ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ዶ/ር መረራ ጉዲና የቀረበባቸው ክስ እውነትነት የሌለውና ተጣሞ የቀረበ ነው አሉ

የአገሪቱን የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ማለትም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ)፣ 38(1)፣ 27(1)፣ 238(1ሀ እና ለ)ን በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በመባል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የቀረበባቸው ክስ እውነትነት የሌለውና ተጣሞ የቀረበ መሆኑን ለፍርድ ቤት ገለጹ፡፡

ዶ/ር መረራ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቀረቡባቸው ክሶች ላይ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረቡት የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ላይ እንደገለጹት፣ በተጠርጠሩበት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 01/2009ን የመተላለፍ ወንጀል በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) በቆዩበት ወቅት የሰጡት ቃል፣ ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ ላይ ተጣሞ ከመቅረቡም በላይ ተቆራርጦ መቅረቡንና ሙሉ ቃላቸው አልቀረበም፡፡

Related stories   “በተለምዶ ‘ሸኔ’ የሚባለው ራሱን ‘የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት’ ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው”

አብረዋቸው ከተከሰሱት አቶ ጀዋር መሐመድ ጋር በኢሜይል ሐሳብ እንደተለዋወጡ የሚጠቀስ ክስ የቀረበባቸው ቢሆንም፣ እሳቸው በኢሜይል የሰጡት ምላሽ ትክክለኛው በክሱ ውስጥ አለመካተቱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም እሳቸውን ለመጉዳት ተቆራርጦ የቀረበው ኢሜይል በሙሉና በአግባቡ ተተርጉሞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ዶ/ር መረራ በቅድመ ክስ መቃወሚያቸው ላይ ጨምረው እንዳስረዱት፣ በኦሮሞ የጥናት ማኅበር (OSA) ላይ ያቀረቡት የእንግሊዝኛ ጽሑፍ እጅግ ሰላማዊና ችግር ፈቺ ጽሑፍ ነው፡፡ የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች የፖለቲካ መፍትሔ አመላካችና በሰላማዊ ውይይት፣ በድርድር፣ በበጎና በቅን መንፈስ መፍታት የሚጠቁመውን ጥናታዊ ጽሑፍ መደምደሚያ ሆን ተብሎ ተቆርጦ መውጣቱ እጅግ በጣም እንዳሳዘናቸው አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ሌላው ያቀረቡት መቃወሚያ፣ በሌሉበት ክስ ከተመሠረተባቸው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሐመድ ጋር አንድ ላይ መከሰሳቸውን ነው፡፡ እንደ ዶ/ር መረራ መቃወሚያ፣ ከዶ/ር ብርሃኑም ጋር ሆነ ከአቶ ጀዋር ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት የድርጅት ቅንጅታዊ መስተጋብርም ሆነ መንገድ ጨርሶ የለም፡፡ ድርጅታዊ ቁርኝትንም የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ ከክሱ ጋር ተያይዞ አልቀረበም፡፡ በመሆኑም በጋራ የቀረበባቸው የክስ ጭብጥ ስለሌለ ክሳቸው ተነጥሎ ለብቻቸው እንዲታይና የፍትሕ ሒደቱም ተፋጥኖ እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡

Related stories   በቡድን ተደራጅተው የውንብድና ወንጀል የፈጸሙት ተከሳሾች ከ18 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ፡፡

ዶ/ር መረራ አገራቸውን በተሰማሩበት የሥራ መስክ ከ40 ዓመታት በላይ ከመርዳት ባለፈ፣ ሊያስከስሳቸው የሚችል ተግባር የፈጸሙ ወይም የሚፈጽሙ ባለመሆናቸው ክሳቸው ተነጥሎ መታየት ብቻ ሳይሆን፣ ውድቅ ተደርጎ በነፃ እንዲሰናበቱም ጠይቀዋል፡፡ ክሱን በዋናነት የሚቃወሙት በወንጀል መከላከል ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130(1፣ 2፣ መ እና ሰ) መሠረት ሲሆን፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 111(1ሐ) እና 112ን አለማሟላቱን በመግለጽ መሆኑን በመቃወሚያቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

Related stories   በቡድን ተደራጅተው የውንብድና ወንጀል የፈጸሙት ተከሳሾች ከ18 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ፡፡

ከዶ/ር ብርሃኑና ከአቶ ጀዋር ጋር በጋራ ወንጀል እንደሠሩ በክሱ የተጠቆመ ቢሆንም መቼ አብረው የወንጀሉ ተካፋይ እንደሆኑ፣ ቀን፣ ወርና ዓ.ም. ተለይቶ አለመገለጹን አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ ክሱ የተሟላ ባለመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ 11 ገጽ የቅድመ መቃወሚያ ዝርዝር ማመልከቻቸውን ተቀብሎ፣ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ እንዲሰጥበት ለሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ ሪፖርተር

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0
Read previous post:
ንግድ ባንክ የፕሮጀክት ብድሮችን ወደ ልማት ባንክ ማዞሩ ድንጋጤ ፈጠረ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለግል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆኑ የብድር ጥያቄዎችን እንደማያስተናግድ ያስተላለፈው ውሳኔ ድንጋጤ ፈጠረ፡፡...

Close