ማይጨው ሰኔ 16/2009 ሰዎችን ከሀገር በማስኮብለል ለሞትና አካል ጉዳት ዳርጓል የተባለው ግለሰብ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የትግራይ ደቡባዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
በፍርድ ቤቱ የማይጨው ምድብ ችሎት ዳኛ አቶ ገብረኪሮስ አማረ እንደገለጹት ታደለ ሃፍቱ ካውዬ የተባለው ይሄው ግለሰብ ባለፈው ዓመት ሶስት ሰዎችን ወደ ሳውዲ አረቢያና የመን እልካችኋለሁ በማለት 11ሺህ 500 ብር በመቀበል በመኪና አሰፍሮ ከወሰዳቸው በኋላ በሽፍቶች እንዲገደሉ አድርጓል፡፡
እንዲሁም ከሌሎች ሁለት ግለሰቦች 4ሺህ 800 ብር ተቀብሎ ከሀገር አስኮብልሎ በሽፎቶች እንዲታገቱ በማድረግ ከቤተሰቦቻቸው ተጨማሪ ገንዘብ በመውሰድ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት መሆኑም ተረጋግጦበታል፡፡
አቶ ገብረኪሮስ እንዳስታወቁት ተከሳሹ በተለያየ የሀሰት መታወቂያዎች ስሙን በመለዋወጥና ገንዘብ በመቀበል ወደ ግብረ አበሮቹ የመላክ ተግባር ሲፈፅም ቆይቷል፡፡
ግለሰቡ ክሱን ለመከላከል ቢሞክርም በአቃቢ ህግ ማስረጃ ጥፋተኝነቱ በመረጋገጡ ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት ቅጣቱ የተወሰነበት መሆኑን ዳኛው ገልጸዋል፡፡