* ያለውን የስኳር እጥረት ለመቅረፍ ከአልጀሪያ 366ሺ፣ ከታይላንድ 334ሺ በድምሩ 700ሺ ኩንታል ስኳር በመግዛት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሕጋዊ የግዥ ሂደት ተጠናቅቆ ስኳሩ ጂቡቲ ወደብ የደረሰ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አገር ውስጥ መጓጓዝ ይጀምራል፡፡

*ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ ከሞያሌ የተመለሰውን ስኳር 10 ኩንታሉን በ 500 የአሜሪካ ዶላር ሂሳብ 100ሺ ኩንታል ለመሸጥ በሰነድ ስምምነት ቢያደርግም ስኳሩ የተላከው ምንም አይነት ቅድመ ክፍያ ሳይፈጸምበት እንደነበርም ጠቁሟል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን 700 ሺ ኩንታል ስኳር በግዢ ወደ አገር ውስጥ ሊያስገባ ነው፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት ያለውን የስኳር እጥረት ለመቅረፍ ከአልጀሪያ 366ሺ፣ ከታይላንድ 334ሺ በድምሩ 700ሺ ኩንታል ስኳር በመግዛት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሕጋዊ የግዥ ሂደት ተጠናቅቆ ስኳሩ ጂቡቲ ወደብ የደረሰ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አገር ውስጥ መጓጓዝ ይጀምራል፡፡

ከውጭ ከሚገባው ስኳር ባሻገር ሰሞኑን ከሞያሌ ወደ አገር ውስጥ የተመለሰው 44ሺ ኩንታል በምግብ መድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በኩል ፍተሻ እየተደረገበት እንደሚገኝ ገልጸው፤ ጤናማነቱ ሲረጋገጥ ለገበያ እንደሚውልና ይህም ወደ አገር ውስጥ እየገባ ካለው ስኳር ጋር ተዳምሮ የአቅርቦቱን ችግር እንደሚያቃልል አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ባወጣው ኮታ መሰረት ለአዲስ አበባ ሸማቾች 112ሺ፣ ስኳርን በግብዓትነት ለሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች 170ሺ፣ ለክልሎች 287ሺ በድምሩ 569ሺ ኩንታል በወር ኮርፖሬሽኑ ማቅረብ ቢገባውም አቅርቦቱ መስተጓጎሉን በተለይም ለኢንዱስትሪዎች የሚሰጠው መቋረጡን ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በ2009 በጀት አመት በአምስት ስኳር ፋብሪካዎች አምስት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማምረት አቅዶ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ አማካኝነት በሸንኮራ አገዳ ማሳ ላይ ባጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በተለያዩ ፋብሪካዎች ላይ በደረሱ ጉዳቶች ምክንያት 3 ሚሊዮን 500ሺ ኩንታል ብቻ ማምረቱንና ይህም አሁን ላጋጠመው የስኳር እጥረት አንዱ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ እጥረት እያለ ወደ ኬንያ የተላከው ስኳር ኬንያ ባጋጠማት ድርቅ ስኳር ለመግዛት ጥያቄ በማቅረቧ ኮርፖሬሽኑ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በማሰብ ወደ ውጭ ለመላክ ያዘጋጀውን 100ሺ ኩንታል ለመሸጥ መወሰኑንና ግዥውን ከፈጸመው « አግሪ ኮሞዲቲ ኤንድ ፋይናንስ » ከተባለ የውጭ ኩባንያ ጋር 10 ኩንታል በ500 ዶላር ሂሳብ ውል መፈራረማቸውን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ጋሻው ማብራሪያ ኮርፖሬሽኑ ስኳሩን በ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በሰነድ ስምምነት ቢሸጥም በገለልተኛ አካል የተረጋገጠ የክብደት ማረጋገጫ አልተሰጠም በሚል ምክንያት ገዥው ኩባንያ ምንም አይነት ክፍያ አልፈፀመም፡፡ ሆኖም ምንም አይነት ኪሳራ ቢደርስ ኩባንያው ተጠያቂ እንደሚሆን ኮርፖሬሽኑ ደብዳቤ በመጻፍ ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

የስኳር ሽያጩ የተከናወነው የኮርፖሬሽኑ ስራ አመራር ቦርድ ለኮርፖሬሽኑ ባስቀመጠው ራዕይ መሰረት በአለም ላይ ስኳር ከሚያመርቱ አስር አገራት ተርታ ለመሰለፍ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት፣ ልምድ እንድታገኝ በማስፈለጉ፣ የሎጂስቲክ አቅሙን ለማወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ኮርፖሬሽኑ አትራፊ የልማት ድርጅት በመሆኑ የስኳር ዋጋ በአለም ገበያ ሲቀንስ ገዝቶ ማስቀመጥ፣ ሲጨምር መሸጥና የሚገኘውን ገቢ ለፋብሪካዎች ጥገና ማዋል እንዲቻልና የውጭ ምንዛሬ ለማስግኘት ታስቦ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

«ኩባንያው ስኳሩን ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚወስድለትን አካል በማወዳደር ከብራይት ትራንስፖርት ማህበር ጋር ውል የተፈራረመ ቢሆንም፤ በዋናነት ስኳሩ ሊመለስ የቻለው በትራንስፖርት ማህበሩና በገዥው ኩባንያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ነው» ያሉት አቶ ጋሻው፤ ይህም ማህበሩ 110 ተሽከርካሪዎችን በማዘጋጀት እያንዳንዱ ተሽከርካሪ 400 ኩንታል በመጫን ስኳሩ እንዲጓጓዝ ቢያደርግም፤ ሞያሌ ሲደርስ በኬንያ የመንገድ ህግ አንድ ተሽከርካሪ ጭኖ ሊያልፍ የሚችለው 280 ኩንታል ብቻ በመሆኑ መግባት እንደማይችሉ መደረጋቸውንና የትራንስፖርት ክፍያውን ሙሉ በሙሉ መክፈል ባለመቻሉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ብራይት ትራንስፖርት ማህበር ጭነቱ ሳይራገፍ በመቆየቱ ምክንያት ስኳሩ በሙቀት ሃይል መበላሸቱን፣ የተሽከርካሪዎች ጎማና ባትሪ መጎዳቱንና አሽከርካሪዎቹ ለማህበራዊ ቀውስ መዳረጋቸው በመጥቀስ ኮርፖሬሽኑ ስኳሩን እንዲቀበላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን፤ የማጓጓዣ ወጭውን እንደሚሸፈንና ለሚደርሰው ኪሳራም ተጠያቂ እንደሚሆን በመተማመን ስኳሩ ተመላሽ እንዲሆን መደረጉን አቶ ጋሻው ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ፤ ኮርፖሬሽኑ በ2010 በጀት አመት ስምንት የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎችን ማለትም ወንጂ፣ ፊንጫ፣ መተሃራ፣ ከሰም፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ተንዳሆ፣ ኦሞኩራዝ ቁጥር 1 እና 2 ወደ ስራ በማስገባት ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት አቅዷል።

ፋብሪካዎቹ የክረምት ጥገናቸውን አጠናቀው ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ሲመቻችም የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን በፋብሪካዎቹ ብቻ ማሟላት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 20/2010

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *