“Our true nationality is mankind.”H.G.

ሕወሀት፣ኢህአዴግና የኤርትራ ጉዳይ አዲስ ፖሊሲ ወይስ አዲስ ራዕይ?

መግቢያ

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማሪያም ሁመራ አካባቢ ብቅ ብለው ባደረጉት ንግግር በኤርትራ ላይ ድርጅታቸውና መንግስታቸው ይዘውት የቆዩት ፖሊሲ የተፈለገውን ውጤት ባለማስገኘቱ በቅርቡ አዲስ ፖሊሲ ነድፈው ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ገልጠው ነበር። ከዚያም በመቀጠል የተለያዩ ስርእቱን የሚደግፉም የሚቃወሙም ጸሐፊዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን አካፍለዋል፡፡

ስርአቱ የተነገረለትን “አዲስ ፖሊሲ “ ለመንደፍ የተለያዩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን  አስተሳሰብ እንደግብአት ወስዶ ፖሊሲውን ይቀርጻል ለማለት የሚያሰችል ታሪክ የለውምና አሁንም ይህ ይሆናል  ብሎ መጠበቅ ጉም እንደመጨበጥ የሚቆጠር እንደሆነ የሚገመት ነው።

በኔ በኩል አሁን ባለንበት ሁኔታ  “አዲስ ፖሊሲ” መንደፍን በተመለከተ ግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው  ጥቂት መሰረታዊ ነጥቦችን ለማንሳት አሻለሁ።

የኤርትራ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ  ስለሆነ የህዝብ ድምጽ መደመጥ አለበት

የኤርትራ ጉዳይ ሲነሳ በዋናነት የምንነጋገረው ስለሀገራችንና ህዝባችን  አንድነት እንዲሁም የሀገራችን ደህንነትና ኢኮኖሚ ላይ ታላቅ ቦታ ስለሚኖረው የኢትዮጵያ ታሪካዊና ህጋዊ የባህር በር ባለቤትንት ጭምር እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው። በዚህ አይነት ታላቅ ሀገራዊ ጥያቄ ላይ የሚወሰድ እርምጃም ያንድ ድርጅትን የፖለቲካ ፕሮግራም የሚያንጸባርቅ ሳይሆን ባጠቃላይ የባለድርሻዎችን አመለካከት ያካተተ መሆን ይኖርበታል።

ኤርትራን ለሻቢያ ያሰረከበው ሂደት የህወሀት/ኢህአዴግን የፖለቲካ ፕሮግራም መሰረት አድርጎ የተነደፈና በጥድፊያ የተከናወነ ተግባር እንደነበር ዛሬ የህወሀት/ኢህአዴግ አባላት ሳይቀሩ የሚቀበሉት እውነታ ሆኗል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደህዝብ በሁኔታው ላይ አስተያየቱ በምንም መልክ እንዲንጸባረቅ አልተደረገም። ህወሀት ኢህአዴግ ምን እንደሚያደርግ ሲወስን የህዝቡን ድምጽ በምንም መልኩ ይሁን ቦታ ሳይሰጥ ነበር።  በመሆኑ እስከ አሁኗ ሳአት ድረስ ከኢትየጵያ ህዝብ ታላቅ ቅሬታና ተቃውሞ እንደገጠመውና  ህወሀት/ኢህአዴግም በቀላሉ ሊላቀቀው ያልቻለው ትልቅ ጠባሳ ሆኖበት እንደቀጠለ ይታያል።

አንዳንድ የህወሀት/ ኢህአዴግ ደጋፊወች ቀደም ያሉት የኢትዮጽያ መንግስታት አጼ ቴወድሮስ፣ አጼ ዮሀንስ፣ አጼ ምንሊክ ቀዳማዊ ሀይለስላሴና ሊቀመንበር መንግስቱ የወሰዷቸውን ዋና ዋና እርምጃወች ሲወስዱ ህዝብን አማክረው አልነበረም። ስለዚህ ህወሀት/ኢህአዴግም አዲስ ነገር ሊጠበቅበት አይገባም የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይደመጣል። ይህ ታላቅ ስህተት ነው፣ ዛሬ ያለው ሁኔታና በዘመነ ነገስታቱ የነበረው ሁኔታ አንድ አይደሉም፣፡ የህዝብ የፖለቲካ ንቃትም አንድ አይደለም፣ ጊዜው ተለውጧል። ዛሬ ባለንበት ክፍለ ዘመን አዲስ እስተዳደርና አዲስ አይነት የህዝብ ባለቤትነት የግድ ነው። ህዝብ በሀገሩና በመብቱ ጉዳይ ላይ መደመጥ ይፈልጋል፣ የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተም የጉዳዩ ባለቤትም ህዝብ እንጂ አንድ ድርጅት አይደለም።

ስለዚህ የመጀመሪያው እርምጃ ራስን ከሚመስሉ ጋር ደግሞ ደጋግሞ መነጋገሩን አቁሞ ሌሎች ባለድርሻወችን፣ አዋቂዎችን፣ ብዙ ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ዜጎችን ማዳመጥ ነው። የኢትዩጵያን እስትራተጂያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ምን መደረግ አለበት ብሎ በቅን መንፈስ መጠየቅ፣ ማዳመጥና የሚሰነዘሩ አስተያየቶችንም በፖሊሲው ውስጥ ለማካተት መዘጋጀት ያሻል።

የህዝብን ድምጽ ሳያዳምጥ መቀጠልን ከመረጠ የህወሀት/ኢህአዴግ የኤርትራ ፖሊሲው ላለፉት 26 አመታት በኢትዪጵያ ህዝበ  (የህወሀት/ኢህአዴግ ደጋፊወች ጨምሮ) ተቀባይነት እንዳጣ እንደሚቀጥል ማመዛዘን ተገቢ ነው። በህዝብ ተቀባይነት የሌለው ፖሊሲ ደግሞ እንኳንስ በሌሎች መንግስታት ላይ ውጤት ያለው ተጽእኖ ሊያመጣ፣ የሚኖረው ዋጋ ከተጻፈበት ወረቀት ዋጋ ሊበልጥ መቻሉ አጠራጣሪ ነው።

Related stories   ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

አዲስ ፖሊሲ መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ከአዲስ ራዕይ መመንጨት ይኖርበታል

የህወሀት/ኢህአዴግ የኤርትራ ፖሊሲ የሕወሀት የትጥቅ ትግል ጊዜ እስትራተጂ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። የራዕይ መሰረቱ የኢትዮጵያንና የህዝቧን ረዥም ውስብስብና ጥልቅ ታሪክ በበቂ ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን የሚከተለውን ጽንፈኛ የግራ ርእዮተአለም እንደወረደ በጥሬው የተቀበለም ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ የራሱን ብሄረተኛ ትግል ጥንካሬ የመስጠትና በትግሉ ወቅትም ኤርትራን መሰረት ካደረጉ ተቃዋሚወች (ሻአቢያና ጀበሀ ) ሊያገኝ የሚችለውን ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና  ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞች ማጠናከርን እሳቤ ውስጥ ያስገባ ነበር።

ከደርግ መወገድ ጋር ተያይዞ ህወሀት ከትግራይ አልፎ መላ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር እድሉ ባጋጠመው ጊዜም ቀደም ካለው ከትግል ጊዜ አስተሳሰብና እስትራተጂ ያልተላቀቀ “ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነች ለነጻነት ስለታገሉም የመገንጠል መብታቸው መጠበቅ ይኖርበታል” ወዘተ የሚል ግልብ አስተሳሰብና ፖሊሲን ነው ተግባራዊ አድርጎ የኢትዮጵያን ጥቅም ቦታ ሳይሰጥ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ያመቻቸው።

ይህ ደግሞ ላለፉት 26 አመታት ሀገራችን እየጎዳ ስርአቱንም ባለበት እንዲረግጥ እያደረገው እንደሆነ እንመለከታለን። ይህን የከሽፈ አመለካከት አሁንም መሰረት እድርጎ መጓዝ ሀገራችንን በገባችበት አዙሪት ውስጥ ከመሽከርከር ውጪ ከአረንቋ ሊያወጣት ከቶውንም አይችልም።

ሀገራችን በተተበተበችበት የርእዮተአለምና ያመለካከት አረንቋ ውስጥ ስትማስን በኤርትራ፣ በሶማሊያ፤ በጅቡቲ፣ በደቡብ ሱዳንና ሌሎችም ያካባቢው ሀገሮች የሚገኘው የባእዳን የጦር ካምፕ ግንባታው፣ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከበባና  እምቅ የጣልቃገብነት አደጋ ወዘተ እጅግ ፈጣን በሆነ መልክ እየተቀየረ ይገኛል። የሚገርመው ግና አሁንም ይህን አይን ስር የሚታይ አደጋ በትክክል ለመቀበል አለመቻልና ማቅማማት በሰፊው የሚታይ መሆኑ ነው።

ኢትዮጵያ ከገባችበት ማጥ እንድትወጣ ከተፈለገ አዲስ ራዕይን መሰረት በማድረግ  ያለፈውን ስህትት በትክክል ማገናዘብና እንደገና ላለመድገም በቆራጥነት መወሰን ያሻል። ይህ ባልሆነበት፣ ግልጽ የሆነ የግንዛቤና የራእይ ለውጥ በሌለበት ሁኔታ የሚነደፍ  ፖሊሲ አርቆ ማሰብ የተሳነው፣ ግራ የተጋባ፣ የተምታታ ጉዞና ተጨማሪ ስህተት የሚጋብዝ እርምጃ ከመሆን ብዙም አያልፍም ።

ይህ ደግሞ እጅግ እየተለዋወጠ በሚገኘው ያካባቢያችን ሁኔታ ውስጥ የሀገራችንን ጥቅም በተመለከተ አሁን ካለው ሁኔታ በባሰ  ጉዳት ላይ ሊጥላት ይችላል።

ስለዚህ ጠርዝ ላይ ከደረሰው ጎጂና ጊዜ ያለፈበት  እይታ መላቀቅ  የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይገባል።

አዲሱ ፖሊሲ  ያለማመንታት የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል

የህወሀት/ኢህአዴግ የኤርትራ ፖሊሲ ከህዝብና ተቃዋሚ ፖሊቲካ ፓርቲወች የሚደርስበት ተቃውሞ፣ አንዱና ዋናው ምክንያት የሀገራችንንና የህዝባችንን ጥቅም ያላስጠበቀ መሆኑ ነው።

ከመጀመሪያው ስህተቱ በተጨማሪም ከአንድም ሁለት ጊዜ በተፈጠሩት አመች ሁኔታወች ተጠቅሞ የሀገራችንን ጥቅም ለመረጋገጥ ከመጣር ይልቅ የሕወሀት/ኢህአዴግ መሪዎች በደርግ መወገድ ማግስት፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትና በአልጀርሱ ድርድር በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ አጋዥ የነበረውን ሁኔታ ህወሀት/ኢህአዴጎች ሳይጠቀሙበት ለሻቢያ አሳልፈው ሰጥተዋል። በመሆኑም በብዙወች ግንዛቤ የህወሀት/ኢህአዴግ ፖሊሲ በዋናነት የኢትዮጵያን ሳይሆን የሻአቢያን (የኤርትራን) ጥቅም ማስጠበቅን መሰረት ያደረገ ነበር።

Related stories   "አንድ ሰዉ መላ አካላቱን ሰውቶ እምብርቱን ብቻ በማዳን እንዴት ህልውናን ያረጋግጣል" Taye Dendea

ይህን ጉዳይ ለመፍታት ደግሞ የዚህ አይነቱን ተደጋጋሚ የሀገራችንን ጥቅም የሚጻረር እርምጃን ማስወገድ ያሰፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ወደፊት በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ሁሉ የኢትዮጵያን እስትራተጂያዊ ጠቀሜታ የሚያስጠብቅ እርምጃን መውሰድ ይጠይቃል።

በዚህ አኳያ አዲሱ ፖሊሲ ቁልፍ የሆኑ ኢትዮጽያ ማግኝት ያለባትን ዋና ዋና ጉዳዮች ለይቶ ያስቀመጠና በዚያም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ውጤት ለማግኝት  የቆረጠ እንዲሆን ያሰፈልጋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የተወሰዱ እርምጃወች ያሰከተሉትን የኢትዮጵያን የባህር በር መብት ማሰከበር፣ የአፋርን ህዝብ ድምጽና ፍላጎት  እውን ማድረግ ፣ የኢሮብና ኩናማ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ላይ ያንዣበበውን አደጋ  ማስወገድ  ጥቂቶቹ ናቸው።

በርግጥ የእያንዳንዱ ግብ እንዲሳካ የሚደረግበት አካሄድ ወይም የተግባራዊነት ዝርዝር የተለያየ መልክ ሊኖረው ይችላል ለምሳሌ ምን ያህል ኪሎሜትር ስፋት ያለው የባህር በር ነው ለኢትዮጵያ የሚገባት፣ የት አካባቢ?  ኢትዮጵያስ በምላሽ ምን ማበረታቻ መስጠት ይገባታል ወዘተ የሚለው አብሮ የሚታይ ነው፡፡ ዋናው ግን ሀገራችን ኢትዮጵያ ማግኝት የሚገባትንና  ልንሰጥ የማይገባነነም ቁልፍ ጉዳይ ለይቶ ማወቅ ይህንንም ማእከል ያደረገ ፖሊሲና እርምጃን ተግባራዊ ማድረግ ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ለወዳጅነትና ለአካባቢያዊ መረጋጋት መቆም አስፈላጊ መሆኑን አጥብቆ ከማናገርና ተግባረዊ ከማድረግ በተጨማሪ የሀገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ ግን ማንኛውም አማራጭ ከግንዛቤ ውጭ አንደማይሆን ማወቅ እንዲሁም የሀገርን ጥቅም ለመጠበቅ አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈልም መዘጋጀት ተገቢ ነው።

ቋሚና መሰረታዊ  መረጋጋት መሰረቱ የህዝብን መብት ማክበር ፣ እንዲሁም እውነተኛ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ብቻ ነው

የስርአቱ ባለስልጣኖች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሚደመጠው አንዱና ትልቁ ጭንቀታቸው ሻአቢያ ለተቃዋሚ ድርጅቶች የሚሰጠው ከለላና ድጋፍ ነው። የአዲስ ፖሊሲ ፍላጎት ሩጫውም ይህንኑ ጭንቃቸውን ለማስተንፈስና ተቃውሞውንም ለማዳከም የሚደረገው ሙከራ አንዱ አካል አንደሆነ በተለያየ መልክ ሲገልጹ ተሰምቷል።

ይህ አመለካከት የተቃውሞውን መሰረት በትክክል ያላገናዘበ፣ መሬት ያልረገጠ  ወይም እውነታውን መቀበል ያልቻለ ነው።

በስርአቱ ላይ ያለው ተቃውሞ በዋናነት ከስርአቱ የፖለቲካ አቋምና በህዝቡ ላይ ከሚያደርሰው በደል የሚመነጭ ነው ።

ለዚህ ደግሞ  ላለፉት 26 አመታት የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መረገጥ፣ የህግ የበላይነት መጥፋት፣ የነጻ ድርጅቶች መታፈን ፣ የመሬት ነጠቃ፣ ተስፋ ያጣው የወጣቱ  ህይወት ፣ የፖለቲካ እስረኞች ላይ እየደረሰ ያለው ግርፋት ስቃይ፣ አስጸያፊ ተግባር ፣ የሀገር ሀብት ምዝበራው ንቅዘቱ ወዘተ በግልጽ የሚታዩ ናቸው።

በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚታየው ተቃውሞም እጅግ ብዙው ከአስመራ የሚነሳ ወይም ደግሞ በሻቢያም ሆነ በሌሎች የውጭ ሀይሎች የተፈጠረና የሚዘወር  ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ መሰረት አድርጎ የተነሳና  የሚንቀሳቀስ ነው።

ጥቂቱን ለማንሳት በ1997 ስርአቱን በካርድ ያሸነፈው ካስመራ የተነሳ ሀይል ሳይሆን እዚያው ሀገር ውስጥ ያለው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ። የአንድነት ፓርቲ፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የመኢአድ የኦፌኮ የመድረክ የሽንጎ እንቅስቃሴ ከአስመራ ጋር የሚያገናኝው  ምንም ጉዳይ የለም።

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ላለፈው ሁለት አመታት ጎልቶ እየታየ ያለው የጎንደርና የጎጃም ህዝብ ንቅናቄ ፣ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ፣ በጋምቤላ የመሬት ነጠቃን መሰረት ያደረገው ተቃውሞ፣ የኦሮሞ ወጣቶች የተቃውሞ ሰልፎች፣ የኮንሶ ህዝብ ተቃውሞ፣ መቀሌ፣ አዲግራትና ደሴ ውስጥ የታየው ተቃውሞ ወዘተ ከሻቢያ ጋር የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ የለም። ይህ ሲባል ሽአቢያ በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጽያን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ውስጥ እጁን ለማስገባት አይሯሯጥም ማለት አይደለም።

ይህ ደግሞ ተቃዋሚወቸች የሚናገሩት ብቻ ሳይሆን የስርአቱ ቱባ ቱባ ባለስልጣኖች ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ በተለያየ ጊዜ ከላይ የተጠቀሰውን የስርአቱን ብልሹነት ማመናቸውን ከራሳቸው አንደበት ተደምጧል። ከስርአቱ የተገለሉ የቀድሞ ባለስላጣኖት ሁሉ (ጠቅላይ ሚኒስቴር ታምራት ላይኔ፣ ፕሬዚደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የመከላከያ ሚኒስቴሩ አቶ ሰየ አብርሃ፣ የኦሮሚያው ፕሬዚደንት አቶ ጁነዲን ሰዶ፣ የትግራዩ ፕሬዚደንት አቶ ገብሩ አስራት፣ የህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣን ወይዘሮ አረጋሽ አዳነ ወዘተ) ተራ በተራ የነገሩንም ይህንኑ ሀቅ ነው። ታዲያ የዚህ አይነት እውነታ በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ዜጎች ለመብታቸው መታገላቸውና ራአያቸውንም እውን ለማድረግ የተለያየ የትግል ስልት ቢመርጡ ምን ያሰገርማል?

ስርአቱ እያደገና እየተወሳሰበ ለመጣው የፖለቲካ ተቃውሞ መፍትሄ ከፈለገ ቁልፉ በራሱ በስርአቱ እጁ ላይ እንደሚገንኝ መገንዘብ ይኖርበታል።

መፍትሄው የአስመራውን መንግስት ወይም ሌሎች መንግስታትን በተቃዋሚወች ላይ ጀርባቸውን እንዲያዞር ለማባበል ወይም ለማሰገደድ መሯሯጥ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብና የተቃዋሚወችን ጥያቄ ባግባቡ መመለስ ነው። የሽአቢያ ድጋፍ ኖረም አልኖረም ስርአቱ መሰረታዊ ለውጥ እስካላደረገ ድረስ ተቃውሞው ይቀጥላል። የህዝብ ቁጣም በተለያየ መልክ ይገለጣል። ከዚህ ውጭ የሆነ ሁኔታን ማሰብ በምናብ አለም ውስጥ ከመኖርና የስሜት ፈረስን ከመጋለብ ውጭ አይሆንም።

ከሁለትና ሶስት ሳምንታት በፊት ከኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ኢሳያስ አፈወርቂ የባለ ብዙ አመታት አኩሪ ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን  “ልብ ወለድ አፈ ታሪክ “ ሲል ነው የገለጣት፣፡ ታዲያ ይህ ሰው ለኢትዮጵያ ምን መልካም ነገር ሊያስብ ይችላል?

ማንኛውም ድርጅት የሚወስደውን ምርጫ ማክበሬ እንደተጠበቀ ሆኖ፤  በኔ አመለካከት የአስመራ ድጋፍ ለተቃዋሚው ጉዳት እንጂ ብዙም ጠቀሜታ የለውም። ከሻአቢያ አይነቱ ጸረ ኢትዮጵያ ሀይል የተላቀቀ ሀገር በቀል ተቃውሞ  ነው ለነፃነታችንና ላንድነታችን መሰረት የሚሆነው።ተቃዋሚወች ይሀን ከስርአቱ ባለስልጣኖች በተሻለ ሁኔታ ያውቃሉ።

ባጠቃላይ ስርአቱ የ26 አመት የጥፋትና የከሸፈ ጉዞውን እንዲያበቃ ሁሉም ዜጋ አስፈላጊውን ተጽእኖ ማድረግ ይኖርበታል። ስህተትን ለማረም ደግሞ ደጋግሞ ጥሩ አጋጣሚ አይገኝም። በጥንቃቄ ካልያዙት ሀገርም እንደሰው እግር አውጥቶ እንደሚሄድ ግልጽ ነው።

አስተያየት ቢኖርወት በሚከተለው አድራሻ ይላኩ

(አክሊሉ ወንድአፈረው)

ethioandenet@bell.net

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0