ሃይማኖትና ፍልስፍና

በነፃነት የመስራትና ንብረት የማፍራት መብት፣ በምዕራብ አውሮፓ ሆነ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ባላቸው ሀገራት በሕገ-መንግስት የተደነገገና የሕግ ጥበቃ የሚደረግለት መብት ነው። ለምሳሌ፣ በምዕራብ አውሮፓ በህዳሴው ዘመን ጀምሮ በተዘረጋው ፖለቲካዊ አስተዳደር ስረዓት ውስጥ የግለሰብ ኢኮኖሚያዊ መብቶች፣ በተለይ በነፃነት የመስራት፣ ንብረት የማፍራት እና ንብረቱን በፍላጎቱና ምርጫው የመጠቀም፣ በዚህም የተሻለ ሕይወት የመኖር መብት የተረጋገጠው ኢኮኖሚው በካፒታሊዝም ስረዓት እንዲመራ በማድረግ ነው። በተመሳሳይ፣ የኢትዮጲያም ገበሬ በነፃነት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የማድረግ መብቱ በሕገ-መንግስቱ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጲያ ገበሬ በሕገ-መንግስት የተሰጠው መብት ያለ “ባህል አብዮት“ በካፒታሊዝም ስረዓት ብቻ ሊረጋገጥ አይችልም። በዚህ ፅሁፍ፣ የኢትዮጲያን ህዳሴ ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነውን የባህል አብዮት ከ14ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ባለው ግዜ ውስጥ በአውሮፓ ከነበረው የህዳሴ ጉዞ አንፃር ለማየት እንሞክራለን።

በህዳሴው ዘመን የምዕራቡ አለም ልሂቆች የታገሉት የሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን በግለሰቦች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከ5ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ታደርግ የነበረውን ተፅዕኖ ነበር። የቤተ-ክርስቲያኗ ተፅዕኖ መሰረቱ ግለሰቦች ዓለማዊና መንፈሳዊ የተቀላቀለበት ሕይወት እንዲመሩ በማስገደድ ነበር። ከ14ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የተደረገው ትግል የግለሰቦችን ሕይወት ከቤተ-ክርስቲያኗ ተፅዕኖ ነፃ ለማውጣት የተደረገ ነው። በመጨረሻም፣ ህዳሴው ሊረጋገጥ የቻለው ዓለማዊውን ሕይወት ከመንፈሳዊ ሕይወት መነጠል ነው። ማለትም፣ የሰዎችን ዓለማዊ ሕይወት በሕግ የሚስተዳድር ዴሞክራሲያዊ መንግስት በማቋቋም እና የቤተ-ክርስቲያኗ ተፅዕኖ በመንፈሳዊ (ዘላለማዊ) ሕይወት ላይ ብቻ እንዲወሰን ማድረግ የአውሮፓን ህዳሴ ማረጋገጥ ተችሏል። በዚህም፣ የሮማ ካቶሎካዊ ቤተ-ክርስቲያን በግለሰቦች ዓለማዊ እንቅስቃሴ ሆነ በመንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ እንዳትገባ በማድረግ የሕዝቦች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን በሕግ በመንፈሳዊ እሳቤ ሳይሆን በሕግ እንዲከበሩ ተደርጓል።

ነገር ግን፣ ከሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን በተለየ የኮፕቲክ ቤተ-ክርስቲያን ስር ካሉት፣ በተለይ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን፣ ከግብፅ፣ ሶሪያና ቱርክ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያኖች በተለየ በእስልምና ሃይማኖት ተፅዕኖ ስር አልወደቀችም። በዚህ ምክንያት፣ የስረዓቱ ባለቤት በሆነችው ግብፅ እንኳን ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ፣ ከእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የጠፋው ቢሆንም፣ ክርስትናን ከጥንታዊው የፈረኦኖች እምነት ጋር የቀላቀለ ሃይማኖታዊ ስረዓት አሁንም በኢትዮጲያ እንዲኖር አስችሎታል። በወር ውስጥ ያሉትን ቀናት መላዕክት ስም በመሰየም የመዘከሩ ተግባር በጥንታዊቷ ግብፅ በፈረኦኖች ዘመን የነበረ የእምነት ስረዓት ሲሆን፣ ሄሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ የታሪክ ፀኃፊ፣ በወቅቱ እምነቱ የሚተገበረው በአባይ ቄሶች (በሃይማኖቱ መሪዎች) ብቻ እንደነበር ይጠቅሳል። በዚህ ዘመን ግን፣ ከኢትዮጲያ በስተቀር በየትኛውም የአለም ክፍል ያለ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ዘንድ የሌለ ኃላ-ቀር የሆነ፣ የግብፃዊያን አስተሳሰብ ባርነት ቀንበር ምልክት ነው። ይህ ኃላ-ቀር የሆነ ለስራ ቀንና ሰዓትን እየቸረቸረ የሚሰጥ ስረዓት በሮማ ካቶሊካዊ ቤተ-ክርስቲያን የሚራመድ ቢሆን ኖሮ፣ በሁሉም የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ሕገ-መንግስት ውስጥ፣ “ማንኛውም ሰው፤ በፈለገው ግዜና ቦታ የፈለገውን ስራ የመስራት እና ንብረት የማፍራት፣ በዚህም የተሻለ ሕይወት የመኖር መብት አለው“ የሚል ድንጋጌ በማስቀመጥ፣ ይህን ያረጀና ያፈጅ ኋላ-ቀር የፈረኦኖች የአኗኗር ዘይቤ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንዲደመሰስ ያደርጉት ነበር። ነገር ግን፣ ቀንና ሰዓትን እየቸረቸረ የሚሰጥ ስረዓት ያለው፣ በኢትዮጲያ ብቻ ነው።

ለምሳሌ፣ እስኪ የእንድ ኢትዮጲያዊ አርሶ-አደር ገበሬን ሕይወት ለመታዘብ ሞክሩ። አብዛኛው የኢትዮጲያ አርሶ-አደር ገበሬ፣ ከወሩ 30 ቀናት በ15ቱ ብቻ ስራ ሰርቶ 30 ቀን፣ ጠዋት፣ ቀንና ማታ የሚበሉ ሕፃናት የሚያሳድግ ነው። ይህ ሕዝብ የሚኖረው በተዓምር እንጂ በሥራ ነው ለማለት ይከብዳል። ከድህነት ተጣብቆ የመኖር ሱስ ወይም ሥራ ላለመስራት ስንፍና ያለበት ከመሰላችሁም በጣም ተሳስታችኋል። ምንም ይሁን ምን፤ ስንፍና ከርሃብ እና ቸነፈር የበለጠ የሰውን ባህሪ አይገዛም። የኢትዮጲያ ገበሬ ድህነት ከጋህነም እሳት በላይ እንደሚፋጅ ጠንቅቆ ያውቃል። እጅ እና እግር ሰጥቶ፤ በላብህ ሰርተህ፣ ‘ጥረህ ግረህ ኑር’ ብሎ ያዘዘ አምላክ፣ በ12ኛው ከሰራህ ገሃነም ተገባለህ እንደማይል ያውቃል። እግዚያብሄር በእምነት የሚገኝ ፀጋ እንጂ በሃይማኖት የሚሰጥ ሽልማት እንዳልሆነ ልቦናው ያውቃል።

እርግጥ ነው፣ በአስተሳሰብ ባርነት ስር የወደቀ ግለሰብ ነፃ አስተሳሰብ እና የግንዛቤ ሊኖረው አይችልም። በዚህም፣ የተጫነበት የባርነት ቀንበር ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችል አቅም አይኖረውም። በመሆኑም፣ የኢትዮጲያ አርሶ-አደር ገበሬ የተጫነበትን የባርነት ቀንበር መጣል፤ ማነቆውን በጣጥሶ ለመጣል አይቻለውም። ግለሰቦች የአስተሳሰብ ባርነቱን መሰረት ባይረዱም ሥረዓቱ የግለሰብ መብትን የሚጨቁን መሆኑን ብቻ በመረዳት ሊታገሉት ይሞክራሉ። ሆኖም ግን፣ እንዲህ ያለ የአስተሳሰብ ባርነት በመሰረቱ ግለሰባዊ ሳይሆን ማህበራዊ ስለሆነ፣ ማህበራዊ ጥበቃ ይደረግለታል። ስለዚህ የባርነት አስተሳሰብ እራሱን አስጠብቆ መኖር ይቻለዋል። ይህም ግን ሌላ አይደለም፤ ሰው በግሉ እና በማህበር ሲሆን የሚያስበው የተለያየ ስለሆነ ነው። ማንም በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ መኖር አይሻም። ነገር ግን፣ እራሳቸውን ከዚህ አጉል ልማድ ለማውጣት አይቻላቸውም። ይህ ማህበራዊ ልማድ ነው፣ ደንብ እና መመሪያ አለው። ከማህበራዊ ሕይወት እንዲገለሉ ያደረጋል፣ ያስቀጣል፣ ያስወግዛል።

እያንዳንዱ ግለሰብ ግን፣ በግሉ፣ በእራሱ…ለእራሱ በወር 30 ቀን ስርቶ መኖር ይሻል። በማህበር ግን፣ እሱ የማይፈልገውን ከሌሎች ጋር ሆኖ በሌሎች ላይ ይጭናል። የሀገሬ ሕዝብ ሥራ እንዳይሰራ እጅ እና አዕምሮው ታስሯል። በተለይ የኢትዮጲያ አርሶ-አደር ገበሬ በአስተሳሰብ ባርነት ስር ወድቆ፤ የግብፅ የባርነት ቀንበር ተጭኖበት ዝንተ-አለም ድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ እንዲቀር ተፈርዶበታል። ከዚህ የድህነት አዙሪት መውጣት የሚቻለው፤ ይህ የድህነት አስተሳሰብ ከየት እና እንዴት እንዲህ እጅ እና አዕምሮችንን ሊያስረው እንደቻለ መረዳት ስንችል ነው።

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ሃይማኖት ያለ የሥልጣኔ ጠላት የለም። የምዕራባዊያን ከዚህ የሥልጣኔ መቅሰፍት የተረፈው በሕዳሴው ዘመን በነበሩ የምዕራብ አውሮፓ ምሁራን እና ፈላስፎች ባደረጉት ትግል ነው። የፕሮቴስታንቲዝም ሃይማኖት መምጣት ጋር ተያይዞ የሃይማኖት እኩልነትን በመደገፍ፣ ከግብፅ ሥልጣኔ ጀመሮ ሲወርድ-ሲዋረድ የመጣውን፤ ሃይማኖት እንደ ፖለቲካዊ፣ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ሥረዓት የመጠቀም ልማድን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥረዓት መግታት በመቻላቸው ምክኒያት የመጣ እድገት እና ብልፅግና፤ ሥልጣኔ ነው።

ethiothinkthank.com

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *