ሰማኸኝ ጋሹ አበበ

ህወሃት አንዲት ኢንች እንኳን ለመለወጥ ሃሳብ እንደሌለዉ ከአወጣዉ መግለጫ መረዳት ይቻላል። እስኪ የተወሰኑትን የመግለጫዉ ሃሳቦች እንመልከት። “እንደሚታወቀው ሁሉ ህወሓት የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በየደረሰበት የትግል ምእራፍ ውስጥ ሁሉ የሚገጥሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በሰከነ ሳይንሳዊ ኣመራርና በኣባላቱና በህዝብ የተሟላ ተሳትፎ በአስተማማኝ እየመከተ ለድል የበቃ ድርጅት ነው” ይላል።

ሀወሃት ሳይንሳዊ አመራር የሚለው ምኑን ነዉ ብለን እንጠይቅ። ሳይንሳዊ አመራር የተባለዉ ማርክሲዝም ሌኒንዝም እንደሆነ ከሌሎች የህወሃት ሰነዶች እንረዳለን። በ1968 ሀውሃት ባወጣዉ ማኒፌስቶ “ማርክሳዊ-ሌኒናዊ ትክክለኛና ሳይንሳዊ የላብ-አደር ርእዮተ-ዓለም መሆኑን በማመንና በአሁኑ ጊዜ የሚካሄደው አብዮት ከግቡ ሊደርስ የሚችለው ይህንን መመሪያ በማድረግ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፦” እንደሆነ ይገልፃል። አሁንም ችግሮችን ለመፍታት እንደ ሳይንሳዊ መመርያ የሚጠቀመዉ የማርክሲዝም ሌኒንዝምን ነው ማለት ነዉ። ይህ ማለት በህገ መንግስቱ የተገለፁት ዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ትርጉም የሌላቸዉ መሆኑንና አሁንም ህወሃት በማሌሊት መመርያ እየተጠቀመ መሆኑን ነዉ።

ሌላው በመግለጫዉ የተገለፀዉ “የህዝብን ፀረ-ጭቆና፣ ፀረ ኃላቀርነትና ፀረ-ድህነት ትግል ለስኬት ለማብቃት የሚያስችሉ የጠራ መስመር፣ መስመሩን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ስትራተጂዎችና ስልቶችን እየቀየሰ ከኣንድ የትግል ምዕራፍ ወደ ሌላው የትግል ምዕራፍ ለመሸጋገር የቻለበት ምስጢር ግልፅ ነው፡፡ “ የሚል ነዉ። እስከዛሬ የሄደበትን የሚዘረዝረዉ ይህ ክፍል በተለይ ፀረ ጭቆና የሚለዉ ምንድን ነዉ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። ሀውሃት እራሱ እንደሚለዉ ጨቋኝ የነበረዉን ስርአት ደምስሼ ዴሞክራሲ አምጥጫለሁ እያለ እንዴት ስለጭቆናል ሊናገር ይችላል ብለን ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ጨቋኝ እራሱ ሀውሃት ቢሆንም አሁንም አማራዉን ጨቋኝ አድርጎ እንደሚያቀርብ የሚያሳይ ነዉ። ይህን ሃሳብ በ 1968 ዓም ከወጣዉ ፕሮግራም ጋር ስናስተያየዉ አማራ የሚለዉን ከማዉጣቱ ዉጭ ተመሳሳይነት አለዉ- “የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ፀረ-የአማራ ብሔራዊ ጭቆና፣ ፀረ-ኢምፐርያሊዝም እንዲሁም ፀረ-ንኡስ ከበርቴያዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው። ስለዚህ የአብዮታዊው ትግል ዓላማ ከባላባታዊ ሥርዓትና ከኢምፐርያሊዝም ነፃ የሆነ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ማቋቋም ይሆናል።”

ዋናዉ ችግራችን ብለዉ ያቀረቡት “አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቲክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙርያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርንና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል፡፡” ይላል። ፀረ ዴሞግራሲያዊ ተግባርና አስተሳሰብ የሚለዉን ለሚያነብ ሰዉ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ለዉጥ ለማድረግ አቅደዋል ብሎ ሊያስብ ይችላል። ነገር ግን ፀረ ዴሞክራሲ ማለታቸዉ በህወሃት ዉስጥ ዋናዉ መርህ የሆነዉን ዴሞግራሲያዊ ማእከላዊነት መርህን ጥሰዋል ለማለት ነዉ። መለስ ዜናዊ በ 1993 ስብሰባ እረግጠዉ የወጡትን በተመሳሳይ መልኩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ናቸዉ በሚል ነበር የመታቸዉ። አሁንም ፀረ ዴሞክራሲ የሚሉት በተመሳሳይ መልኩ የስልጣን ሽኩቻዉን አሸንፈዉ ለመዉጣት የሚጠቀሙበት ዜዴ ነዉ። እነሱ የሚያወሩት ዴሞክራሲ ስለ ዉስጣዊ ዴሞክራሲያዊ አስራር እንጅ በአገሪቱ ስላለዉ የዴሞክራሲያዊ ስርአት መጥፋት አይደላም።

ሌላው ሀውሃት ምንም አይነት ለዉጥ ለማምጣት እንዳልፈለገ የሚያሳዉ መልእክት ያስተላለፈዉ ለ “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች፣ ላብአደሮችና ልማታዊ ባለሃብቶች” መሆኑ ነዉ። ይህ አባባል የህወሃትን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ የሚያስረግጥ ነዉ። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት ወዝ አደሮችና ላብ አደሮች የህወሃት ወዳጆች ሲሆኑ ምሁራንና ወያኔን የማይደግፉ የህብረተሰብ ክፍሎች (እኛ ማለት ነዉ) እንደጠላት ስለሚቆጠሩ ለነሱ መልእክት ማስተላለፍ አላስፈለገም። አሁንም ተቃዋሚዉን ሃይል እንደ ጠላት ቆጥሮ ለማጥፋት ያለ የሌለ ሃይሉን ለመጠቀም አቅዷል ማለት ነዉ።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የአዴፓ በረራዊ ጋዜጣዊ መግለጫ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *