የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ሕወሃት በግምገማ “መሞሻለቅ” ከጀመረ ሰነባብቷል። ይኽ “የከረረ” የተባለ ግምገማ ተከትሎ የሃሳብ መለያየት የታየበት፣ መቧደን የተስተዋለበት፣ ስብሰባ ረግጦ መውጣት የተደረሰበት፣ “አሞኛል” በሚል ሰበብ አንዳንዶች መደበቅ የመረጡበት እንደነበር ከመቀሌ መረጃዎች አስቀደምመው ሲደመጡ ነበር። ዛሬ ራሱ ህወሃት ለመንግስት መገናኛዎች ባሰራጨው መረጃ በከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት የ”ታላቁ መሪ” ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መታገዳቸውንና አቶ አባይ ወልዱ ከስራ አስፈጻሚነታቸው ዝቅ እንዲሉ መደረጋቸው ታውቋል።
ከወራት በፊት ወ/ሮ አዜብ ከሙስና የጸዱ፣ በሃቅ ላይ የተመሰረተ ግምገማና ለውጥ እንደሚመኙ፣ የራሳቸውን ልምድና ችሎታ ተጠቅመው መስራት የሚችሉ፣ ወዘተ ዓይነት ሰው መሆናቸውን በምግለጽ በዛሚ ሬዲዮ ከሚሚ ስብሃቱ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚሁ ቃለ ምልልስ ሕዝባዊነት መጥፋቱንና ሙስና መንሰራፋቱን እንዲሁም በእሳቸው ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚካሄድባቸው በተደጋጋሚ ተናገረው ነበር። ቃለ ምልልሳቸውን ” ኑዛዜ” በሚል ያጣጣሉባቸው፣ አዜብ መስፍን ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ የሰላ ትችት ሰንዝረውባቸዋል። ከድርጅትም አካባቢ በርካቶች ይህንኑ ራሳቸውን የቀደሱበትን ቃለ ምልልስ እንዳልወደዱላቸው የቅርብ አዋቂዎች አመልክተዋል።
መለስን በማግባታቸው ከአማራነት ወደ ትግራይ የተቀየሩት ወ/ሮ አዜብ ከህወሃት ማዕከላዊ ስራ አስፈጻሚ አባልነታቸው መታገዳቸው ይፍ ከመሆኑ ውጪ በኤፈርት ሃላፊነታቸው ስለመቆየታቸው የተባለ ነገር የለም። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት ግን ወ/ሮ አዜብ አብቅቶላቸዋል። ከኤፈርት ሃላፊነታቸውም ተነስተዋል።
ከሰፋፊ ንግዶች ጋር ስማቸው የሚነሳውና ከፍተኛ ብር ከሚሽከረከርበት የጫት ንግድ ጋር ቁርኝት እንዳላቸው የሚነገርባቸው ወ/ሮ አዜብ ” ታግደው ቁጭ እንዲሉ ተወስኗል” መባሉ የቁም እስረኛ መደረጋቸውን የሚያሳይ ሆኖ ተገኝቷል። የባለቤታቸውን “ራዕይ” አንዳችም ሳትበረዝ በሚል ምሽግ ሲሰሩ የነበሩት ወ/ሮ አዜብ በሙስና ወንጀል መገምገማቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ቢናገሩም ድርጅቱ ግን በምክንያት ደረጃ የገለጸው ነገር የለም።
የህወሃት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ሊቀመንበር አቶ አባይ ወልዱ የአቅም ማነስ ችግር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ የሚነገር ቢሆንም ከስራ አስፈጻሚነታቸው እንዲነሱና ዝቅ ብለው በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ እንዲመደቡ መደረጉ ታውቋል። የቀሩትን እርምጃዎችና ደርጀቱ የሰጠውን መረጃ ዋቢ በማድረግ የኢህአዴግ ሬዲዮ ፋና የሚከተለውን ዘግቧል።
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ ማዕከላዊ ኮሚቴ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።