሶውን ንፍጡ እየተዝረበረበ ጭምር ለቀቀው! ባለቤቱና ክብረ ሊያጽናኑት ይሞክራሉ እሱ ግን መጽናናት አልቻለም! “ተይኝ ባክሽ ተይኝ!” እያለ እንደሕፃን ልጅ መነፍረቁን ቀጠለ፡፡ እኔ ይሄንን ሁኔታ ፈጽሞ ስላልጠበኩ በሆነው ነገር በጣም ደነገጥኩ፡፡ እንዲህ ተደራራቢ ችግር ያለበትን ሰው ያውም ከሥራ ቦታ በሰዎች ፊት በዚህ መልኩ ይሆናል ብየ ባልጠበኩት ሁኔታ አስከፍቸ በማስለቀሴ እግዚአብሔር በዚያኑ ዕለት የሆነ ነገር የሚያደርገኝ መስሎኝ የምር ጭንቅ ብሎኝ ነበር፡፡

ልጁ እንዲያ በሚነፈርቅበትና እነ ክብረ ተስፋዬ ለማጽናናት ጥረት በሚያደርጉበት መሀል ጥቂት የማይባሉ ደቂቃዎች ባክነው ስለነበረ ይሄንን ሰዓት በዘፈን ለመሸፈን ተገደው ነበር፡፡ ከሁለት ሦስት ዘፈኖች መጫወት በኋላ ክብረና የልጁ ባለቤት አየር ላይ ተመልሰው ቀሪውን ሰዓት ሸፈኑት፡፡ እሱ ግን በዚያ ሰዓትም የጣቢያው አለቆች ፊት ቀርቦ እየነፈረቀ ነበር፡፡ እንደሰማሁት እንድከሰስለት ሁሉ ጠይቆ ነበር፡፡ ከንግግራችን የሱን ውለታቢስነትና ክፉነት የሚያሳይ ነገር እንጅ ሊያስከስስ የሚችል ነገር ባለመገኘቱ ክሱ ቀረ እንጅ፡፡ በቃ ከዚያ የኔና የሱ ነገር በዚሁ ተቋጨ እላቹሀለሁ፡፡

እና ይሄ ልጅ ማለት በወያኔነት ላይ እንዲህ ዓይነት ችግሮች የሰፈሩበት መፃጉዕ ነውና ሰው መስሏቹህ ቦታ እየሰጣቹህት የእሱም እንግዳ እየሆናቹህ አትቅረቡ፡፡ እንዲህ በማድረጋቹህ ልጁ ያለ አቅሙ እንዲሰቀልና ባገኘው እውቅናም ወያኔያዊና ዕኩያዊ ተልእኮውን ለመወጣት ዕድል እንዲያገኝ አስችሎታልና ይህ ስሕተት ከዚህ በኋላ መቀጠል ስለሌለበት እዛው መሰል የወያኔ ቅጥረኞችን እየጋበዘ ይጨማለቅ እንጅ ኢትዮጵያዊነትን የምታቀነቅኑ የማኅበረሰባችን ልኂቃን (Elite) ግን በፍጹም በምንም መልኩ እንዳትጠጉት አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር ከያኔ ታማኝ በየነ የልጁ እንግዳ ሆኖ ሊቀርብ መሆኑ አስከፍቶኛል፡፡ ቃለ ምልልሱ ገና ያልተደረገ ከሆነ ታማኝ ለዚህ ልጅ ቃለምልልስ ሰጠ ማለት “በወራዳ ተግባርህ ግፋበት!” ብሎ ማበረታታት በመሆኑ ከያኔ ታማኝ ቃለምልልሱን እንዲተው አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ከዚህ ጀርባ ከያኔ ዓለምፀሐይ ወዳጆ እንዳለች ይሰማኛል፡፡ ግምቴ ትክክል ከሆነ በከያኔዋ ማዘኔን ላሳውቃት እሻለሁ፡፡

ይሄው ነው እንግዲህ የዕኩይ ሰው ማንነት የታየበት ጽሑፍ በመሆኑ ነገሩ እረዘመና እዚህ ደረሰ፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ! እርግጠኛ ባልሆንም ልጁ “አላየሁም አልሰማሁም!” ብሎ ለማለፍ ጥረት ያደርጋል እንጅ ለዚህ ጽሑፍ መልስ መስጠት የሚሞክር አይመስለኝም፡፡ ደሞ የሬዲዮው (የነጋሪተ ወጉ) አልበቃ ብሎት በቴሌቪዥንም (በምርዓየ ኩነትም) ሕዝብ እያየው ይነፍርቅ እንዴ! ደግነቱ ስርጭቱ ቀጥታ አይደለም፡፡ ይሄ ልበ እውር ከዚህ ከጻፍኳቸው እውነታዎች አንዳቸውንም እንኳ ለማስተባበል ቢሞክር በሌላ የብዙኃን መገናኛ ከእሱ ጋር አቅርቦ በማመሳከር እውነትን ማግኘት ቀጣፊን ማሳፈር የሚፈልግ ብዙኃን መገናኛ ቢኖር ፈቃደኛ መሆኔን አስቀድሜ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ከዚህ በታች በጠቀስኩት አድራሻ ኢሜይል (ነመልክት) አርጉልኝ አመሰግናለሁ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *