Skip to content

መስፍን ኢንጂነሪንግ የሕንድ ትራክተሮችን መገጣጠም ጀመረ

ከተለያዩ የአውሮፓ ተሽከርካሪ አምራቾች ጋር ስምምነት በመፍጠር  አውቶሞብሎችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም የጀመረው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ ሶናሊካ የተባለውን የሕንድ ትራክተሮች አምራች ምርቶችን በኢትዮጵያ መገጣጠም ጀመረ፡፡

መስፍን ኢንጂነሪግ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት በመፈጸም እየገጣጠማቸው ከሚገኙ የቤት አውቶሞብሎችና የጭነት ተሽከርካሪዎች ባሻገር የእርሻ መሣሪያዎችን ለመገጣጠም ከሕንዱ ኩባንያ ጋር በገባው ውል መሠረት፣ በኢትዮጵያ የተገጣጠሙትን የመጀመሪያዎቹን ትራክተሮች ቅዳሜ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

ከመቀሌ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ውቅሮ ከተማ የተገነባው የትራክተር መገጣጠሚያ፣ በአሁኑ ወቅት ለገበያ ያቀረባቸው ትራክተሮች፣ ከ60 እስከ 110 የፈረስ ጉልበት ያላቸው ሕንድ ሠራሽ፣ የሶናሊካ ኩባንያ ብራንዶች ናቸው፡፡  ትራክተሮቹ ይፋ በተደረጉበት ፕሮግራም ወቅት እንደተመለከተው፣ የውቅሮው ፋብሪካ በወር 240 ትራክተሮችን የመገጣጠም አቅም አለው፡፡

ከመስፍን ኢንጅነሪንግ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ ከትራክተሮቹ በተጨማሪ ሌሎች የእርሻ መሣሪያዎችንም ለመገጣጠም ዝግጅት መጠናቀቁን፣ ሌሎችም ለእርሻ ሥራ የሚውሉ መሣሪያዎች ማለትም መከስከሻ፣ ማረሻ፣ መዝጊያና የመሳሰሉት ማሽኖች ይገኙባቸዋል፡፡

ሶናሊካ ኩባንያ በሕንድ ከሚገኙ አምራቾች ሦስተኛው ግዙፍ ትራክተር አምራች ነው፡፡ ከ20 የፈረስ ጉልበት ጀምሮ በተለያየ ደረጃ እስከ 120 የፈረስ ጉልበት ያላቸው፣ በፍጥነታቸው፣ በማሳ ዝግጅትና በችግኝ ተከላ፣ በአጨዳና በሌሎችም የእርሻ ሥራዎች መስክ አገልግሎት የሚሰጡ ልዩ ልዩ የትራክተር ሞዴሎችን በማምረት ምርቶቹን በ80 አገሮች ውስጥ ማሰራጨት የቻለ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1969 የተመሠረተው ሶናሊካ ኩባንያ እስካሁን ከ300 ሺሕ በላይ ትራክተሮችን በማምረት ለዓለም ገበያ ማቅረቡም ይነገርለታል፡፡

መስፍን ኢንጅነሪንግ ከዚህ ቀደም ከቻይናው ጂሊ የተሽከርካሪ አምራች ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት፣ የጂሊ ሞዴል የቤት አውቶሞቢሎችን በመገጣጠም ይታወቃል፡፡ ባለፈው ዓመትም ከታዋቂው የፈረንሣይ አውቶሞቢል አምራች ፔዦ ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት፣ የተለያዩ የቤት አውቶሞቢሎችን በመገጣጠም ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ከሚታወቀው የጀርመኑ ኤምኤኤን (MAN) ኩባንያ ጋር በደረሰው ስምምት መሠረትም፣ የኩባንያውን ምርቶች መገጣጠም ጀምሯል፡፡

በትግራይ መልሶ ማቋቋም የኢንዶውመንት ፈንድ (ትዕምት) ሥር ከሚተዳደሩ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነውና የመስፍን ኢንዱስትሪያል እህት ኩባንያ የሆነው ትራንስ ኢትዮጵያ በበኩሉ፣ የስካንያ የጭነት ተሽከርካሪዎችና አውቶብሶች የጅቡቲና የኢትዮጵያ ወኪል ሆኖ ለመሥራት ከስዊድኑ ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈጸሙ ይታወቃል፡፡

ምንጭ – ረፖርተር 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

Read previous post:
“ችግር ላይ ነን” የቆሼ አደጋ ተጎጂዎች

ከ130 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የቆሼ የቆሻሻ ክምር መደርመስ አደጋ ከተከሰተ አምስት ወራት ቢያስቆጥርም፣ በወቅቱ ከአደጋው ተርፈው ዕገዛ ይደረግላቸዋል ተብለው...

Close