ስለ ወቅታዊ የሀገራችን ኹኔታና ሰላም፡- በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት፣ ከጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ፣ ለኹለት ሱባዔ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፤ ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሠተው ግጭት ተወግዶ ሙሉ ሰላምን የማስፈኑ ሥርዓት ተፋጥኖ እንዲረጋገጥ ጠይቋል፤ በግጭቶቹ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻችን፣ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባለው መዋቅር የብር 6 ሚሊዮን ድጋፍ […]

via የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጠናቀቀ፤ ከጥቅምት 27 ቀን ጀምሮ የኹለት ሱባዔ ጸሎተ ምሕላ ዐወጀ፤ ባለ17 ነጥቦች መግለጫ አወጣ — ሐራ ዘተዋሕዶ

ስለ ወቅታዊ የሀገራችን ኹኔታና ሰላም፡-
 • በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት፣ ከጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ፣ ለኹለት ሱባዔ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግተወስኗል፤
 • ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሠተው ግጭት ተወግዶ ሙሉ ሰላምን የማስፈኑ ሥርዓት ተፋጥኖ እንዲረጋገጥ ጠይቋል፤
 • በግጭቶቹ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻችን፣ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባለው መዋቅር የብር 6 ሚሊዮን ድጋፍ እንዲደረግ ተስማምቷል፤
 • ኅብረተሰቡ፥ በትዕግሥትና በመቻቻል፣ በመከባበርና በመናበብ፣ በመደማመጥና በመግባባት መንፈስ በአንድነት ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪውን አስተላልፏል፤
 • ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ አህጉር የነጻነት ምልክት እንደኾነች ኹሉ የሰላምና የጸጥታም ምልክት መኾን አለባት፤
 • በውጭ ሀገር ከሚኖሩ አባቶች ጋር ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም አኹንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ውሳኔ አሳልፏል፤
Related stories   በእነ ጃዋር የህክምና ጥያቄ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሁሉንም ተከራካሪዎች ጥያቄ ውድቅ አደረገ፤ ቃሊቲ ሆነው ይታከማሉ፤

የውግዘት እና እግድ ውሳኔዎች፡-
 • በጋሻው ደሳለኝ የተባለ ግለሰብ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ለምእመናን ሲያስተላልፍ የነበረው የክሕደት ትምህርት በመረጃ ተሰብስቦ ችግሩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ከቀረበ በኋላ፣ ከ15/02/2010 ዓ.ም. ጀምሮ የክሕደት ትምህርቱን በማውገዝ ከቤተ ክርስቲያናችን እንዲለይ ተደርጓል፤ በቤተ ክርስቲያናችንም ስም እንዳያስተምር ተወግዟል፡፡
 • በተመሳሳይ መልኩም፣ በአሜሪካን ሀገር በዋሽንግተን ዲሲ የሚያገለግሉት አባ መዓዛ ክርስቶስ በየነ፣ እያስተማሩት ያለው የክሕደት ትምህርት ለቅዱስ ሲኖዶስ በመረጃ ቀርቦ የተረጋገጠባቸው ስለኾነ፣ ሥልጣነ ክህነታቸው ተይዟል፤ ያሉበትን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በማናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል
 • “ወልደ አብ” በሚል ርእስ፣ ገብረ መድኅን በተባለ ግለሰብ የተጻፈው የክሕደትና የኑፋቄ ትምህርት፣ የቅብዓትንና የጸጋን የክሕደት ትምህርት የሚያስፋፋ በመኾኑ፣ ካህናትን ከካህናት፣ ምእመናንን ከምእመናን የሚያጋጭ ከመኾኑ ጋር፣ ከቤተ ክርስቲያንም አልፎ በሀገራችን ሁከት ለማስነሣት ታስቦ የተዘጋጀ ኾኖ ስለተገኘ፣ መጽሐፉ ከማናቸውም አገልግሎት እንዲለይ ተወግዟል
 • “ተሐድሶ” እየተባለ የሚጠራው የኑፋቄ እምነት ማኅበር፣ ራሱን ኦርቶዶክሳዊ በማስመሰል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና እየተፈታተነ ከማስቸገሩ የተነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ በየአህጉረ ስብከቱ ተቋቁሞ የመከላከልና ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ ሥራ እንዲያከናውን ውሳኔ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡ አኹንም ከማእከላዊ አስተዳደር እስከ አህጉረ ስብከት ባለው መዋቅር የተቋቋመው የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ ተጠናክሮ የመከላከሉን ሥራ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጥቷል፡፡
 • የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስከ አኹን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደኖረ ኹሉ አሁንም፣ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
 • የ36ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ፣ አንዳንድ ማሻሻያ በማድረግ፣ የጋራ መግለጫው፣ የ2010 ዓ.ም. በጀት ዓመት ተግባር ኾኖ ያገለግል ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
 • በቃለ ዐዋዲው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደርያ ደንብ መሠረት፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች የኾኑት ወጣቶች፣ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው በሰንበት ት/ቤት ተደራጅተው በየሰበካ ጉባኤው አመራር ሰጭነት እንዲማሩምልአተ ጉባኤው አመራርን ሰጥቷል፡፡
 • በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማደግ ያስችለው ዘንድ ከክፍሉ ሊቀ ጳጳስ የቀረበውን ፕሮፖዛል ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
 • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማሠልጠኛ አቋቁመው ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ማኅበራት የሚያገለግል እስከ አኹን ድረስ የተዘጋጀ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ የሌለ በመኾኑ፣ ለወደፊቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑንና ቃለ ዐዋዲውን መሠረት ያደረገ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ በሕግ ባለሞያዎች እንዲዘጋጅ ጉባኤው ተስማምቶ ወስኗል፡፡
 • ለገዳማት መተዳደርያ እንዲኾን የተዘጋጀው ደንብ፣ ረቂቁ ተስተካክሎ የቀረበ በመኾኑ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
 • በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሒሳብና በጀት መምሪያ ተዘጋጅቶ የቀረበው፣ የ2010 ዓ.ም. በጀት የክፍያው ጣሪያ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
 • የነገድ፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይኖር፣ ለጋራ ህልውና፣ ለጋራ ዕድገትና ለጋራ ብልጽግና ለሀገራችን ኢትዮጵያ ለጎረቤት አህጉር ብሩህ ተስፋ ሰንቆ እንደሚመጣ የተነገረለት የዓባይ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊነቱን እያስመሰከረ ስለመጣ አሁንም የፕሮጀክቱ ሥራ ተጠናክሮ ለውጤት እስከሚበቃ ድረስ ኹሎችም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ድጋፍ በመለገስ እንዲተባበሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
 • ምልአተ ጉባኤው፣ እስከ ግንቦት ርክበ ካህናት ድረስ ባሉት ቀጣዮቹ 6 ወራት፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ጋራ በመኾን የውሳኔዎቹን አፈጻጸም የሚከታተሉ የሦስት፣ የሦስት ወራት የቋሚ ሲኖዶስ ተለዋጭ አባላትን ሠይሟል፡፡ በዚህም መሠረት፡– ከኅዳር እስከ ጥር፡- ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ ብፁዕ አቡነ ሰላማ፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ናቸው፡፡ ከየካቲት እስከ ግንቦት፡- ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እና ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *