ሰማይ ሙሉ ህይወት — ሰማይ ሙሉ ሲሳይ — ይኖራል ቢባልም
ይህ ሁሉ ባንድ ላይ — አለ ቢሉኝ እንኳን — ካንቺ ሳቅ አልድንም።
መዳን ምን ያደርጋል — መዳን የት አባቱ
ባንቺ መሞት ማለት — ሩቅ ነው ልኬቱ
ጥልቅ ነው ስሌቱ
ባንቺ መሞት ማለት — ሰፊ ነው ግዛቱ
አለም ነው ርስቱ
.ያ ግሩም ጨዋታሽ
መሰረቱ ሰፊ — መሰረተ-ጽኑ
መሰረተ ህይወት — ተዋበ ዘመኑ
.ያ ግሩም መአዛሽ
እንደ አደይ አበባ — ልብን የሚሠልበው
በማያልቅ ‘ሽክርክሪት — ጎትቶ ጎትቶ — ገነት የሚያገባው
.
ያ ግሩም ውበትሽ
እንደ አደይ አበባ — ውሥጤን ያሥደመመ
ውበትሽ ሳይደክም — አይኔን ያደከመ
.
ያ ግሩም ድምቀትሽ
እንደ አደይ አበባ – – ብርሃን የሚተፋ
መንገደኛው ሁሉ — በጨረርሽ ታግዞ– ዙሪያሽ የማይጠፋ
.
ያ ግሩም ፈገግታሽ
እንደ አደይ አበባ — ከሩቅ የሚጣራው — ቀልብን አንሰፍስፎ
ተናፋቂው ሳቅሽ – – ለሠው እንደሚሠጥ — ወዛወዝሽን ጨልፎ
.
በእነዚህ ሃብቶችሽ — ሃብቶቼ በሆኑት
ካንቺ እየፈለቁ — ለኔ በሚፈሱት
እምልልሻለሁ
ብትመጪም ባትመጪም — እጠብቅሻለሁ