ኢህአዴግ በሁለተኛው መንታ መንገድ ላይ

ከቻይና ጋር የጀመሩት መወዳጀት ሥር ሰድዶ በሁለት እግሩ ከመቆሙ በፊት አቶ መለስ በሞት ከተለዩ በኋላ የኢህአዴግና የቻይና ግንኙነት በርካታ መንታ መንገዶች እየገጠሙት መጥተዋል፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ገንዘብ በበጀት ድጎማም ሆነ በዕርዳታ የሚሠጠው ኢህአዴግ ምዕራባውያን ከቻይና ጋር ካላቸው ፍጥጫ አንጻር እየገባበት ያለው አጣብቂኝ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ “ምርጫው በምርጫ” እየተወሳሰበበት የመጣው ኢህአዴግ በአንድ በኩል የአሜሪካንን ፍላጎትና ጥያቄ መፈጸምና ማስፈጸም፤ በሌላ በኩል ደግሞ አፈናውን ለማጠናከርና የግዛት ዘመኑን ለማርዘም ከቻይና የሚያገኘው በቅድመ ሁኔታ ያልታሰረ “ጥቅም” በሁለት ጽንፍ ወጥረውታል፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ “ወጣሪ” ብቅ ብሎ በመንታው መንገድ ላይ ሌላ መንታ ፈጥሮበታል – ጃፓን!

ቻይና በተለይ በአፍሪካ እያደረገች ያለችው የንግድ እንቅስቃሴና ኢንቨስትመንት የምዕራባውያንን ዓይን ከሳበ ቆይቶዋል፡፡ በተለያዩ ሰበቦችም የቻይናን እንቅስቃሴ ለመሰለል ምዕራባውያን በግልጽ መረጃ ከመሰብሰብ እስከ ወታደራዊ ተ  ቋማት መገንባት ከዚያም አልፎ በቻይና “ፍቅር” ተለክፈው እንቅፋት የሆኑባቸውን እስከ “ማስወገድ” ዓላማቸውን ሲያሳኩ ቆይተዋል፤ አሁንም እያደረጉት ይገኛሉ፡፡

በጂኦግራፊዊ አቀማመጥ ምስራቃዊ ከመሆን በስተቀር የምዕራቡ ዓለም አካል የሆነችው ጃፓን፤ የቻይናን ሁኔታ በቅርብ ስትከታተል ቆይታለች፡፡ በተለይ ሁለቱ አገራት ካላቸው ታሪካዊ ጥላቻ አኳያ ጃፓን ቻይናን በማሳደዱ ተግባር ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሆና እስከ አፍሪካ ዘልቃለች፡፡abe and abe

በቅርቡ የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር ሺንዞ አቤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት “የሁለቱ አገራት የቆየ ግንኙነት …” ብሎ ኢቲቪ እንደዘገበው የቀለለና ጥሩ የፎቶ ዕድል ፈጥሮ ያለፈ ብቻ አይደለም፡፡ ቀልደኛው የጃፓን መሪ አቤ “ትምህርት ቤት ሳለሁ ልጆች ሁሉ አበበ እያሉ ይቀልዱብኝ” ነበር እንዳሉትና የሻምበል አበበ ቢቂላን ፎቶ ተሸልመው የሄዱበት የመዝናኛ ጉብኝትም አልነበረም፡፡ ጠ/ሚ/ር አቤ አህጉር አቋርጠው የመጡት ለሌላ ጉዳይ ነው – ቻይና!!! ተያይዞም ከምዕራባውያን ጋር የተገመደ ወታደራዊ የበላይነት በአፍሪካ!

ጃፓን “ተለውጣለች”

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ “ሰላማዊነት” መመሪያዋ አድርጋ ለዘመናት የቆየችው ጃፓን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በውጭ ፖሊሲዋ ላይ ለውጦችን አካሂዳለች፡፡ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሕገመንግሥቷ አንቀጽ 9 እንደሚለው ጃፓን ሰላማዊ መንገድን የምትከተል፤ በሌሎች አገራት ጣልቃ የማትገባ ብቻ ሳትሆን ድርጊቱን “ለዘላለም የምታወግዝ”፤ ዓለምአቀፍ ግጭቶችን ለማስወገድ የጦርነት እርምጃ በጭራሽ የማትወስድ አገር መሆኗን ያስረዳል፡፡ ሲቀጥልም የጦርነት እርምጃው በምድር፣ በባህር እና በአየር የሚደረገውን ሁሉ የሚጠቀልል እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ነበር ሌሎች አገራት ጦራቸውን “የመከላከያ ሠራዊት” እያሉ ሲጠሩ ጃፓን ግን የአገሯን ጦር “የጃፓን ራስን የመከላከል ኃይል” በማለት የሰየመችው፡፡

መስከረም አንድ (ሴፕቴምበር 11) በአሜሪካ “የአሸባሪዎች ጥቃት” ከደረሰ ወዲህ የጃፓን ህገመንግሥትም እየላላ፤ በማሻሻያዎችም ለውጥ እየተደረገበት መጥቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ዓለምአቀፋዊ ሰላምና ትብብርን” ለማጎልበት በሚል ጃፓን ጦሯን ከዓለምአቀፍ ኢምፔሪያሊስቶች ጋር ማሰለፍ ጀመራለች፡፡ አሜሪካ አፍጋኒስታንን በወረረች ጊዜ ጃፓን የድጋፍ ክንዷን ዘርግታለች፤ በቀጥታ ውጊያ በመሳተፍ ባይሆንም በተዛማጅ አገልግሎቶች፡፡

ቻይና ከአፍሪካ አምባገነኖች ጋር በጥቅም በመተሳሰር እየመሠረች ያለችው የጠበቀ ግንኙነት ዓይናቸውን “ያቀላው” ምዕራባውያን በቻይና ላይ የሚያደርጉትን ስለላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ለዚህ ተግባር የጃፓን ተሳትፎ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ተሳትፎው ለምዕራባውያን በራሱ የሚሰጠው ጥቅም ቢኖርም ለጃፓን በተለይ ከታሪካዊ ጠላቷ ቻይና ጋር ለምታደርገው ሁለገብ ፉክክር የራሱን የቻለ እገዛ ያደርግላታል፡፡

ምዕራባውያን፤ ጃፓን እና ቻይና

ቻይና በተለይ በአፍሪካ የምታደርገውን መጠነሰፊ ኢንቨስትመንት በቅርብ ለመሰለልና ማንኛውንም እንቅስቃሴዋን ለመቆጣጠር አሜሪካ በፖሊሲ ደረጃ የወሰደችው እርምጃ በአፍሪካ ወታደራዊ የበላይነትን መጎናጸፍን ነው፡፡ (ጎልጉል: “በአልቃይዳ ሰበብ ቻይናን መቆጣጠር፤ የኦባማ አስተዳደር መጪው የአፍሪካ ዕቅድ” በሚል የዘገበው እዚህ ላይ ይገኛል:: “አሜሪካ በአፍሪካ ወታደራዊ የበላይነቷን ልታረጋግጥ ነው! ፕሮግራሙን ለማስፈጸም 35 አገሮች ተመርጠዋል” በሚል የተጻፈው ተጨማሪ ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)

ይህንን ወታደራዊ የበላይነት ተግባራዊ ለማድረግ አሜሪካ በአፍሪካ እጅግ ዘመናዊ ወታደራዊ ተቋማትን እየመሰረተች ትገኛለች፡፡ በከፍተኛ መኮንኖቿም አማካኝነት የአፍሪካን ወታደሮች በማሰልጠን “የአህጉሩን ሰርዶ በአህጉሩ በሬ” እያስኮመኮመች ነው፡፡ የአፍሪኮም (AFRICOM) መቋቋም እንዲሁም በአፍሪካ የተካሄዱ የቅርብ ጊዜ ጦርነቶች ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አቶ መለስ ኢትዮጵያን በማይመለከታት ጦርነት ከሶማሊያ ጋር ያናከሷት ይኸው ለምዕራቡ ዓለም ካላቸው ተላላኪነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት የተነሳ እንደነበር ይታወሳል፡፡camp lemonnier

