ኢትዮጵያዊነት በአንጻረ ጎሰኝነት

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ

“ቴዎድሮስ ካሳሁንን እና ሙዚቃውን ለምን ህዝብ ይወዳቸዋል?” ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ “እሱ እና ሙዚቃው ኢትዮጵያዊነትን ስለሚዘምሩ ነው፤” የሚል ነው። በሌላ አነጋገር፥ ጎሰኝነትን ስለማያራምዱ ነው።

ባለፉት 48 ዐመታት በተማሪዎች ቆስቋሽነት የተጀመረው ጎሰኝነት ባለፉት 25 ዐመታት እንደ ሰደድ እሳት ተዛምቶ፥ በኢትዮጵያዊነት ላይ የማያቋርጥ ዘመቻ አካሂዶ፥ ኢትዮጵያዊነት ጨርሶ አለማክተሙ እና ማንሰራራቱ የሚያስገርም ነው። ኢትዮጵያዊነትን ለሚጠሉ ደግሞ አስደንጋጭ መርዶ ነው። እውነት ይህን ያህል ህዝብ ጎሰኝነት አንገፈገፈኝ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን ናፍቋልን? መልሱ አዎንታዊ ይመስላል።

በእርግጥም ኢትዮጵያን ሊያድናት የሚችለው ኢዮዬጵያዊነት ነው። ለመሆኑ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ምንድነው? ኢትዮጽያስ ለምን ኢትዮጵያ ተባለች? ኢትዮጵያ ማለት በሱባ (ከግእዝ በፊት የነበረ የጥንት ወገኖቻችን ቋንቋ) ብጫ ወርቅ ስጦታ (ለእግዚአብሄር) ማለት ነው። የዛሬ 4000 ዐመት የኖረው የንጉሥ ንጉሥ የካህን ካህን በመሆን ዐለማዊና መለኮታዊ ማእረግ የነበረው አባታችን ኢትዮጵ በዚህ ስም ይጠራ ስለ ነበር ሀገሪቱን ኢትዮጵያ አሰኛት። የኢትዮጵያን ስልጣኔ ልጆቹ በመላው አፍሪካ በማዳረሳቸው እስከዛሬ 600 ዐመት ድረስ መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ ይባል ነበር። አሁንም በኢትዮጵያውያን አፋሮቻችን ምክንያት አፍሪካ ይባላል። ዞሮ ዞሮ ከእኛ ስም አልወጣም።

ኢትዮጵ 10 ወንዶች ልጆች ወልዶ 10ስሩ ተባዝተው ዛሬ ሁላችንም ከነሱ ተገኘን። ስለዚህ በእያንዳንዳችን ደም ስር ውስጥ የኢትዮጵ ደም እየፈሰሰ ሁላችንንም እዛምዶናል ማለት ነው። ትውልደ ኢትዮጵያ የሆንን ሰዎች ሁሉ ወደድንም ጠላንም አመንን አላመንም፣ እውስጣችን የእዚህ ትልቅ ሰው እና የክብርት ሚስቱ የንግሥት እንቁዮያጳግዮን ደም ይፈስሳል። ይህም እጅግ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም። ይህን የማይቀበል ክቡር እና ግዙፍ የሆነውን ማንነቱን የማያውቅ ብቻ ነው። ወይም በፓለቲካ ልቦናውን የታወረ ነው።

ጎሳስ ምንድነው? ጎሳ አንድ ቋንቋ የሚየናገሩ ሰዎች ማለት ነው። ዘርፉ ከቋንቋ እንጂ ከዘር አይደለም። የአማራ ወይም የኦሮሞ ጎሳ ማለት አማርኛ ወይም ኦሮምኛ የሚናገር ሰው ማለት እንጂ ዘሩን አይጠቁምም። ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ ብቻ ነው እንጂ በደም የሚያገናኝ አይደለም። በደም፥ ያው ከፍ ብዬ እንዳልኩት የኢትዮጵ ልጆች ነን። ኢትዮጵያ ውስጥ 82 ቋንቋዎች ተናጋሪዎች አሉ። በዘራቸው ግን አንድ ናቸው። የመነጩት ከኢትዮጵ ደም ነውና። ስለዚህ ሁሉንም ትውልደ ኢዮያጵያውያንን በስጋ የሚመያዛምዳቸው ኢዮዮጵ ነው እንጂ ቋንቋው አይደለም። የዚህን ዝርዝር ለማየት “የኦሮሞ እና አማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የተሰኘውን መጽሀፌን መመልከት ይጠቅማል።

እንግዲህ ኢትዮጵያዊነትን በአሁኑ ሰዐት ሰው ሁሉ የፈለገው ውስጡ ያለው ደመነፍስ ኢዮጵያዊነቱን ስለ አረጋገጠለትና ጎሰኝነት ዋጋቢስ መሆኑን ስለተገነዘበ ነው። ከአሁን በኋላ ኢዮጵያዊነት ለምልሞ ያብባል እንጂ ጠውልጎ አይደርቅም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *