ገዚዎች ራሳቸውን ክፉ ስድብ ሲሰደቡ። በጠቂቱ ሸተናል፣ ገምተናል፣ በስብሰናል፣ኪራይ ስብሳቢ ነን፣ ሙሰኞች ነን፣ ነቅዘናል፣ እንደ ስርዓት ሟምተናል፣ መተማመን አልቻልንም፣ ጸረ ዴሞክራሲ ነን፣ ሕዝብ ፊት መቆም አልቻልንም እናፍራለን፣ ተሸርሽረናል፣ ተገዝግዘናል፣ ሞተናል፣ ሕዝብ ጠልቶናል፣ ሕዝብ አንቅሮ ተፍቶናል፣ በእኛ ምክንያት አገሪቱ አደጋ ላይ ወድቃለች፣ ልትፈራርስ ነው፣ ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፣ ደላሎችና ኮንትሮባንዲስቶች ሆነናል……… ይቀጥልና …. ተሃድሶ፣ ጥልቅ ተሃድሶ፣ የጠለቀ ለውጥ፣ ስር ነቀል ለውጥ… ይቀጥልና ለጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ፣ ሂስ፣ ግለ ሂስ… ይቀጥልና አሮጌ አመራር ከች!!
ሕዝብ እንዲህ ይል ነበር። አሁንም እያለ ነው። በጥቂቱ፤ በቃን፣ መረረን፣ ፍትህ አጣን፣ ሙሰኞች ይወገዱ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ናፈቀን፣ ነቅዛቹሃል፣ በስብሳቹሃል፣ ሸታቹሃል፣ ፍትህን ከልክላችሁሃል፣ አትሰሩን፣ አትግደሉን፣ አትግረፉን፣ ውረዱ፣ በመረጥነው እንተዳደር፣ አትበታትኑን፣ አትከፋፍሉን፣ አገራችንን አታክስሙ፣ አትነገዱብን፣ …. ቀጥሎ አመጽ ገነፈለ፣ ሕዝብ ተነሳ፣…. ቀጥሎ ሕዝብ ተገደለ፣ ታሰረ፣ ተገረፈ፣ ቀጥሎ… ቀጥሎማ አሁንም ሕዝብ እንደቶቆጣ ነው። የቻለም ሽፍቷል ይባላል።
ሰላም ይብዛላችሁ። በያላችሁበት ክብር ለናንተ ይሁን።አሁን ባለው ሁኔታ ሰማእታት እነማን ናቸው? ያበደው ጠየቀ። አዎ መልሱ አጭር ነው። ሲሞቱም ሲገሉም፣ ሲያስገድሉም ” ሰማእታት” እነሱ ብቻ ናቸው። ግን አሁን ሰው ሰማእት ተባለ አልተባለ… ሰው ከበሰበሰ በሁዋላ … ያበደው ቀላመደ። ….
አሁን ያበደው ሁለቱንም ወገኖች አሰባቸው። ሕዝብና ገዢዎቹ ቋንቋቸው አንድ ሆነበት። ራሳቸውን ከሚሰድቡት በላይ ማን ሰድቧቸው ያውቃል? ችግሩ ሌሎች የራሳሸውን ቃል እንኳን ተጠቅመው ሲናገሯቸው ነው።
ራሳቸውን ይሰድባሉ። ራሳቸውን ያጠለሻሉ። ራሳቸውን ያዋርዳሉ። ራሳቸውን ” ብስብስ” ይላሉ። ሌሎች ” ብስብስ” ሊሏቸው ሲሰባሰቡ አፈሙዝ ይወድራሉ። ግን ራሳቸው ለራሳቸው ባወጡት ስም፣ አይ እቺ አገር ቦሰና ሲከፋት የምትለው ነው።
ቦሰና ሲነሳባት ክፉ ናት። ደጎል እንኳን ገሸሽ ይላል። ቦሰና “አሁን በደብረጽዮን እና በሌሎቹ መካከል ምን ልዩነት አለ?” አለች። “ሁሉም ሲበሰብሱ ደብረጽዮን ሽቶ ይነፉ ነበር?” ጠየቀች። አስከትላ ” አሁንስ ማይሙን እንኳ ማታለል አቃታቸው” እንደ ልማዷ ጢቅ አደረገች።
ሰዎቹ አያረጁም? አይሰለቻቸውም? ማረፍ አይፈልጉም? እንደ ሰው አርፈው ማለፍ አይመኙም? ለመጪው ትውልድ አስረከበው ቀሪ ዘመናቸውን በአደባባይ ቡና እየጠጡ፣ ካሻቸውም እያስቀደሱ አይኖሩም? ሰው ነብስ ካወቀበት ጊዜ ጀመሮ በቁማር አድጎ እንዴት እንደቆመረ ይገነዛል? ቤተስብስ አይመክርም? በቃ አባባ አይልም? አይበደው ደነዘዘው። ሰው እንዴት ነጻነት ይጠላል? ስብሃት ነጋ፣ አባይ ጸሃዬ፣ ስዩም መስፍን፣ አርከበ እቁባይ፣ ራስዋ አዜብ፣ አባይ ወልዱ፣ የአቶ ባሌማ ልጅ…. ሁሉም በተፈጠሮ ሂደት እንኳን አትሸነፉም? የጤናችሁ ሁኔታ አያሳስባችሁም….. ሱስ ማለት ይህ ነው!! በሽታ ማለት ይህ ነው። በሙጋቤ እየሳቁ ፣ ብዙ ሙጋቤዎችን አቅፎ መኖር!!
ያበደው ተስፈነጠረ። በቁጣ ተርጎመጎመ። ችግር በመጣ ቁጥር የገዢዎች መሃላ አጥወለወለው። ሁሌ ቀለም መቀያየር፣ መታደስ፣….. ባትታደሱስ? እንደ ሸተታሽሁ ብትኖሩስ፣ ሕዝብ ምን አገባው። የትኛው ፍቅሩ? የት መረጣችሁ? የት ነው ውል የገባችሁት?… በታመማችሁ፣ በተቧደናችሁ፣ ግራ በተጋባችሁ ጊዜ ሁሉ ” ቆይ ልንታደስ ነው” የምትሉት? ሕዝብ ምን አገባው። ያለ እናንተ ሌላ ትውልድ የለም? ያለ እናንተ አገር ሌላ ዜጋ የላትም? ነው ወይስ ነገሩ ምንድን ነው? ያበደው ጠየቀ!! ለውጥ ለሚፈልጉ ሁሉ አባይ ተነስተው ደብረጽዮን ቢመጡ ባይመጡ ምኑ ነው? ሙክታር ተባረው ለማ ቢተኩ ባይተኩ….
በፌደራሉ ቋንቋ እናውራው ፣ በመለስ አባባል እንተንትነው። ህወሃት ታደሰ አልታደሰ ለነቀምቴ፣ ለነጆ፣ ልባሌ፣ ለአርሲ፣ ለሃረር፣ ለጎንደር፣ ለጎጃም፣ ለሸዋ፣ ለአዲስ አበባ፣ ለቤኒሻንጉል፣ ለጋምቤላው…. ሕዝብ ዜና ነው? ምኑ ነው? ልክ “የአክሱም ሃውልት ለሌላው ምኑ ነው?”
ቦሰናም በዚህ ሃሳብ ትስማማለች። ደጎልም በዚህ ጉዳይ ጭራውን አይቆላም። አንገቱን ቀና አድርጎ ነው ድጋፍ የሚሰጠው። ጉድ እኮ ነው…. ለሁለት የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ፣ በሰላ የሂስ ጅራፍ ተገረፉ…. እና ምን ይሁን? የናንተ መሰዳደብ የሕዝብን ጥያቄ ይመልሳል?
ያበደው ጮኸ። አገር ነፍራለች፣ አገሪቱ ልክ አይደልችም፣ የቀለም ቅብ ፖለቲካ አይሰራም። እባካችሁን ስሙ፣ ሁሉም ቦታ አደገኛ ቀጣና እየሆነ ነው፣ ሁሉም ያልፋል፣ ለመጪው ትውልድ ስትሉ፣ ለፈጣሪ ስትሉ፣ ለህጻናት ስትሉ …. አሁን የተነሳውን ሰደድ እሳት እናጥፋ፣ ቆራጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ ወስኑ፣ ሁሉንም አካቱ፣ ሁሉንም ሰብስቡ፣ ሕዝብ እንዲወስን አድርጉ፣ ስሜት ጎሿል። ጥይት መልስ ሊሆን አልቻለም። ከጠመንጃ ጋር የሚጋፈጡ ….. ደም በፈሰሰ ቁጥር ….. ሰላም ሁኑ !!ጉድ ነው። አጃኢብ ነው። የጥልቅ ተሃድሶ መንፈስ!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *