አዲስ አበባ – በህክምናና በህግ ትምህርት ተሞክሮ ከፍተኛ ውጤት ያስገኘው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ምዘና /EXIT EXAM/ ከ2011 ጀምሮ በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች እንደሚካሄድ የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ከመጪው 2011 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የመውጫ ምዘና የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ተፈላጊውን ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲላበሱ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

የመውጫ ምዘናው ተመራቂዎች ተፈላጊውን አነስተኛ የምሩቅ ፕሮፋይል ለማሟላታቸው ማረጋገጫ የሚሰጥ ተማሪዎች፤ ከመመረቃቸው በፊት ብቃታቸውን የሚያረጋግጡበት የምዘና አይነት መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ምዘናው በብዙ አገራት የተለመደና ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት በገለልተኛ አካል የተዘጋጀን ምዘና ወስደው ብቃታቸውን የሚያረጋግጡበት አሠራር መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዲኤታው፥ በኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት በህግ እና በህክምና ትምህርት ተሞክሮ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተመራቂ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት በማድረግ በራሳቸው እንዲተማመኑና ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችል፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተማሪዎቻቸውን በጥሩ ውጤት ለማሳለፍና ያላቸውን ተፈላጊነት ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው ዶክተር ሳሙኤል አመልክተዋል።

መምህራንም ተማሪዎቻቸው ብቃት ተላብሰው እንዲመረቁ ለማስቻል በኃላፊነት ተከታታይ ምዘና በማካሄድ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ክፍተቶች እንዲሞሉ፣ ቀጣሪ ኢንዱስትሪዎችም በተማሪው ላይ አመኔታ እንዲያሳድሩና ብቃት አላቸው ብለው እንዲያምኑ እንደሚያስችላቸው ሚኒስትር ደኤታው አብራርተዋል።

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት በህክምና እና በህግ ትምህርት ከተገኘው ልምድ በመነሳት ከመጪው ዓመት ጀምሮ የመውጫ ምዘና በ35 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የቅደመ -ምረቃ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የመውጫ ምዘና እንዲወስዱ እንደሚደረግ ገልፀዋል። 

የመውጫ ፈተና በውጤታማ ትግበራ ስኬት አሠራር በአጭር ጊዜ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ከተሰጣቸው ሰባት የትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብሮች አንደኛው መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ህዳር 22፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *