ታይትንና አጭር ቀሚስን ተሻግሮ በአደባባይ ብቅ ያለው ሱሪም ቀሚስም አይደለም – እምብርት እንጂ ፡፡ እንኳን ከዘመነ ጭን ወደ ዘመነ እምብርት አሸጋገራችሁ – አልናቸው እህቶቻችንን ፡፡  እምብርትን አጋልጦ ለማሳየት መደበኛ ሱሪም ሆነ ታይት መጠቀም ይቻላል ፤ ከላይ ደግሞ አጭር አላባሽ ፡፡ እድሜያቸው 14 እና 15 ያልሞላቸው ህጻናት ፣ የደረሱ ወጣቶች ፣ ብዙ ልጆች ያፈሩ እናቶች ሳይቀሩ እምብርታቸውን በየአደባባዩ አሰጡት ፡፡ ለብዙ ወንዶች ትርጉሙ ግልጽ አልነበረም ፡፡

‹‹ ምን ዓይነት ዘመን ነው  ዘመነ ዲሪቶ

አባቱን ያዘዋል ልጁ ተጎልቶ ››

እያለ አቀንቅኗል ድምጻዊ ተሾመ ደምሴ ፡፡ ተሾመ ልማዳዊው ህግ ወይም ስርዓት ተጣርሷል የሚል ጭብጥ ለማስተላለፍ የሞከረ ይመስላል ፡፡ ዜማውን በምሳሌያዊ አነጋገር ለውጡ ብንባል

‹‹ዘመነ ግልንቢጥ

ውሻ ወደ ሰርዶ

አህያ ወደ ሊጥ ›› የሚባለውን ብሂል መጥቀሳችን አይቀሬ ነው ፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ምን ዓይነት ዘመን መጣ ያሰኘው የሴቶቻችን አፈንጋጭ አለባበስ ነበር ፡፡ ዘንድሮ ዘመነ ግልንቢጥ የተባለው ደግሞ በወንዶች ጉዳይ ሆኗል ፡፡ ለመሆኑ እንዴት ነው አህያ ወደ ሊጥ የሄደው ? የሚለውን ጥያቄ ከመፈተሻችን በፊት ትንሽ ስለቀደመው እናውራ ፡፡

ስለሴቶቹ …

መቼም ዘመኑን ሆን ብሎ የሚያጠና ሰው ቢኖር ስለ እያንዳንዱ ግዜና መጠሪያ ስለሚሆነው ጉዳይ ስያሜ አያጣለትም ፡፡ ለአብነት ያህል በ1997 አካባቢ ሴቶቻችን በታይት ተወረው ነበር ፡፡ ይህን ግዜ ‹‹ የታይት ዘመን ›› ብሎ መጥራት ይቻላል ፡፡ የዛኔ የዘፈን ውድድር አለመፈጠሩ እንጂ ለታይት ለባሾቻችን ‹‹ ቀይ ›› ፣ ‹‹ ቢጫ በቀይ ›› ‹‹ ሙሉ አረንጓዴ ›› እያልን ጥሩ ማነጻጸሪያ መስጠት በተቻለ ነበር ፡፡ ታይት የሰውነት ቅርጽንና ውበትን አጋልጦ የማሳየት ኃይሉ ከፍተኛ ስለነበር ራሳቸውን ‹‹ ለቁምነገር የሸጡ ›› ወጣቶችም ጥቂቶች አልነበሩም ፡፡

አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ታይትን ያለ ግልገል ሱሪ በማጥለቅ በየጎዳናው የሚያለከልኩ ወንዶች እንዲበዙ አድርገዋል ፡፡ የነዚህኞቹ ግብ በወንዶች ላይ ‹ ሙድ › ይዞ መዝናናት ይሁን ወይም የግብዣ ማስታወቂያ መስራት በውል የሚታወቅ አልነበረም ፡፡ ለሚነሳባቸው የተጃመለ ትችትም ‹‹ መብታችን ነው ! ›› በማለት የተንዥረገገ ነገር ግን የማይበላ የወይን ፍሬ ነው የሚባልለትን ህገመንግስት ተደግፈው የሚያወሩ ሴቶች ጥቂቶች እንዳልነበሩ እናስታውሳለን ፡፡ ህገመንግስቱ እንኳን የማስልበስን ራሱ የመገንጠልን ካባ በመከናነቡ አያስገርመንም የሚሉ አሽሟጣጮች በበኩላቸው የትራክተር ጎማ የሚያህል መቀመጫ ያላት ሴት በታይት ተወጣጥራ ስትንከባለል እያየን ላለማሳፈር መጣር ከጨዋነት አያስቆጥርም ይሉ ነበር ፡፡ ድርጊቱ የሳቅ ቧንቧን ቷ ! አድርጎ በመክፈቱ በየቦታው አይንና አፍን በመሸፈን የሚንፈቀፈቁ ሰዎች እንዲበራከቱ መንገድ ከፍቷልና ፡፡

ከዚህ ዘመን በኃላ ደግሞ አጭር ቀሚስ የፋሽን መገለጫ ሆኖ መጣ ፡፡ በርግጥ አጭር ቀሚስ ከማለት ይልቅ መሃሉ የተከፈተ ቁምጣ ማለት እውነቱን ቀረብ ያደርገዋል ፡፡ ሴቶቹ ቁጭ ሲሉ ገላቸውን ላለማሳየት ያቺን ምላስ የምታህል ጨርቅ በግድ ሊያረዝሟት ሲታገሉ ማየት ያስቃል ፡፡ ‹ ለምን ለበሱት – ለምን ይጨነቃሉ ? › የሚል ገረሜታ አእምሮን ይወራል ፡፡ የሴቶችን ፍላጎት ጠንቅቀን እናውቃለን የሚሉ ሴት አውሎች ግን በለበሱት ለመጨናነቅ ፣ ለማፈር ፣ የይቅርታ ፊት ለማሳየት መሞከር ሁሉ ድምር ውጤቱ ‹ ሆን ተብሎ የሚተወን የትኩረት መሳቢያ ድራማ  › ነው ባይ ናቸው ፡፡ በርግጥ አጭር ቀሚስ ወዲህ ወዲያ ሲሄዱበት የሚያምር ከሆነ በመቀመጥ ግዜ ገላን ላለማጋለጥ ነጠላ ወይም ሻርብ ነገር እግር ላይ ጣል ማድረግ በተቻለ ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ግን ከስንት አንድ ናቸው ፡፡ ስለዚህ የአጭር ቀሚስ አላማ ከፋሽንነትም በላይ የሚሻገር ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችን ሀሳብ መናቅ የትም አያደርስም ፡፡  ዘንድሮ ይህ ድርጊት ተገልብጦ በመምጣቱ የጭን መጋለጥ ሴቶችን ‹ አያሰጋም › ፡፡ ሱሪያቸው ግን ከኃላ ሆን ተብሎ ያጠረ በመሆኑ ለምሳሌ ያህል ከታክሲ የሚወርዱ ሴቶች መቀመጫቸውን ላለማሳየት ከላይ የለበሱትን ልብስ እስኪቀደድ ድረስ ወደታች ይጎትቱታል ፡፡ እኛም ልብስ መቀየሪያ ክፍል የገባን ያህል ላለማሳፈር ይሁን ላለመሳቀቅ ፊታችንን እናዞራለን – በጨዋ ደንብ ፡፡ ከወረዱ በኃላ ደግሞ  ‹ ምን ያለበሰቸውን ሱሪ ለመልበስ ትታገላለች ! ›  በማለት እናብጠለጥላታለን – በሀሜት ደንብ ፡፡

ታይትንና አጭር ቀሚስን ተሻግሮ በአደባባይ ብቅ ያለው ሱሪም ቀሚስም አይደለም – እምብርት እንጂ ፡፡ እንኳን ከዘመነ ጭን ወደ ዘመነ እምብርት አሸጋገራችሁ – አልናቸው እህቶቻችንን ፡፡  እምብርትን አጋልጦ ለማሳየት መደበኛ ሱሪም ሆነ ታይት መጠቀም ይቻላል ፤ ከላይ ደግሞ አጭር አላባሽ ፡፡ እድሜያቸው 14 እና 15 ያልሞላቸው ህጻናት ፣ የደረሱ ወጣቶች ፣ ብዙ ልጆች ያፈሩ እናቶች ሳይቀሩ እምብርታቸውን በየአደባባዩ አሰጡት ፡፡ ለብዙ ወንዶች ትርጉሙ ግልጽ አልነበረም ፡፡

ሴቶቹ በደፈናው ‹‹ ፋራ አትሁኑ ! ፋሽን ነው ›› አሉ ፡፡ መነሻው ህንድ ይሁን ሱርማ ፤ ጥቅሙ ሀሴት ያምጣ ግርማ ልብ ያለ ግን አልነበረም ፡፡ ወንዶቹ ‹‹ ከፋሽኑ ጀርባ ምን አለ ? ›› በማለት ጠየቁ ፡፡ ይህ ጥያቄያቸው በተለይ ከውበት ጋ የተያያዘ ነበር ፡፡ ምክንያቱም ወንዶች ጸጉር ፣ አይን ፣ አንገት ፣ ጡት ፣ ዳሌ ፣ ሽንጥና ባት እያሉ ሊያዜሙ ፣ ሃሳባቸውን ሊገልጹ ወይም ሊጽፉ ይችላሉ ፡፡ እስካሁን ግን ‹‹ እምብርትሽ ›› ብሎ ያቀነቀነ ዘፋኝ ወይም የጻፈ ደራሲ ወይም ያደነቀ አፍቃሪ አልተሰማም ፡፡ ታዲያ የእምብርት ፋይዳ ምን ይሆን ? መባሉ ግድ ነው ፡፡ አንዳንድ ሴቶች እምብርታቸው ላይ ጉትቻ እስከማንጠልጠል በመድረሳቸው ወንዶቹ እንደሚከተለው አሾፉ ‹‹ እምብርት ምድር ቤት የሚገኝ ጆሮ ነው  እንዴ ? ›› ወይም ‹‹ ከላይኛው የጆሮ ገጽ የዞረ መሆኑ ነው ? ››

ስለ ወንዶቹ …

እነሆ ዘመኑ ተገልብጦ ሴቶች በወንዶች ድርጊት እያዘኑ አልፎ አልፎም እያስካኩም ይመስላል ፡፡ የሴቶቹ እምብርት ተረት ሆኖ የወንዶቹ ቂጥ ወቅታዊ ማፍጠጫ ጉዳይ ስለሆነ ፡፡ ምናለፋችሁ በከተማችን ‹‹ የሚዝረከረኩ ወንዶች ›› ተበትነዋል ፡፡  ‹ እረ ወንድ ልጅ ሴታ ሴት ሲሆን ያስጠላል ! › የሚሉ ቆነጃጅትና እማወራዎች በዝተዋል ፡፡ ‹ ልጆቻችን ምን እስኪሆኑ ነው የምንጠብቀው ? › በማለት በሴት እድሮችና ማህበሮች ላይ ጉዳዩ የመወያያ አጀንዳ እንዲሆን የጣሩ ሴቶች ሞልተዋል ፡፡ ‹ ግብረ ሶዶማዊያን በዛ እያሉ እግዚኦ የሚሉ የሃይማኖት ተቋማትና ጋዜጠኞች የወንዶችን ልብስ መጣል እንዴት ዝም ብለው ያያሉ ? › የሚሉ ተቆርቋሪ እህቶች ሰሚ ያጡ ይመስላሉ ፡፡

የሀገራችን ሴቶች ወንዶች ቀበቷቸውን እንዲያላሉ በህጋዊ መንገድ የሚጠይቁት በአንድ መንገድ ብቻ ነው  ፤ በምጥ ወቅት ፡፡ በርግጥ  በፍቅር ጨዋታ ወቅት የሚኖረውን ውልቂያ የትኛው ክፍል እንደምንመድብ ሳያስቸግርን አይቀርም ፡፡ ታዲያ ዛሬ በህገወጥ መንገድ ቀበቶ አላልቶ ፤ ሱሪውን ከወገቡ ቁልቁል አርቆ ፤ የውስጥ ሱሪውንና የቂጡን ቀዳዳዎች እያስጎበኘ ላይ ታች በሀገራዊ ኩራት የሚጓዘው ‹ ትንሽ – ትልቅ › አበዛዙ ቀላል አልሆነም ፡፡

ወደው አይስቁ አሁን ይመጣል ፡፡ አንዳንድ የውስጥ ሱሪዎች የተቀደዱና ውሃ ካያቸው ዘመናት ያስቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ  ፡፡ አንዳንድ የውስጥ ሱሪዎች ደግሞ ገመዳቸው ላልቶ ነው መሰለኝ ወደ ውስጥ የሰመጡ ናቸው ፡፡ በተለያየ ምክንያት የሚጎነበሱ ፋሽነኞች ታዲያ የሚያስጎበኙት የተራቆተ መቀመጫ በንጽህ ወንድ / አፍቃሪ ግብረሶዶም እና እንስት ባልሆነ / ከታየ ለአይን የሚቆረቁር ፣ የመንፈስ ልዕልናና ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ነው ፡፡ ምክንያቱም  የአንዳንድ ሰው ቂጥ በጎርፍ የተቆረሰ ደለል ይመስላል … የአንዳንድ ሰው ቂጥ በላብና እድፍ ተቦክቶ ልስን የሚጠብቅ ግድግዳ ይመስላል … የአንዳንድ ሰው ቂጥ ወፍጮ ቤት ከዋለ ፊት ጋር  አንድ ነው ፡፡

አሁን ደግሞ የማይገባዎትን ጥያቄ ይወረውራሉ ፡፡ ፋሽኑ ሱሪው ነው ? የላላው ቀበቶ ነው ? ፓንቱ ነው ? የፓንቱና ሱሪው ደረጃ ሰርቶ መታየቱ ነው ? ወይስ የሰውየው ቂጥ ? ከግርምት ፣ ትዝብትና ሳቅ በኃላ ለመሆኑ ምንድነው ዓላማው ? ወይም ፋሽን ተከታዮቹን ምን ያህል ያስደስታል ? ለማለት ይገደዳሉ ፡፡ አብዛኛው ፋሽን ተከታይ በጆሮ ፣ ጸጉር ፣ ጃኬት ፣ ቲሸርት ፣ ጫማ ወዘተ ላይ ሲታይ እንደቆየው የዘመናዊነት መገለጫ ሳያካብዱ መመልከት እንደሚገባ የሚያስገነዝቡ ናቸው ፡፡ ፋሽን ይመጣል ፋሽን ይሄዳል እንዲሉ … ለምን ይቅርብኝ  ወይም ከማን አንሳለሁ በሚል ድሃ መነሻ የማያምርባቸውን ብቻ ሳይሆን የማያውቁትን ነገር የሚከውኑ ወንዶችም ሴቶችም የሚታዘንላቸው ናቸው ፡፡ እነዚህ ምስኪኖች ከሚሆኑትና ከሚለብሱት ዉጪ ስለ ጉዳዩ  አነሳስና ከጀርባው ስለሚጠረጠረው ጉዳይ ለማሰብ ግዜ የሚወስዱ አይደሉም ፡፡ 

 አነሳሱ  …

ሱሪን ከቂጥ በታች አውርዶ መልበስ የተጀመረው በአሜሪካ እስር ቤቶች ውስጥ ነው ፡፡ Sagging Pants ይሉታል ፡፡ እስረኞች ቀበቷቸውን ራሳቸውን ለመግደልና በሌሎች ላይ ወንጀል መስሪያ መሳሪያ ማድረጋቸው ስለተደረሰበት እንዳይጠቀሙ ታገደ ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰፊ ቱታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ሱሪያቸው ታች መውረዱ ግድ ሆነ ፡፡

የጀርባው ንባብ  …

ይህ ‹‹ ፋሽን ›› በጥርጣሬ ጨጎጊቶች የተከበበ ነው ፡፡ አንዳንዶች በእስር ቤት ልብስን ዝቅ አድርጎ መልበስን የሚያገናኙት ከግብረ ሶዶማዊነት ተግባር ጋ ነው ፡፡ የወሲብ ግንኑነታቸው መጠቆሚያ ስልት ነው በማለት ፡፡ አንዳንዶች የእስር ቤት አስተሳሰብ መሆኑን በመግለጽ በተለይ ጥቁሮች ‹ አሁንም እስር ላይ ነን › የሚል መልዕክት ያስተላልፉበታል ይላሉ ፡፡ አንዳንድ ጉዳዩን ያጠኑ ምሁራን ደግሞ ‹‹ በአሜሪካ የባርነት ዘመን ነጭ አለቆች የአፍሪካን ጥቁር ወንዶች አስገድደው ይደፍሯቸዋል ፡፡ ተግባሩ ከተፈጸመ በኃላ ተጠቂው ሱሪውን ዝቅ አድርጎ እንዲለብስ ይደረጋል ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አለቃው በቀጣይነትም ግንኙነት መፈጸም ሲፈልግ በቀላሉ እንዲለየው ነው ›› በማለት ቃላችን ርግጠኛ ነው ሲሉ ይደመጣሉ ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ በ 1990ዎቹ አካባቢ የሂፕ ሆፕ አርቲስቶች ሱሪን አውርዶ መልበስን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወታቸው ብዙዎችን ያስማማል ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ባህልና ፋሽንን ከመግለጽ በተጨማሪ የነጻነት ማሳያም እንደሆነ ይጠቆማል ፡፡

በዚህ እሳቤ የኛዎቹ ፋሽን ተከታዮች ምን መልዕክት እያስተላለፉ መሆኑ ግራ ያጋባል ፡፡ በርግጥ በሀገራችን ግብረሰዶማዊነት እየተስፋፋ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ የሱሪው መውረድ ሰምና ወርቅ ፋሽንና ያልተለመደ ወሲባዊ ግንኙነትን እያመላከተ ይሆን ?  ግብረ ሰዶማዊያን ለመግባቢያነት ይረዳቸው ዘንድ ጆሮአቸው ላይ ጌጥ ያደርጋሉ ፤ ሱሪ አውርደው ከሚፏልሉት ወገኖቻችን ገሚሶቹም ጆሮአቸውን ማስዋብ ይወዳሉ ፡፡ ግብረ ሰዶማዊያን  አንድ ጆሮ ላይ ጌጥ ካደረጉ ‹ አልተያዝኩም › ማለት ፈልገው ነው ፤ ሱሪ አውራጆቻችንስ ‹ አልተያዝኩም › ነው ወይስ  ‹ የማውቀው ነገር የለም ›  እያሉ  ነው የሚገኙት ፡፡ ሀገራችን እንደ ሌሎች አፍሪካዊያን ቅኝ ያልተገዛችና የባርነት ቀንበር ያልቀፈደዳት ቢሆንም ከሀገራዊ ባርነት መቼ ተላቀን እያሉበት ይሆን ? ነው አለማቀፉን ምልከታ ያልተረዳ ተራ የፋሽን ጉዳይ ?

ያን ግሩም ሙዚቀኛ ‹ ተቀበል ! › ማለት አሁን ነበር ፡፡

አቦ ተቀበል ! አፈሩ ይቅለልህና

‹ እሺ ልቀበል ! › …

‹‹ ምን ዓይነት ዘመን ነው በል ! ››

‹ ምን አይነት ዘመን ነው › …

‹‹ ምን አይነት ዘመን ነው – ዘመነ ዥንጉርጉር

 በምናገባኝ ቅኝት በኬሬዳሽ መዝሙር

 እንደሰጡት ሆኖ እንዳጣው የሚያድር

 አይገደውም ከቶ

 ‹ አይገደውም ከቶ › …

ለማያውቀው አንቀጽ ውል አጥብቆ ሲያስር

 በእውር ፈረስ ጀርባ ሽምጥ ሲኮረኩር ››

በልልኝ አቦ !!

‹  በእውር ፈረስ ጀርባ ሽምጥ ሲኮረኩር › …

ማስታወሻ፡- ይህ ፅሑፍ በቁም ነገር መፅሔት ቅፅ 12 ቁጥር 159 ላይ የወጣ ነው፡፡ ፅሑፉን በሌላ ሚዲያ ላይ የምትጠቀሙ ከሆነ ምንጩን እንድትጠቅሱ ትለመናላችሁ፡፡

Alemayehu Gebeyehu አሌክሶ ገጽ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *