ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

“…ማንነቱን ያገኘ ሰው ከፍታ ማማ የወጣ ሰው ነው፤ ከወጣበት ከፍታ ማንም ሊያወርደው አይችልም…” ቴዲ አፍሮ – ዘውድ አልባው ንጉስ እንደ ሞሊዬር!!

Image result for tewodros kassahun….ራሱን ፈልጎ ሲያገኝ  ግን የተውኔት ባለሙያ ሞሊዬር ተባለ ኪነጥበብም ዓይኗን የጣለችበት ደመ ገብ የጥበብ ሰው ሆነ። ሞሊዬር በፍቅርዋ ሰክሮ ለጥበብ ባለው ፍቅር ምክኒያትም እየወደቀ እየተነሳ ብዙ ዋጋን ከፍሏል። ኪነጥበብን ለእውነት እንጅ ለሸቀጥ አላቀርብም ያለው ታማኙ የኪነጥበብ ሰው ሞሊየር ታስሯል፤ ተሰድዷል ብዙ መንገላታት ደርሶበታል። ይሁን እንጅ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ሞሊየር በፈረንሳይ ህዝብ ልብ ውስጥ ልዩ ክብር የተቸረው ዘውድ አልባው ንጉስ ተብሏል። የኛው ቴዲ አፍሮ ከሞሊየር ጋር የተመሳሰለብኝ እዚህ ላይ ነው…

ኤድዋርድ ፍራንክሊን አልቤ 3ኛ በመባል የሚታወቀው አሜሪካዊው ጸሃፊ ተውኔት አንድ ወቅት በአሜሪካን የቲአትር ክንፍ እልፍኝ ውስጥ በተደረገለት ቃለ መጠየቅ ጋዜጠኛው “ አንድ ሰው  እንዴት ጸሃፊ ተውኔት መሆን ይችላል?” ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “ ጸሃፊ ተውኔት ለመሆን ጸሃፊ ተውኔት ሆኖ መወለድ ያስፈልጋል። ሌላውም እንዲሁ ባለቅኔው፤ ፖለቲከኛው ያን ሆኖ መወለድ አለበት።” ብሎ በማስረገጥ ተናግሮአል።

ዛሬ ይህንን ለጽሁፌ መግቢያ የሆነኝን አገላለጽ ወዲህ አምጥቼ መዶሌ ቢመቸኝ ነው ባምንበት። እርግጥ ነው ዘመኑ ሆነና የአብዛኛው ሰው የመጀመሪያ ጥያቄ ለምን ዓላማ ነው የተወለድኩት? ምን ዓይነት ስጦታ ነው በእኔ ውስጥ ያለው? ይህንን ልዬ ስጦታ እንዴት ልግለጸው የሚል ሳይሆን ከዚያ ይልቅ ያበላል ወይ፤ ወደላይ ያወጣል ወይ? የሚል ሆነ። እንዴት ዓይነት ገበሬ ሊሆን የሚችለው ሰው ፖለቲከኛ ካልሆንኩ ብሎ ሲንገታገት ስታዩት፤የተዋጣለት አስተማሪ ቢሆን ብዙ ደቀመዛሙርት በማፍራት የሚያስደምመን ሰው ነጋዴ ካልሆንኩ ብሎ ነጭነጫ ሲሆን ምን ትላላችሁ?። ሰው ግን አስተውሎ በተወለደበት ዓላማ መስመር ራሱን ሲያገኘው አበቃ ያ ሰው ተራ ሰው ሆኖ አያልፍም ክስተት ይሆናል።

ማርክ ቲዊንስ “በህይወትህ ሁለት አስፈላጊ ቀኖች አሉ እነርሱም የተወለድክባቸውና ማንነትህን ያገኘህባቸው ቀናቶች ናቸው ።”  ማንነቱን ያገኘ ሰው ከፍታ ማማ የወጣ ሰው ነው ያን ሰው ከወጣበት ከፍታ ማንም ሊያወርደው አይችልም ምክኒያቱም ከተፈጠረበት ዓላማ ጋር የሚለቀቅ፤ ዓላማውን የሚያከብር ልዬ መለኮታዊ  ሃይል አለና። ቴዲ አፍሮ እንዲህ ነው እሱ ክስተት ነው! ከተፈጠረለት ዓላማ ጋር የተጋመደ  በመለኮት ክብር የተከበበ ደማቅ ኮከብ!!!።

የህግን ትምህርት በዪኒቨርሲቲ ያጠናው ጀን ባፕቲስት ፖኪውሊን ትንፋሽ ወስዶ ራሱን ፈልጎ ሲያገኝ  ግን የተውኔት ባለሙያ ሞሊዬር ተባለ ኪነጥበብም ዓይኗን የጣለችበት ደመ ገብ የጥበብ ሰው ሆነ። ሞሊዬር በፍቅርዋ ሰክሮ ለጥበብ ባለው ፍቅር ምክኒያትም እየወደቀ እየተነሳ ብዙ ዋጋን ከፍሏል። ኪነጥበብን ለእውነት እንጅ ለሸቀጥ አላቀርብም ያለው ታማኙ የኪነጥበብ ሰው ሞሊየር ታስሯል፤ ተሰድዷል ብዙ መንገላታት ደርሶበታል። ይሁን እንጅ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ሞሊየር በፈረንሳይ ህዝብ ልብ ውስጥ ልዩ ክብር የተቸረው ዘውድ አልባው ንጉስ ተብሏል። የኛው ቴዲ አፍሮ ከሞሊየር ጋር የተመሳሰለብኝ እዚህ ላይ ነው።Image result for tewodros kassahun

ቴዲ አፍሮ ለኪነጥበብ የከፈለው ዋጋ እጅግ ብዙ ነው ስደት፤እስራት፤ አፈናና ልዩ ልዩ መንገላታትን አሳልፏል አሁንም ግን በጽናት ቆሟል ደማቁ ኮከብ የበለጠ ደምቋል። ወጣቱ ኢትዬጵያዊ የኪነጥበብ ሰው ቴዎድሮስ ካሳሁን በህዝብ ከተወደዱት አስደማሚ ስራዎቹ ሌላ ፈጠራዎቹ የህዝብ ጩኽት፤ እንባ፤እምነት፤ የሃገር ፍቅር ስሜት የተቀላቀለባቸው በመሆናቸው በአገዛዞቹ ፊት ባይወደድም  እንኳን በህዝብ ልብ ውስጥ ግን ቴዲ ዘውድ አልባ ንጉስ ነው። ቴዲ የህዝብን ልብ ሲገዛ ልምጭ አልቆረጠም፤አፈ ሙዝ አልደገነም በሙያው ግን በትውልድ መሃከል ስፍራ አገኘ። መንፈሳዊ ነን ለምትሉት እግዚአብሄር የነገስታት ንጉስ ነው።

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ይህ ክብርና ከፍታ ከሜዳ ላይ እንዲያው እንዲሁ የሚታፈስ ሳይሆን በብዙ ልፋትና ድካም ብሎም የአምላክ እርዳታ ተጨምሮበት ከውዴታ፤ ከፍቅር የተገኘ ምላሽ ነው። ለቴዲ አፍሮ ኢትዬጵያ ማተቡ ናት!። ያቀነቅንላታል፤ ይዘምርላታል፤ይቀኝላታል። ኢትዬጵያን ኢትዬጵያ ያሰኟት የታሪክ፤ የባህል፤የቅርስ፤ የዕምነት ሃብቶቿም ለቴዲ ስራዎች ዋነኛ ንጥረነገሮች ናቸው። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ደግሞ የአንድ ህዝብ ማንነት የልቡ ውስጥ ቁምነገሮች ናቸው። ውሉ እዚህ ላይ ነው ቴዲ በህዝብ ልብ ውስጥ የልብ ሰው የሆነው ህዝብ ማንነቴ የሚላቸውን ንብረቶቹን በጥበቡ የሚያስውብ እውነተኛ የህዝብ ልጅ ሆኖ በመገኘቱ ነው። እናም ቴዲ ሲነካ  ህዝብ ይቆጣል አቅም ቢያጣ እንኳን ያለቅሳል።

ታሪክ እንደሚነግረን የጣሊያኖች ሬኒሰንስ መነሻ ሀረጉ ኪነጥበብ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው የግሪኮች ስልጣኔና ኃይል ሲዳከም በላቲን ቋንቋ የተጻፉ ተውኔቶችንና ልዩ ልዩ የኪነጥበብ  ውጤቶችን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጉያዋ ደብቃ አቆይታቸው ነበር።  ጊዜው ሲደርስ  ቤተክርስቲያኗ በዪኒቨርሲቲ ለሚማሩ ወጣቶች ዶኪመንቶችን እያወጣች መስጠት ጀመረች ወጣቶቹ እያወጡ ይዘረዝሩት ገቡ በዚህም ምክኒያት የተሃድሶ ዘመኑ ፍንዳታ ምክኒያት ሆነ። እዚህ ላይ ቤተክርስቲያኗን ባለውለታ ያደርጋታል። በእኛም ሃገር ሁኔታ የኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ ኃላፊነቷ በተጨማሪ የኢትዬጵያን ስነጽሁፍና ዜማ ተሸክማ ድርብ ውለታን በማድረጓ ምስጋና ይገባታል ባይ ነኝ። እንደዚሁ ሁሉ ቴዲም የጥበብንም የሃገርንም ጉዳይ ደራርቦ የተሸከመ ከእድሜው በላይ የሰራ ባለውለታ ነው። እናም የዚህ ጀግና የጥበብ ሰው ጉዳይ ከድምጻዊነትም በላይ ነው።

እንደ ተችዎቻችን  ቴዎድሮስ ጸጋይና ዳኝነት የተባሉ ጋዜጠኞች ወይስ ምን? አልገባኝም የጋዜጠኛ ልክን ስላላየሁ ምን ልበል? ብቻ እንደእነርሱ አገላለጽ መንጎቹ ፤ምስኪኖቹ  እኛ (የቴዲ አፍሮ ደጋፊ ለሆነ ሁሉ የተሰጠው ስያሜ መሆኑ ነው።)ሰለ ጥበብ ጀግናቸን እንናገራለን። በመሰረቱ መንጋ የብዛት መገለጫ ቢሆንም  ለሰው ግን አይሰጥም ነውር ነው ለእንስሳ እንጅ!። እንስት ፤ ተባዕት የሰው ልጅ የፆታ መገለጫ አይሆንም እሱም ለእንሰሳ ነው እገረ መንገዴን ላንሳው ብዬ ነው። የሬዲዬው ወገኞች ንቀት ከዚህ ይጀምራል። ጥያቄዬ ለምን የቴዲ አፍሮ ስራ ለትችት ቀረበ? የሚል አይደለም ትችቱን የሄዱበት መንገድና የተላገዱበት ድምጸት ግን ቃናው መሰሪነት መሰሪነት፤ ምቀኝነት ምቀኝነት ይላል።Image result for tewodros kassahun

በተውኔት ዓለም ውስጥ ቋንቋ በልዩ ልዩ መንገድ ማለትም በአካል  ፤በድምጽ እና በቃል ይገለጣል። ሁሉም መገለጫዎች ግን በተውኔት ዓለም ውስጥ የመድረክ ላይ ቋንቋዎች ናቸው። በሼክስፒር ተውኔቶች ላይ የቋንቋን ውበት የምናየው ከአካላዊ እንቅስቃሴ ይልቅ በቃል ነው። በእነ ሳሙኤል ቤኬት እና በእነ ብሬኽት ውስጥ ደግሞ በአብዛኛው አካላዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት የተውኔት ዓይነት  ነው። የድምጽ ሚና ደግሞ በአብዛኛው የሚታየው በኦፔራና ሙዚቃዊ ድራማ ላይ ነው። እናም በሙያዬ የድምጸት ትርጓሜ እነ ቴዎድሮስ ጸጋይ በደማቁ ኮከብ የኪነጥበብ ሰው ቴዎድሮስ ካሳሁን ላይ ተሳለቁ ነው የሚባለው የንግግራቸው ድምጸት በስላቅ የተሞላ ዝባዝንኬ ነው። በእዉኑ በኢትዬጵያ የሙዚቃ ሂደት ውስጥ አብዬት ባካሄደ፤ በትውልድ መካከል ክስተት በሆነ ሰው እና እፁብ  ድንቅ በሆነ ድምጻዊ ላይ እንዲህ ዓይነት ስላቅ ተገቢ ነውን? እንደ እንስሳ መንጋዎቹ የተባልነውን ያስቆጣን ይህ ቀልቡ የተሰወረ ድፍረታችሁ ነው። ስራው ይገምገም ከተባለም ስለሙያው ግርድፍ እውቀት ባላቸው እና ቅንነት በጎደላችው ሰዎች አማካኝነት ሳይሆን ሙያውን ሰልቀው በሚያውቁት ሰዎች ቢሆን በተገባ ነበር።

Related stories   ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

ቴዲ ክስተት ነው፤ ንጉስ ነው የምንለው ዝም ብለን አይደለም። በተሰማራበት የሙያ መስክ ሚዛን የደፋን ስራ ሰርቶ በመገኘቱ ነው። እኔ በእድሜዬ እንደኪነጥበብ ባለሙያነቴም ቴዲ አፍሮ በተሰማራበት ዘርፍ እንደ እርሱ መሬት ረግጦ የቆመ፤ የዜማን የወንዝ አናት የግጥምን ሃሳብ ጎተራ ያገኘ እንደ ቴዲ ያለ አላየሁም። በዛ ላይ ለሙያው ያለው ትኩረትና ስነ-ምግባር፤በማዕበል ውስጥ ሰንጥቆ የሚያልፈው ጽናቱ፤ለዕውነት ስለሚከፈለው ዋጋ ያለው ዕውቀቱ እናም ሙያዊ ብቃቱ እንዲህ ያለ የተሟላ ስዕብና ያለው ድምጻዊ አላውቅም።

በቴዲ ላይ ቅንነት የጎደለው ትችት ለማቅረብ የተነሱት ወገኖች ቴዲ አፍሮን  ከጥላሁን ገሰሰ ጋር በማወዳደር ሁለቱንም የኪነጥበብ ሰዎች በሚያከብራቸውና በሚወዳቸው ህዝብ መሃከል የሚያደናግርን ሃሳብ በመርጨት የጥላሁን አድናቂዎች በቴዲ አፍሮ ላይ ተገቢ ያልሆነ ንግግርን እንዲናገሩ ለማድረግ ስሬቱ ወያኔያዊ የሆነ መሰሪነትን ሲጠመጥሙ ታዝቤአለሁ። መንጋ የተባለው ህዝብ ግን አስተዋይ ነው እንዴት እንድሚመዝን ያውቅበታል። ጥላሁን ገሰሰ ሌላ ነው ቴዎድሮስ ካሳሁን ሌላ ነው። ይሁን እንጅ ቴዲ ከጥላሁን የድምጽ አወጣጥና የድምጽ ልቀት ጣራ ላይ ለመድረስ ወጣቱ ከያኒ ብዙ መሄድ እንዳለበት አምናለሁ። እርግጥ ነው ጥላሁንን ልዩ የሚያደርገው በተፈጥሮ የተሰጠውን ድንቅ ስጦታ በመጠበቅ ከደረጃው ሳይወርድ ለብዙ ዓመታት በመቆየቱ ነው። ቴዲ ይህንን እንደሚያደርገው በታሪክም በሙያው ዘርፍ እጅግ አስገራሚን ነገር እንደሚፈጥር ቅንጣት  አልጠራጠርም። “ የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው ቴዲ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ተጽዕኖ ፈጣሪ ድምጻዊ እንደሚሆን በትልቅ ተስፋ እጠብቀዋለሁ። ይህንን ያልኩበትን ምክኒያቴን በማስረገጥ ስናገር ቴዲ ዜማና ግጥም የሚሰሩ ሰዎችን ፍለጋ የሚኳትን እነርሱ ባይኖሩ የሚከስም ድምጻዊ አይደለም። በአስፈላጊው ጊዜ አስፈላጊውን መልዕክት ይዞ ከተፍ የሚል የጥበብ ጀግና ነው።

ምሳሌ ልጥቀስ ሙሉቀን መለሰ እጅግ የማከብረውና የማደንቀው፤ለእኔ ከጥላሁን ቀጥሎ ቦታ የምሰጠው ትልቅ ድምጻዊ ነው።ሙሉቀን መለሰ የዜማና የግጥም ደራሲ ባይሆንም እንኳን ዜማንና ግጥም የመምረጥ ችሎታውን ግን አብረውት የሰሩት ይመሰክሩለታል። ይህ ከያኒ በእምነቱ ምክኒያት ከኪነጥበብ መድረክ ከራቀ ከራረመ ታዲያ ለምን መዘመር አልቻለም? መልሱን ለተወዳጁ ድምጻዊ ልተወው።ማለት የፈለግሁት የብዙ ድምጻውያን ህልውና ከዜማና ግጥም ደራሲዎች ጋር የተያያዘ ነው።  ጥሩ ጥሩ ዜማና ግጥም ደራሲዎች ባይኖሩን ኖሮ ብዙዎች ተወዳጅ ድምጻውያንን በዚህ መልክ ላናገኛቸው እንችል ነበር። ቴዲ ከዚህ ጥገኝነት የተላቀቀ ባለተሰጥዖ ድምጻዊ ነው ይህ በራሱ ማስተዋል ላለው እና ከቅናት ለጸዳ አድማጭ ለድንቁ ከያኒ አክብሮት እንዲሰጠው ያደርገዋል።

Related stories   ምርጫውን ለማደናቀፍ ያሴሩ አካላት ህልማቸው አይሳካም – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በመሰረቱ ለአንድ ድምጻዊ መሰረታዊ ነገር ጆሮ ገብ የሆነ ዜማ ማግኘት ነው። በአንድ ዘፈን ወይም መዝሙር ውስጥ ራስ የሚሆነው ዜማ ነው! የአድማጭን ጆሮ የሚቀማ!። እርግጥ ነው ግጥሙም ዜማውም ተመጣጣኝ ጉልበት ቢኖራቸው የተመረጠ ነው ነገርግን ምንም ያክል ጠንካራ፤ የበሰለ ግጥም ቢኖረን ዜማው የተወዛዘፈ ከሆነ ጥሩውን ግጥም ይዞት ይሞታል። በአንጻሩ ደግሞ ግጥሙ ያንን ያክል እንኳን የበሰለም ባይሆን ጆሮ ገብ ዜማ ካገኘ ደካማው ግጥም ይነሳል። የቴዲ አፍሮ የግጥምና ዜማ ስራዎች ግን በሁሉም መልኩ ደረጃቸውን የጠበቁ፤በአንጣጣሪ አልሞ ተኳሾች እየሞተ ያለውን ሙያ በዘርፉ ደግፈው የያዙ ባላዎች ናቸው።

እርግጥ ነው  ከቅኝቶቻችን ወርደ ጠባብነት የተነሳ ማለትም የዜማዎቻችን መነሻ ባለ አምስት ድምጽ  ማለትም ነጮቹ ፔንታቶኒክ ስኬል የሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው። ይህ እስኬል ወደ ሃገረኛው ሲመለስ አምባሰል፤ ትዝታ፤ አንችሆዬ እና ባቲ ተብለው ይመነዘራሉ እነዚህንም ወደ ሜጀርና ማይነር ስንመልሳቸው ስምንት ዓይነት ቅኝት ይኖራቸዋል። ያም ሆኖ ግን አሁንም ወርደ ጠባብነት ይታይባቸዋል በዚህም ምክኒያት የዜማ የመመሳሰል ችግር ሊገጥመን ይችላል።

እስራኤሎች ከሃያ ከሰላሳ አመት በፊት ዜማዎቻቸው በፔንታቶኒክ ስኬል ውስጥ የሚንከባለሉ ነበሩ አሁን ግን በሙዚቃ ልሂቆቻቸው ጥንካሬ ወደባህሩ ዲያቶኒክ ስኬል ውስጥ ገብተው ከምስራቅ ምዕራብ የተራራቁ ዜማዎችን እየሰሩ ነው። በእኛም ሁኔታ ወደፊት እንደሃገር የሙዚቃ ሙያተኞቻችን ሙያቸውን እንደሙያ የሚያከብርና የሚያሰራ ምህዳር ሲያገኙ ተሰባሰበው መሰራት ያለባቸው ታላቅ የቤት ስራ አለ ብዬ አምናለሁ ። ይሁን እንጅ ችግሩ በሃገር ደረጃ እስኪፈታ የዜማ የመመሳሰል ሁኔታ በስራው መሃከል እንዳይፈጠር ቴዲ ብዙ መስራት፤ ብዙ መድከም ይጠበቅበታል። በዚህ በኩል ደግሞ ቴዲ አፍሮን ብዙ ችግር ይገጥመዋል ብዬ አልሰጋም ምክኒያቱም ብዙዎችን ከመሰመር የሚያስወጣው፤ ከደረጃ የሚያወርደው የስነ-ምግባር ችግር ቴዲ ላይ አልሰለጠነም አይታይምም። ቴዎድሮስ ፀጋይ ግን ቴዲ አፍሮን ቁጭ ብሎ መስራት፤ ማንበብ እንደማይችል የዚህንም ምክኒያት በውስጠ አዋቂነት ጠንቅቆ እንደሚያውቀው ነግሮናል እኛም አንድ ጥያቄ እናቅርብ  ተወዳጁ ቴዲ ጊዜ ወስዶ ካልሰራ እነዚህን የመሳሰሉ ድንቅ ስራዎች በአስማት አወረዳቸው እንበል? ለነገሩ ቴዲ እግዚአብሄር አምላኩን በንጽህና የሚያመልክ ትሁት ሰው ነው።Related image

በመጨረሻም ለተወዳጁ የኪነጥበብ ሰው ለቴዲ አፍሮ ያለኝ መልዕክት ነቃፊዎችህ ለተንጨረጨሩበት ደጋፊዎችህ ደግሞ ሃሴት ላደረጉበት “ኢትዬጵያ” ለሚለው ድንቅ ስራህ ከመደመም በቀር ምን ልበል? ከታሪኳ ዘግነህ፤ከመለኮታዊው ሃሳብ አጣቅሰህ፤ከተኛንበት ልታነቃን ፤ውለታዋን ልታሳስበን፤ ሌማቷ ሙሉ ይሁን ባርከህ፤ በማህሌተ ዜማ አዋዝተህ ከጥበብህ ዓለም ወደ እኛ ላቀረብከው ሃገር አድማቂ ጥሪ እኛም አብረንህ እንላለን ኢትዬጵያ፤ ኢትዬጵያ፤ኢትዬጵያ፤ኢትዬጵያ…

 ነጋ አባተ (ዋሺንግተን ዲሲ)