የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ 18ቱም የግልና የመንግሥት ባንኮችን በአክሲዮን ባለቤትነት በማካተት የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት በዲጂታል ዘዴ ለመምራት የተቋቋመው ኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር፣ ዓምና የ23.7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማስመዝገቡን ይፋ አደረገ፡፡

ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው የአክሲዮን ኩባንያው አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ይፋ ከተደረገው የማኅበሩ ሪፖርት ለመረዳት እንደተቻለው፣ ኩባንያው ዓምና ከ7.7 ሚሊዮን በላይ ክፍያዎችን በማስተናገድ 2.9 ቢሊዮን ብር ቢያንቀሳቅስም ዓመቱን በኪሳራ አሳልፏል፡፡

የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የኩባንያው የ2009 ዓ.ም. የኦፕሬሽን አገልግሎቶች የተሳኩ መሆናቸውን፣ በብሔራዊ ክፍያ ሥርዓቱ በኩል ሲተላለፉ የነበሩ የገንዘብ ዝውውሮች ብዛትና የገንዘብ ልውውጡ ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ አገልግሎቱን ለማግኘት በሚደረጉ ሙከራዎች ወቅት ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ ይኸውም የአንዱ ባንክ ደንበኞች በሌሎች በደንበኝነት ካልተመዘገቡባቸው ባንኮች በኤቲኤም አማካይነት ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ከሞከሩ 783,258 ተጠቃሚዎች ውስጥ፣ 583,103 አገልግሎቱን በአግባቡ አግኝተዋል፡፡ ቀሪዎቹ ግን በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ማግኘት አለመቻለቸውን ከኩባያው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደ ኩባንያው ሪፖርት ከሆነ፣ በ2009 ዓ.ም. ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ቢጋፈጥም ከዓመታዊ ዕቅዱ 67 በመቶ ብቻ ማሳካቱ ተገልጿል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ዓምና ያገኘው ገቢ 16.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ለዓመቱ ካቀደው ገቢ አንፃር ያሳካው 54 በመቶ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ገቢው የተመሠረተው ከእያንዳንዱ የገንዘብ ልውውጥ የ0.25 ሳንቲም የአግልግሎት ክፍያ እንደሚያገኝ በተቀመጠው ሥሌት መሠረት ነው፡፡

ሁሉንም ባንኮች በማስተሳሰር ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው በመሄድ የየትኛውንም ባንክ ኤቲኤም በመጠቀም ገንዘብ ማውጣት በሚያስችለው ዘመናዊ አሠራር አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኢትስዊች፣ ይህ አገልግሎቱ ግን የተለያዩ ቅሬታዎች የሚቀርቡበት ቢሆንም፣ በኩባንያው በኩል ሊነሳ የሚችለው ቅሬታ አነስተኛ ስለመሆኑ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

‹‹ባንኮች የደንበኞቻቸውን ቅሬታዎች በሲስተሙ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በመፍታት ረገድ አልፎ አልፎ በተከሰቱ መዘግየቶች ምክንያት የተፈጠሩ የባንክ ተጠቃሚዎች ቅሬታዎች ቢኖሩም፣ በአጠቃላይ በባንኮች አማካይነት በኢትስዊች ሲስተም ውስጥ የተዘመገቡት ቅሬታዎች ቁጥር አነስተኛ ነው፤›› በማለት አቶ ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡ ለኩባንያው የቀረቡት ቅሬታዎች 43,583 መሆናቸውን የሚጠቁመው የሊቀመንበሩ ሪፖርት፣ በዓመቱ ከተስተናገደው ጠቅላላ የገንዘብ ልውውጥ ወይም ክፍያ ብዛት ውስጥ የ0.57 በመቶ መጠን እንደሆነ አሳይቷል፡፡

በብሔራዊ የክፍያ ሥርዓቱ አማካይነት ሲተላለፉ የነበሩት ክፍያዎች ብዛትና የገንዘብ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ኩባንያው በዓምናው እንቅስቃሴው የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ያወሱት አቶ ጥሩነህ፣ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ በብሔራዊ ክፍያ ዘዴው አማካይነት ከተላለፉት ክፍያዎች ውስጥ በአማካይ 42 በመቶው ክፍያ እንዲያስተናግዱ የተሞከረባቸው ቢሆኑም፣ የክፍያ ካርዶቹን ለደንበኛው በሰጡ ባንኮች (Issuer Banks) ሊስተናገዱ አለመቻላቸው አንዱ ችግር ነበር፡፡ በብሔራዊ ስዊች በኩል ከተላለፉት 7.7 ሚሊዮን ክፍያዎች ውስጥ 2.2 ሚሊዮን ወይም 29 በመቶው ካርዱን በሰጡት ባንኮች በኩል ሙሉ በሙሉ ሊፈቱ ወይም ሊቀንሱ በሚችሉ ችግሮች ምክንያት ተከስተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ደንበኞች በተሳካ ሁኔታ ሳይስተናገዱ ለመቅረታቸው ችግሩ የባንኮች ጭምር ነበር ተብሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ደንበኞች  በአገልግሎቱ ላይ ያደረባቸውን እምነት በአሉታዊነት ሊጎዳ ከመቻሉም በላይ፣ በኩባንያውም ሆነ ለኤቲኤም አገልግሎት የወጣው ወጪ ያለምንም ገቢ እንዲቆይ ማስገደዱ ተጠቅሷል፡፡

ከጥር 27 ቀን እስከ ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ውስጥ በብሔራዊ ስዊች በኩል እንዲፈቀዱ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲላኩ የቆዩ የባንኩ ደንበኞች ትራንዛክሽኖችን ለማስተናገድ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ሳቢያ አገልግሎት ከመስጠት ታቅቦ መቆየቱም ሌላው የዓመቱ ተግዳሮት እንደነበር ኩባንያው አስታውሷል፡፡

የተፈጠረውን ችግር ያብራሩት አቶ ጥሩነህ ሦስት የኮድ ችግሮችን ዋቢ አድርገዋል፡፡ አንደኛው ኮድ 801 የተባለው ሲሆን፣ ይህም ካርዱን በሰጠው ባንክ ሲስተም በኩል ጥያቄ ለቀረበበት ክፍያ የሚሰጠው ምላሽ መዘግየትና የተመደበው ጊዜ አልቋል በማለት የሚሰጠው ምላሽ የፈጠረው ችግር አንዱ ነው፡፡ ኮድ 802 ወይም ካርዱን የሰጠው ባንክ ስዊች ወይም ኮር ባንኪንግ ሥርዓት ለጊዜው ከአገልግሎት ውጪ በማለት የሚሰጠው ምላሽ እንዲሁም ኮድ 827 ወይም ካርዱን ከሰጠው ባንክ ሥርዓት፣ በካርድ የሚመጣውን የክፍያ ጥያቄ አታስናግድ የሚል ተገቢ ያልሆነ ምላሽ መስጠት ዋና ዋና ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህም በተገልጋዩ ላይ ካስከተሉት መጉላላት በተጨማሪ፣ ኩባንያው ከአገልግሎቱ ማግኘት የሚገባው ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ተመልክቷል፡፡

ዓምና በተሳካ ሁኔታ ከተስተናገዱት ትራንዛክሸኖች ቁጥር አንፃር የተመዘገቡት የባንክ ደንበኞች ቅሬታዎች ብዛት አነስተኛ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በተዘረጋው የክፍያ ሥርዓት ሲጠቀሙ ችግር ላጋጠማቸው ደንበኞችና ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በጊዜው ማስተናገድን በተመለከተ፣ አንዳንዶቹ ባንኮች የሚሰጡት መፍትሔ መዘግየት በደንበኞች የሚነሱ ተጨማሪ ቅሬታዎችን እንዳስከተለ ኩባንያው ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

‹‹ኩባንያው እያገኘ ያለው ገቢ፣ ከወጣበት የኢንቨስትመንትና ሌሎች ወጪዎች አንፃር ሲታይ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ገቢው በዓይነትና በመጠን የተሻለ ደረጃ ላይ እስኪደርስ የኩባንያው የፋይናንስ አዋጭነትና ዘላቂነት ላይ አሉታዊ ሁኔታዎች ተደቅነዋል፤›› ያሉት አቶ ጥሩነህ፣ በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት ኩባንያው ያጋጠሙትን ችግሮች ተጋፍጦ የዕቅዱን 67 በመቶ በማሳካት ዓመቱን እንዳገባደደ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ዓመት የተያዙ ዕቅዶችን በተመለከተ እንደተገለጸው፣ ኩባንያው ስድስት አዳዲስ የአገልግሎት ትግበራዎችን ያስጀምራል፡፡ በኢትስዊች በኩል ይፈጸማሉ የተባሉ ስድስቱ አዳዲስ አገልግሎቶችም በኤቲኤም አማካይነት ከአንድ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ በካርድ የሚደረግ የገንዘብ ማስተላለፍ፣ ካርድ በሌላቸው ሒሳቦች መካከል በሞባይልና በኢንተርኔት የሚደረግ የገንዘብ ማስተላለፍ፣ በኤቲኤም አማካይነት የሞባይል ቶፕአፕ ክፍያ፣ በኤቲኤም አማካይነት ለተቋማት ክፍያ ማስተላለፍና በኤቲኤም አማካይነት የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውኃና የቴሌኮሙዩኒኬሽን የአገልግሎት ክፍያዎችን መፈጸም ለዓመቱ የተያዙ አዳዲስ የክፍያ ዘዴዎች ናቸው፡፡

ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ኩባንያውን በቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ ግለሰቦች ተመርጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ (ባንክ ሱፐርቫይዘር) አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ የኩባንያው ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ከምርጫው በፊት የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የአሁኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና ሲመሩት የነበረውን ኩባንያ አቶ ጥሩነህ ተረክበው ቢቆዩም፣ በአዲሱ ምርጫ አቶ ጥሩነህ በዚያው በቦርድ ሊቀመንበርነታቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡

ኢትስዊች ወደ ሥራ ከገባ ወደ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን 300 ሚሊዮን ብር በማሳደግ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡

ዳዊት ታዬ/  ሪፖርተር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *