ኢትዮዽያ በቀጣይ አመት 10 ሺ ቶን ስኳር ወደ ኬንያ ልትልክ ነው።

 የስኳር ኮርፖሬሽን ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ የ2009 በጀት አመት አፈጻጸሙን አቅርቧል።

በሪፖርቱም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 የስኳር ፋብሪካ በመጋቢት ወር ስኳር ማምረት መጀመሩን የገለጸ ሲሆን ፥ሌሎችም የስኳር ፋብሪካዎች የሙከራ ምርት ማምረት መጀመራቸውን ነው የገለጸው፡፡

ሌሎቹ የስኳር ፋብሪካዎች እስከሚቀጥለው አመት መጀመሪያ ድረስ ወደ ማምረት የሚገቡ መሆናቸውን የኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብትሆ ገልጸዋል።

ፋብሪካው ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት ከቻለ እቅዱን ማሳካት የሚችልበት ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑንም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አለሚቱ ፉፋ ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ የ2009 በጀት አመት ሪፖርቱን ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ፥ በመጪው አመት አስር ሺህ ቶን ስኳር ለውጪ ገበያ አቀርባለሁ ብሏል።

የኮርፖሬሽኑ ስራ አፈፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብትሆ ስኳሩ ለኬንያ ለማቅረብ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ከዛሬ ሁለት እና ሶስት አመት በፊት ስኳር ኮርፖሬሽኑ ለውጪ ሀገር ገበያ ስኳር እንደሚያቀርብ እና ለሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ይፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፥ ይህንኑ ግቡን ማሳካት አለመቻሉን ተነስቷል፡፡

ካሁን ቀደም በምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ስኳር ፋብሪካዎችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ አልቻለም የሚል ወቀሳ የቀረበበት ኮሚሽኑ፥ዛሬ ለውጪ ሀገር ገበያ ስኳር አቀርባለሁ ማለቱ ምን ተማምኖ የሚል ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም እንደተናገሩት ፥የኦሞ ኩራዝ 2 ፣ከሰም፣ተንዳሆና አርጆ ዴዴሳ የስኳር ፋብሪካዎች በዚህ አመት ስኳር ማምረት መጀመራቸውን እንደ አንድ አስቻይ ሁኔታ ጠቅሰዋል፡፡

ነባር ፋብሪካዎች በተሻለ አቅም እንዲሰሩ እና አዳዲሶቹም በተጠናከረ ሁኔታ ስራ እንዲጀምሩ የማድረግ ጥረት በመደረጉ ለውጡ መምጣቱን ነው አቶ ጋሻው ያብራሩት፡፡

በተጨማሪም የገንዘብ አቅምና የቴክኖሎጂ ግብአትን ችግር ለመቅረፍም ጥረት እያደረገ መሆኑን በሪፖርቱ የጠቀሰው ኮርፖሬሽኑ፥ ኢንቨስትመንት ስራዎች የሚውል ፈንድ ማፈላለግን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር በሽርክና መስራትን መፍትሄ ማድረጉን ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ ከሼባ ቦንድ ለኩራዝ 2፣ 3እና 5 ፕሮጀክቶች ብድር ማግኘቱን እና ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክም 13 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ብድር መገኘቱን ጠቅሷል ።

ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነቶች መፈራረሙን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርቷል፡፡

በትእግስት ስለሺ አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *