·        ለአምስት ጊዜያት፣ በስልክ እና በደብዳቤ መልእክት ሲያደርሳቸው ቆይቷል

·        በከፍተኛ ትምህርት ቢያመካኙም፣ ከአጠናቀቁ ሁለት ዓመታት አልፏቸዋል

·        “ወደ ሀገሬ ልገባ ነው፤ ብለው ብንሸኛቸውም ቃላቸውን አጥፈዋል” /ምእመናን/

 

ለመንፈሳዊ አመራርና አገልግሎት ከተመደቡበት የሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ሀገረ ስብከት ተነሥተው ወደ ሀገር ቤት እንዲዛወሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቢወሰንም፣ ሳይመጡ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠሩት ብፁዕ አባ ኤዎስጣቴዎስ ሊቀ ጳጳስ፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ፣ የመጨረሻ ጥሪና ማስጠንቀቂያ ተላለፈላቸው።

ሊቀ ጳጳሱ እንዲመለሱ ከተወሰነበት ጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በስልክና በደብዳቤ ተደጋጋሚ መልእክት ሲያደርሳቸው እንደቆየ ያወሳው የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ቀኖናዊ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ጥሪ እንዲደረግላቸው በግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው መወሰኑን ጠቅሷል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ለስድስተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ለሊቀ ጳጳሱ ባስተላለፈላቸው ጥሪ፣ እስከ መጪው ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ሀገር ገብተው ለጽ/ቤቱ እንዲያሳውቁ መታዘዛቸውን ገልጿል። “ካልመጡ ግን ቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የሚገደድ መሆኑን ጉባኤው ወስኗል፤” በማለት አስጠንቅቋል – በቁጥር 245/699/2009 በቀን 18/09/2009 ዓ.ም.፣ ለብፁዕነታቸው በአድራሻ በጻፈላቸው ደብዳቤ።

ብፁዕ አባ ኤዎስጣቴዎስ ሊቀ ጳጳስ፣ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም. በተካሔደውና በቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርእሰ መንበርነት በተመራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ፣ ከነበሩበት የካሊፎርኒያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሲነሡ፣ የተዛወሩት ወደ ባሌ ሀገረ ስብከት እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል።

ይኸው ውሳኔ ከተላለፈበት ወቅት ጀምሮ፣ “ቅዱስ ሲኖዶስ ሊያነጋግርዎ ስለሚፈልግ ወደ ሀገርዎ እንዲገቡ” በሚል፦ ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም.፣ ኅዳር 8 ቀን 2004 ዓ.ም.፣ ታኅሣሥ 18 ቀን 2005 ዓ.ም.፣ ግንቦት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. እና ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፈላቸው አምስት ደብዳቤዎችና በስልክም ተደጋጋሚ መልእክት ቢያደርሳቸውም እንዳልመጡና ለጉዳዩም የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት እንዳልቻለ ጽ/ቤቱ በደብዳቤው አትቷል።

ምንጮቹ እንደገለጹት፣ ሊቀ ጳጳሱ ወደ ሰሜን አሜሪካ ሲመደቡ፣ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስነት እንዲሠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውንም እንዲቀጥሉ በቀድሞው ፓትርያርክ እንደተፈቀደላቸው በዐውደ ምሕረት ይናገሩ ነበር፤ ወደ ሀገር እንዲመለሱ ሲጠየቁም የሚሰጡት ምክንያት፣ “ትምህርቴን ልጨርስ” የሚል ነበር። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በአሜሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት ጊዜ እንዳገኟቸውና “ወደ ሀገር ቤት ይግቡና ሲኖዶሱ በሚመድብዎት ስፍራ ሓላፊነትዎን ይወጡ፤” እንዳሏቸው፤ ብፁዕነታቸውም፣ “የጀመርኩትን ትምህርት ልጨርስና እገባለሁ፤ በቤተ ክርስቲያን ስም ቃል እገባለሁ፤ ትምህርቴን እንድጨርስ ብቻ ይፈቀድልኝ፤” በማለት እንደተማፀኑና ለዚህም የቪዲዮ ማስረጃ እንዳላቸው ምንጮቹ አስረድተዋል።

አያይዘውም፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ከሁለት ዓመት በፊት እንዳጠናቀቁና፣ “በ2008 መጀመሪያ ወደ ሀገሬ እገባለሁ፤ የቤተ ክርስቲያኔን ወቅታዊ ፈተና ፊት ለፊት ሆኜ እዋጋለሁ፤” በማለታቸው፣ “በበጎ አድራጊ ካህናትና ምእመናን፥ መሸኛ ተደርጎላቸው፤ መዋጮውም ተበርክቶላቸው ነበር፤” ያሉት ምእመናኑ፣ “ይሁንና ቃላቸውን አጥፈው፣ የቤተ ክርስቲያን ፈተና ወደ መሆን እየተሻገሩ ነው፤” ሲሉ አማረዋል። ከቅዱስ ሲኖዶሱና ከፓትርያርኩ ተደጋጋሚ ጥሪ በተጨማሪ፣ በሚቀርቧቸው ካህናትና መምህራንም ተደጋጋሚ ምክር ቢሰጣቸውም፣ “ሰዉ በብዙ መከራና ገንዘብ የሚመጣባትን ርስት ምድር አሜሪካንን ጥዬ አልወጣም፤ እንዲህ ያለ ሐሳብ ወደ እኔ ይዛችሁ አትምጡ፤” በሚል ወደ ሀገር ቤት ላለመመለስ እያንገራገሩ እንዳሉ፣ ለዝግጅት ክፍሉ በከፍተኛ ሐዘን ገልጸዋል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ትላንት ማምሻውን ድረስ፣ በዚያው በአሜሪካ የሚገኙት ሊቀ ጳጳሱ፣ ለቅዱስ ሲኖዶሱ የመጨረሻ ጥሪና ማስጠንቀቂያ፣ የሰጡት ይፋዊ ምላሽ የለም። ብፁዕ አባ ኤዎስጣቴዎስ ሊቀ ጳጳስ፣ በነሐሴ 1997 ዓ.ም.፣ በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አንብሮተ እድ ከተሾሙት 17 ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ ሲሆኑ፤ በካሊፎርኒያ ከመመደባቸው በፊት፣ የተሾሙት በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ነበር። በከፍተኛ ትምህርታቸው፣ በሥነ መለኰት የዶክትሬት ዲግሪ ማግኘታቸው ተገልጿል።

የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ሕግ እንደሚደነግገው፥ ሊቀ ጳጳስ የሚሾመው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ሀገረ ስብከት ወይም አስፈላጊ የሥራ ቦታ ሲሆን፤ ተጠሪነቱም ለቅዱስ ሲኖዶሱ ነው። ሊቀ ጳጳሱ ሲሾም ከተመደበበት ሀገረ ስብከት ሊዛወር አይችልም። ይሁንና፣ በሥራ ወይም በሌላ አጥጋቢ ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር አስፈላጊ ከሆነና በተመደበበት ቦታ ለመቆየት አስቸጋሪ ሆኖ ከተገኘ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተጠንቶ በውሳኔ ሊዛወር ይችላል። የኤጲስ ቆጶስነት ማዕርጉንም፣ ያለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በገዛ ራሱ ለመተው አይፈቀድለትም።

sendeknewspaper

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *