የደቡብ አፍሪቃ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ሊከሰሱ ይችላሉ ሲል ዛሬ ውሳኔ አሳለፈ። በፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሠረት ዙማ በጎርጎሮሳዊው 1990 ከተፈፀሙ የጦር መሣሪያ ግዥ ውሎች ጋር በተያያዙ 800 በሚሆኑ የሙስና ክስ ጭቦች ሊከሰሱ ይችላሉ። በዙማ ላይ ተይዞ የነበረው የክስ ጭብጥ እንዲሰረዝ የሐገሪቱ አቃቤ ሕግ ከዚህ ቀደም ውድቅ አድርጎት ነበር። ይሁን እና የበታች ፍርድ ቤት የአቃቤ ሕጉን ውሳኔ በመቃወም ክሱ እንዲቀጥል በ2016 ወስኗል። ፕሬዝዳንት ዙማ ክሱ እንዲቀጥል መወሰኑን በመቃወም ሲከራከሩ ነበር።
የዛሬውን ውሳኔ ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤታቸው የሚያበሳጭ ብሎታል። ተንታኖች እንደሚሉት ዙማ እና ፓርቲያቸው የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት። ከደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዲርክ ኮትዘ ።«እንደሚመስለኝ ለዙማ ቡድን ሆነ ለአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በአጠቃላይ ይህ መጥፎ ዜና ነው። ምክንያቱም ውሳኔው ጉዳዩ እንደገና በፍርድ ቤት እንደሚታይ ያረጋግጣል ፤ ፕሬዝዳንት ዙማም ክስ ሊመሰረትባቸው ይገባል። ይህ ደግሞ ብዙ ጥርጣሪዎችን ያጭራል።»
ዛሬ ያስቻለው ፍርድ ቤት ዳኛ ኤሪክ ሊህ ከዚህ ቀደም ክሱ ተቋረጠ ማለት በዛ ጉዳይ ላይ ሌላ ምርመራ አይደረግም ማለት አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። ተቃዋሚው የዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ ከ2009 ዓም አንስቶ ከዘር መድልዎ ስርዓት በኋላ ከተፈፀሙ አወዛጋቢ ወታደራዊ ውሎች ጋር የተያያዙ 783 የክስ ጭብጦች እንደገና እንዲንቀሳቀሱ ሲታገል ቆይቷል። በሙስና በማጭበርበር እና በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በማዘዋወር የሚከሰሱት ዙማ በተደጋጋሚ ንጹህ ነኝ ይላሉ። ጀርመን ሬዲዮ