አሜሪካ በአፍሪካ ከምታካሂደው ወታደራዊ የበላይነት እንቅስቃሴ በተለይ “አሸባሪነትን ለመዋጋት” በሚል በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የምትፈጽመው ተግባር ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ በድርጊቱም የዛሬ 10ዓመት አካባቢ በጅቡቲ የሚገኘውን ለሞኒር የጦር ሠፈር የራሷ አደረገች፡፡ ብዙም ሳትቆይ የጦር ሠፈሩን በማዘመን ቀድሞ ከነበረበት በአምስት እጥፍ አሳደገችው፡፡ ይህ የሆነው የጦር ሠፈሩን ከፈረንሳይ ከተረከበች ሦስት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በዚህ የጦር ሠፈር አራቱም የአሜሪካ ወታደራዊ ክፍሎች – ምድር ጦር፣ አየር ኃይል፣ ባህር ኃይል እና ማሪን – የሚገኙ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የሚገኙት ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬኒያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ዑጋንዳ፣ ሲሸልስና የመን በጣምራ ጦሩ ዕይታ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አገራት በተለይ በኢትዮጵያ በብላቴና ሁርሶ በኬኒያ ደግሞ በማንዳ ቤይ የጅቡቲው ጦር ሠፈር ቅርንጫፍ የሆኑ የዕዝ ማዕከላት ይገኛሉ፡፡ ታህሳስ 27፤1999 የታተመው ኢትዮጵያን ሔራልድም ይህንኑ በማመን “የኢትዮጵያ መካላከያ ሠራዊት” በብላቴና ሁርሶ ውስጥ በአሜሪካውያኑ እንደሚሰለጥን ዘግቧል፡፡ ኢህአዴግ ሶማሊያን በወረረ ጊዜ ሠራዊቱ ከአሜሪካውያኑ የተቀበለውን ሥልጠና በተግባር የማዋል ብቃቱን ለማሳየት ወረራው የወታደራዊ ሳይንስ ቤተሙከራ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ይህ በጅቡቲ የሚገኘው የጦር ሠፈር እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት ኢስት አፍሪካን የተባለው የኬኒያ ጋዜጣ አሜሪካ የጦር ሠፈሩን በተረከበች ጊዜ ለአካባቢው አገራት የምትሸጠው መሣሪያ የዋጋ መጠን 1ሚሊዮን ዶላር ያህል የነበረው ከሦስት ዓመት በኋላ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማደጉን ዘግቧል፡፡ ይህ አኻዝ የዛሬ 7ዓመት አካባቢ የተነገረ ሲሆን የቅርብ ጊዜውን መጠን በዚሁ ስሌት ለመገመት አያዳግትም፡፡

abe djibouti

ጃፓን በህገመንግሥቷ የጸናውን “ሰላማዊነት” በማሻሻያ ከቀለበሰች ወዲህ ወታደራዊ ተስፋፊነቷ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሶማሊያ የባህር ላይ ውንብድናና የመርከብ ዝርፊያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው በሚል ኢኮኖሚያዋ በባህር ንግድ ላይ የተመሠረተው ጃፓን አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብኝ በማለት ቻይናን በእጅ አዙር ለመግጠም ወደ አፍሪካ ብቅ አለች፡፡ ቻይናን ከተለያየ አቅጣጫ የጠመዱት ምዕራባውያን ለጃፓን ውሳኔ ይሁንታ በመስጠት ግልጽ ድጋፍ አደረጉ፡፡ የሶማሊያን ችግር የመፍታት አማራጭ ከመውሰድ ይልቅ ሶማሊያን ፈርሳ በምትኩ የምዕራባውያን አሻንጉሊት የሆነ አዲስ አገር በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ተላላኪ መሪዎች መፍጠር “ቀላሉ” አማራጭ ሆኖ በመወሰዱ ነበር ፑንትላድ የተመሠረተው፡፡ አሜሪካ በሶማሊያ ላይ ካላት የቆየ ቂም አንጻር በአሁኑ ጊዜ ፑንትላንድን ማንኛውንም “አሸባሪ” ብላ የምትፈርጀውን ለማጥቃት እንደፈለገች የምትፈነጭበት አገር አድጋታለች፡፡ ኢህአዴግም ለፑንትላንድ መሪዎች በልምድ ያካበተውን “ንቃት” የሚሰጥ ሲሆን በቅርቡ የፑንትላንዱ መሪ አዲስ አበባን መጎብኘታቸው ከዚህ ጋር አብሮ የሚጠቀስ ነው፡፡

አሜሪካውያኑ “አሸባሪነትን” ምክንያት በማድረግ የጦር ሠፈሮችንና ወታደራዊ ተቋማትን ያለ ከልካይ ሲገነቡ ጃፓንም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የተጠቀመችው “ምክንያት” በወቅቱ በቀይ ባህርና በሰላጤው መተላለፊያ የሰፈነው የመርከብ ጠለፋና የባህር ላይ ውንብድናን ነበር፡፡

በኤድን ሠላጤ በየዓመቱ 20ሺ የሚሆኑ የጭነት መርከቦች ያልፉበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 10በመቶው የጃፓን መርከቦች ሲሆኑ ኢኮኖሚያዋ በከፍተኛ ሁኔታ በውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ላይ ጥገኛ የሆነችው ጃፓን 90በመቶ የሚሆነው የውጭ ንግድ ሸቀጦቿ በዚሁ የባህር መንገድ ላይ ጥገኛ ነው፡፡ በመሆኑም የባህር ላይ ውንብድናው እየከፋ ሲመጣ ጃፓን ህልውናዋን ለማስከበር እርምጃ እንድትወስድ በከፈተላት በር ተጠቅማ ለሞኒየር ጦር ሠፈር የከተመውን የአሜሪካንን ኃይል “አስጠጉኝ” ማለት ጀመረች፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ጃፓን ከአገሯ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ የጦር ሠፈር በጅቡቲ መሠረተች፡፡ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ሠፈር ሲመሰረት ከ40ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈጅቷል፡፡

pirates

በጅቡቲ ትልቁ ወታደራዊ የበላይነት ያላት ፈረንሣይ በዚህ ሁሉ ውስጥ “የዓለምአቀፋዊ ኢምፔሪያሊዝም” አካል እንደመሆኗ ወታደራዊ ተስፋፊነቱ የእርሷም ፖሊሲ ነው፡፡ ከቻይና ጋር “በፍቅር የሚወድቁ” የአፍሪካ አገራትን ለይታ በማጥቃት ቀድሞ የነበራትን የቅኝ ግዛት ተስፋፊነትና የበላይነትን በእጇ ለማስገባት የምትጥረው ፈረንሣይ፤ ቻይና በተበረገደ በር ገብታ የምትዝቀው የአፍሪካ ሃብት “ዓይን ከማቅላት” በላይ ሆኖባታል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኮትዲቯር አሁን ደግሞ በመካከለኛው የአፍሪካ ሪፑብሊክ ፈረንሳይ የተጠመደችበት ጦርነት በመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ሌላ መስሎ ቢቀርብም ጉዳዩ ግን ቻይናን ነጥሎ ከመምታት ያለፈ እንዳልሆነ ወታደራዊ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ከጦርነቶቹ ጋር አብሮ የሚነሳው የዘር፣ የሃይማኖት፣ ወዘተ ግጭትና የሕዝብ ዕልቂት እሣተጎመራው ሲፈነዳ እንደሚቃጠለው ሣር ዓይነት በእንግሊዝኛው አጠራር “collateral damage” የሚባለው ነው፡፡ ይህ የአፍሪካውያን ሰቆቃና ዕልቂት የሚፈልጉትን ዓላማ እስካስፈጸመ ድረስ ለምዕራባውያን ብዙም የሚገዳቸው እንዳልሆነ አደጋን በማያያዝ በራሳቸው ህዝብ ላይ የሚፈጽሟቸው “ወንጀሎች” ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ፈረንሣይና ጃፓን

japan and france

ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ አገራትን በጎበኙበት ሰሞን የውጭ ጉዳይና የመከላከያ ሚኒስትሮቻቸው ከፈረንሣይ ጋር መጠነሰፊ ስምምነት ለማድረግ ፓሪስ ነበሩ፡፡ በደሴቶች የይገባኛል ጥያቄ ከቻይና ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ጃፓን የመከላከያ ኃይሏን በማጠናከር ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም ዘመነኞቹ ፈረንሣይ ሰራሽ የጦር መሣሪያዎች፣ ሔሊኮፕተሮች፣ የባህር ውስጥ መርከቦች (ሰብማሪን) በእጅጉ ያስፈልጓታል፡፡ ፈረንሣይ ከቻይና ጋር በተያያዘ በአፍሪካ ላይ ለተጠመደችበት ተግባር የጃፓንን ድጋፍ ትፈልጋለች፡፡ ለዚህም ነው በቀድሞዎቹ የፈረንሣይ ቅኝ አገራት – ማሊና መካከለኛው አፍሪካ – ፈረንሣይ እያካሄደች ለምትገኘው ጦርነቶች ጃፓን ቀጥተኛ ድጋፍ እንደምትሰጥ በይፋ ያስታወቀችው፡፡ ይህ ከቃል ያለፈው ድጋፍ በተግባር ተተርጉሞ ለማሊው ጦርነት ጃፓን 735 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ ለፈረንሣይ ጦር ሰጥታለች፡፡ ለመካከለኛው አፍሪካ ጦርነትም ተመሳሳይ ድጋፍ እንድትሰጥ ይጠበቅባታል፡፡

ለእንደዚህ ዓይነቱ የ“እከክልኝ ልከክልህ” ወዳጅነት ጃፓንም ከቻይና ጋር ለምትቆራቆስባቸው ደሴቶች ጉዳይ የፈረንሣይን ግልጽ የፖለቲካ ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ሁለቱ ሚኒስትሮች ፈረንሣይን ከጎበኙ በኋላ በወጣው የጋራ መግለጫ ፈረንሣይ በሳንካኩ/ዲያዖዩ ደሴቶች ጉዳይ የቻይናን ተስፋፊነት አውግዛለች፡፡ የጃፓኑ ውጭ ጉዳይ ሚ/ርም ከፈረንሣይ ጋር የፈረሙት አዲሱ ስምምነት ሁለቱ አገራት “በደኅንነትና መከላከያ ዙሪያ ለሚያደርጉት ትብብር አዲስ ፈር ቀዳጅ” እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢህአዴግ ጭንቀት

ኢህአዴግ በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን ማንኛውንም ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ የተቃውሞ ድምጻቸውን የሚያሰሙትን ሁሉ “አሸባሪ” በማለት እስርቤት ሲያጉር፣ ሲያሰቃይ፣ ሲገድል፣ … መቆየቱ በግልጽ የፈጸማቸው ተግባራቱ ከበቂ በላይ ማስረጃ ናቸው፡፡ የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር ኢትዮጵያን በጎበኙ ወቅት በአዲስ አበባ የሚገኙ ቻይናውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህም ብቻ አላበቁም፤ አዲስ አበባ በሚገኘው የጃፓን ኤምባሲ በመሄድ አምባጓሮ ፈጥረው እንደነበር በዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል፡፡ በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የሚገኙ ቻይናውያንን ፊርማ በማሰባሰብ ተቃውሟቸውን ለኤምባሲው አቅርበዋል፡፡ አሶሺየትድ ፕሬስ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ቻይናውያኑ “ሳንካኩ ደሴት የእኛ ናት” የሚል ትልቅ መፈክር ሰቅለውም ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ “በአሸባሪነት” የወነጀላቸው የለም፡፡

በኢትዮጵያ የቻይናው አምባሳደርም የከረረ ተቃውሟቸውን በጠ/ሚ/ር አቤ ጉብኝት ላይ ሰንዝረዋል፡፡ ጃፓን የቻይናን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እየሠራች መሆኗንና “ወታደራዊ የበላይነቷን” እንደገና እያንሰራራችው እንደሆነ ወንጅለዋል፡፡ ጠ/ሚ/ሩን “ችግር ፈጣሪ፣ አዋኪ” በማለት የከሰሱት አምባሳደር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጃፓን ሠራዊት በቻይናውያኑ ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ ተግባር የሚያሳይ ፎቶ በማሳየት ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ETHIOPIA-CHINA-JAPAN-DISPUTE  CDS1148
Enter a caption

የፈለገውን ዓይነት በቴክኖሎጂ የረቀቀ የአፈና መሣሪያ ከቻይና ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እያገኘ ያለው ኢህአዴግ ከቻይና የሚያገኘውን ጥቅም ከምዕራባውያን ከሚቀበለው ዕርዳታና የበጀት ድጋፍ ጋር ለማስታረቅ መንገዱ እየጠበበበት እንደመጣ የሚጠቁሙ ክስተቶች አሉ፡፡ ሁኔታው በአምባገነንነት ከመቀጠሉ ኅልውናው ጋር የተሳሰረ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡ የዓለም ባንክ የሚሰጠውን ዕርዳታ በተመለከተ ሊወስድ የተዘጋጀበት እርምጃ እንዳለ ሆኖ ለምዕራባውያን በመላላክና ጉዳይ በማስፈጸም “ብቃታቸውን ያስመሰከሩት” መሪውን ካጣ ወዲህ ኢህአዴግ ከቻይና በሚያገኘው ጥቅምና የታዘዘውን እየፈጸመ ከምዕራባውያን በሚያገኘው ዕርዳታ መካከል መንታ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡

ምዕራባውያን ከጃፓን ጋር ወግነው የሚያደርጉት ተግባራት በቻይና ላይ ቀጥተኛና አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ ኢህአዴግ በግድ መልስ የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህም ደግሞ በግንኙነት መሻከርም ሆነ መጎልበት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ አለ፡፡ ለዚህም ይመስላል የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር ኢትዮጵያን በጎበኙ ሰሞን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት በአፈቀላጤው አማካኝነት “የአያገባኝም ማስተባበያ” የሰጠው፡፡ ዲና ሙፍቲ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ይኼ የቻይና መንግሥት ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ የእኛ ጉዳይ አይደለም … ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ በዚህም ልክ ከጃፓንም ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ ይህንን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንፈልጋለን፡፡ …  ከአገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት በአንዱ ኪሳራ አናራምድም” ብለዋል፡፡ ይህ ጃፓን እንዳትቀየም የተሰጠ ማስተባበያ ቻይናም እንዳታኮርፍ በመለማመኛነት የቀረበ ጭምር ነው፡፡abe_africa

የውጭ ጉዳዩ በዚህ ዓይነት የተወጠረ ሁኔታ ላይ ያለው ኢህአዴግ በአገር ውስጥም የሕዝቡን ዕለታዊ ጥያቄዎች ለማሟላት አለመቻሉ ከፍተኛ ምሬት እያስነሳበት ይገኛል፡፡ በተለይ የከረረ ተቃውሞና ነቀፋ ከደጋፊዎቹና ጥቅመኛ ባለሟሎቹ እየቀረበ መምጣቱ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ መውደቁን ገምተው በድል አጥቢያ አርበኛነት የተናገሩት ይሁን ወይም የለውጥ ፍላጎታቸውን የገለጹበት ጊዜውን ጠብቆ የሚታወቅ ቢሆንም ቀድሞ ሲባል እንደነበረው በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ “የመንግሥት ሌቦች” ያሉት ድርጅት ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ የዚያ “ባለማዕረግ” ሆኗል፡፡

በአንድ መልኩ በአገር ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ማኅበራዊ ነውጥ ለማክሸፍ፣ በሌላ በኩል በቻይና ድጋፍ የሕዝቡን ድምጽ በማፈንና መብት በመርገጥ በአምባገነንነት ለመቀጠል የሁልጊዜ ምኞቱ የሆነው ኢህአዴግ “ምርጫውን በምርጫ” የሚያሳክር “ምርጫ” ተደቅኖበታል፡፡ የደም ሥሩ የሆነውን የምዕራባውያን ድጎማ ላለማጣት ለአሜሪካና ለቻይና ታሪካዊ ጠላት ጃፓን መንበርከክ የማይፈልገው ቢሆንም የማይቀርና በመንታው መንገድ ላይ የተፈጠረ ሌላ መንታ ሆኖበታል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለመጪው ምርጫ በሩን እንዲከፍት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እየደረሰበት ያለው ጫና ከሕዝብ ብሶትና ዕሮሮ ጋር ተዳምሮ የኢህአዴግን “ፍንዳታ” አቀሬነትና ቅርብነት በካድሬዎቹና ደጋፊዎቹ ጭምር እንዲተነበይ አድርጎታል፡፡ (ከላይ የሚታየው ፎቶ ሺንዞ አቤና ሃይለማርያም ደሳለኝ ውይይት ከማድረጋቸው በፊት ሁለት ባለሥልጣናት የደረቀ አንበሳ ፊት ቆመው ሲመክሩ ነው – ፎቶው ከ Wall Street Journal የተገኘ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *