ይህ ምክር ቤት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት የተለየ ነው፡፡ የመጀመርያው ራሱን የቻለ ተቋም አይደለም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ምክር ቤት ነው፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ ኢታማዦሩ፣ የደኅንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ኃላፊውን የያዘ ምክር ቤት ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 257/1994፣ በ1994 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ የምክር ቤቱን አባላትም የሚገልጸው ይኼው ሕግ ነው፡፡ ጸሐፊውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር የጸሐፊነቱን ተግባር የሚወጡት የመከላከያ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ (አዋጁን ያሻሻለ ሌላ ሕግ መኖሩን ጸሐፊው ማወቅ አልቻለም፡፡)

ምክር ቤቱ ከላይ በተገለጹት አባላት ሳይወሰን ተጨማሪ አባላት ሊኖሩትም ይችላል፡፡ በአዋጁ ላይ ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉትን የመጨመር (ብዛታቸውንም ማንነታቸውንም ጭምር) ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክር ቤቱ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ ሙያዊ ምክር ለመለገስ እንዲገኙ ሊጋበዙ ይችላሉ፡፡ ምክር ቤቱ በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መሳተፋቸውን ያስተዋልነው በዚህ ሁኔታ እንዲሳተፉ ይጋበዙ ዘንድ ሕጉ ስለፈቀደ ነው፡፡

በመሆኑም፣ ምንም እንኳን በአዋጁ ላይ በቋሚነት የተዘረዘሩት አባላት ብዛት ሰባት ቢሆንም አንድም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰያሚነት ከእዚህ ሊልቅ ይችላል፡፡ የሌሎች አገሮች የደኅንነት ምክር ቤት ከሚያካትታቸው ባለሥልጣን ውስጥ የማይዘለለው የፍትሕ ሚኒስትሩ (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን) ነው፡፡ የእኛ አገር ግን የተለየ ነው፡፡ የውሳኔዎቹን ሕጋዊነት የሚከታተለው ምርመራና ክስንም ቢሆን በበላይነት የሚመራው አካል በቋሚነት እንዲካተት ማድረግ የተለመደ ነው፡፡

ከተቋቋመ 15 ዓመታት ቢሞላውም ብዙም በሕዝብ ዘንድ እብዛም የሚታወቅ አይመስልም፡፡ ለዚያም ይመስላል በተለያዩ ሚዲያዎችን የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡት፡፡ ግርታን ይበልጥ የፈጠረው ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ጋር የተለየ ወይም ተመሳሳይ መሆን ወይም አለመሆን ነው፡፡ ይህን ነጥብ ወደ ኋላ ላይ እንመለስበታለን፡፡

ምክር ቤቱን ለማቋቋም ያስፈለገበትንም ምክንያት አዋጁ ይናገራል፡፡ ለአገሪቱ ብሔራዊ የደኅንነት ጉዳዮች ተጨማሪ ዋስትና መስጠት ነው፡፡ ተጨማሪነቱ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ይመስላል፡፡ ከዚህ ተቋም የዘወትር ሥራና ተግባር ያለፈ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ችግር እንደሚከሰት ሲገመት ነው፡፡ አገሪቱን ያልታሰበ የደኅንነት ችግር ሲያጋጥማት ወይንም አመጣጣቸውን መገመት የሚቻል ፈተናዎች እየመጡ ከሆነም እነሱን እልባት ለመስጠት ሲባል በተጨማሪነት የተቋቋመ ነው፡፡

ስለዚህ በመደበኛነት የአገሪቱን የደኅንነት ሁኔታ ለሚከታተለው ተቋም በተደራቢነት ነገር ግን ከፍ ያለ ሥጋት በሚኖርበት ጊዜ ከአንድ መሥሪያ ቤት በዘለለ በምክር ቤት ደረጃ ውሳኔ ለመስጠት በሚያመች መልኩ የተቋቋመ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እስኪ ደግሞ የምክር ቤቱን ተግባራት እንመልከት፡፡ ተግባራቱን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ የመጀመርያው የአማካሪነት ሚና ነው፡፡ የሚያማክረውም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ነው፡፡ የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች የውስጥ፣ የውጭና የመከላከያ ፖሊሲዎች በሙሉ እርስ በራሳቸው የተስማሙና የተቀናጁ እንዲሆኑ በማድረግ ተፈጻሚነታቸውም በመከታተል በአጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ ምክሩን ይለግሳል፡፡

ዘርዘር ተደርገው ሲታዩ ለአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት የሥጋት ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች በመለየት እንዴት ሊፈቱ እንደሚችሉ መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች ጭምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክሩን ያቀርባል፡፡ የአገሪቱን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱና መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች በተመለከተ መመርያዎችን ያዘጋጃል፡፡ የአገሪቱን ደኅንነት በሚነካ ጉዳይ ላይ ይመክራል፡፡ እንግዲህ በዚህ መንገድ የሚቀርቡ መፍትሔዎች፣ ዕርምጃዎችና መመርያዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲፀድቁ ብቻ ነው፡፡ ከአዋጁ አንቀጽ 4(1) እና (2) ላይ መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ተግባራቱ በአማካሪነት የተወሰኑ ናቸው፡፡

ሁለተኛው የምክር ቤቱ ተግባር ቋሚና መደበኛ  የሆነ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 4(3) እንደተገለጸው ይህ ኃላፊነቱ የሚመጣው በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚተገብረው ወይም የሚያስተዳረው ይህ ምክር ቤት ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ በሚዘረዘረው መሠረት ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ይህን ተግባሩን ለሌላ አካል መስጠት አይቻልም፡፡ ቋሚ ግዴታው ነው፡፡

በመሆኑም ሁለተኛው ተግባሩ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በምትተዳደርበት ወቅት ብቻ የሚመጣ ነው፡፡ እንግዲህ ባለፈው ዓመት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ ተከትሎ የመጣው ኮማንድ ፖስት የሚል ስያሜ የነበረው መሠረቱ ይህ ምክር ቤት ነው፡፡ ለነገሩ ራሱ ምክር ቤቱ ነው ማለትም ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲተገበር ያደረጉት የመጀመርያውን ተግባሩን መሠረት ያደረገ እንጂ ሁለተኛውን ሊሆን አይችልም፡፡

ፌዴራላዊም የአገር አስተዳደር አወቃቀር የሚከተሉ ሆነው በአንድ ዕዝ ሥር ያለ የፖሊስ ተቋማት ያላቸው አሉ፡፡ በርካታ የፖሊስ ተቋማት ያሏቸው፣ በጥምረትና በቅንጅት የሚሠሩበት መጠን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የእያንዳንዱ ፖሊስ ተቋማትም ተግባርና ኃላፊነት ግልጽ ድንበር ከመኖር አንፃር የተለያዩ አሠራሮች አሏቸው፡፡ የፖሊስ ተቋማት ብዛትና የዳበረ ቅንጅታዊ አሠራር መኖር ወይም አለመኖር፣ ከግለሰብ መብት መከበር፣ ከመልካም አስተዳደርና ከተጠያቂነት ጋር ግንኙነት አለው፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የፖሊስ ተቋማት መበራከት ለራሱ ለመንግሥትም ቢሆን አቀናጅቶ ከመምራት አንፃር ፈተና ሊሆንበት ይችላል፡፡ ለእዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በተከሰቱት ግጭቶች ውስጥ የተለያዩ ክልሎች ልዩ የፖሊስ ኃይሎች የነበራቸውን ተሳትፎ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ሁኔታ በመገንዘብ ይመስላል ወጥ የሆነ የፖሊስ አሠራር መኖር እንዳለበት በቅርቡ የተናገሩት፡፡

ቀድመው አኃዳዊ የአስተዳደር ዘይቤ ይከተሉ የነበሩ አገሮች የፀጥታና የፖሊስ ተቋማት አወቃቀራቸው ወጥ ነው፡፡ ለየክልሎቹ የራሳቸውን የፖሊስና የሚሊሻ ኃይል ማቋቋምን ይከለክላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራርን አይፈቅዱም፡፡ ለነገሩ ክልሎችም የራሳቸው ሕገ መንግሥትም የላቸውም፡፡ ቀድመው ራሳቸውን የቻሉ ሉዓላዊ አገሮች የነበሩና ኋላ ላይ በፌዴሬሽን የተዋሃዱ ከሆኑ ግን የራሳቸውም ሕገ መንግሥትም የፀጥታ አካላት ስለሚኖራቸው የያዙትን ይዘው መቀጠል የተለመደ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ግን ከላይ ከተገለጸው የአገሮች ልምድና አካሄድ አኳያ በተቃራኒው የተጓዘ ነው፡፡ የክልሎችና የፌደራል ፖሊስ አሉ፡፡ የክልሎች ደግሞ መደበኛና ልዩ ኃይል አላቸው፡፡ የአካባቢ ፖሊስም አለ፡፡ በፌዴራልም፣ ከልዩ ኃይሉ በተጨማሪ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ፖሊስ አለ፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ፣ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባርና ሌሎችም የፖሊስ አደረጃጀቶች ነበሩ፡፡ ሌላው ደግሞ የክልሎችና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ፖሊሶች አሉ፡፡

የዚህ ዓይነት አወቃቀር መሠረቱ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ የፌዴራሉንና የክልሎችን ሥልጣን በሚዘረዝሩት አንቀጾች 51(6) እና 52(2) (ሰ) ላይ እንደተገለጸው ሁለቱም መንግሥታት የየራሳቸውን የፖሊስ ተቋሟት እንደሚያቋቁሙ ይገልጻል፡፡ ሁሉም የክልል ሕግጋተ መንግሥታትም ይኼንኑ ሥልጣናቸውን በድጋሜ አረጋግጠዋል፡፡ በመሆኑም በክልሎች ውስጥ ስላሉ የሕግና ሥርዓት ማስከበር፣ የሕዝብ ደኅንነትና ሰላምን ማስጠበቅ የየራሳቸው ተግባር ነው ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ዋና ዋና አገር አቋራጭ ጎዳናዎችን በፌዴራል ፖሊስ አስተዳደር ሥር እንዲሆኑ ሲወስን የክልሎቹ የፖሊስ ኃይል በአግባቡ ማስተዳደር አልቻለም ማለት ነው፡፡ ለወትሮው እንዲህ ዓይነት ተግባራት የሚከናወኑት በክልሎች ነበር፡፡ በቅርቡ በተፈጠሩት ግጭቶች ውስጥም በየክልሉ ያሉ የተወሰኑ የፀጥታ ሠራተኞችም ተሳትፎ እንደነበረበትም ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡ በተጨማሪም የክልል ባለሥልጣናትም በሕግ መጠየቅ እንደሚገባቸው ወስኗል፡፡

እንደ ሕገ መንግሥታዊ አወቃቀርና ሥርዓቱ፣ በተለይም በትክክልና በሀቀኝነት የሚተገበር ሲሆን፣ በየክልሎቹ ወንጀል ከተፈጸመ  ፈጻሚው ማንም ይሁን ማን የወንጀል ምርመራውን በበራሳቸው መጀመር ነበረባቸው፡፡ ክሱምን ማዘጋጀትና መክሰስ የነበረባቸው እንዲሁ የክልል ዓቃቤያነ ሕግጋት ነበሩ፡፡ ክሱንም መመልከት የነበረባቸው በክልል ፍርድ ቤት ነበር፡፡ የፌዴራል ወንጀል ከሆነም ውክልና እስካለቸው ድረስ ሥልጣኑ የክልሎች ፍርድ ቤት ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የተፈጠሩት ጉዳዮች ግን ክልሎች በራሳቸው ከላይ የተጠቀሱትን የወንጀል አስተዳደር ሒደት ለመፈጸም ፍላጎት ያላቸው አይመስልም፡፡ እናም ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ የወሰነው ክልሎች መፈጸም የነበረባቸውን ነው፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸው ቁምነገሮች ምክር ቤቱ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ከተቋቋመበት አዋጅ አንፃር ሲለካ ሕጋዊ ቀጥሎም ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኖች አሉት ወይ? የሚሉት ናቸው፡፡ ከመጀመርያው አንፃር ቅድሚያ እንመልከተው፡፡

በመከላከያ ሚኒስትሩ አማካይነት ይፋ ከተደረጉት የምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳቦች ውስጥ ዋና ዋና ጎዳናዎችን በፌዴራል መንግሥት ጥበቃ ማድረግ የተለያዩ የክልል የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች ባለሥልጣናት ወደ ፍትሕ እንዲቀርቡ ማድረግን ያካትታል፡፡ ለእዚህ ውሳኔ መነሻ የሆኑት ምክንያቶች የአገሪቱን ደኅንነት ሥጋት ላይ እንደሚጥል ከአዝማሚያው የሚገመት ነው ከተባለ በአዋጁ አንቀጽ 4(1) እና (2) ላይ ይካተታል፡፡

ሁለተኛው ተግዳሮት የሕገ መንግሥታዊነቱ ነገር ነው፡፡ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ከማስፈጸም ውጭ ያሉት ተግባራቱ የአማካሪነት ነው ብለናል፡፡ በምክሩ መሠረት ውሳኔዎችን የማስተላለፍ ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ያሳልፍ ዘንድ ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ሰጥቶታልን? የሚለው ነው፡፡

ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 74ን ስንፈትሽ ለጥያቄው የሚቀርቡ ሁለት ንዑሳን አንቀጾችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው የመስተዳድሩን (Government) የሥራ አፈጻጸም የመቆጣጠርና የዕርምት ዕርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያስችል ሥልጣን መሰጠቱ ነው፡፡ ከእዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት የፌዴራል መንግሥቱ መስተዳድርን የሚመለከቱ ኃላፊነቶችን የማስፈጸም፣ የመቆጣጠር እንዲሁም የዕርምት ዕርምጃዎችን በራሱ የመውሰድ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር እንዳለበት መረዳት ይቻላል፡፡ በመቀጠል ደግሞ የፌዴራሉ ሳይሆን የክልል መንግሥታትም የሚያደርጓቸውን ድርጊቶች መከታተልና በራሱ ባይሆንም በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ዕርምት ማስወሰድንም ያካትታል ማለት ይቻላል፡፡

ሁለተኛው ንዑስ አንቀጽ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ግዴታ የሚጥለበት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያስከብሩ ግዴታ ከጣለባቸው ውስጥ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶችና የአገሪቱ ሕልውና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ግዴታም ሆነ ኃላፊነት ምንጩ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13(1) ነው፡፡ መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ብቻ ሳይሆን እንዲያስከብርም ኃላፊነት አለበት፡፡ ከመንግሥት አካላት አንዱና ዋነኛው አስፈጻሚው ነው፡፡ አስፈጻሚው የሚመራው ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሆነ ይኼንን የማስከበር ግዴታም ተጥሎበታል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙት መፈናቀል፣ የሕይወት መጥፋት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሳቸው ለእነዚህ የዕርምት ዕርምጃዎች መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ማስከበር ማለት የአገሪቱን ሕልውና ማስጠበቅም ሊሆን ይችላል፡፡ ሕልውናዋን የሚፈታተኑ የደኅንነት ሥጋቶች መኖራቸውን ምክር ቤቱ ሲያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀብሎ መወሰንን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የሚፈጸሙበት አካሄድ የክልሎችን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚነካ ከሆነ ውሳኔው የሚፈጸምባቸው አካሄዶች አሉ፡፡

እነዚህ አካሄዶች ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡ የመጀመርያው ክልሉ በራሱ አቅም ሊቋቋመው የማይችለው ወይንም በክልሉ ሕግ አስከባሪ ተቋማት መቆጣጠር የማይችለው የፀጥታ ችግር ሲያጋጥመውና ራሱ በጠየቀ ጊዜ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወይም መከላከያ ሠራዊት እንዲገባና ሁኔታውን እንዲያረጋጋ የፌዴራል መንግሥቱን ሲጠይቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ በዚህ መንገድ ማስፈጸም ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር የክልልና የፌዴራል መንግሥታቱን ስምምነት ይጠይቃል፡፡

ሁለተኛው አገባብ ደግሞ በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተከናወነ መሆኑን የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያረጋግጥ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን  በመጥራትና የጋራ ስብሰባ በማካሄድ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባና የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን እንዲያስቆም ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከእዚህ አንፃርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወስነውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሎም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስወሰንን  ይጠይቃል፡፡

ሦስተኛ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ ማለትም በክልሉ መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና በትጥቅ የተደገፈ አመፅ፣ ከሌላ ክልል ወይም ብሔር ጋር ችግር ሲፈጠር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥቱን ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ተፈጥረው ከሆነም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ በእዚህ መንገድ ማስፈጸም ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች በፊት ለፊት ሲታዩ በክልል ሥልጣን ሥር የሚወድቁ ባይመስሉም፣ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ማሳለፍ የተፈለገው የፌዴራሉ ስላልሆኑ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቀድሞም የፌዴራሉ መንግሥት እየተገበራቸው ቢሆን ኖሮ መደበኛ ተግባሩ እንደሆኑ በመቁጠር እንደወትሮው ማስቀጠል ይቻል ነበር፡፡

የምክር ቤቱን አስተያየት መነሻ በማድረግ የተላለፈውን ውሳኔ ክልሎቹ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለማስተላለፍ የሚያስችል ሁኔታ የለም ካሉ፤ እንዲሁም ውሳኔው የክልሎችን ሥልጣን የሚጋፋ እንደሆነ ካመኑ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉምን የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ቅሬታ እንዳለ ደግሞ ቢያንስ የኦሮሚያ ክልል የፍትሕ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በማኅበራዊ ሚዲያ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ አቋም ይሁን አይሁን ባይታወቅም፡፡

ከላይ የተነሱት መደምደሚያዎች ምንም ይሁኑ ምን፣ ስለአገር ሕልውና ሲባል ወይም አገራዊ ምክንያታዊነት (Reason of State) ከሕግም ከሕገ መንግሥትም የዘለለ አሠራርን ለመከተል የሚገደዱባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ዓላማውም የአገርን ሕልውና ማስቀጠል ነው፡፡ ሕልውናዋን በማስቀጠል ወደቀድሞው ሕጋዊ ሥርዓት መመለስ፡፡ በዚህን ዓይነት ሁኔታ ቅድሚ የሚሰጠው የግለሰቦች መብት ሳይሆን የሕዝብ እንደ ቡድን ደኅንነትና ዋስትና ነው፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በእርግጥ የአገሪቱ ሕልውና አደጋ ውስጥ ስለወደቀና በመደበኛው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መመለስ ስላልተቻለ ነው ወይ የሚለው ዝርዝር መረጃ ሳይኖር መመለስ አይቻልም፡፡

ይሁን እንጂ፣ በኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች የተሠራጨው ባለ 26 ገጽ ሰነድ በትክክል የመንግሥት ከሆነ እንዲሁም በውስጡ የተካተቱት ሥጋቶች ካሉ አሁን ካለው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ የክልልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት አንፃር የአገር ውስጥ የደኅንነት ሥጋት ስላለ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ውሳኔ ተገቢ መሆኑን ያሳያል፡፡ ተገቢ ነው ማለት ግን ሕጋዊ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ነው ማለት ለየቅል ናቸው፡፡

source- Reporter  አንባቢ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *