Skip to content

አጠያያቂው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኝነት

በውብሸት ሙላት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሕገ መንግሥቱ ላይ በተገለጸው መሠረት በአዋጅ የተቋቋመ፣ ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ተቋም ነው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሠፈሩትን እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀችው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ላይ የተገለጹ መብቶችን እንዲያስከብር ሲባል የተቋቋመ ነው፡፡ ዋና ዋና ሊባሉ የሚችሉ አራት ዓበይት ተግባራትም አሉት፡፡

አንደኛውና ትልቁ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ማከናወን ነው፡፡ የግንዛቤ ማስፋፋት ሥራው በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሰነዶች ላይ በሠፈሩት የሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ ኖሮት፣ መብቶቹን አውቆ ለመብቱ ዘብ እንዲቆም ብሎም በማክበርና በማስከበር ረገድ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን አፅድቃለች፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች፣ በሕፃናትና በሴቶች መብቶች ዙሪያ የተፈረሙ ስምምነቶችን ተቀብላለች፡፡ ስምምነቶቹም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ እንደተደነገገው እንደ ሌሎቹ ሕጎች ሁሉ የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡

ሁለተኛው ትልቁ የኮሚሽኑ ተግባር በአዋጁ መሠረት የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ያለበትን ሁኔታ ክትትል ማድረግ ነው፡፡

ሦስተኛው ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም የምርመራ ሥራ ማከናወን ነው፡፡ ምርመራ ሲባል የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ከተጣሱ ወይንም እንዴት እንደተያዙ ከሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ ምን እንደሚመስል ለማወቅ መሬት ላይ ያሉትን እውነታዎችን መገምገምና ማጣራት ሊሆን ይችላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካለም ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡

በአራተኛ ተግባር ደግሞ ስለ ሰብዓዊ መብት ለሚመለከተው አካል የምክር አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ የማማከር ሥራው ለመንግሥት ሊሆን ይችላል፡፡ ማሻሻል የሚገባው ነገር ካለ፣ አሊያም ሊወሰዱ የሚገባቸው የማስተካከያ ዕርምጃዎች ካሉ ለመንግሥት በወቅቱ ምክር መለገስን ይመለከታል፡፡

እንግዲህ እነዚህን ዓበይት ተግባራት ለማከናወን ሲባል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ ተቋሙ፣ እነዚህን ተልዕኮዎቹን ለመፈጸም ነፃና ገለልተኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በዋናነት ነፃና ገለልተኛ መሆን የሚጠበቅበት ደግሞ ከአስፈጻሚው አካል መሆኑ የታመነ ነው፡፡ ተግባራቱን በአግባቡ ሲያከናውንና የሚጠበቅበትን ሁሉ ሲወጣ ዓለም አቀፍ ዕውቅናንም ይጎናፀፋል፡፡ ሕዝቡም ይቀበለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዓለም አቀፍ ደረጃው “ለ” ነው፡፡ ያለበትን ደረጃ የሚያውቁት ጠቅላይ ሚኒስትርና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሩ ስለ ዓለም አቀፍ ዕውቅናውና ስለሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች ተቀባይነት ሲጠየቁ “ዋናው ነገር በሕዝባችን ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት ነው፤” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ኮሚሽነሩም፣ እንደ አስፈጻሚው ሁሉ ስለ ሰብዓዊ መብትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርመራ ወይም ትዝብት ሲጠየቁ የአገር ሉዓላዊነትን በመከላከያነት ያነሳሉ፡፡

እንዲህ ሁኔታ ውስጥም ስለ ተቋሙም ነፃነትና ገለልተኝነት አብዝተው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ለመሆኑ ገለልተኛና ነፃ ተቋም የሚያስብሉት መለኪያዎች ምን ምን ናቸው? ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምን ይጠብቃል? በምንስ መሠረት? የሚሉትን ነጥቦች እንዳስሳለን፡፡ ለዚህም፣ የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የኮሚሽነሩን ቃለ መጠይቆችና ሪፖርቶች፣ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን የሚመለከቱትን ዓለም አቀፍ መርሖች በተለይም የፓሪስን፣ እንዲሁም በሌሎች ተቋማት የቀረቡ ሪፖርቶችን መነሻ እናደርጋለን፡፡

ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት

ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የማቋቋምን አስፈላጊነት በተመለከተ ሁሉን አቀፉን የሰብዓዊ መብት መግለጫ ሲወጣ ጀምሮ አጀንዳ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከምሥረታው ጀምሮ የረሳው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ተጨባጭ ይሆነ ዕመርታ ያሳየው ከአራት አሥርት ዓመታት በኋላ ነው፡፡

በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 20 ቀን 1999 ዓ.ም. የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ አንድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የውሳኔ ቁጥር 48/144 በመባል ቢጠራም የሚታወቀው ግን “የፓርስ መርሖች” በመባል ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የምንመለከተው ነፃና ገለልተኛ ብሔራዊ (አገራዊ) የሰብዓዊ መብት ተቋማት መቋቋምን ነው፡፡ በዚህ በተመድ ውሳኔ መነሻነት እንዲቋቋሙ የሚጠበቁትና የሚመለከተውም በመንግሥት የሚቋቋሙትን እንጂ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አይመለከትም፡፡

ተቋማቱ፣ አገሮች በሕገ መንግሥታቸው፣ ወይንም በአዋጅ የሚያደራጇቸውን እንዲሁም በመንግሥት በጀት የሚያስተዳድሯቸው ወይንም የሚደግፏቸው ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ተጠሪነታቸውም በጭራሽ ለአስፈጻሚው አካል አይሆንም፡፡

የአገሮችንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ፣ የሰብዓዊ መብትን ግንዛቤ በመፍጠር የሚያሰርፁ፣ የሚያስከብሩ፣ የሚቆጠጠሩና ሪፖርትም ጭምር እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ የፓሪስ መርሖች ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን አፈጻጸም፣ ነፃነት፣ ገለልተኝነት፣ ወዘተ የመሳሰሉትን እሴቶች ሥራ ላይ ለማዋል በመለኪያነት ያገለግላል፡፡

ዜጎችም ይሁኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚጠብቀው ይኼንኑ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቋቋሚያ አዋጅ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ከአምስት ዓመት በኋላ በማውጣት ከእንደገና አራት ዓመታት ቆይቶ ኮሚሽኑ ተቋቁሟል፡፡

ገለልተኛነት በፓሪስ መርሖች

ለብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እጅግ በጣም ተፈላጊ ከሆኑ እሴቶች ውስጥ ዋናው ገለልተኝነት ነው፡፡ አስፈላጊነቱ የሚመነጨው ሊኖረው ከሚችለው ሚና ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን ለመጣስ ተጋላጭ የሆነው አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ሲሆን በጀትና ሌሎች ነገሮችንም ማሟላትም የሚጠበቀው ከእሱው ነው፡፡ ተቋሙ ደግሞ ቁጥጥርና ሪፖርት የሚያደርግበት በዋናነት አስፈጻሚውን ነው፡፡

በመሆኑም ገለልተኛ ካልሆነ የተጣለበትን ወይንም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በሚፈለገው መጠን ሊወጣ አይችልም፡፡ ይህንን የገለልተኝነት መርሕም ከፓርሱ መርሖች ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ በመሆኑም፣ ተቋማቱ በቅን ልቦና፣ ያለ አድልኦና ማዳላት፣ ወገንተኛ ሳይሆኑ በተቋም ደረጃ ብቻ ሳይወሰኑ ከኮሚሽነሩ ጀምሮ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ግለሰቦች የገለልተኝነታቸው ጉዳይ ሁል ጊዜም የሚነሳና የሚያጨቃጭቅ ነው፡፡

ገለልተኛነቱን ለማረጋገጥ ሲባል በሕገ መንግሥት ወይም ፓርላማው በሚያወጣው አዋጅ ብቻ መቋቋም አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያም ይኼንን መሥፈርት በትክክል ያሟላል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን ለማለት እንጂ አዋጁንና ተግባሩን ለማለት አይደለም፡፡ ከማቋቋሚያ አዋጁ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ኮሚሽነርና ከነምክትሎቹ የሚሾሙት በፓርላማው ነው፡፡ ኮሚሽነርና ምክትል የሚሆኑትን ሰዎች የሚጠቁም ኮሚቴም ይዋቀራል፡፡ የኮሚቴው ብዛት አሥራ ስድስት ነው፡፡

ጥንቅሩም የሚከተለውን ይመስላል፡፡ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች፣ ሰባት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሁለት የፓርላማ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና አራት የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችን ይይዛል፡፡ ይኼ እንግዲህ ገለልተኛ ሰዎችን ለመሾም ነው፡፡

ከዚህም ብዙ ነገሮችን መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ግን ሁለት አንድምታዎችን ብቻ መርጠናል፡፡ አንደኛው ከኮሚቴው ውስጥ ዘጠኙ የገዥው ፓርቲ አባላት ብቻ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡ ሥልጣን የያዘው ፓርቲ ማንም ይሁን ማን አፈ ጉባዔዎቹ ከገዥው ፓርቲ ውጪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሰባት የፓርላማ አባላት ከተባለ በኋላ ከተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ሁለት እንደሚመረጥ መቀመጡ፣ ሰባቱ የገዥው ፓርቲ እንዲሆኑ ታቅዶ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ከኮሚቴው አብላጫው ከአንድ ፓርቲ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ፣ ከሰብዓዊ መብት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አካላትን ሙሉ በሙሉ ያገለለ መሆኑን ነው፡፡ ለአብነት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሰብዓዊ መብት የጥናትና የትምህርት ማዕከላት፣ ወዘተ ከኮሚቴው ውጪ ናቸው፡፡ በኮሚቴው ውስጥ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው አካላት ቢያንስ በተቋም ደረጃ አልተወከሉም፡፡

በጥቅሉ ከአመራረጡ ጀምሮ ወደ አንድ ወገን ያዳላ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ከሚቀርቡት ዕጩዎች ውስጥ በፓርላማ ሁለት ሦስተኛ ድጋፍ ያገኘ ኮሚሽነር ሆኖ ይመረጣል፡፡ መቶ በመቶ በአንድ ፓርቲ በተሞላ ፓርላማ ውስጥ ከአስመራጭ ኮሚቴው መካከል የሚወከል ሁለትም ቢሆን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም አይኖሩም፡፡

ስለሆነም ከጅምሩም ሕጉ በራሱ በኮሚሽነሮች ምርጫ ብሎም ገለልተኝነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር የተመቻቸ ነው፡፡ አሁን እንዳለው ፓርላማ ከሆነ ደግሞ ሁኔታውን ያባብሰዋል፡፡ የተለያየ አመለካከት ያላቸውን አካላትም ሆነ የኅብረተሰብ ክፍል ለማካተት የተመቻቸ መደላድል የለውም፡፡

ሌላው ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ በዋስትናነት የሚያገለግለው የጥቅም ግጭት አለ የሚያስብሉትን ሁኔታዎች እንዲሁም በሚፈጠሩበት ጊዜ እንዴት መፈታት እንዳለባቸው አስተማማኝ ዘዴ ማስቀመጥን ይመለከታል፡፡ ጉዳዩን የበለጠ ለማስረዳት የጥቅም ግጭት እንዴት ሊፈጠር እንደሚችል አንድ ማሳያ ብቻ እንጥቀስ፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት በዋናነት ማጠንጠኛው ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችም ሊነሱ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ብሔር ነክ የሆኑ ግጭቶች ሲከሰቱ የሰብዓዊ መብትን ጥሰት ምርምራ ውስጥ የማይሳተፉ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ሆኑ ኮሚሽነሩን በተመለከተ በዝርዝር በሕግ መቀመጥ አለበት፡፡ ለምሳሌ ብሔርን መሠረት ያደረገ በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል ግጭት ተከስቶ የሚያጣራውም ሆነ ምርመራውን በበላይነት የሚመራው የኮሚሽኑ ሰዎች ከሁለቱ ብሔሮች ውጪ መሆን አለባቸው ማለት ነው፡፡ ይህም ሪፖርቱን እውነተኛ፣ እንዲሁም ተዓማኒ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

የፓርሱ መርሖችም ላይ የጥቅም ግጭት መቅረፍ የሚያስችል አሠራር መዘርጋትን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም ገለልተኛነት ከአስፈጻሚው አካል ብቻ ሳይሆን ከገዥውም ይሁን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከብሔር፣ ከሃይማኖት ተቋማት ተፅዕኖ የመሳሰሉትንም ይጨምራል፡፡

ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ዓለም አቀፋዊ ደረጃ

በእነዚህ መርሖች ላይ ተመርኩዞ ማረጋገጫና ዕውቅና የሚሠጥ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን የሚያቀናጅ ዓለም አቀፍ ኮሚቴ አለ፡፡ ኮሚቴው ሦስት ደረጃዎች አሉት፡፡ “ሀ”፣ ”ለ” እና “ሐ” ይባላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ የፓሪሱን መርሖች ያሟሉ ተቋማት የገነቡ ናቸው፡፡ ይህንንም ስለማከናወናቸው ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ኮሚቴውም አጣርቶ ላሟሉት ይህንን ደረጃ ይሰጣል፡፡ የተወሰኑ ሰነዶችን ያላሟሉ ቢሆንም እንኳን የ“ሀ” ደረጃን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ የሚጎድላቸውን በሌላ ጊዜ እንዲያቀርቡና እንዲያሟሉ ተጠባባቂ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

የ“ለ” ደረጃ ላይ የሚቀመጡት ደግሞ ተቋማት ኖሯቸው ነገር ግን የፓሪስን መርሖች የማያሟሉ አገሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያም የሚገኘው በዚሁ ደረጃ ውስጥ ነው፡፡ በአፍሪካ እነ ሩዋንዳና ቡሩንዲን ጨምሮ 18 አገሮች በ“ሀ” ደረጃ ላይ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቋም መገንባት ሲችሉ ኢትዮጵያ ግን እንዳቃታት ናት፡፡ አሊያም አልፈለገችም፡፡

የ“ሐ” ደረጃ ላይ የሚገኙት በዚህ ዓይነት የተመሠረቱ ተቋማት የሌላቸው ናቸው፡፡ የተሻለ መብት ጥበቃ የላቸውም ማለት ግን ላይሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲዊዘርላንድን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም እስካሁን ድረስ በ2013 ያገኘችውን ደረጃ ይዛ ሳታሻሽል ቀጥላለች፡፡ በተቃራኒው እንደውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ የተባባሰ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ገሀድ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ስለ ገለልተኝነቱ

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከላይ እንደተገለጸው አገሪቱን በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋርም የማገናኘት ሚና አለው፡፡ ይሁን እንጂ ልክ እንደ መንግሥት ሁሉ ስለሌሎች ተቋማት ቀና ሊባል የሚችል ምልከታ ያለው አይመስልም፡፡ መንግሥት እንደሚታወቀው ከአገር በቀል የሰብዓዊ መብትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጋር አወንታዊ የሚባል ግንኙነት የለውም።

በተለይ አንዳንዶቹን ጋር ደም የተቃቡ ግለሰቦች ያህል ፀበኞች የሆነ ይመስላል፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ ካሉት “ሒውማን ራይትስ ዎች” እና “አምነስቲ ኢንተርናሽናል”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ለሚያወጡት ወቀሳ የመንግሥትም የኮሚሽኑም ምላሽ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህንን የኮሚሽኑን መልስ ደግሞ በቅርቡ ኮሚሽነሩ ለኢኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሰጡት ቃለ ምልልስ መታዘብ ይቻላል፡፡

  • ጋር የመንግሥት ምላሽና አቋም የተለሳለሰ ወይንም ዝምታ ወይንም “ዋናው በሕዝባችን አመኔታ ማትረፉ ነው” የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በቅርቡ ኢትዮጵያን መጥተው የነበሩት የተባበሩት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር መጎብኘት ከፈለጓቸው አካባቢዎች ውስጥ የተወሰኑት አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡ የመንግሥትም ዋናው ምላሽ አገሪቱ ሉዓላዊ ስለሆነች ይኼንን ማድረግ ስለምትችል ነው የሚል ይዘት ያለው  ነው፡፡

ከቀረቡ ሪፖርቶች ውስጥም የምናገኘው ተመሳሳይ ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጠሩ ግጭቶችን አስመልክቶ ባለፈው ዓመት እንዲሁም በ2009 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ያደረገውን ምርመራ ተመሥርቶ ያጠናቀረውን ሪፖርት ለፓርላማ አቅርበዋል፡፡ በሁለተኛው ሪፖርቱ ላይ በጌዲኦ ዞን ተከስቶ የነበረውን ግጭትም አካትቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎን በተመለከተም ሪፖርት አቅርቧል፡፡ የቀረቡትን ሪፖርቶች መሠረት በማድረግ መንግሥትም ይሁን ኮሚሽኑ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እንዲጠናከሩና ለገለልተኝነቱም በምሳሌነት በማንሳት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህንና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስላላቸው ግንኙነት የኮሚሽነሩን ምላሽ እንመልከት፡፡

በአንድ ወቅት ሪፖርተር ጋዜጣ ለአሁኑ ኮሚሽነር “የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደረጃን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሚሰጣቸው ውጤቶች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ተቋማችሁ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? ምንስ ላይ ለመድረስ ያቅዳል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ብለው ነበር፡፡

ኮሚሽነሩም ሲመልሱ “ከተመድ በፊት ሕዝቡ እንዲፈርደን ያስፈልጋል የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ ሕዝባችንን ምን ያህል አርክተናል በሚል ነው፡፡ እኛ ራሳችንን በቅጡ መጠየቅ የሚገባን ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ላይ ነው ፍርድ ሊሰጡን የሚገባው፡፡”

ከኮሚሽነሩ ምላሽ መረዳት የምንችላቸው ቁምነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ከላይ ከተገለጸውና አገሪቱ በ2013 ያላገኘችውን/የተሰጠችውን ደረጃ ማስታወስ ይጠቅማል፡፡ የ“ሀ” ደረጃን ማግኘት ለምን እንዳልቻለች ሊነግሩንም ጭምር ይገባ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደገልጽነው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አገርን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጋር የማገናኘት ድርብ ሚና አላቸው፡፡

በእርግጥ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እጅግ ተፈላጊ ግብ ነው፡፡ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ተቋም በሌሎችም አያቅተውም፡፡ ይህ ዓይነቱ መልስ የሚጠበቀው ከአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ነው፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ኮሚሽኑ የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን መብት የሚመለከት ተልዕኮ ቢኖሩበትም ከቡድን በዘለለ፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆነን ሰውም ጭምር መሆኑ ላይ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በመሆኑ ከላይ ከሰጡት ምላሽ በተጨማሪም በቅርቡ ኢኤንኤን ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጹት ሳይሆን የተቋቋመው ለብሔረሰቦች ሳይሆን በጠቅላላው ለሰዎች መሆኑን ነው፡፡

ኮሚሽነሩ ስለሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርትና ነቀፌታ እንዲሁም ከምርጫ 1997 ዓ.ም. በኋላ የወጡ ሕግጋት የሰብዓዊ መብት ላይ ያላቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ምን እንደሚመስል ሲጠየቁም መልሳቸው ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ማውጣት ያለባትንም ይሁን የሌለባትን ሕግ የማታውቅና ነፃም የሆነች አገር እንደሆነች ያስረዳሉ፡፡ በተለይ የተወሰኑ ሕጎችን ማውጣት የለባችሁም፣ አልበለዚያም ቀይሩት የሚባል ነገር ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም በማለት መልሰዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አገሪቱ ሉዓላዊ ስለሆነች የሚል ነው፡፡ በዚህ ምላሻቸው ውስጥ እንደ ሰብዓዊ መብት ተቋም ኃላፊነታቸው የሰብዓዊ መብት ሁሉን አቀፍነት ደንበርም ሆነ ሌላ አጥር እንደሌለው በመውሰድ ከሉዓላዊነት ጋር እንዴት መጣጣም እንዳለበት ቢያስረዱ መልካም ነበር፡፡

የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕግን መውጣት ተከትሎ አብዛኞቹ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመዘጋታቸው የሚኖረውን ተፅዕኖ እንዲያብራሩ ሲጠየቁም የመለሱት የሚከተለውን ነው፡፡ “ከሴቶች ማኅበራት፣ ከወጣቶች፣ ከሕፃናት ጋር እንሠራለን፡፡ ከእነዚህ ማኅበራት ጋር የምንሠራው ዋናው ነገር የግንዛቤ ማስፋፋቱ ሥራ ተደራሽነቱ እንዲረጋገጥና ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ስናየው እኛ የተጎዳብን ነገር የለም፡፡ ማኅበራቱ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የማኅበረሰብ አካላት ጋር እየሠራን ስለሆነ እኛ ያጣነው የቀነሰብን ነገር የለም፡፡”

በተጨማሪም እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል፡፡ “የሲቪክ ማኅበራት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝብን ወክለው ያወጡት ሕግ ግን መከበር አለበት፡፡ ከሕጉ ጀርባ ደግሞ አሳማኝ የሆኑ ነጥቦችም አሉ፡፡”

ለማጠቃለል፣ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በርካታ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ይህን ሚናቸው ደግሞ በብቃትና በገለልተኝነት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጥብቅና መቆም ያለባቸውም ለሰብዓዊ መብት መከበር ነው፡፡ ከዚህ ረገድ አንደኛው አልቆ ሁለተኛው የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር ከታቀደ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ የመጀመሪያው መርሐ ግብር ምን እንዳመጣ የሚያውቀው መንግሥት ነው፡፡ ኮሚሽኑም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን ሲወጣ ከአስፈጻሚው በሚለይና በተሻለ መልኩ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ስለ ሰብዓዊ መብት ያለበት ሁኔታ የሚናገሩትን ማስተባበያ በመቀበል ብቻ ማንፀባረቅ መሆን የለበትም፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ የመንግሥት አካላትም ልክ እንደ ግለሰቦች በፍጥነት ለፍትሕ እንዲቀርቡ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እንደ ቂሊንጦው ማረሚያ ቤት ቃጠሎም ሰዎቹ ከተከሰሱ በኋላ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ፣ ሪፖርት ማቅረብ ማቋቋሚያ አዋጁን ከመጣሱ በዘለለ ለዓቃቤ ሕግ ተጨማሪ ማስረጃ የመሰብሰብ ድርጊት ዕርዳታ ማበርከት ነው፡፡ ተከሳሾቹንም መጉዳት ነው፡፡ የኮሚሽኑ መጠናከር ሕዝቡንም ይጠቅማል፡፡ መንግሥትንም ከዓለም አቀፍ ውግዘት ያድነዋል፡፡ ገለልተኛነቱም ኮሚሽኑ በተግባርም ሊያሳየን ይገባል፡፡

Reporter Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
የአዲስ አበባ አስተዳደር ለኳታር ኩባንያ 60 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ፈቀደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኳታር ግዙፍ ኩባንያ ኢዝዳን ሆልዲንግ ግሩፕ፣ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች መስተንግዶ መመርያ መሠረት 60 ሺሕ...

Close