Skip to content

ቴዎድሮስ አድሃኖም – ካልተመረጡ እምነታቸው በሆነው የጎሳ ፖለቲካ የመጀመሪያው ሰለባ ሆነው ይመዘገባሉ!!

የኢትዮጵያ ሃኪሞች ማህበር ሊቀመንበር ዶክተር ገመቺስ ማሞ ዶከተር ቴዎድሮስ አደሃኖምን በሚያወድሰው ንግግራቸው ወቅት ኮሌራን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ” መንግስትን ጠይቁ” ሲሉ መለሱ። በከፍተኛ ውዝግብ የታጀበው የዓለም ጤና ድርጅት ምርጫ ውዝግብ የአገሪቱን የፖለቲካ ክሽፈትና የጥላቻ ፖለቲካ ግለት የሚያሳይ  እንደሆነ ተጠቆመ። ከተሸነፉ እምነታቸው በሆነው የጎሳ ፖለቲካ የመጀመሪያው ሰለባ እንደሚሆኑም እየተነገረ ነው።
ከቪኦኤ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱት ዶክተር ገመቺስ በተደጋጋሚ ስለ ኮሌራ ተጠይቀው ሲመልሱ ” መንግስት ኮሌራ ነው ሲለኝ በሽተኛዬን አክመዋለሁ” ነው ያሉት። በተደጋጋሚ የመንግስትን ስም በመጥራት ጥያቄውን ወደ መንግስት ገፍተዋል። የኮሌራ ጉዳይ አሁን በስተመጨረሻ መነሳቱ ድንጋጤ የፈጠረ መሆኑንን ተከተሎ ለማስተባበል ቢሞከርም ከመንግስት ውጪ ገለልተኛ ወገኖች ያሉት ነገር የለም። ሪፖርተርም  ” ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ  የአተት በሽታ /የኮሌራ ለማለት ይመስለናል/

Lilesa shows his solidarity with the Oromo people after crossing the finish line at the 2016 Rio Olympics [Reuters/Athit Perawongmetha

በአገሪቱ ተከስቶ ይፋ እንዳላደረጉ ኒውዮርክ ታይምስ ሰሞኑን ዘግቧል፡፡ ይህንን በተመለከተ ዶ/ር ገመቺስ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በዚህ ላይ መልስ ሊሰጡ እንደማይችሉ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመጡ ኃላፊዎች ሊመልሱት እንደሚችሉ ዕድሉን ቢሰጡም መልስ ሳይሰጥ ቀርቷል” ቀርቷል ሲል ዘግቧል።
የዶክተር ቴዎድሮስ ጉዳይ እጅግ አነጋጋሪና አወዛጋቢ ጉዳይ ከሆነ ከርሟል። ሁለት ጎራ በለየ እምነት የተወጠረው የዶከተሩ የዓለም የጤናው ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ምርጫ በሚቀጥለው ሳምንት እልባት ያገኛል። ለጉዳዩ ገለልተኛ የሆኑ ክፍሎች ደጋፊዎችንም ሆነ ተቃዋሚዎችን ጭፍን ናቸው ይላሉ። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሆነው በሙሉ ከሚጠየቁት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስን በጄኖሳይድና ኮሌራ እንዲደበቅ አድርገዋል በሚል ይከሳሉ። እንደ እነሱ አባባል የስርዓት ለውጥ ቢመጣ በጄኖሳይድ ከሚጠየቁት መካከል አንዱ እሳቸው ናቸው። የአማራን ብሄር ለይተው የማምከኛ መርፌ እንዲሰጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ አስተላልፈዋል። በዚህ ስብእናቸው ለድርጅቱ አይመጥኑም ባይ ናቸው። ሌላም ሌላም ይላሉ።
ደጋፊዎቻቸው በበኩላቸው እሳቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዘመን ተሰራ የሚሉትን በመዘርዘር ይሟገታሉ። የጤና ባለሙያ እንደ አሸን የፈላው በሳቸው ዘመን ነው። የእናቶችና የህጻናት ሞት የቀነሰው ሲሉ የሳቸውን ስራ ያጎላሉ። አሜሪካ ሬዲዮ ያናገራቸው የኢትዮጵያ ሃኪሞች ማህበር ሊቀመንበር ዶክተር ገመቺስ ” ብቃት አላቸው” ሁለት ሺህ በላይ አባለት ባለው ማህበራቸው ስም ይሁን በግላቸው ግልጽ ሳይደረግ አወድሰዋቸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይም ” ፋና ወጊ” ሲሉ ጠቅሰዋቸዋል። እሳቸው እንዳይመረጡ መታገል ኢትዮጵያዊ ስነምግባር እንዳልሆነም አመልክተዋል። የሱዳንን፣ የሶማሊያንና የአባይ ግድብን በማንሳት ታላላቅ ስራ መስራታቸውን በመጠቆም ሞግተዋል።
ጉዳዩን የሚከታተለው የሎንዶን ነዋሪ አሳምነው ለጎልጉል እንዳለው ” የማየው ሁሉ ክስረት ነው” ሲል ይጀምራል። ዶክተር ቴዎድሮስን ከኢህአዴግ ለይቶ መመረቅ ራሱን ኢህአዴግን መስደብ እንደሆነ ያክላል። ስያስረዳም ለኢህአዴግ  ስኬትም ሆነ ክስረት ዶ/ር ቲዎድሮስ አሉበት። በስብአዊ መብት ጉዳይ ኢህአዴግ መክሸፉን፣ ዓለም ሁሉ የተስማማበት ጉዳይ ነው። ኢህአዴግ እራሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን መግደሉን ሲያምን ” ይህን ሲደረግ ዶክተር ቴዎድሮስ የሉበትም አላለም” በዚህ ሁኔታ ኢህአዴግ ለሚከሰሰባቸው የስብአዊ መብት ጉዳይ በሙሉ እሳቸው ከፊት ሰልፍ ከሚሰለፉት ተጠያቂዎች መካከል አንዱ ናቸው።
በሌላ በኩል በጤና ኤክስቴንሽን ተሰራ የሚባለው ሁሉ የመንግስት ስራ መሆኑንን በማመልከት፣ እንደ አገር ጥፋት ቢኖርባቸውም እንዴት መስማማት አቃተን የሚለው ጉዳይ ሊሰመርበት እንደሚገባ አስተያየት ሰጪው ያነሳል። “ከአንድ የአገር ዜጋ ይልቅ ሌላ ይመረጥ” ብሎ መነሳትና ዘምቻ ማድረግ አስደንጋጭም፣ አሳዛኝም፣ የጉዟችን መደረሻስ የት ነው የሚያሰኝ ይሆናል።
እንደ አሳምነው ገለጻ ይህ ሁሉ ኢህአዴግ የዘራው የዘረኛነት አስተሳሰብ ፍሬ ነው። ጥላቻ የቱን ያህል ስር እንደሰደደ የሚያመለክት ነው። ” ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበትና ዘመቻ የተካሄደበት፣ ቦታው ዝም ተብሎ ማንም የሚታጭበት ሳይሆን ከእጩዎቹ ጀርባ የሚሰራ ስራ ስላለ፣ ወንበሩ የረቀቁ የጥፋት ተልዕኮ የሚከወንበት በመሆኑ ቴዎድሮስ መመረጣቸው አይቀርም። እኔን የሚያሳስበኝ የግለሰቡ መመረጥና አለመመረጥ አይደለም። ይህንን ስር የሰደደ ጥላቻ ተሸከመን እንዴት ነው የምንዘልቀው› ይሚለው ነው” ሲል ጥያቄ ይጠይቃል።
አሁን በሁሉም ጎራ የሚታየው ድጋፍና ተቃውሞ ግለሰብ ላይ ያተኮረ እንዳልሆነ የሚያመለክተው አሳምነው፣ ይህ ሁሉ ችግር የአጠቃላይ የኢህአዴግ ፖለቲካ ወደ ከፍተኛው የግለትና የመፈንዳት ደረጃ መቃረቡን እንደሆነ ያመለክታል። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እሳቸው ቢመረጡ ቅር እንደማይለው የሚናገረው አሳምነው ” ይህንን ጉዳይ ተንተርሶ ኢህአዴግ ስለ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ሲናገር መስማት ግን ያሳፍራል። ኢትዮጵያዊነትን አርክሶ ያሸተተና አብሮ የመኖር መልካም ተግዳሮታችንን ሁሉ የበላ ድርጅት እንዲህ የማለት ሞራል የለውም” ሲል አምርሮ ይተቻል።
ከአጠቃላይ የአገሪቱ ችግር ይልቅ የግለሰቦች መመረጥና አለመመረጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ማየት  ቅር እንደሚያሰኝ የገለጸው አሳምነው “ረሃብ ለሚያረገፈው ህዝባቸን እንኳን ይህንን ያህል የሚዲያና የዘመቻ ትኩረት አለመስጥታችን ትልቁ ክሽፈታችን ነው” ይላል። አያይዞም በውጤቱ ከመከራከር መሰረታዊ የፖለቲካውን ችግር መርምሮ ከአደጋ ዞን ለመውጣት መትጋቱ እንደሚሻል ይጠቁማል። አያይዞም ” ቴዎድሮስ አድሃኖም አሸነፉም ተሸነፉም / ያሸንፋሉ/ ውዝግቡ ቢቆምም እንደ አገር ካለንበት የአደጋ ዞን መውጪያውን ብንፈልግ የተሻለ ነው። ይህ የጥላቻ ፖለቲካ ማሳያ የሆነው ውዝግብ በኮማንድ ፖስትና በአስቸኳይ አዋጅ ተቆልፎ ብዙ የሚቆይ አይደለምና!! የሚፈራው ሳይመጣ እንትጋ”
ይህ በንዲህ እያለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአለም አቀፍ የጤና ድርጅት ዳይሬክቶሬት ጄኔራልነት በመወዳደር ላይ ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የምረጡኝ ቅስቀሳውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የአፍሪካ ካሪቢያንና ፓስፊክ ቡድን አባል አገራት ሙሉ በሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል የአፍሪካ ህብረት ለዶ/ር ቴዎድሮስ ሙሉ ድጋፉን መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ሌሎች የደቡብ አሜሪካ የኤሽያና የአውሮፓ አባል አገራት ድምጽ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ምርጫው የፊታችን ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቭ የሚካሄድ ሲሆን የምርጫውን ሂደት የበለጠ ለማጠናከር አንድ የአገራችን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደዚያው ያቀናል፡፡ ፒዲኤፍ ሙሉውን ያንብቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ
ከዚህ በታች ያለው ሪፖርተር የዘገብው ዘገባ ሲሆን በመረጃ እጥረት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምን አስመለክቶ በአብዛኛው የተቃዋሚዎችን ሃሳብ በማስተናገዳችን ለማመጣጠን ሲባል እንዳለ አቅርበነዋል።

ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚደረገው ፉክክር የፊታችን ማክሰኞ ፍፃሜ ያገኛል

የቀድሞው የጤና ጥበቃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች፣ ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚያደርጉት ፉክክር የፊታችን ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በጄኔቫ ፍፃሜ ያገኛል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ለዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ለመወዳደር ያነሳሳቸው ለሙያው ያላቸው ፍቅር፣ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያካበቱት ልምድ፣ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ክህሎታቸውና ለዓለም ጤና ድርጅት አዲስ ዕይታ ለማምጣት ካላቸው ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

አሁንም የምረጡኝ ቅስቀሳቸው የቀጠለ ሲሆን፣ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ለሚያደርጉት ውድድር በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ማኅበራት ድጋፋቸውን ለግሰዋቸዋል፡፡

ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ማኅበራቱ በኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ አማካይነት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ዶ/ር ገመቺስ  እንደገለጹት፣ ዶ/ር ቴድሮስ የአገር ውስጥ የጤና አገልግሎት ሥርዓትንና ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅትን የመለወጥና በአገሮች መካከል መግባባትን የመፍጠር በቂ ልምድ አላቸው፡፡

ለሰባት ዓመታት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው በሠሩበት ወቅት በአገሪቱ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲሻሻል ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ ያስታወሱት ዶ/ር ገመቺስ፣ 3,500 የጤና ማዕከላትና 16 ሺሕ የጤና ኬላዎችን በማቋቋም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጤና ባለሙያ ማሠልጠኛ ማዕከላትን ከሦስት ወደ ሠላሳ ሦስት ማሳደግ እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ የነበሩትን 16,500 የጤና ባለሙያዎች በሰባት እጥፍ ማሳደግ መቻላቸው የጤናውን ዘርፍ የመምራት አቅማቸውን የሚያሳይ በመሆኑ፣ በዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ቢመረጡ በዓለም ላይ በጤናው መስክ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የሕፃናት ሞትን በሁለት ሦስተኛ፣ በወባ የሚከሰት ሞትን በ45 በመቶ፣ በኤችአይቪ የሚሞቱትን በ70 በመቶ፣ እንዲሁም በሳንባ ነቀርሳ የሚሞቱትን 64 በመቶ መቀነስ እንደቻሉ ተገልጿል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዶ/ር የቴድሮስ ተጠቃሽ ስኬታቸው እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህ መስክም ከ38 ሺሕ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሠልጥነው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረጋቸው አንዱ ለስኬት የሚያበቃቸው ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በሠሩበት ወቅትም ግሎባል ፈንድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የመሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ኢቦላን ለመከላከል በተደረገው ዘመቻ ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንድታበረክት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

ለዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በመወዳደር ላይ ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውሷል፡፡ እንደ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ከሆነ፣ የአፍሪካ ካሪቢያንና ፓስፊክ ቡድን አባል አገሮች ሙሉ በሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ፣ የእስያና የአውሮፓ አባል አገሮች ድምፅ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቭ በሚካሄደው ምርጫ አንድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ወደ ሥፍራው እንደሚያቀና በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የአተት በሽታ በአገሪቱ ተከስቶ ይፋ እንዳላደረጉ ኒውዮርክ ታይምስ ሰሞኑን ዘግቧል፡፡ ይህንን በተመለከተ ዶ/ር ገመቺስ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በዚህ ላይ መልስ ሊሰጡ እንደማይችሉ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመጡ ኃላፊዎች ሊመልሱት እንደሚችሉ ዕድሉን ቢሰጡም መልስ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡

የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጋር በተያያዘ ከሳምንት በፊት ወደ ግብፅ አቅንተው የነበረ ሲሆን፣ ካይሮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የግብፅ የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪስ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ በመሐመድ ኢድሪስ በኩል፣ ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ ለዓለም ጤና ድርጅት ለምታደርገው ውድድር ግብፅ ድጋፍ እንደምትሰጥ መናገራቸውን የግብፅ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

ግብፅና ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ያልተፈቱ ጉዳዮች በመካከላቸው እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ስትወዳደር ድምፅ ከነፈጓት አገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች ሲነገር ነበር፡፡ የዶ/ር ቴድሮስ ወደ ግብፅ ማቅናትም ይህንን ጉዳይ አለዝቦ ግብፅ ድምጿን ለኢትዮጵያ እንድትቸር ለመጠየቅ እንደሆነ ግምት አለ፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚጠናቀቀው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ከሚወዳደሩ የመጨረሻ ዕጩዎች መካከል አንዱ እንግሊዛዊው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ ሲሆኑ፣ በጤናው ዘርፍ የአርባ ዓመት ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ በተለያዩ ቦታዎች ስኬታማ ሥራዎችን እንደሠሩና ከእነዚህም መካከል ኢንፍሌዌንዛን መከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ኢቦላን መከላከል እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተመድ ውስጥ የዋና ጸሐፊውንና የ2030 ዘላቂ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ አማካሪ ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡

ሦስተኛ ተወዳዳሪዋ ፓኪስታናዊቷ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር ሲሆኑ፣ በአገራቸው ከ15 ዓመታት በላይ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በኃላፊነት እንዳገለገሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
WHY I RYN

Lilesa shows his solidarity with the Oromo people after crossing the finish line at the 2016 Rio Olympics [Reuters/Athit Perawongmetha]--------------------------------------------------------------...

Close