የኢትዮጵያ ፌዴራል አወቃቀር በዋናነት በቋንቋ ላይ ተመሰረተ ፌዴራል አወቃቀር ነው። ይህ የፌዴራል አወቃቀር የራሱ ችግርና ፈታዎች እንዳሉት ብዙዎች ይናገራሉ። በተለይም በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዙሪያ የተነሱ ግጭቶች፣ ለመቶ ሺሆች መፈናቀልና ለብዙ ወገኖች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል የተከሰተው ግጭት፣ በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ያለው ዉዝግብና በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የጎሳ፣ የዘር ግጭቶች ዋና ምክንያት በቋንቋ ላይ የተመሰረተው ፌደራል አወቃቀሩ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

አሁን ያለው በቋንቋ ላይ የተመሰረተው ፌዴራል አወቃቀር ሲተች ፣ የግለሰብ መብትን ያከበረ፣ በታሪክ፣ በአስተዳደር አመችነት፣ በጂዩግራፊና በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ፌዴራል አወቃቀር እንዲቀየር ሐሳብ ሲቀርብ፣ የማንነት/የብሄር ፖለቲካ አራማጆችና ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያላቸው ወገኖች፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ልትቀጥል የቻለችው በዚህ ፌደራል አወቃቀር ምክንያት እንደሆነ በመግለጽ ይህ የብሄር ብሄረሰብ መብቶችን ያረጋገጠ የሚሉት የፌዴራል ስርዓት ባይኖር ኖሮ ኢትዮጵያ አትኖርም ነበር ብለው ይከራከራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አወቃቅር ጋር በምን እንደሚገናኝ ግልጽ ባይሆን፣ የስዊዘርላንድን የመንግስት አወቃቀር እንደ ምሳሌ በመጥቀስ የኢትዮጵያ አወቃቀር ከሲዊዘርላንድ ሞዴል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ዘመናዊ አወቃቀር እንደሆነም ሲናገሩ ይደመጣሉ።

በቀዳሚነት ሊሰመርበት የሚገባው አንድ ጉዳይ አለ። አንድ መዋቅር ሌላ አገር ሰራ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ይሰራል ማለት አይደለም። ኢትዮጵያዉያን የራሳችን ባህል፣ የችግር አፈታት ዘዴ፣ ረጅም ታሪክ ያለን ነን። የፈረንጆችን ታሪክና ባህል ብቻ ከማወደስ ወደኛው ታሪክ ብንመለስ ብዙ የአሁኑ ትዉልድ ሊማረው የሚገባ ትላልቅ ቅርሶች እናገኝ ነበር። እንደውም አላወቅነውም እንጂ ብዙ ችግሮቻችን ከፈረንጆች አስተምሮ፣ ፈረንጆችን ለመምሰል ከመፈለጋችን የተነሳ የመጡ ችግሮች ናቸው። ማርክሲዝም ብለው አገራችን የተበጠበጠችው ከዉጭ በመጣ አስተምሮ አይደለም እንዴ ? በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የነበሩ ሚሲዎናዊያን የልጆቻችንን አይምሮ ስላበላሹት አይደለም እንዴ በአንዳንድ አካባቢዎች ጸረ-ኢትዮጵያ የጥላቻ ፖለቲካ ሊያድግ የቻለው? ከፈረንጆች የመጣ ነገር በሙሉ ጠቃሚ ነው ማለት አይደደለም።

ይሄን ስል የሲዊዘርላንድ ሞዴል ትክክል አይደለም ማለቴ አይደለም። ሞዴሉ ለመከራከሪያ እንደ ዋና ምክንያት ሆኖ መቅረቡን ስላልተመቸኝ እንጂ። እንደዚያም ሆኖ፣ ለውይይት ያህል፣ የነርሱ መከራከሪያ የሆነውን የሲዊዘርላንድን ሞዴል ብንቀበልም፣ መከራከሪያቸው ዉሃ የሚቋጥር ሆኖ አላገኝሁትም። የስዊዘርላንድን ሞዴል እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱ ወገኖች ስለ ሲዊዘርላንድ ሞዴል ትክክለኛ መረዳት ያላቸውም አይመስለኝም።

 

ስዊዘርላንድ በጣም ትንሽ አገር ናት። የኢትዮጵያ አንድ አስረኛ ትሆናለች። በውስጧ ካንቶንስ ይሏቸዋል፣ 26 ከፍለ ሃገራት አሉ። እያንዳንዳቸው ካንቶኖች የተዋቀሩት በዋናነት ታሪክን እና ቋንቋ በመመርኮዝ ነው። በአሥራ ስምንቱ ካንቶኖች የስራ ቋንቋ ጀርመንኛ ነው። ጀርመንኛ የሥራ ቋንቋ በሆኑባቸው ካንቶኖች ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ ተናጋሪዎች ከ3 ወይም 2 በመቶ አይበልጡም። ስለዚህ ጀርመንኛ ብቻ የስራ ቋንቋ መሆኑ ችግር አልፈጠረም። በሶስት ካንቶኖች ፈረንሳይኛ ብቻ ነው የሥራ ቋንቋ። በአንድ ካንቶን ደግሞ ጣሊያንኛ። ይሄም የሆነበት ከቋንቋዎቹ ዉጭ የሚናገሩ እጅግ በጣም ትንሽ በመሆናቸው ነው። ከ5% በታች።

በሶስት ካንቶች (በርን፣ ፍሪበርግና ዋሊስ) ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ የካንቶኖቹ የሥራ ቋንቋዎች ናቸው። በበርን፣ ጀርመንኛ ተናጋሪዎች 84% ሲሆኑ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች 8% ናቸው። 8% ትልቅ ማይኖሪቲ ስለሆነ ነው ፈረንሳይኛ ከጀርመንኛ ጋር የካንቶኑ የሥራ ቋንቋ የሆነው። በፍሪበርግና በዋሊስ ፈረንሳይኛ ተናጋሪው 68% በመቶ ነው። ጀርመን ተናገሪዎች ደግሞ ወደ 28% ናቸው። ጀርመኖች ማይኖሪቲ ቢሆኑም፣ ትልቅ ማይኖሪቲ ናቸው። በመሆኑ ጀርመንኛ ፈረንሳይኛ የካንቶኖቹ የሥራ ቋንቋ ሆኑ። ግራቡንደን በሚባለው ካንቶን፣ ጀርመን ተናጋሪዎች 75% ናቸው። ሆኖም ጣሊያኖች 12%፣ ሮማኒያን የሚባሉ 15% በመሆናቸው፣ በካንቶኑ ከጀርመንኛ ጋር ጣሊያንኛና ሮማንኛ የኦፊሴል ቋንቋዎች ናቸው።

በሕዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት በኦሮሚያ ባጠቃላይ 15% የሚሆነው፣ በአዳማ ልዩ ዞን 85%፣ በጂማ ልዩ ዞን 60%፣ በቡራዮ ልዩ ዞን 45%፣በምስራቅ ሸዋ ዞን 33%፣ በአርሲ ዞን 18%፣ በሰሜን ሸዋ ዞን 17%፣ በሆሮ ጉርዱ ወለጋ 14%፣ በምስራቅ ወለጋ 11% ፣ በምእራብ ሐረርጌ 9% እና በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን 15% የሚሆኑት ነዋሪዎች አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች አይደሉም። ሆኖም በነዚህ ዞኖችና በክልሉ አፋን ኦሮሞ ብቻ ነው የሥራ ቋንቋ።

ወደ ሃረሪ ክልል ስንሄድ አደሬዎች የክልል 8% ሲሆኑ፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ወደ 50% ናቸው። ወደ 28% አማርኛ ተናጋሪ ሲሆን፣ ጉራጌኛ፣ ሶማሌኛ ተናጋሪዎችም አሉ። ሆኖም ወደ 28% አማርኛ ተናጋሪ እያለ፣ 8% የሚናገረው አደሪኛ ከአፋን ኦሮሞ ጋር የሥራ ቋንቋ ሲሆን አማርኛ ግን የክልሉ የሥራ ቋንቋ መሆን አልቻለም።

እንግዲህ በስዊዘርላንድ ፣ በበርን ካንቶን 8% የሆኑ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች በግራቡንዱን 12% የሆኑ ጣሊያንኛ ተናጋሪዎች ቋንቋቸው የካንቶኖቹ የሥራ ቋንቋ ከሆኑ ፣ ስዊዘርላንድን እንደ ሞዴል የሚወስዱ፣ በኦሮሚያና በሃረሬ ክልል አማርኛም የሥራ ቋንቋ እንዲሆን መስማማትና መግፋት ነበረባቸው። ይሄ አንዱ ነጥብ ነው።

ሲዊዘርላንድ የኦሮሚያ 14% ወይም አንድ ሰባተኛ ብቻ አካባቢ ናት። በሕዝብ ብዛት ካየነው የሲዊዘርላንድ ህዝብ በኦሮሚያ ከሚኖረው ህዝብ አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው። ከዚህ የምንረዳው የሲውዘርላንድ ካንቶኖች በጣም ትናንሾች መሆናቸውን ነው። በቋንቋ ብቻ ቢሆን ኖሮ ፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ከ26 ካንቶቹ 18 ጀርመንኛ ተናጋሪ እንደመሆናቸው አንድ ትልቅ የጀርመኖች ክልል/ካንቶን ይሆኑ ነበር። ይሄ ሁለተኛ ነጥብ ነው።

የሲዊዘርላንድ አወቃቀር ከቋንቋ በተጨማሪ ታሪክን እና የአስተዳደር አመችነትንም ከግምት ያስገባ አወቃቀር ነው። ለምሳሌ የዙሪክ ካንቶንን እንውሰድ። ሻርልማኝ የተባለው አንጋፋ ንጉስ የልጅ ልጅ፣ ንጉስ ሉዊስ በ853 ዓ.ም Fraumünster abbey የተባለን ገዳም ለሴት ልጁ ሂልደጋርድ ይመሰርታል። ለገዳሙ የቤኔዲክቲን መነኩሴዎች የዙሪክና የዩሪ መሬቶችን እና የአልቢስ ጫካን ከግዛቱ ይሰጣቸዋል። በ1045 ንጉስ ሄንሪ 3ኛ ገዳሙ የራሱ አስተዳደር እንዲኖረው ይፈቅዳል። መነኩሴዎች ገዳሙን እና አካባቢውን ማስተዳደር ጀመሩ። በ1218 ዙሪክ የራሷ ነጻ ግዛት ሆነች።፡ ከዚህ ታሪክ የተነሳ ነው ዙሪክ የራሷ ካንቶን የሆነችው። ሌሎችም ካንቶኖች ተመሳሳይ ታሪክ ነው ያላቸው።

እንግዲህ የማንነት/ብሄር ፖለቲካ የሚያራምዱ ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያላቸው ልሂቃን የሲዊዘርላንድን ሞዴል እንደ ሞዴላቸው ከወሰዱ ለታሪክ ግምት በመስጠት፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ..የሚሉ ክልሎች ሳይሆን ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ወለጋ፣ ጂማ፣ ከፋ….የመሳሰሉ ታሪካዊ ክልሎች ይኖሩ ዘንድ ይከራከሩ ነበር። እንደ እዉነቱ ከሆነ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራል አወቃቀር መላ ቅጡ የጠፋበት ፌዴራል አወቃቀር ነው። እንደገና ቋንቋን፣ ታሪክን፣ የሕዝብን አሰፋፈር፣ ኢኮኖሚን፣ ጂዪግራፊን፣ የአስተዳደር አመችነትን፣ የሕዝብን ፍላጎትን ባካተተ መልኩ መዋቀር አለበት። ለእድገት፣ ለትሥር፣ ለዜጎች መብት መከበር በሚያመች መልኩ።

satenaw

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *