alemneh mekonene

ዛጎል ዜና- በአማራ ክልል በተለይም በጎንደርና አልፎ አልፎ በባህር ዳርና በተለያዩ የጎጃም ክፍሎች የተለያዩ የግድያና የመንግስት መዋቅሮችና ንብረቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የሚያመለክቱ ዜናዎች መስማት የተለመደ ሆኗል። በማህበራዊ ገጾችም ሆነ በተለያዩ መገናኛዎች የሚወጡት የጦርነት መረጃዎች በመንግስት በኩል ማስተባበያ ወይም አጸፋዊ ዜና ሲቀርብባቸው አይሰማም።
በጎንደር የሚኖሩ ተከታታዮቻችንን በመጠየቅ እንደነገሩን፣ ታመነም አልታመነም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጠመንጃ ያነሱ ሃይሎች የተለያዩ ጥቃቶች ፈጽመዋል። እየፈጸሙም ነው። መጠነኛ የማጋነን ጉዳይ ቢኖርም፣ እስከ አሁን ድረስ “ሊናቅ የማይችል ትግል አለ” እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት ይህ በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰማው የትጥቅ ትግል ሕዝብ ጉያ ውስጥ ያለና ሕዝብ ከለላ የሚሰጠው ነው። ለዚህም ይመስላል ኢህአዴግ በተካነበት የደፈጣ ጥቃት የተቸገረው ሲሉም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
“ደርግ ህወሃትን በጊዜ አጣድፎ ይቀብረው ነበር። ዋናው ችግሩ የነበረው ትግሉና ታጋዮቹ ሕዝብ ጉያ ስር በመሆናቸው አፈር እየላሱ ተነስተዋል። ዕድሜ ቆጥረው ገዝፈዋል” ሲሉ በአማራ ክልል የተጀመረው የትግል ስትራቴጂ መመሳሰል እንዳለ የሚጠቁሙት የጎንደር ነዋሪዎች ” ልዩነቱ የፈለገው ቢመጣ ህወሃት ደርግ ትግራይን ለቆ እንደወጣው ጎንደርን ወይም የአማራውን ክልል ለቆ ይወጣል ተብሎ አለመታሰቡ ነው። እስከ መጨረሻው ይዋደቃል።በተመሳሳይ በአማራው ሕዝብ ዘንደ ያለው ቅያሜ እየከረረ በመሄዱ ችግሩ መልኩን ወደ አስከፊ ሁኔታ ሊቀይር ይችላል ” ሲሉ ስጋታቸውን ያክላሉ። የትግራይ እግር ኳስ ከለቦች አማራ ክልል መጥተው መጫወት የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸው፣ የአማራ ተጫዋቾች ትግራይ ሄደው መጫወት የማይችሉበት ደረጃ መደረሱንም ከሁሉም በላይ ያለውን ችግር ማሳያ አድርገው ይወስዱታል።
እንግዲህ ይህ እየትባለና ይህንን መሰል መረጃዎች እየወጡ ባሉበት ሰዓት ነው በባህር ዳር የከፍተኛ ባለስልጣን ዋና ጥበቃ ተገደለ የሚል መረጃ የወጣው። በአብዛኛው የባለስልጣናት የመጀመሪያ ደረጃ ጠባቂዎች የብአዴን ሰዎች እንደሆኑ በሚነገርበት ሁኔታ ይህ ዜና መሰማቱ ዜናውን የጎላ አድርጎት ሰብቷል። በገለልተኛ ሚዲያዎች ባይረጋገጥም ለስርዓቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ላይ ተወሰደ ከሚባለው ርምጃዎች ጋር መዳመሩ ብቻ ሳይሆን የወጥመዱ አቅጣጫ ከፍ ማለት ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው
የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዓለምነው መኮንን የግል ዋና ጠባቂ አንዋር አህመድ አሟሟት ግልጽ አይመስልም። ፖሊስ ራሱን አጠፋ ይላል። ዜናውን አስቀድሞ የዘገበው ኢሳት አቶ አንዋር መገደሉን ነው ምንጮቹን ጠቅሶ ይፋ ያደረገው። በማህበራዊ ገጾችም በተመሳሳይ የወጡት መረጃዎች ተመሳሳይና የድል ብስራት ይዘት ያላቸው ናቸው። ፖሊስ የሰጠው ማብራሪያ ብዙም የጠራ ባይሆንም አቶ አንዋር ህይወታቸው ስለማለፉ ያመነ ነው።
ሪፖርተር ያናገራቸው የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ መመርያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ሟች ራሱን እንዳጠፋ መረጋገጡን ነው ያስታወቁት። ሟች በራሱ ሽጉጥ ራሱን ሲያጠፋ የተኩስ ድምጽ በሆቴሉ ስለመሰማቱ ተጠይቀው ” ሬሳው የተገኘው አድሮና ውሎ ነው፡፡ ምናልባት ጥይቱ የተተኮሰው ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በኋላ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ ” ነው ያሉት። በተቃራኒው ‹‹አልጋ ይዘው ከጎን ያደሩት ሰዎች በአካባቢው የጥይት ድምፅ አለመስማታቸውን ነግረውናል›› ማለታቸውን ሪፖርተር ገልጿል።
ኢሳት እንዳለው ዋና ተፈላጊው በአማራ ክልል ህዝብ ዘንድ እና በራሱ በብአዴን ውስጥ ብዙም እንደማየወደዱ የሚነገርላቸው አቶ አለምነው መኮንን ነበሩ። ኢሳት ” ግድያው በዋናነት የተነጣጠርው በአቶ ዓለምንው መኮንን ላይ እንደነበር የሚገልፁት ምንጮች አጃቢያቸው ተባባሪ ሆኖ ባለመገኘቱ ሣይገደል እንዳልቀረ አመልክተዋል። ሟች ከአቶ ዓለምነህ ጋር የአንድ አካባቢ ሰዎች እንደሆኑም መረዳት ተችሏል” ምንጮቹ እንደነገሩት አመልክቶ ዘግቧል። ከግድያው ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል ወንጀል መከላከል ሃላፊ ኮማንደር አሠፋ ስንታየሁ ሥራቸውን መልቀቃቸውምንም ዜናው አክሏል።
ሟች በተደጋጋሚ የቦንብ ጥቃት ከተሞከረበት፣ በባህርዳር ቀበሌ 04 በሚገኘው ግሪንላንድ ሆቴል በሌላ ሰው ስም በተያዘ አልጋ መተኛቱን ኢሳት አመልክቷል። ለሪፖርተር መረጃውን የሰጡት ኮማንደር ዋለልኝ ሟች በተመሳሳይ በተጠቀሰው ሆቴል አልጋ መያዙን አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ በማን ስም አልጋ እንደይዘ አልተናገሩም፤ ጥያቄውም አልቀረበላቸውም። ከዚሁ ድንገተኛ ግድያ ጋር በተያያዘ በራሳቸው ፈቃድ ስራ ለቀቁ ስለተባሉት የፖሊስ መኮንንም የተባለ ነገር የለም። በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ስለመኖራቸውም አልተገለጸም። ከዚሁ ጋር የተያያዘ ይሁን በሌላ በይፋ የተባለና ለግድያው ሃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም በኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ተባባሪዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ እቅድ እንዳለ በተደጋጋሚ ሲነገር መሰንበቱ አይዘነጋም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *