Written by ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)

the holy waterመጽሐፈ ብሉይ እንደሚነግረን፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ሁልጊዜ በውኃ ላይ ነው፡፡ ውኃን በአንድ ስፍራ ተሰብስቦ ሲያዩት ጉልበት፤ ግርማ ሞገስና ውበት አለው፡፡ ውኃ ለሥነ ፍጥረት ሁሉ መሠረት መሆኑም እሙን ነው፡፡ እናም ከሰው የተባረከና የተቀደሰ የመኖሩን ያህል ከውኃም የተባረከና የተቀደሰ አለ፡፡ እግዚአብሔር  በዘፍጥረቱ ገነትንና በገነት ውስጥ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ዛፎችን እንዲያጠጡ የፈጠራቸው ዐራት ወንዞች የተባረኩና የተቀደሱም ናቸው፡፡ በኋላ  የተጠመቀበት ባሕረ ዮርዳኖስም በቅዱስነቱና በፈዋሽነቱ ይታወቃል፡፡
ፈጣሪ ከሠራቸው ዐራት አፍላጋት ውስጥ የግዮንን (የዓባይን) ወንዝ በሁለተኛ ረድፍ አስቀምጦታል። (ዘፍጥ፤ 2፤ 13) ይኸውም የኢትዮጵያን ምድር  ሁሉ የሚከብበው ውኃ ነው፡፡ በመጀመሪያው  ክፍል  የምናገኘው ሉልና የከበረ ደንጋይ፤ ወርቅ የምናገኝበትና  የኤውላጥን ምድር ሁሉ  ቅዱስ ወንዝ  ኤፌሶንን (ፊሶንን) ነው፡፡ በሦስተኛው ተርታ  የተቀመጠው የተቀደሰው የጤግሮስ  ወንዝ ሲሆን ይኸውም በአሶራውያን ምድር የሚፈስሰው  ነው። ዐራተኛው የተቀደሰው ውኃም ኤፍራጥስ ነው፡፡ ጌታ በተወለደ ጊዜ በክርስቶስ በተአምራዊ ሥራው፣ የእኛው ወንዝ ግዮን ወደ ወተትነት ፤ ኤፌሶን  ወደ ወይንነት እንደተቀየሩ ከመጻሕፍት እንረዳለን። የዓባይ ወንዝ ግዮን ተብሎ መጠራቱም የታወቀ ነው፡፡
እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ አገላለጥ፤ ኢትዮጵያ የግዮን ምንጭ (የዓባይ ውኃ) ዙሪያዋን የሚከብባትና የሚያጠጣት የገነት ተምሳሌት ናት፡፡ ለምን ቢባል ከኢትዮጵያ በስተቀር  የግዮን ምንጭ  (የዓባይ ውኃ) ዙሪያዋን የሚከብባትና የሚያጠጣት
ሌላ ሀገር በምድር ላይ የለችምና ነው፡፡ የአልዌሮ፤ (ጋምቤላ (ዴዴሳ፤ (ወለጋ) ዳቡስና (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) ሌሎች ወንዞችም የዓባይን ወንዝ የሚከተሉ፤ አጅበው  ኢትዮጵያን የሚከብቡና አብረውት  ወደ ውጭ የሚፈስሱ አጋሮቹ ናቸው፡፡
የተቀደሰውን የግሽ ዓባይ የገነት ምንጭ  ውኃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማየት የቻልኹት የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፤ “ሕያው የጥበብ ጉዞ ወደ ዓባይ ጣና ምድር” በሚል መርሕ ግንቦት 12 ቀን 2009 ዓ. ም በቁጥር 75 የሚሆኑ ተጓዦችን  የዓባይ ወንዝ የውኃ ጋን ወደ ሆነቺውና ወደ ተቀደሰቺው የገነት ምንጭ ውኃ ግሽ ዓባይ፣ ሰከላ አቡነ ዘርዐ ብሩክ ገዳም ሄጀ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
የግሽ ዓባይ ምንጭ መነሻ የሆነቺው ሰከላ ወረዳ ናት፡፡ ሰከላ የምትገኘው  በጮቄ ሰንሰለታማ ተራራዎች ሥር ነው፡፡ ጮቄ በርካታ ወንዞች የሚፈልቁበትና ልዩ ልዩ ምንጮች  የሚመነጩበት፣ ውኃ አዘልና ውርጭ አዘል ተራራ ነው፡፡ የግሽ ዓባይ ስያሜ ከኢትዮጵያዊው ጻድቅ ከአቡነ ዘርዐ ብሩክ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይኸውም ዓባይ ወይም በአገውኛ አባዊ የሚለው የውኃው ስም ሳይዘነጋ፣ እኒህ ጻድቅ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በቦታው ላይ ተቀምጠው ሲጸልዩና  ሲያስተምሩ፤ የገነት ምንጭ በሆነው የዓባይ ውኃ ጸበልም በሽተኞችን  ሲያጠምቁበትና ሲፈውሱበት ነበር። በጉብኝቱ ወቅት  የደብሩ አገልጋይ የሆኑት መሪጌታ መርሐ ጽድቅ እንደተናገሩት፤ አቡነ ዘርዐ ብሩክ በዚህ ዓይነት የቅድስና ተግባር ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ ወደ ጎንደር ሲሔዱ መጽሐፎቻቸውን በጨርቅ ሸፋፍነው በዓባይ ምንጭ ውስጥ ደብቀዋቸው  ይጓዛሉ፡፡ ከሰባት ዓመት በኋላ ወደ ቦታው ይመለሱና ከዓባይ ጸበል መነሻ ላይ ሆነው መጽሐፎቻቸውን ለማግኘት ሲፈልጉ አባ ዘሩፋኤል የተባሉት ጓደኛቸው  ተገርመው፤ ”እንዴት በ7 ዓመት ይገኛል?” ይሏቸዋል።
አቡነ ዘርዐ ብሩክም ከምንጩ አናት ላይ ቆመው፣  ለዐራት ጊዜ  ጸሎት አድርሰው  ከጨረሱ በኋላ “ግሥዒ ግዮን መጻሕፍትየ” (ግዮን ሆይ መጽሐፎቼን ትፊ) ሲሉ መጽሐፎቹ አቧራ እንደለበሱ፤ ርጥበት ሳይኖርባቸው ተንኳፈው ወጥተዋል፡፡ ከዚያም ለጓደኛቸው፤ “አባ ይህንን ተአምር እይ” በማለት አሳዩዋቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የቦታው ስም  በግእዝ ግሥዒ ዓባይ ያሉት ቃል ተቀይሮ ግሽ ዓባይ እንደተባለ፤ ቦታውም ከገነት ወደ ዓለም እንደ ቧንቧ በሚፈስሰው ጸበል የተባረከና የተቀደሰ፤ ልዩ ምሥጢርም ያለው  ውኃ  እንደሆነ መሪ ጌታው አስረድተውናል፡፡
በዚህ ዓይነት የግሽ ዓባይ  ጸበል ከውኃው አናት ላይ ሲነሣ እንደ ትንሽ ምንጭ ይሆንና እዚያው ሰከላ ትንሽ ወረድ ሲል ደግሞ ማዕበል እየሆነ የግልገል ዓባይን ድልድይ ያቋርጥና በጣና ላይ እየሰፈፈና ቁልቁል ወደ ጢስ ዓባይ እየጎረፈ፤ በደጀን በኩል ወደ ሱዳን ካርቱም፤ ግብጽና ወደ ሜዲትራንያን ባሕር ወርዶ ይቀላቀላል፡፡ ይህ ወንዝ በሱዳኖችና በግብጾች ዘንድም  ቅዱስ ውኃ ነው ተብሎ ይታመንበታል፡፡
የዓባይ ውኃ፤ ከፖለቲካዊ ፋይዳውና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር፣ በባህልና በእምነት አንጻር የጎላ ሚና አለው፡፡ ውኃው በሚፈልቅበትና የዓባይ ወንዙ በሚፈስስበት ቦታ የሚኖረው ሰው ያመልከዋል፡፡ ተረት፤ በእንቆቅልሽ፤ በዘፈን፤ በግጥም፤ በቅኔ፤ በዜማ፤ በቀረርቶ፤ በፉከራ ያወድሰዋል። በስሙ ይጠራበታል፡፡ አዝመራውን ውርጭ እንዳይመታውና ትልና በረድ እንዳያጠቃው፤ ቤቱ ሁሉ በረከት እንዲኖረው፣ በሰኔ ሚካኤልና ጳጉሜ 3 ቀን በተቀዳ የዓባይ ጸበል ይረጫል፡፡
ከብቶች ተቅማጥ ሲታመሙ፤ እንዲሁም ያለ ሳንካ እንዲወልዱና እንዲራቡ የዓባይ ጸበል  በጨው እየተደረገ እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ መካን ሴትም በዓባይ ጸበል ትወልዳለች ተብሎ ይታመናል፡፡ ለምን ቢባል ከየገዳማቱ፣ በየተራራዎችና ሐይቆች ላይ ከሚገኙ አድባራትና ገዳማት  የሚፈልቁት የጸበል ውኃዎች፣ የገነት ምንጭ ከሆነው ከዓባይ ጋር ወርደው ሲቀላቀሉ ፈዋሾች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡
አንድ ሰው የዓባይን ወንዝ  ሲሻገር ትንሽ ቁጭ ይልና  የዓባይ አምላክ  ወደ አገሬ በሰላም መልሰኝ ብሎ ይማጸናል፡፡ ለዋና ወደ ዓባይ ለመግባት ያሰበ ሰውም ውሓውን ጠንቆል እያደረገ ደረቱን፤ፊቱን ያስነካዋል፡፡ መሐላም በዓባይ ይምላል፡፡

አዲስ አድማስ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *