ዛጎል ዜና – አርበኞች ግንቦት 7 ከትግራይ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደህሚት/ ጋር በጥምረት ለመስራት የሚያስችለው ደረጃ ላይ መድረሱን ለኢትዮጵያ ሲባል አስር ጊዜ ሞኝ ልሁን ያሉት ፐሮፌስር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አርቆ አሳቢዎች ቁጭ ብለው የሚመክሩበት ደረጃ ላይ መድረሱንም አወሱ። በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ትልቅ አገር አቀፍ ንቅናቄ እንደሚፈጥር ጠቆሙ። በኤርትራ ምድር ከሚነቀሳቀሰው የአማራ ድርጅት ጋርም ህብረት ለመፍጠር መቃረባቸውንም አልደበቁም።
” አስከዶም ሲከዳ ነገሮች ተበላሹ” ሲሉ ቀደም ሲል ከደሚት ጋር ተጀምሮ ስለነበረው ጥምረት ያወሱት የአርበኞች ግንቦት 7 መሪ፣ ድርጅቱ ክዚያን ጊዜ በሁዋላ ዓመት ያክል ራሱን ሲገመግምና በውስጡን ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ሲፈታ መቆየቱን አውስተዋል። ከሁለት ወር በፊት ጉባዔ አካሂደው አዲስ አመራር መሰየማቸውንና የጥምረት ንግግሩ መጀመሩን አመልክተዋል።
ከሁለቱም ወገን አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ግንባር ፈጥረው የሚታገሉበትን ህብረት ለመመስረት እየሰሩ መሆናቸውን ያስታወቁት አርበኛ ብርሃኑ፣ ” ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ ከሌሎች ጋር በመሆን ለመታገል በጉባኤ አቁዋም ይዘዋል” ሲል አክለዋል።
ከኦጋዴን ብሄአራዊ ነጻነት ግንባር ጋር ስምምነት ሲያደረጉ መነሻቸው ” ታሪክ ከቆፈርን የትም አንደርስም” በሚል ስምምነት እንደነበር ያወሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ በቀጣይ ስድስት ወር በሚሰራ ስራ አንድ ታላቅ አገራዊ ንቅናቄ እንደሚፈጠር ቃል ገብተዋል።
የጋምቤላ፣ የኦሮሞና የቤኒሻንጉል ድርጅቶች የተካተቱበት ቅንጅት አባል የሆነው ኦብነግ በቀጣዩ ንግግሮች ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር ህብረት ከፈጠሩት ድርጅቶች ጋር የጋር በመሆን የጋር ንቅናቄው እንደሚመሰረት ከማብራሪያቸው ለመረዳት ተችሏል።
ፕሮፌሰሩ ይህንን ሲናገሩ ” ከዚህ በፊት እንዳንነጋገር ያደረገንን የመገንጠል አጀንዳ እን\ትለዋለን” በማለት ለአንድነት ናፋቂዎች ተስፋ ሰጥተዋል። ይህንን ሲሉ እንደ ሞኝነት የሚቆጥሩ እንዳሉ በማስታወሰ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል አስር ጊዜ ሞኝ ቢሆኑ እንደሚመርጡ አመላክተዋል።
ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ የመገንጠል አጀንዳን ከጫንቃቸው ላይ ያወረዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሰባስበው በኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚመከሩ ሲያስገነዝቡ ” አማራውስ” የሚል ጥያቄ ሳይነሳ መልሱን እንደሚሰጡ በማስታከክ ነበር።
ራሳቸው ጥያቄውን አንስተው ሲመልሱ ” ኤርትራ ምድር የሚንቀሳቀስ የአማራ ድርጅት እንዳለ ታውቃላችሁ?” ነበር ያሉት። ስም ለይተው ካልጠሩት ድርጅት ጋር ንግግር እንደተጀመረና ” በውስጣችን የምናስተካክለው ነገር አለ ትንሽ ጊዜ ስጡን” ማለታቸውን ያወሱት ፐሮፌሰር ብርሃኑ፣ ይህ ንግግር በቅርቡ ተጋባርዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ታሪክን በማንሳት መወዛገብ እንደማይጠቅምና ታሪክን ታሪክ ለሚያጠኑት በመተው የዚህ ትውልድ ተጋብር ታሪክ መስራት ብቻ መሆን እንዳለበት የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ መጪው ትውልድ “ምን ሰራችሁልን? ምን አስቀመጣችሁልን?” ብሎ ስለሚጠይቅ እዛ ላይ ማተኮሩ አግባብ አንደሚሆን ምሳሌ በማንሳት ትምህርት ለመስጠት ሞክረዋል።
“እንደሚያስብ የዚህ ዘመን ሰው” በማለት የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማሳየት ምሳሌና ተሞክሮ እያጣቀሱ ንግግር ያደረጉት የአርበኞች ግንቦት 7 መሪ ” ነገሮች መልክ ሲይዙ አዲስ ነገር እንደሚፈጠር እናውቃለን” ሲሉም ተደምተዋል። አያይዘውም ጊዜው ጎረምሶች እየተነሱ የሚዘባርቁበት ሳይሆን አርቆ አስተዋዮችና የበሰሉ ወገኖች ቁጭ ብለው የሚመክሩበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የሳቸውን ንግግር ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ስያሜና ድርጅርት የሚጠሩ የማህበራዊ ገጽ ምዕራፎች አብጠልጥለዋቸዋል። ክፉኛም የዘለፉዋቸው አሉ። እሳቸው እንዳሉት የስድብና የተረት ዝናብም ያወረዱባቸው አሉ።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገነነ የመጣው የፌስ ቡክ የተቃውሞና የድጋፍ አምባጓሮ የሰለቻቸው እንደሚሉት በአማራ ስም የሚሰራጩ አቋሞችና መግለጫዎች ለምን ወደ አንድ ቋት እንዲመጡ አይደረግም ሲሉ ይጠይቃሉ። መተቻቸትና ተቃውሞም ካለ አግባብ ባለው መንገድ ለምን አይካሄድም ሲሉያክላሉ። እንዲሁም ያዋጣናል በሚሉት መንገድ ስድባና ተራ ዘለፋን በማስወገድ ለምን ትግላቸውን አይቀጥሉም ሲሉ ትዝብታቸውን ያስቀመጣሉ። ከሁሉም በላይ ግን እንደዚህ ተካሮ ወደ ተራ ዘለፋና ስድብ የተደረሰበትን አግባብ መነጋገርና ማስወገድ ያልተቻለበት መንገድ እንቆቅልሽ እንደሆናባቸው ሳይሸሽጉ ይናገራሉ።
ከፋኝ በሚል ስያሜ የሚጠሩትና በጎበዝ አለቆች ተደራጅተው ጦርነት በማካሄድ ያሉትን ክፍሎች ገድል አርበኞች ግንቦት 7 የራሱ እያስመሰለ ያቀርበዋል በሚል በንዴት ወደ ጥላቻ እንደገቡ የሚናገሩት ወገኖች፣ በበኩላቸው የተፈጠረው ችግር እንዲሁ በቀላሉ የሚፈታ አይደለም ሲሉ ይደመጣሉ። በዚህ የባለቤትነት ውዝግብ ባለበት የትግል ስፍራ በጦርነት ድል ስለመገኘቱ ከሁሉም ወገን መገለጹ እንደቀጠለ ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ ግጭቱ በአካባቢው ሚሊሻዎች ምላሽ የሚሰጠው ዓይነት መሆኑንን ከመግለጸ ባለፈ በይፋ ማስተባበያ አይሰጥም። ሆኖም ግን አስቸኳይ አዋጅ አውጆ በጥብቅ የሚቆጣጠረው አካባቢ ቢኖር የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እንደሆነ መርጃዎች ይጠቁማሉ።
አንዳንዴ የፍርድ ቤት ዜናዎችም ይህንኑ ችግር የሚያሳበቁ ሆነው ይታያሉ። ከዚህም በላይ የሰራዊት ማጓጓዝና አዲስ ምልምል ማዘጋጀት፣ ከሆስፒታል የሚወጡ መረጃዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያስተላልፉት መርጃዎች ግጭቱ ከኢህአዴግ በኩል እንደሚባለው ተቃሎ የሚታይ እንዳልሆነ አመላካች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *