“Our true nationality is mankind.”H.G.

ዳያስፖራና “Halloween”

(መክብብ ማሞ)

አገራችንን ለቅቀን ከወጣንበት ጊዜ ጀምሮ በባዕድ አገር በርካታ የምንማራቸው፤ የምንለምዳቸው ባህሎች አሉ፡፡ የዚያኑ ያህል መማር የሌለብን ወይም እንዳልተማርን መሆን ያለብንም አሉ፡፡ በተለይ በአሜሪካ ከበርካታዎቹ ሸግዬ ባህሎች መካከል የምስጋና ቀን “Thanksgiving Day” የሚጠቀስ ነው – ወደ ታሪኩና ዝርዝሩ ሳልገባ እንደው በደፈናው ማመስገን መልካም ነው፤ ለዚያም ቢያንስ በዓመት አንዴ ቀን መመደብ ተገቢ ነው በሚለው እሳቤ ብቻ፡፡ ከማማረርና ማጉረምረም አንዳንዴም ባርኮትን ቆጥሮ (ጥቂትም ቢሆን) ማመስገን ሸጋ ነው – ምስጋናው ደግሞ ለፈጣሪ ብቻ ሳይሆን፤ ለወላጅ፣ ለቤተሰብ፣ ለፍቅረኛ፣ ለትዳር ጓደኛ፣ ለልጆች፣ ለወገን፣ ላገር ልጅ፣ … ማብቂያ የለውም፡፡ ታዲያ “ሃሎዊንስ”? የመሰልጠናችን፣ የፈረንጁን ባሕል የመልመዳችን፣ ከኋላ ቀርነት የመላቀቃችን፣ … ምልክት ስለሆነ ይሆን የምናከብረው? እየፈራን ስለምናስፈራ፤ እያስፈራራን ስለምንፈራ …?

ከላይ እንዳልኩት በዚህ የውጪ አገር ብዙ ነገሮችን ከመማራችን የተነሳ ምርቱን ከግርዱ መለየት ያቃተን ይመስላል፡፡ አገር ቤት ሳለን ፈጽሞ የማንነካውን የአሳማ ሥጋ እዚህ መጥተን ከነቆዳው እናስነካዋለን፡፡ እኛ እንኳን ባናደርገውም ልጆቻችን ከአሳማ ሥጋ እስከ አምባዛ፣ ሽሪምፕ፣ … ባገኙት ቦታ – ትምህርት ቤት፣ ምግብቤት፣ … እንዲመገቡ ከመፍቀድ አልፈን ሃይማኖታችን እና የምናነበው መጽሐፍ (በእስልምናም ሆነ በክርስትና) እንደማይፈቅድ እያወቅን “እነርሱ እዚህ ስለተወለዱ ነው፤ ባሕላቸው ነው፤ … ” የሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች እየሰጠን ይህ ሥልጣኔ መስሎን የተሸወድን ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ሌላው የተሸወድንበት ደግሞ ይኸው ከጥቂት ቀናት በኋላ የኦክቶበር ወር ሲያልቅ የሚከበረው “ሃሎዊን” የተባለውን በዓል በማክበር ነው፡፡ ለመሆኑ ሃሎዊን ምንድነው? እንዴት ተጀመረ? ታሪካዊ አመጣጡስ ምን ይመስላል? ከተለያየ ቦታ የቃረምኩትን ባጭሩ እንዲህ ላቅርበው፡፡ በነገራችን ላይ የሃሎዊን ትክክለኛ አመጣጥና አከባበር ዝርዝር በምሁራን ዘንድ እስካሁን ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት አጨቃጫቂ ጉዳይ መሆኑን ሳልጠቁም አላልፍም፤ አጠቃላይ ስምምነት የተወሰደበት ታሪክ ግን ይህንን ይመስላል፡፡

 

አሁን አየርላንድን፣ እንግሊዝን እና ሰሜን ፈረንሳይን በሚያካልለው ስፍራ ከመካከለኛው ዘመን በፊት ይኖር የነበረ “ሴልቲክ” የሚባል ህዝብ ነበር፡፡ ሴልቲኮች ወቅቶቻቸውን አሁን እንዳለው ሳይሆን በሁለት ነበር የተከፈሉት – በጋውን “ግማሽ ብርሃን” ክረምቱ ደግሞ “ግማሽ ጨለማ” በማለት፡፡ እነዚህ ሁለቱ ወቅቶች የሚቀያየሩት ደግሞ ኦክቶበር 31 ነበር – በጋው የሚያበቃበትና የቀኑ ብርሃን አጭር በሆነውና በሞት በሚመሰለው የክረምት ወራት የሚተካበት፡፡ በሴልቲኮች እምነት ወራቶቹ ሲቀያየሩና ብርሃን በጨለማ ሲተካ ኦክቶበር 31ቀን የሕያዋን ምድርም ሆነ የሙታን ምድር በብዥታ የተሞላ ይሆናል፤ ሙታንም ነፍሳትን ለመጎብኘት ወደዚህ የህያዋን ምድር ይፈልሳሉ፡፡ እነዚህ የሙት መናፍስት ጉብኝታቸውን ሲያደርጉ ለመደበቅና ላለመታወቅ የሚፈልጉት ሴልቲኮች ጭምብል (ማስክ) በማድረግና ራሳቸውን በመቀየር ለማምለጥ ሙከራ ያደርጋሉ – (trick the ghosts)፡፡ እንዲያውም የሴልቲክ ካህናት ለሕዝቡ የሚሰጡት ምክር ነበር – ነዋሪው ሁሉ በየቤቱ እየሄደ ከሰዉ ሁሉ ጣፋጭ ምግቦችን እንዲሰበስብና ጭራቅ፣ አጋንንት፣ መናፍስት፣ ወዘተ በመምሰል ሊጎዷቸው ለሚመጡት የሙታን መናፍስት ጣፋጩን በመስጠት እንዲያባብሏቸው፡፡ አለበለዚያ መናፍስቱ በሚገባው ካልተስተናገዱ በሰዉ ላይ የማታለል ተግባር (trick) እንደሚፈጽሙ … ምን ያስታውሳችኋል? ባሁኑ ጊዜ ሃሎዊን ሲከበር ለልጆች ከረሜላ ሲሰጥ ምንድነው የሚባለው – (trick or treat) – ነገሮች ከምንም አይጀመሩም፡፡

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ሌላው በዚህ የወቅት መለወጫ ጊዜ “የብርሃን ዘመን” መጠናቀቁን ለማወጅና መናፍስቱ ከመጪው የክረምት ወራት ሕዝቡን እንዲታደጉ የችቦ ደመራ ይበራል – ጭለማው የክረምት ጊዜያት የበራ እንዲሆን በመመኘት፡፡ በዚህ ምሽት በርካታ ጥንቆላ፣ ከአጋንንት የመነጋገር ተግባራትም ይፈጸማሉ፡፡ ሰዎች የሞቱባቸውን ዘመዶቻቸውን በመናፍስቱ አማካኝነት ይጠራሉ፤ መጪው የሰብል ዘመን ምን እንደሚሆን ይጠይቃሉ/ያስጠነቁላሉ፤ መስተፋቅር ይጠየቃል፤ ሴቶች መስታወት ፊት ሻማ ይዘው በመቆም የወደፊት የትዳር ጓደኛቸውን በመስታወቱ ውስጥ ብቅ ሲል ለማየት ጭለማ ውስጥ ያፈጥጣሉ፡፡ ሌሎችም እጅግ በርካታ መናፍስትን የመጥራትና ከአጋንንት ጋር የመገናኘት ተግባራት ይከናወናሉ፡፡

“የሰይጣን ዱባ”

በሃሎዊን ጊዜ በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውለው ዱባ (እኔ ለዚህ ጽሑፍ ስል “የሰይጣን ዱባ” ያልኩት) ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ሴልቲኮች የሙት መናፍስት እንዳይጎዷቸው ከእነርሱ ለማራቅ ከሚጠቀሙት ብልሃቶች መካከል አንዱ ይህ ነበር፡፡ ዱባውን በቅርጽ በማውጣት ውስጡን በሻማ በማብራት መናፍስቱን ለማስፈራራት ይጠቀሙበታል፡፡ ሌሎች ደግሞ “የኩራዙ ጃክ” (“Jack of the Lantern”) በሚባለው አፈታሪክ መሠረት አንድ ጃክ የተባለ ግለሰብ ለዲያቢሎስ አንዳንድ ቀልዶች በመንገር ሰይጣንን በልጦ ለመገኘት ባደረገው ሙከራ ዲያቢሎስ በመናደዱ ጃክ ዕድሜውን በሙሉ የበራ ኩራዝ ይዞ እንዲዞር በማድረግ ሰዎች ዲያቢሎስን እንዳያታልሉ የማስጠንቀቂያ መማሪያ እንዲሆን ብሎ ያደረገው ነው ይላሉ፡፡

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ሃሎዊን ክርስትና ውስጥ እንዴት ሰርጎ ገባ?

በቀደምት ክርስቲያኖች ዘንድ “የሁሉም ቅዱሳን ቀን” ተብሎ በዘመናት ሰማዕት የሆኑ የሚዘከሩበት (ሰማዕታቱ “ዘክሩን” ብለው ባይጠይቁም) ቀን ነበር – የሚከበረው ኖቬምበር 1ቀን ነው፡፡ ከዚህ ቀን በፊት ያለው የዋዜማ ቀን “የቅዱሳን ዋዜማ ቀን” ወይም በእንግሊዝኛው “All Hallows Eve” እየተባለ መጠራት ሲጀምር አንዱ አላስፈላጊ በዓል ሌላ በጣም አላስፈላጊ የሆነ በዓልን እየፈጠረ መጣ፡፡ ይኸው “All Hallows Eve” የተባለው በዓል ስሙ ሰብሰብ፣ አጠር ተደረገና “Hallow-e’en,” ሲባል ቆይቶ በመጨረሻ “Halloween” እነሆኝ አለ!

ክርስትና ወደ ምዕራብ አውሮጳ ግስጋሴ ሲያደርግ በርካታ የአረማውያንን ሃይማኖቶች በመንገዱ ሲጋፈጥ ቆይቷል፡፡ ያገኛቸውንም “እነዚህን የጣዖት አምልኮዎችን አስወግዱ” በማለት ሕዝቡን ወደ አዲስ እምነት ከማምጣት ይልቅ “እናንተንም ሆነ ባዕድ አምልኳችሁንም እናጠምቃለን (ክርስትና እናነሳለን)” በማለት ጣዖት አምልኮ ወደ ቤ/ክ ሰተት ብሎ እንዲገባ በር ተከፈተ፡፡ የሳምንቱ ቀናት ተቀየሩ፣ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የባዕድ አምልኮዎች የክርስትና ስም እየተሰጣቸው ወደቤ/ክ ገቡ፡፡ ገና፣ ፋሲካ፣ … በዚሁ መልክ ነው ወደ ቤ/ክ ሰጥመው በመቅረት ክርስቲያናዊ በዓላት ሆነው የቀሩት፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሴልቲኮች ጣዖት አምላኪ አረማውያን ስለነበሩ የመኸር ወራት ተጠናቅቆ የክረምቱን ወራት ከመጀመራቸው በፊት ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ሰብላቸውን ይሰበስባሉ፣ ክረምቱን ለማለፍ የሚያቅታቸውን እንስሳት ያርዳሉ፣ … ህይወት ዝግ እያለ ይመጣል፤ ቀኑ ያጥራል፤ ሌሊቱ ይረዝማል፤ የእርሻው መሬት እዳሪ ይሆናል፤ … ይህ ሁሉ በሞት፣ በአፅም፣ በራስ ቅል አፅም፣ በጥቁር ቀለም፣ … እየተመሰለ ከመሄድ አልፎ የዘመኑ ሃሎዊን ሲከበር ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ሆነ፡፡ ከዚሁ በዓል ጋር ተያይዞ የሚደረጉትን ሌሎች አጋንንት የመጎተት፣ መናፍስትን የመጥራት፣ ጥንቆላ፣ ወዘተ ተግባራት በመዘርዘር አላፈላጊ ወደሆነ አጀንዳ ውስጥ ለመግባት አልፈልግም እንጂ ይህንን መሰል እጅግ በርካታ ተግባራት ይፈጸሙ ነበር፡፡

የበዓሉ አመጣጥና ትርጉም ይህ ሆኖ ሳለ እኛ ኢትዮጵያውያን ለመሆኑ ከየትኛው አስተሳሰባችን፣ ባህላችን፣ አኗኗራችን ጋር ተዛምዶ ነው ለዚህ በዓል ይህንን ያህል ክብር በመስጠት የምናከብረው? ወይስ ሥልጣኔ ነው? ምዕራባዊነት? ፈረንጅ ካደረገው ትክክል መሆን አለበት-ነት? በነገራችን ላይ የሰሜን አሜሪካው ገበያ ከዚሁ በዓል 3.3 ቢሊዮን ዶላር ይሰበስባል ተብሎ ይጠበቃል – እኛም ተሳታፊ ነን፡፡

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “ሥልጣን፤ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ” በሚለው መጽሐፋቸው በርካታ አጥፊ ባህሎች እንዳሉን ይጠቅሳሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በየቦታው በሥልጣን ላይ የሚገኙ ሰዎች (በመንፈሣዊውም ሆነ በፖለቲካው) የሚሠሩትን ጥፋትና በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙትን በደል እያነሳን እንደምንነጋገርባቸውና እንደምንነቅፍ ይጠቅሳሉ፡፡ በአንጻሩ ግን የራሳችን ጥፋትና በደል እንደማይታየን በዚሁ መጽሐፋቸው ላይ ይናገራሉ፡፡ “በየቤቱ በሚስቶችና ልጆች ላይ የሚደርሰው ጭቆናና ግፍ፤ በየቤቱ ሠራተኞች ያላቸው ሰዎች በሠራተኞቻቸው ላይ የሚፈጽሙት ጭቆናና ግፍ በጥሞና ካየነው ባለሥልጣኖቻችን ከሚያደርሱብን ግፍና ጭቆና ጋር የባህርይ ልዩነት የለውም” ይላሉ፡፡ ይህንን የመሳሰሉ አጥፊ ባህሎች ከእኛ መወገድ እንዳለባቸው በመምከር “በዘመናት ፋይዳቸው የማይለወጥ ለጨዋነትና ለመተማመን መሠረት የሚሆኑትን” ባህሎቻችንን እንድናዳብር ያሳስቡናል፡፡ ለኢትዮጵያውያን “የባህል ምሶሶ” ናቸው የሚሏቸውን አራቱን፡- ክብርና ኩራት፤ ቆራጥነትና ጀግንነት፤ መተዛዘንና መረዳዳት፤ ጨዋነት፣ አደራ አክባሪነትና ሃይማኖተኛነት፤ በመጥቀስ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡ ልናነበው፣ ልንለማመደው፣ ለልጆቻችን ልናወርሰው የሚገባ ምክር ነው፡፡

ስለሆነም መማር ያለብንና የሌለብንን እንወቅ፤ እንደ መልካም ባህል የሙጥኝ ያልናቸውን – ሰው ምን ይለኛል፣ ይሉኝታ፣ አድመኝነትን፣ ዘረኝነትን፣ ጠባብ ወገንተኝነትን፣ … አጉል ባህሎች አውልቀን በመጣል ግልጽነትን፣ የሌላውን መብት (ከማሰብ ጀምሮ እስከ መናገር) ማክበርን፣ ትህትናን፣ ቅንነትን፣ … በየዕለቱ ህይወታችን፣ በንግግራችን፣ በፓልቶክ ውይይታችን፣ በስብሰባችን፣ በቴሌኮንፍራንሶች፣ ወዘተ እንለማመድ፡፡ ሥልጣን ላይ ባሉት የሰላ ሒስ ስንሰነዝር እኛም በሌሎች ላይ ሥልጣናችንን እንዴት እንደምንለማመድ እንጠይቅ፡፡ ዕብጠትን፣ ከኔ በላይ ላሳር-ነትን እናስወግድ – የባህል ለውጥ እናካሂድ፡፡ ጥራዝ ነጠቅ አንሁን፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ብዙ የምንማረው ባህል አለ፡፡ ሃሎዊንና የመሳሰሉት ግን ቢቀሩብን የሚቀርብን ምንም ነገር የለም፡፡

 

mekbma@yahoo.com

ለጽሁፌ ጥንቅር በዋቢነት የሚከተሉትን ድረገጾች ተጠቅሜያለሁ፡-
http://www.gty.org/Resources/Articles/1126
http://amazingdiscoveries.org/the-origins-of-halloween

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0