አምስት ተጠርጣሪ ተከሳሾች በነፃ ተሰናበቱ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የተመሠረተባቸው የሽብር ወንጀል ክስ በወንጀል ሕጉ ተቀይሮ እንዲከላከሉ ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ብይን ተሰጠ፡፡

ከአቶ በቀለ ጋር አብረው የተከሰሱ 16 ተከሳሾችም በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1፣ 3፣ 4 እና 6)ን ተላልፈዋል ተብለው የቀረበባቸው ክስ ወደ አንቀጽ 7(1) ተቀይሮ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ሌሎች አምስት ተከሳሾች ዓቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ እንዳላቀረበባቸው ተገልጾ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ፣ ብይን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

አቶ በቀለ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኛነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1፣ 3፣ 4 እና 6)ን ተላልፈዋል ተብለው የቀረበባቸው ክስ፣ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ከእስር እንደተፈቱ ኦፌኮን ሽፋን በማድረግ በውጭ አገር ከሚገኙ የኦነግ አመራሮች ጋር አሜሪካ ተገናኝተዋል፡፡ ከተገናኙ በኋላም የሽብርና የአመፅ ተልዕኮ ተቀብለው ወደ አገር ውስጥ በመመለስ የተቀበሉት ተልዕኮ ኦሮሚያ ላይ እንዲቀጣጠል ተልዕኮ በመስጠትና ሥራ በመከፋፈል፣ እሳቸው በአዳማ ከተማ፣ አብረዋቸው የተከሰሱት አቶ ጉርሜሳ አያኖ በቡራዩ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ በአምቦ ከተማ፣ አቶ አዲሱ ቡላላ በጉጀላን ቡሌሆራ እንዲሰማሩ አመራር ሰጥተዋል የሚል ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ያስረዱልኛል ያላቸውን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተገኙ የሰነድ ማስረጃዎችን ያቀረበ ቢሆንም፣ የቀረቡት ማስረጃዎች አቶ በቀለ የሽብር ተግባር ወንጀልን ስለመፈጸማቸው የሚያስረዱ ሳይሆን፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 ማለትም በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን መፈጸማቸውን የሚያስረዱ ሆነው እንዳገኛቸው ፍርድ ቤቱ በብይን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ በክሱ የጠቀሰውን አንቀጽ የቀየረው አቶ በቀለ በኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በአመፅ እንዲደራጁ፣ በአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች እንዲፈርሱ፣ እንዲቃጠሉ፣ መንገዶች እንዲዘጉ፣ በፀጥታ ኃይሎችና ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ሰነዶቹ እንደሚያስረዱ በመግለጽ ነው፡፡

በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ሰነዶች አቶ በቀለ በተለይ የጉራጌና የሥልጤ  ተወላጆች ከኦሮሚያ መውጣት እንዳለባቸው በመግለጽ ያስተላለፉት ትዕዛዝ፣ ተስማምተው የሚኖሩ ሕዝቦችን ለአመፅ ማነሳሳት መሆኑን እንደሚያስረዱና ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ቢሆኑም፣ መንግሥትን ማውረድ የሚቻለው በምርጫ ብቻ በሚደረግ ውድድር ሒደት መሆኑን እያወቁ በኃይል ከሥልጣን ለማውረድ ያስተላለፉት መልዕክት አግባብ አለመሆኑን የሚያስረዱ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ በብይኑ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም አቶ በቀለ ዓቃቤ ሕግ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 14 እና 23(1) መሠረት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያገኘው ማስረጃ፣ ከላይ የተጠቀሱትን የሚያስረዱ ሆነው በመገኘታቸው በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/አ 113(2) መሠረት በመቀየር፣ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 257(ሀ) ማለትም ‹‹መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር›› የሚለውን መተላለፋቸውን በማስረዳቱ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

አብረዋቸው ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ጉርሜሳ አያኖ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ አዲሱ ቡላላም በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ረብሻና ብጥብጥ እንዲስፋፋ በማድረጋቸውና በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ባስተላለፉት የቅስቀሳ መልዕክት አመፁ እንዲስፋፋ በማድረጋቸው፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1)ን ተላልፈው በሽብር ተግባር ወንጀል ውስጥ መሳተፋቸውን የሚያሳይ በመሆኑ ተቀይሮ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ ሌሎቹም ተከሳሾች የተጠቀሰባቸው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ ወደ አንቀጽ 7(1) ተቀይሮ እንዲከላከሉ ተበይኗል፡፡ ጭምሳ አብዲሳ፣ ፍራኦል ቶላ፣ ጌታቸው ደረጀና ሀልካኖ ቆንጮራ የተባሉ ተከሳሾች፣ የቀረበባቸው ማስረጃ ድርጊቱን እንደፈጸሙ ለማስረዳት ብቃት እንደሌለው ተገልጾ፣ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ተሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠው ዓቃቤ ሕግ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 14(1) እና 23(1) መሠረት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስላቀረበ በቀጥታ ተወስዶ ሳይሆን፣ የአግባብነታቸው ነገር እንደ ማንኛውም ማስረጃ ከእያንዳንዱ ተከሳሽና ከቀረበበት ጉዳይ አንፃር እየታየ ወይም እየተመዘነ መሆኑን፣ ፍርድ ቤቱ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ብይኑን አስታውቆ እንደጨረሰ፣ የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ማመልከቻ፣ አቶ በቀለ የተጠቀሰባቸው አንቀጽ መቀየሩን ተከትሎ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጥያቄያቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ነግሮ፣ የመከላከያ ምስክሮችን ለማስማት ከነሐሴ 8 እስከ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር አማርኛ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *